ዓለም አቀፍ ዜናዎች
ታንዛንያ አንድ ቢሊየን ዶላር የሚያስገኝ የካርበን ሽያጭ ፕሮጀክት ይፋ አደረገች
Feb 8, 2024 1415
አዲስ አበባ፤ ጥር 30/2016 (ኢዜአ)፦ ታንዛንያ አንድ ቢሊየን ዶላር የሚያስገኝ የካርበን ሽያጭ ፕሮጀክት ይፋ ማድረጓ ተገለጸ፡፡ ስፑትኒክ ድረገጽ የአገሪቱን ምክትል ፕሬዝደንት ቢሮ ጠቅሶ እንደዘገበው ታንዛንያ ከተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ 2023 ወዲህ 35 የካርበን ሽያጭ ማመልከቻዎችን ተቀብላለች፡፡ በቢሮው የአካባቢ ደህንነት ኃላፊ ሴሌማኒ ጃፎ እንደተናገሩት የካርበን ሽያጭ ለአገሪቱ የገቢ ምንጭ እየሆነ ይገኛል፡፡ የካርቦን ሽያጭ ከ2018 እስከ 2022 ባሉት አመታት በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ የተተገበረው የካርበን ሽያጭ ለአገሪቱ ከ12 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘቱን ተናግረዋል። “የካርቦን ሽያጭ የታንዛንያን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ለማገዝና የተፈጥሮ አካባቢን ለመንከባከብ የራሱ አስተዋጽኦ አለው“ ያሉት ሴሌማኒ ጃፎ ጠቀሜታውን ለህብረተሰቡ በማስረዳትና በስፋት በማሳተፍ እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል። በዱባይ በነበረውም የኮፕ 28 የአየር ንብረት ጉዳዮች ጉባኤ ላይ የሃገራቸውን መልካም ተሞክሮ በማቅረብ ዘርፉ ላይ ከሚሰሩ አካላት አዎንታዊ ግብረመልሶች ማግኘት መቻሉን አላፊው ገልጸዋል፡፡ በተገኘው ውጤትም ታንዛንያ የአንድ ቢሊየን ዶላር የሚያስገኝ የካርበን ሽያጭ ፕሮጀክት ይፋ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ታንዛንያ ከሶስት አመታት በፊት ብሔራዊ የካርበን ሽያጭ መመሪያ በማዘጋጀት ባለድርሻ አካላት እንዲመሩበት ማድረጓ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ በደን ልማት ዘርፍ እያከናወነች ባለው ሥራ እ.ኤ.አ እስከ 2030 ከካርበን ሽያጭ 100 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት እቅዳ እየሰራች ይገኛል፡፡
የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና አተገባበርን የሚዳስስ ምክክር መካሄድ ጀመረ
Jan 26, 2024 1311
  አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2016(ኢዜአ) ፦ “የአፍሪካ ብልጽግና ምክክር” በሚል መሪ ሀሳብ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የአተገባበር ሁኔታን የሚዳስስ የመሪዎችና ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የምክክር መድረክ በጋና እየተካሄደ ነው። ከዛሬ ጀምሮ ለሶሰት ቀናት የሚቆየው የምክክር መድረኩ የነጻ ንግድ ቀጣናው ወቅታዊ ሁኔታና የፕሮቶኮል አተገባበርን እንደሚገመግም ተመልክቷል። የጋና መንግስትና አህጉራዊ ተቋማት በጋራ ባሰናዱት የምክክር መድረክ የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ፣ የአህጉራዊና አለማቀፋዊ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉ የጋናው ግራፊክ ኦንላየን ዘግቧል። በመድረኩ በነጻ ንግድ ቀጣናው ወቅታዊ አተገባበር የታዩ ክፍተቶችና መፍትሔያቸው እንደሚዳሰስም በመረጃው ተጠቁሟል። ጎን ለጎንም አፍሪካዊ ምርቶች ለተሳታፊዎች ቀርበው አህጉራዊ የቢዝነስ ትስስር ለመፍጠር እንደታቀደም ነው በዘገባው የተመለከተው።  
ቤጂንግ ያለ አሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱ የፖሊስ ፓትሮሎችን አስተዋወቀች
Jan 17, 2024 675
አዲስ አበባ፤ ጥር 8/2016(ኢዜአ)፦ የቻይናዋ ቤጂንግ ከተማ ያለ አሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱ የፖሊስ ፓትሮል ተሽከርካሪዎችን በማስተዋወቅ የእንቅስቃሴ ሙከራ አካሄደች። ተሽከርካሪዎቹ ለአካባቢ ቅኝት፣ ለህዝባዊ በአላት ደህንነት እንዲሁም ለድንገተኛ አደጋ የመከላከል ስራዎች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ በመረጃው ተመልክቷል። ቤጂንግ እ.አ.አ በ2020 በስማርት ሲቲ ማዕቀፍ ስር 160 ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት ያለው አሽከርካሪ አልባ ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱበት አካባቢ የገነባች ሲሆን የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆኑ አሽከርካሪ አልባ የፖሊስ ፓትሮሎችን አስተዋውቃለች። ተሽከርካሪዎቹ ደረጃ አራት ያለ አሽከርካሪ የሚያንቀሳቀስ መኪና ቴክኖሎጂ እንደተገጠመላቸው እና በየ30 ሰከንዱ ራሱን የሚያድስ ባትሪ በዚህም 100 ኪሎ ሜትር የመጓዝ አቅም እንዳላቸው ተነግሯል። በተጨማሪም ተሽከርካሪዎቹ በ120 ሜትር የአካባቢ ስፋት ውስጥ የሚካሄዱ ነገሮችን የመለየት ብቃት እና የመንገድ ደህንነት ግብረ መልስ የሚሰጥ ቴክኖሎጂ እንደተገጠመላቸው ነው የተመላከተው። በቤጂንግ አሽከርካሪ አልባ መኪኖች ልምምድ ቦታ የተዋወቁት 15 የፖሊስ ፓትሮሎች ሲሆኑ ከፖሊስ መኮንኖች ጋር በመሆን የአደጋ ጊዜ ልምምድ ማካሄዳቸውንም የዘገበው ሲጂቲኤን ነው። በአሽከርካሪ አልባ ፓትሮሎቹ የተካሄዱት ሙከራዎች በአደባባይ ዝግጅቶች ደህንነትን ማረጋገጥ፣ ህዝባዊ ማስጠንቀቂያዎችን መስጠት እና የአደጋ ጊዜ ተልዕኮዎችን መለየት መሆናቸው ተመልክቷል። በአሁኑ ወቅት በቤጂንግ አሽከርካሪ አልባ መኪኖች ልምምድ ቦታ ላይ 28 አምራች ኩባንያዎች መሰማራታቸው እና 800 ተሽከርካሪዎች ደግሞ በሙከራ ላይ መሆናቸው ተገልጿል።    
ከ 100 በላይ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በቻይና መንግስት የተመቻቸ የስኮላርሽፕ እድል አገኙ
Jan 15, 2024 722
አዲስ አበባ ፤ ጥር 6/2016 (ኢዜአ)፡- 143 በተለያየ የትምህርት መስክ ላይ ያሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በቻይና መንግስት የተመቻቸ የስኮላርሽፕ እድል አገኙ፡፡ የቻይና ኢትዮጵያ የስኮላርሽፕ ወዳጅነት ማብሰሪያ ስነስርአት ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) እንደተናገሩት የቻይና መንግስትና ዩኒቨርሲቲዎች ከአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ጠንካራ እና ትርጉም ያለው ትብብር አላቸው ፤ፋካልቲዎችንና ተማሪዎችንም እያሰለጠኑ ነው ብለዋል፡፡ በቻይና እና በኢትዮጵያ የትምህርት አካዳሚዎች መካከል ያለው ትብብር የቻይና ኢትዮጵያ ግንኙነትን የሚያጠናክር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን በበኩላቸው የስኮላርሽፕ እድሉ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያን ለሃገራቸው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ያስችላቸዋል፡፡ የአዲስ አባባ የኒቨርሲቲና ምሩቃኑ በቻይና ኢትዮጵያ ግንኙነት በጎ አስተዋፅኦ አበርክተዋል ያሉ ሲሆን በቀጣይም እንዲጠናከር አዲስ አበባ የኒቨርስቲ እንደ ድልድይ ሆኖ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡ ስኮላርሽፕ ካገኙት ኢትዮጵያውያን መካከል ሙሉጌታ አየለ በሰጠው አስተያየት እድሉን ያገኘን ኢትዮጵያውያን ትምህርታችንን ለማሳደግና በሀገራችን ልማት ላይ ለመሳተፍ ያስችለናል ብሏል፡፡ የቻይና ኢትዮጵያ የስኮላርሽፕ ወዳጅነት ማብሰሪያ በተካሄደ ስነስርአት ላይ በቻይንኛ ቋንቋ ክህሎት የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ 22 ኢትዮጵያውያን መሸለማቸውንም ፒፕልስ ዴየሊ ኦንላየን ድረገፅ ዘግቧል፡፡
የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ ስምምነት ለባህር በር መዳረሻና ለስትራቴጂካዊ ግንኙነት ቁልፍ እርምጃ ነው
Jan 12, 2024 661
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የተፈራረሙት ስምምነት ለባህር በር መዳረሻ እና ለቀጣናው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ቁልፍ እርምጃ መሆኑ ተመላከተ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል። በሥምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር መገንባት የሚያስችላትን ቦታ በሊዝ የምታገኝ ሲሆን ሶማሌላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ የልማት ኩባንያ ድርሻ የምታገኝ ይሆናል። ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነትን በተመለከተ ሰፊ ትንታኔን ያቀረበው አፍሪካን ኒውስ ስምምነቱ በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ አውዶች ረገድ ግዙፍ ፋይዳዎች እንደሚኖሩት አመልክቷል።   ስምምነቱ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ ከማስቻሉ ጎን ለጎን ምርቶች የሚከማቹበት ተጨማሪ ወደብ በማስገኘት የገበያ ተደራሽነቷን እንደሚያሰፋው ነው የተመለከተው። የሰፊ ህዝብ ባለቤትና ከፍተኛ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ የሆነችው ኢትዮጵያ ቁልፍ ስምምነት ማካሄዷን ያተተው ዘገባው ስምምነቱ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል ያለውን የማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት እንደሚያጠናክረው አብራርቷል። በቀጣናው የኢኮኖሚና ተዛማጅ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አሊ ሆጂጅ በዘገባው ላይ እንዳመለከቱት ኢትዮጵያ የቀጣናው ግዙፍ ኢኮኖሚና ህዝብ ባለቤት እንደመሆኗ የእድገት ጉዞዋን የሚመጥን ዘርፈ ብዙ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋታል። ከሶማሌላንድ ጋር ያካሄደችው ስምምነትም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ከማጠናከር ባለፈ በጅቡቲ ብቻ የነበረውን የወደብ ተጠቃሚነት በማስፋት የባህር በር እንድታገኝ ያስቻለ ቁልፍ ርምጃ መሆኑን አብራርተዋል። ስምምነቱ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር ሆና በተቀላቀለችበት ወቅት የተካሄደ መሆኑም ትልቅ ስኬት ነው ያሉት ባለሙያው ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የሚኖራትን ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር የሚኖራትን ሁለገብ ግንኙነት እንድታሰፋ የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት። በቀጣናውና በመካከለኛው ምሥራቅ በሚካሄዱ የንግድ እንቅስቀሴዎች ላይም በባለቤትነት ለመሳተፍ ይህ ስምምነት ቁልፍ መሆኑን ያተቱት ባለሙያው ሶማሌላንድ እንደ ሀገር እውቅና እንድታገኝና በአካባቢው የሚኖራትን ተሰሚነት የሚያሳደግ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር  ለመስራት የወሰደችው እርምጃ  ብልህነት የተሞላበት ነው
Jan 11, 2024 467
አዲስ አበባ ፤ጥር 2/2016 (ኢዜአ)፦ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት የወሰደችው እርምጃ ብልህነት የተሞላበት መሆኑን የአልአረብ ፐብሊሺንግ ኩባንያ ዋና አዘጋጅ (ዶ/ር )ሃይታም ኤል ዞባይድ ገለፁ። ሃይታም ዘአረብ ዊክሊ ድረገጽ ላይ ባሰፈሩት ረዘም ያለ ጽሁፍ የአለም ስርአት በእጅጉ መድልዎ የተሞላበት ነው። በማሳያነትም ሶማሊላንድ ነጻነቷን ማግኘት የነበረባት በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1990ዎቹ መጀመሪያ አንደነበር በማንሳት ። በእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ጥላ ስር የቆየችው ሶማሊላንድ በ1960ዎቹ ነጻ ስትወጣ ከጣሊያን ሶማሊ ጋር እንድትቀላቀል የተደረገበት መንገድ ተንኮሎች እንደነበሩት በምልሰት ያስታውሳሉ። እንደሌሎቹ የባህረሰላጤው ሃገራት የተትረፈረፈ የነዳጅ ሃብት ቢኖራት ኖሮ ልእለሃያላኑ ሀገራት ከሶማሊ ጋር እንድትቀላቀል አይፈርዱባትም ነበር ሲሉም ይሞግታሉ። ቀደም ሲል አሜሪካን ጨምሮ ከ35 ያላነሱ ሃገራት እውቅና የሰጧት ሶማሊላንድ በግዴታ ወደ ሶማሊያ መዋሃዷ ዜጎቿ ለተቃውሞ ዳርጎ ነበር ፤ በ1990ዎቹ የዚያድባሬ አገዛዝን ተከትሎ የተቀሰቀሰው የሶማሊያ የእርስበእርስ ጦርነት የሶማሊላንድን ዳግም ውልደት እስኪያመጣ ድረስ ። የዚያድባሬ አገዛዝ መገርሰስ የእርስበእርስ ጦርነት፣ የባህር ላይ ዝርፊያ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ያለመረጋጋት ማንገሱን ያተተው የዶክተሩ ጽሁፍ ሶማሊላንድ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥም ሆና ዜጎቿን ማረጋጋት፣ የባህር ክልሏን መጠበቅ ብሎም ምርጫዎችን በማካሄድ የሉአላዊ ሃገር ተግባራትን ስትፈጽም እንደቆየች አትቷል። የትኛውም ሃገርም ሆነ ባለሃብት የረጅም ጊዜ ትርፉን አስቦ እንደሚንቀሳቀስ ነጋሪ እንደማይፈልግ የገለጹት ዶክተሩ ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ብዛት፣ የገበያ አቅም፣ የመልማት እድል ብሎም የዲፕሎማሲ ትስስር አኳያ ለሶማሊላንድ ሊታለፍ የማይችል መልካም አጋጣሚ ነው። ዶክተሩ ሃሳባቸውን ሲቋጩ እስካሁን በነበረው ሁኔታ የሞቃዲሾ አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ አንዳንድ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሃገራት ታማኝ የልማት አጋር ሆነው ተባብረው የመስራት ብሎም የመለወጥ እድላቸውን በተከተሉት የአስተዳደር ዘይቤና ስግብግብነት ምክንያት ያባከኑ መሆናቸው ያስታውሳሉ። ከዚህ በተቃርኖ ኢትዮጵያ በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስና በኤሽያ ሃገራት የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን በመረዳት ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት መወሰኗ ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን ይሞግታሉ።
የመግባቢያ ስምምነቱ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነው
Jan 6, 2024 536
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 27/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እና በሶማሌላንድ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ ነው ሲሉ በሳህል ቀጠና የቀድሞ የአሜሪካ ልዩ መልክተኛና የአትላንቲክ ካውንስል የፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪ አምባሳደር ጄ ፒተር ፋም ገለጹ። አምባሳደር ጄ ፒተር ፋም በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል የተደረገውን የመግባቢያ ስምምነት አስመልክቶ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል። አምባሳደሩ ስምምነቱ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ብዛትና የመልማት አቅም እንዲሁም ከወደብ ኪራይ ዋጋ ውድነት አንጻር በጅቡቲ ወደቦች ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና መቀጠል እንደማትችል ከተገነዘበች ቆይታለች ብለዋል። የመግባቢያ ስምምነቱ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለውን ነባራዊ ሁኔታዎች ያገናዘበ፣ በሰጥቶ መቀበልና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ መሆኑንም አብራርተዋል። በተጨማሪም ስምምንቱ የቀጣናውን አካባቢ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ሊያሻሽል የሚችል መሆኑንም አስረድተዋል። በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1960ዎቹ በርካታ ሀገራት ሶማሌላንድን በነጻና ሉአላዊት ሀገርነት እውቅና ሰጥተዋት የነበረ መሆኑን አስታውሰው ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ከሶማሊያ ግዛት ጋር እንድትቀላቀል ተደርጓል ነው ያሉት። ከዚያድ ባሬ አስተዳደር መፈራረስ በኋላ ሶማሌላንድ የራሷ የሆነ ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎች በማድረግ የራሷን አስተዳደር መስርታ ከሰላሳ አመታት በላይ መቆየቷንም አስታውሰዋል። ከኢትዮጵያ ባሻገር ሌሎች ሀገራትም በሶማሌላንድ መዋእለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ መሆናቸውን በማውሳት የእንግሊዝ ኩባንያዎች ከተባበሩት አረብ ኤሚሬትሱ ዱባይ ፖርትስ ኩባንያ ጋር በመሆን ቢሊዮን ዶላሮችን በማውጣት በበርበራ ወደብ ልማት ላይ እየተሳተፉ መሆኑን አንስተዋል። ቢዘገይም ቢፈጥንም፤ ቢፈለግም ባይፈለግም ሶማሊላንድ አለም አቀፍ እውቅና የማግኘቷ ጉዳይ አይቀሬ ነው ሲሉ ተናግረዋል አምባሳደሩ።
በኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የተፈረመው ስምምነት ለቀጣናው አዲስ ምእራፍ የሚያስተዋውቅ ነው
Jan 5, 2024 480
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የባህር በር አጠቃቀምን በሚመለከት የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ለቀጣናው አገራት አዲስ ምእራፍ የሚያስተዋውቅ መሆኑን የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አንድሪው ኮሪብኮ ገለጹ። ሰርቫይቭ ዘ ኒውስ በተባለው ድረገጽ ላይ የሰፈረው የተንታኙ ዘለግ ያለ ጽሁፍ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ የሶማሊላንድ ወደብን ለኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ አገልግሎት ለመጠቀም የገባችው ስምምነት ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ትስስር ከማሳደግ ባለፈ ሌላ አላማ አለመያዙን አስረድተዋል። ብዝሃ ባህልና ሃይማኖት የሚተገበርባት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ አጠቃቀምን በሚመለከት የደረሰችበት የመግባቢያ ሰነድ ወደ ሙሉ ትግበራ ሲገባ ከሶማሊላንድ ባለፈ ወደ ሌሎች የአካባቢው አገራት የሚሻገር ትሩፋት እንዳለው ያተተው የተንታኙ ጽሁፍ ጥቂት የማይባሉ አካላት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ስምምነቱን ጥላሸት እየቀቡት ይገኛሉ ብለዋል። ስምምነቱን ተከትሎ የተቃርኖ አስተሳሰቦችን የሙጥኝ ብለው የያዙ ሰዎች ከምንም በላይ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተውን ስምምነትና መልካም ምሳሌ ይጸየፋሉ ሲሉ ወቅሰዋል። ተንታኙ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር መሆኗን ባረጋገጠችበት እለት የተፈረመው ይሄ የመግባቢያ ሰነድ ለሶማሊላንድ ህዝብና መንግስት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን በማንሳት ሁነቱ ለአፍሪካ ቀንድ አገራት ህዝቦች በተለይም ለሶማሊላንድ ዜጎች አዲስ የሚባል የታሪክ ክስተት ሆኖ ሊመዘገብ የሚገባው ነው ብለዋል። ስምምነቱ በትብብር የጋራ ተጠቃሚነትን ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ከመሆኑም ባሻገር በሰጥቶ መቀበል መርህ በቀጣናው አካባቢ ያለውን የጸጥታ ችግር መቅረፍ እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በአለም ላይ በአንድ ቦታ እንደተቀመጠ የሚገኝ ነገር አለመኖሩን የሚያሳዩ ተጨባጭ ክስተቶች መኖራቸውን በማሳያዎች ያብራሩት ተንታኙ የአፍሪካ ቀንድ አገራት በእጅጉ ኋላ ከቀሩበት የኢኮኖሚ ደረጃ ተመንጭቀው መውጣት ካለባቸው መሰል ስምምነቶችን አድርገው እድገታቸውን ማስቀጠል የግድ ይላቸዋል ብለዋል። ኢትዮጰያ ካላት ሁለንተናዊ አቅም አንጻር መሰል ስምምነቶችን አድርገው የጥቅም ተጋሪ መሆን የሚችሉ አገራት መሪዎች ይሄንን ሁነት ቀለል አድርገው ሊመለከቱት እንደማይችሉ በማተት በጉዳዩ ላይ የሶማሊያ ፌደራል መንግስትና የሽብር ቡድኑ አልሽባብ አብረው ለመስራት ያደረጉት ያልተቀደሰ ጋብቻ መጨረሻው መጠፋፋት መሆኑን አስምረውበታል።  
የስዕል ማራቶን ክብረ ወሰንን የሰበረው ናይጄሪያዊ የሥነ ጥበብ ተማሪ
Jan 4, 2024 387
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2016(ኢዜአ)፡- ለተከታታይ 100 ሰዓታት የተለያዩ ስዕሎችን የሳለው ናይጄሪያዊው የሥነ ጥበብ ተማሪ የአለም የስዕል ማራቶን ክብረ ወሰንን ሰብሯል። በአሜሪካ ጆርጂያ ግዛት በሳቫና የስዕልና ዲዛይን ኮሌጅ ተማሪ የሆነው ቻንስለር አሀጎቱ ለረጅም ሰዓታት በመሳል የአለም ክብረ ወሰንን እንደጨበጠ ጊነስ ወርልድ ሪከርድስ አስታውቋል። ከዚህ ቀደም እ.አ.አ በ2013 በቤልጄየማዊው የስነ ጥበብ ተማሪ ሮናልድ ፓልሜርትስ የተያዘውን ለ60 ሰዓት የመሳል ክብረ ወሰን በመስበር ነው እውቅናውን የጨበጠው። ለአራት ቀናት ገደማ ቻንስለር ባካሄደው የስዕል ስራ የታዋቂ ሰዎችን ጨምሮ፣ ምግቦች፣ ዕጽዋትና እንሰሳት እንዲሁም 106 ልዩ ልዩ ስዕሎች መሳሉን ዘገባው አመልክቷል። ለተከታተይ 88 ሰዓታት በስዕል ስራው ላይ ከቆየ በኋላ የድካም ስሜት ታይቶበት ነበረ ያለው ዘገባው ድካሙን በማሸነፍ ክብረ ወሰኑን መስበሩን አስነብቧል። ቻንስለር አሀጎቱ እውቅናውን ተከትሎ በሰጠው አስተያየት “ወደ ስነ ጥበብ ትምህርት ቤት የመጣሁት ሕልሜን እውን ለማድረግ ነው፣ ለ100 ሰዓታት ያለ እረፍት በመሳል ያሳካሁት ድል ነው ብሏል።
የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን አመት ስኬታማ ነበር
Jan 1, 2024 424
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2016 (ኢዜአ)፡- በተጠናቀቀው የአውሮፓውያኑ አመት የኢትዮጵያና የቻይና ሁለንተናዊ ግንኙነት ስኬታማ ሆኖ ማለፉን ምሁራን ገለጹ። የሀገራቱ ግንኙነት በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ የማይለወጥ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት፣ የእውቀትና የመረጃ ልውውጥ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ትብብር በአውሮፓውያኑ 2023 ከተከወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል መሆናቸውን ዥንዋ አስነብቧል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቻይና ቤጂንግ ባደረጉት ጉብኝት የሀገራቱ ግንኙነት በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ የማይለወጥበት ደረጃ ላይ መድረሱ ይፋ እንደተደረገ ያስታወሰው ዘገባው ኢትዮጵያና ቻይና በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ አብረው ሊሰሩባቸው የሚያስችሉ በርካታ እድሎች እንዳሉ አስነብቧል። ስለጉዳዩ አስተያየታቸውን የሰጡት በኢትዮጵያ የስትራቴጂክ ግንኙነት ተቋም የአለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ተመራማሪው መላኩ ሙሉአለም የአውሮፓውያኑ 2023 በኢትዮጵያና በቻይና ግንኙነት ሂደት ውስጥ “ታሪካዊ” ተብሎ ሊታወስ የሚችል መሆኑን ገልጸው አመቱ ከሚተባበሩባቸው የአለም ሰላምና ሁለንተናዊ ልማት ባሻገር የሃገራቱ ምጣኔሃብታዊ ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር የደረሰበትን ደረጃ አመላካች ነው ብለዋል። “አመቱ ኢትዮጵያና ቻይና በልማትና ዘርፎች ለመርዳት የገባችውን ቃል ማክበሯን በተግባር ያሳየችበት ነው” ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ፐብሊክ ፖሊሲ ፕሮፌሰር ቆስጠንጢኖስ በርሄ ተስፋ ናቸው። በተጠናቀቀው አመት ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል እንድትሆን የቻይና ድጋፍ ጉልህ እንደነበር ያስነበበው ዘገባው፤ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ኢትዮጵያ በብሪክስ ቡድን የምታደርገው ተሳትፎ ከራሷ አልፎ ለአካባቢው ሃገራትም የሚተርፍ እንደሚሆን ተገልጿል። “በደቡብ-ደቡብ ትብር ውስጥ ኢትዮጵያ ወሳኝ የሚባል ድርሻ ስላላት አባል በሆነችበት የብሪክስ ቡድን ውስጥም ይሄንን ሚናዋን አጉልታ ታሳያለች” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መናገራቸውን ያስታወሰው ዘገባው ቻይና ከቴክኒክና ሙያ በባቡር መሰረተልማት እንዲሁም በሳተላይት ዘርፎች ለኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የምትሰጠውን የአቅም ማጎልበቻ ስልጠናዎች አጠናክራ ትቀጥላለች ብሏል።  
በመጪው  ከጥር እስከ መጋቢት  ወራት የአፍሪካ ቀንድ   ከባድ ዝናብ  ያስተናግዳል
Dec 31, 2023 406
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 21/2016 (ኢዜአ)፦በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከጥር እስከ መጋቢት ከባድ ዝናብ እንደሚጥል ኢጋድ አስጠነቀቀ። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን የአየር ንብረት ትንበያ ማዕከል እንዳስታወቀው፤ በጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ከጥር እስከ መጋቢት 2024 ወራት አብዛኛው የአፍሪካ ቀንድ ከባድ ዝናብ እንደሚጥል ተንብይዋል። በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚጠበቀው ከባድ ዝናብ የኤልኒኖ ተጽኖ ምክንያት መሆኑንም ማዕከሉ አስታውቋል። መቀመጫውን በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ያደረገው ማዕከሉ በትንበያው እንዳስታወቀው፤በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለሚጥለው ከባድ ዝናብ ምክንያት የሁኑ እርጥበታማ የአየር ሁኔታዎች በደቡባዊ እና ኢኳቶሪያል አካባቢ በሚገኙ የቀጠናው ክፍሎች ላይ ከወትሮው በበለጠ ሁኔታ እንደሚጠበቁ ማዕከሉ ገልጿል። ከጥር እስከ መጋቢት ከባድ ዝናብ ከሚያስተናጉዱት ሀገራት መካከልም ታንዛኒያ፣ብሩንዲ፣ኬንያ፣ደቡብ ኡጋንዳ እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ እና ሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ እንደሚገኙበት ማዕከሉ አስታውቋል። ማዕከሉ ጨምሮ እንዳስታወቀው፤ በዚህ ወቅት ከመደበኛው ሁኔታ በላይ ደረቃማ ሁኔታ እንደሚኖር አመልክቷል። ደረቅ የሚሆኑት አካባቢዎችም በማዕከላዊ ኬንያ፣ በሰሜን እና በምዕራብ ታንዛኒያ በሚገኙ ጥቂት ቦታዎች ላይ ነው ብሏል። የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በአጠቃላይ ከጥቅምት እስከ ታህሣሥ ባለው ጊዜ በገጠማቸው የዝናብ እጥረት ድርቅ እንደነበረ ያስታወሰው ማዕከሉ፤ ይህም የአየር ንብረት ለውጥ የአየር ሁኔታውን እየቀየረ መሆኑን ገልጿል። የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን የአየር ንብረት ትንበያ ማዕከል በአካባቢው ከሚጠበቀው ከባድ ዝናብ በተጨማሪ፣ የሙቀት መጠኑ ከመደበኛው በላይ እንደሚሆንም አመልክቷል። በዚህ ወቅት በመኪሰተው ሙቀት የከፋ ጉዳት የሚደርስባቸው ቦታዎች የሰሜን ኬንያ፣ የሶማሊያ እና የኢትዮጵያን የተለያዩ ክፍሎች እንደሚያጠቃልል ያስታወቀው ማዕከሉ፤ በዚህ ወቅት የሚከሰተው የሙቀት መጠን ከ32 እስከ 40 ዲግሪ ሴልስየስ ሊጨምር እንደሚችልም ተንብይዯል። የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሊጠናቀቅ ሰዓታት በቀሩት የፈረንጆቹ ዓመት ፈጣን የአየር ሁኔታ ለውጦች ማገጠሙን ያመለከተው ማዕከሉ፤ በጥቅምት ወር በአካባቢው የጣለው የኤልኒኖ ዝናብ በጎርጎርሲያኑ አቆጣጠር ከጥር 2024 እስከ መጋቢት ባለው ጊዜ ከፍተኛ ዝናብ አስከትሎ ይከሰታል ብሏል። በቀጠናው የተራዘመ ድርቅ አለያም የጎርፍ አደጋዎች በሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ዥንዋ ዘግቧል።
ህንድ ለጂኦ ኢንተለጀንስ አገልግሎት የሚውሉ 50 ሳተላይቶችን ልታመጥቅ ነው
Dec 29, 2023 402
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2016 (ኢዜአ)፡- ህንድ ለጂኦ ኢንተለጀንስ አገልግሎት የሚሰጡ 50 ሳተላይቶችን ወደ ህዋ የማመንጠቅ ዕቅድ እንዳላት ተገለጸ። የአገሪቱን የጠፈር ምርምር ድርጅት ዋና ኃላፊ ኤስ ሶማታንን ጠቅሶ የዘሂንዱ ድረገጽ እንደዘገበው ሳተላይቶቹ በሚቀጥሉት አምስት አምታት ወደ ህዋ የሚመነጠቁ ናቸው። እስካሁን የአብዛኛዎቹ ሳተላይት ንድፍ እና ቀመር መጠናቀቃቸውን ኃላፊው ጠቁመው ሳተላይቶቹ በጠፈር ላይ በተለያዩ ምህዋሮች እየተሽከረከሩ ከሺህ ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ እንቅስቃሴዎችን ከመከታተል ባለፈም የምስል መረጃ የመላክ አቅም ያላቸው እንደሆኑም አብራርተዋል። ህንድን ከአለም ጠንካራ አገሮች ተርታ ለማሰልፍ ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል የመረጃ ሳተላይት ሰርቶ የማመንጠቅ ስራ አንዱና ዋነኛው መሆኑን የጠፈር ምርምር ተቋም ሊቀመንበር ኤስ ሶማታን ተናግረዋል። በአሁኑ ሰዓት አገሪቱ የምትጠቀምባቸው የሳተላይት ቴክኖሎጂዎች አቅም ውስንነት ያለባቸው መሆኑን ጠቁመው ወደፊት አገሪቷ የምታምጥቃቸው የሳተላይት አይነቶች በብቃት ከአሁኖቹ በአስር እጥፍ የላቁ መሆናቸውን አስረድተዋል። ህንድ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዙ የሳተላይት ቴክኖሎጂዎችን አምርቶ ለማመንጠቅ መዘጋጀቷንም መረጃው አስታውሷል።  
የኡጋንዳ መከላከያ ኤዲኤፍ የተሰኘው የሽብር ቡድን መሪ መገደሉን ገለጸ
Dec 29, 2023 358
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2016 (ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 19/2016 (ኢዜአ)፦ የኡጋንዳ መከላከያ ሰራዊት በምዕራባዊ ኡጋንዳ የሽብር ጥቃቶችን እየፈጸመ ነው ያለውንና የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ግንባር በሚል የሚጠራውን ቡድን መሪ መግደሉን አስታወቀ። የኡጋንዳ ህዝቦች መከላከያ ሠራዊት እንዳስታወቀው በዚህ ወር በሀገሪቱ ተከስቶ ለነበረውና 13 ሰዎች ለሞቱበት የሽብር ተግባር ተጠያቂ የነበረው የኤዲኤፍ መሪ መከላከያ ሠራዊቱ በወሰደው ወታደራዊ ዘመቻ ተገድሏል። የሰራዊቱ ምክትል ቃል አቀባይ ኮሎኔል ዴዎ አኪኪ እንደተናገሩት የሽብር ቡድኑ መሪ ሙሳ ካሙሲ እርምጃ ተወስዶበታል። አሸባሪው ታህሳስ 8 እና 16 በኪባሌ ብሔራዊ ፓርክ በተፈጸመው ጥቃት ዋነኛ መሪ የነበረ ሲሆን በዚህም የሰዎች ህይወት ማለፉ ተገልጿል። በአሁኑ ወቅትም የኡጋንዳ ህዝቦች መከላከያ ሠራዊት ቀጣናውን ከአሻባሪዎች ነጻ የማድረግና ወደ ቀደመ ሰላሙ የመመለስ ተግባር በተጠናከረ ሁኔታ እያከናወነ እንደሚገኝ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። አሸባሪ ቡድን ከቅርብ አመታት ወዲህ በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቱሪስቶችን ጨምሮ በንጹሃን ላይ የሽብር ተግባር በመፈጸም ተጠያቂ የተደረገ ቡድን መሆኑን አናዶሉ ዘግቧል።    
ቻይና ለአየር ንብረት  ትንበያ የሚያገለግሉ አራት ሳተላይቶችን ወደ ህዋ ላከች
Dec 27, 2023 336
አዲስ አበባ ፤ ታህሣሥ 17/2016 (ኢዜአ)፦ ቻይና ለአየር ንብረት ትንበያ የሚረዱ አራት አዲስ ሳተላይቶችን በያዝነው ሳምንት ወደ ህዋ መላኳን አናዶሉ አስነብባል። ከሀገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ ጂውኩዋን ከተባለው የጠፈር ማምጠቂያ ማእከል የተደረገው ሳተላይቶቹን የማምጠቅ ሂደት ስኬታማ እንደነበርና በእለቱም ሁዋይ ዡ 1ኤ የተሰኘችው ሮኬት እንደመጠቀች ይፋ ተደርጓል። ሁዋይ ዡ 1ኤ የተባለችው ሮኬት ለ24ኛ ጊዜ መምጠቋን ተከትሎ ቻይና ለንግድ፣ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ አገልግሎት የሚውሉ ተጨማሪ አራት ሳተላይቶችን ከቀናት በፊት እንዳመጠቀች ተገልጿል። ወደ ህዋ የተላኩት ሳተላይቶች ወደታቀደላቸው ምህዋር መድረሳቸውና የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን እንደሚልኩም በመረጃው ተመላክቷል። ቻይና ማክሰኞ ወደ ህዋ ከላከቻቸው አምስት ሳተላይቶች መካከል ሶስቱ ሺያን -24ሲ የሚባሉና የስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ነክ ለሆኑ ምርምሮች የሚያገለግሉ እንደሆነም ተገልጿል።
በኮፕ28 የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችል ታሪካዊ ስምምነት ላይ ተደረሰ
Dec 24, 2023 375
አዲስ አበባ ፤ ታኅሣስ 14/2016 (ኢዜአ) በኮፕ28 ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችል ታሪካዊ ስምምነት ላይ መደረሱ ይፋ ተደረገ። የኮፕ28 ፕሬዚዳንት ሱልጣን አሕመድ አል ጃባር እንዳስታወቁት የተመድ የአየር ንበረት ለውጥ ጉባኤ ተሳታፊዎች “ታሪካዊ ስምምነት” ላይ ደረሰዋል። የተደረሰው ስምምነት ከዚህ ቀደሞቹ የተሻለ፣ ስህተቶችን ያረመና ለተግባራዊነቱ ሁሉም አጽንኦት የሰጡበት ነው ብለዋል ፕሬዚዳንቱ ። በዚህም ስምምነት የአየር ንበረት ለውጥን ለመከላከል የሚያስችሉ የገንዘብ፣ የፖሊሲና ሰትራቴጂ ቅየሳዎች መካተታቸውንም ተናግረዋል። የታዳሽ ኃይል ተግባራትን ለማከናውን የሚያስችሉ ማዕቀፎች በስምምነቱ ከተካተቱ አንኳር ጉዳዮች አንዱ መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ መናገራቸውን ሲጂቲኤን ዘግቧል። ኢትዮጵያም በኮፕ 28 ጉበኤ የአየር ጠባይ ለውጥን ለመከላከል እየከወነች ያለችውን ተጨባጭ መፍትኄ በአረንጓዴ አሻራ መካነ ርዕይ ያቀረበች ሲሆን መካነ ርዕዩን የሀገራት መሪዎችና የአለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች መጎብኘታቸው ይታወሳል።
የጃፓን ተመራማሪዎች አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን በመጠቀም የእአምሮ እንቅስቃሴን የሚያሳይ የመጀመሪያውን ምስል ማግኘታቸው ተነገረ
Dec 19, 2023 443
አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 8/2016 (ኢዜአ)፡- የጃፓን ተመራማሪዎች የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም ሠው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የሰው ልጅ አእምሮ የድርጊት እንቅስቃሴን የሚያሳይ የመጀመሪያውን ምስል መፍጠራቸው ተነገረ። የጃፓን ብሔራዊ የኳንተም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንሰቲቲዩት እንዲሁም ሌሎች ተመራማሪዎች የሰው ልጅ አእምሮ ምስል ከሳች እንቅስቃሴ ላይ ባካሄዱት ጥናት አዲስ ውጤት ማግኘታቸው ተነግሯል። ተመራማሪዎቹ ሠው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም ባካሄዱት ጥናት በአእምሮ ውስጥ እንዴት ሙሉ ምስል ሊከሰት አንደሚችል የሚያሳዩ ቅድመ ሁኔታዎችን መገንዘባቸው የተመላከተ ሲሆን የአቦ ሸማኔ ሙሉ ገጽታን፣ የአውሮፕላንን ቅርጽንና የማብራት ምልክቶችን ግልጽ ምስል ማግኘታቸው ነው የተገለጸ። በበዚኅም የሠው ሰራሽ አስተውሎትን በመጠቀም የአእምሮ ምስል ከሳች እንቅስቃሴን በጉልህ የሚያሳይ የመጀመሪያውን ምስል ተመራማሪዎቹ ማግኘታቸውን ዥንዋ ዘግቧል። "የአንጎል ዲኮዲንግ" የሚል ስያሜ በተሰጠው የቴክኖሎጂ ምርምር 1200 ምስሎች እና መሬት ላይ ያሉ ግዑዝ አካላት ከአእምሮ ጋር ያላቸው ግንኙነት የተጠና ሲሆን ምርምሩ በአእምሮ እንቅስቃሴ ላይ በመመስረት የሰው ልጅን የማስተዋል ይዘቶች ለማለየት እንደሚያስችል ተነግሯል። የምርምሩ ግኝቶች በቅርቡ በሚታተመው ኢንተርናሽናል ሳይንቲፊክ ጆርናል ለእይታ እንደሚበቃም በመረጃው ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም