ማህበራዊ
በዞኑ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ164 በላይ አዳዲስ የአቅመ ደካሞች ቤቶች ተገንብተዋል
Aug 3, 2024 83
ነገሌ ቦረና፤ ሀምሌ 27/2016 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ቦረና ዞን በዞኑ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ164 በላይ አዳዲስ የአቅመ ደካሞች ቤቶች መገንባታቸውን የዞኑ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡ በጽህፈት ቤቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ነመራ ቶሎሳ፣ በዞኑ በዚህ ክረምት ከ15 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች መሰማራታቸውን ገልጸዋል። ከሀምሌ 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ መጀመሩንም ጠቅሰው ዘንድሮ በዞኑ ከአንድ ሺህ 790 በላይ የአቅመ ደካሞች ቤቶችን ለመገንባትና ለማደስ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል። እስካሁን በበጎ ፈቃደኞቹ ድጋፍና ትብብር ከ164 በላይ አዳዲስ የአቅመ ደካማ ሰዎች ቤቶች ግንባታ መጠናቀቁን አስታውቀዋል። ከዚህም በላፈ በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚተዳደሩ አባወራዎችና እማወራዎች 23 የወተት ላሞችና 200 እንቁላል ጣይ ዶሮዎች ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል። ወላጆቻቸው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚተዳደሩ 222 ህጻናት 111 ደርዘን ደብተርና 61 እሽግ እስኪርብቶ መከፋፈሉንም ጠቁመዋል። በዞኑ እስካሁን የተከናኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች በጋራ ድጋፍና ትብብር ብዙ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑንም ገልጸዋል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ ተጠቃሚዎች በበኩላቸው አገልግሎቱ ችግራቸውን እያቃለላቸው መሆኑን ተናግረዋል። የነገሌ ቦረና ከተማ 01 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ፈታ ነጋሽ፣ በጉልበት ስራ እሳቸውን ጨምሮ 7 ቤተሰቦቻቸውን በማስተዳደር ላይ እንደሆኑ ገልጸዋል። የሚያገኙት አነስተኛ ገቢ ያረጀ መኖሪያ ቤታቸውን ለማሳደስ ባለመቻለቸው ችግር ውስጥ መቆየታቸውን አንስተዋል። ዘንድሮ በመንግስትና በህዝብ ትብብር 21 የቆርቆሮ ክዳን ቤት ተሰራልን፣ እኔና ቤተሰቦቼም በደስታና በተስፋ መኖር ጀምረናል ብለዋል፡፡ የዚሁ ከተማ ነዋሪ አቶ ባቦ ቁልቁሉ፣ የሚኖሩበትን ቤት ለማደስ አቅም ስለሌላቸው በክረምት ለዝናብ በበጋ ለጸሀይና ለነፋስ ሲጋለጡ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ችግሬን የተረዱት በጎ ፈቃደኞች 32 ክዳን ቆርቆሮ ቤት ሰሩልኝ፣ የመረዳዳት ባህላችን የሚያኮራ በመሆኑ በተደረገልኝ ድጋፍ ሁሉ ተደስቻለሁ ብለዋል፡፡
ተመራቂዎች በሰለጠኑበት መስክ ሕዝብና አገርን  በታማኝነት በማገልገል የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ
Aug 3, 2024 82
ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 27/2016 (ኢዜአ)፡- ተመራቂ ተማሪዎች በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ለትውልድ የሚተርፍ ስራ በማከናወን ሕዝብና አገርን በታማኝነት በማገልገል የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ። ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 8ሺህ 524 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል። በዚህ ወቅት የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ አባል ወይዘሮ አስቴር ዘውዴ እንዳሉት፤ መማር፣ መመራመርና ዕውቀትን መገበየት የአገርን ዕድገት ያፋጥናል። ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ፍላጎቶቿን ለማሟላትና የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ሳይንሳዊ በሆነ አግባብ ለመፍታት ጥረት የሚያደርግ ሀገር ወዳድ ትውልድ ያስፈልጋታል ብለዋል። ለዚህም የዛሬ ምሩቃን ወደ ስራው ዓለም ሲገቡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት፤ ለትውልድ የሚተርፍ ስራ በማከናወን ሕዝብና አገርን በታማኝነት በማገልገል የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃቸው 8 ሺህ 524 ተማሪዎች በመደበኛው፣ በክረምት፣ በተከታታይና በርቀት ትምህርት መርሃ ግብሮች ያስተማራቸው መሆኑን አስታውቀዋል። ተመራቂዎቹ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በመጀመሪያ፣ ሁለተኛ፣ ሶስተኛ ዲግሪና በሰርተፍኬት የተመረቁ ሲሆን፤ ከመካከላቸውም 3 ሺህ 34 ሴቶች መሆናቸውን አመልክተዋል። ዩኒቨርሲቲው የመውጫ ፈተና ካስፈተናቸው ተማሪዎችም ከ93 በመቶ በላይ ማሳለፉን ጠቅሰው፤ ተመራቂ ተማሪዎችም በተመረቁበት የሙያ መስክ ሕዝባቸውንና አገራቸውን በቅንነት ማገልገል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ከተመራቂዎች መካከል በአካውንቲንግ እና ፋይናንስ ትምህርት በሁለተኛ ዲግሪ የተማረችው ሰላማዊት ተመስገን በሰጠችው አስተያየት፤ መማርና ማወቅ ትልቁ ዓላማ ከራስ ባለፈ ሀገርን መጥቀም እንደሆነ ተናግራለች።   እኔም በተማርኩበት የትምህርት ዘርፍ ሀገሬንና ህዝቧን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ ነኝ ስትል ገልፃለች። የመጀመሪያ ዲግሪውን በመካኒካል ኢንጂነሪንግ ሰልጥኖ እንደተመረቀ የተናገረው ሚኪያስ መንግስት በበኩሉ፤ በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ ሀገራችን ትልቅ ደረጃ እንድትደርስ አስተዋፅኦ ለማድረግ ዝግጁ ነኝ ብሏል።   በተማረበት የሙያ ዘርፍም የመንግስትን ስራ ሳይጠብቅ በራሱ ስራ ለመፍጠር ከወዲሁ ማቀዱንም አስታውቋል። ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት ከ28 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች እያስተማረ እንደሚገኝም ተመልክቷል።  
ኮሌጁ የካንሰር በሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከአጋር አካላት ጋር የቅንጅት ሥራዎችን ለመሥራት ቁርጠኛ ነው
Aug 3, 2024 102
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ የካንሰር በሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከአጋር አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ አስታወቀ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከአፍሪካ የምርምርና ሥልጠና ማዕከል፤ በአፍሪካ በካንሰር በሽታ ዙሪያ ጥናትና ምርምር ከሚያደርጉ ተቋማት ጋር ምክክር አካሂዷል፡፡ የምክክሩ ዓላማ በአፍሪካ ደረጃ ያለውን የካንሰር ሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችና ስጋቶች ምንድናቸው? እንዴት በጋራ በመሥራት ካንሰር ላይ ለውጥ ማምጣት ይቻላል? የሚል ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የካንሰርና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ምርምር ክፍል አስተባባሪ ዶክተር አዳሙ አዲሴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ካንሰር በአፍሪካ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል፡፡ የዛሬው ውይይትም የበሽታውን አሳሳቢነት ለመቀነስ ችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ እንዴት ማተኮር አለብን? በዘርፉ ያሉ ተዋንያን ምን መሥራት አለባቸው? የሚለው ላይ ተወያይቶ መፍትሔ ለማበጀት የተደረገ መሆኑን ገልፀዋል። በአፍሪካ የካንሰር በሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ መሪዎች ትኩረት መስጠት ይገባቸዋል ሲሉም ዶክተር አዳሙ አዲሴ ተናግረዋል። በተለይም ሴቶች ስለጡትና ስለ ማህጸን በር ካንሰር ግንዛቤ እንዲኖራቸው በየጊዜው ምርመራ እንዲያደርጉ እንዲበረታቱ ማድረግ ይገባል ብለዋል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም በአፍሪካ የካንሰር በሽታ ተጋላጭነትን ለመቀነስ ከአጋር አካላት ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑንም ጠቁመዋል። በጤና ተቋማት ላይ አገልግሎቱ በብቃት እንዲሰጥ የጤና ባለሙያዎች ከታችኛው የአገልግሎት መስጫ ጀምሮ ምልክቶችን በማወቅ ቶሎ አስፈላጊውን ሕክምና ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ለጤና ባለሙያዎች አጫጭር ሥልጠናዎችን በመስጠት፤ በሥርዓተ-ትምህርት ውስጥ ተካቶ እንዲሰጥ እየተደረገ ስለመሆኑ ገልፀዋል፡፡    
ባንኩ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ላይ በንቃት እየተሳተፈ ይገኛል
Aug 3, 2024 96
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን የባንኩ የሰው ሃይል ምክትል ፕሬዚደንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ገለፁ። የዘንድሮው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር "የምትተክል ሀገር፤ የሚያፀና ትውልድ" በሚል መሪ ሃሳብ በመካሄድ ላይ ነው። በዚሁ መርኃ ግብር የተለያዩ ተቋማት አሻራቸውን እያኖሩ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራርና ሠራተኞች በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል።   የባንኩ የሰው ሃይል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ እንዳሉት፤ ባንኩ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር በተለያዩ ሀገራዊ መርኃ ግብሮች ላይ በንቃት እየተሳተፉ ይገኛል። ከዚህም አንዱ በሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ንቅናቄ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በንቃት እየተሳተፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ባንኩ በዘንድሮው መርኃ ግብር በአዲስ አበባ ማዕከል ብቻ ከ50 ሺህ በላይ ለምግብነት የሚውሉ፣ ሀገር በቀልና ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ዛፎችና ችግኞች ለመትከል አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል። ከአዲስ አበባ ማዕከል በተጨማሪ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ 23 ዲስትሪክቶች የችግኝ ተከላው እንደሚካሄድ ነው የተናገሩት። የባንኩ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኑሪ ሁሴን በበኩላቸው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ለመጭው ትውልድ የተሻለች ሀገር የምናስረክብበት ነው ብለዋል።'   በዚህም ባንኩ አስፈላጊውን በጀት በመመደብ በልዩ ትኩረት እየተሳተፈ መሆኑን ተናግረዋል። በመርኃ ግብሩ የተሳተፉ ሰራተኞችም አሻራቸውን በማኖራቸው መደሰታቸውን ገልጸው ለእንክብካቤውም ተዘጋጅተናል ብለዋል። በ2016 ዓ.ም ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው።
ድርጅቱ በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የገንዘብ ድጋፍ አደረገ
Aug 3, 2024 103
ሳውላ ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ6 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ። የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክ አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) የድርጅቱ ሠራተኞችና አመራሮች በክስተቱ እጅግ ማዘናቸውን ተናግረዋል። የተቋሙ ሠራተኞችና አመራሩ ከተጎጂዎች ጎን መሆናቸውን ለማረጋገጥ ዛሬ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።   በድጋፉ ድርጅቱ የ5 ሚሊዮን ብር፤ የተቋሙ አመራረና ሠራተኛው ደግሞ ከ1 ሚሊዮን 912 ሺህ ብር በላይ በማዋጣት በጠቅላላ ከ6 ሚሊዮን 912 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። በየደረጃው ያለው የክልሉ መንግስት መዋቅር እና የአካባቢው ማህበረሰብ በነፍስ አድን ሥራው ያደረጉት ርብርብና አስተዋጾ የሚደነቅ መሆኑንም ተናግረዋል። ድርጅቱ የጀመረውን ድጋፍ በቀጣይም እንደሚያጠናክር ገልጸው፣ ለሟች ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል።  
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ አደረገ
Aug 3, 2024 108
ሳውላ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት ምክንያት ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚውል 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገ። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ መሀዲ(ዶ/ር) ምክር ቤቱ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ሀዘኑን ሲገልጽ እንደቆየ ገልጸዋል። ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እንዲውልም 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል። በምክር ቤቱ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ስለሺ ኮሬ(ዶ/ር ኢ/ር) በበኩላቸው፤ በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም ምክር ቤቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ድጋፉን የተረከቡት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጅነር ዳግማዊ አየለ፤ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሀዘኑን ሲገልጽ መቆየቱን አስታውሰው፤ ለተደረገው ድጋፍም በተጎጂዎቹ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ትውልድ የመገንባት ሚናን እየተወጣ ያለ ተቋም ነው - አቶ መሀመድ እድሪስ
Aug 3, 2024 147
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ታሪክ፣ እድገትና ትውልድ የመቅረጽ ጉልህ ሚና የነበረውና ይህን አጠናክሮ እየቀጠለ ያለ ተቋም መሆኑን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ ገለጹ። የልጆችን የንባብ ባህል ለማዳበር ከዲጂታል ዓለም በተጨማሪ በወረቀት፣ ብራናና በሌሎች የተጻፉ ጽሁፎችን እንዲያነቡ ማድረግ ይገባል ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትርና የኢፕድ የቦርድ አባል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ናቸው። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት "ብላቴናት" የተሰኘ ልጆች ላይ የሚያተኩር ባለቀለም ሕትመት ያለውና ባለ 40 ገጽ መጽሔት ምረቃ ሥነ-ሥርዓት እየተካሄደ ይገኛል። በመጽሔት ምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ ሚኒስትሮች፣ የመገናኛ ብዙኃን አመራሮች፣ ደራሲያን፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የእድሜውን ያህል አንጋፋና ጥበብ የተሸከመ የታሪክ ማኅደር የሆነ ተቋም ነው። ተቋሙ ትውልድን የሚጠቅም ሀገር መገንባት የሚያስችሉ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አንስተው፤ አሁን ላይ የጀመረው ሥራ ለሀገር የሚመጥን ትውልድ መገንባት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል። ሌሎችም የተቋሙን አርዓያነት በመከተል ቀላል በሆነ መንገድ ለህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተለያዩ ሕትመቶችን ተደራሽ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።   የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ላለፉት ስምንት አሥርት ዓመታት ሀገርን ሲገነባና ትውልድ ሲያንጽ መቆየቱን አንስተዋል። በ83 ዓመት ጉዞው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በየሳምንቱ በልጆች አምድ አስተማሪ ይዘቶች ሲያቀርብ እንደቆየ ተናግረው፤ ሀገር ተረካቢ ህፃናት የሕትመት ሚዲያ እንዲኖራቸው "ብላቴናት"ን ለማሳተም መብቃቱን ተናግረዋል። መጽሔቱ በትምህርት ቤቶችና በሕዝብ ቤተ-መጽሐፍት አማካኝነት የሚሰራጭ ሲሆን፤ በአዟሪዎች ማግኘት የሚቻል መሆኑንም ገልፀዋል። መጽሔቱ ልጆች እየተዝናኑ እውቀት የሚገበዩበት፣ ስለሀገራቸው ወጥ አረዳድ እንዲኖራቸው፣ በስነ-ምግባር እንዲታነፁና አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል። የይዘት ዝግጅቱ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች፣ የስነ-ጽሑፍ ባለሙያዎችና ሰዓሊያን የሚሳተፉበትና በቀጣይ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በሌሎች ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።   የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትርና የኢፕድ የቦርድ አባል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ከዲጂታል ዓለም በተጨማሪ ልጆችን በወረቀት፣ በብራናና በሌሎች የፅህፈት መሳሪያዎች የተፃፉ ጉዳዮችን እንዲያነቡ ማድረገ ይገባል ነው ያሉት። የንባብ ባህልን ለማሳደግ ልጆች በሚውሉበት ስፍራ ፅሁፎችን ማስቀመጥ አስፈላጊ እንደሆነ አንስተው ለዚህም ከወላጆች ጀምሮ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል። "ብላቴናት" በመላ ሀገሪቱ የሚሰራጭ፣ በቀጣይ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚኖሩባቸው ሀገራት ተደራሽ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን፤ አምዶችን በመከፋፈል ከ3 እስከ 9 ዓመት በላይ የሚሆኑ ልጆችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑም ተገልጿል። "ብላቴናት" መጽሔትን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ መርቀውታል።
በወላይታ ዞን ጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት እንዳያደርስ ቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ ነው 
Aug 3, 2024 121
ሶዶ ፤ሐምሌ 27/2016 (ኢዜአ)፦ በወላይታ ዞን የክረምት ዝናብን ተከትሎ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት እንዳያደርስ ቀድሞ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የዞኑ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዳዊት ደሳለኝ እንደገለጹት በዞኑ በክረምት ዝናብ ምክንያት ሊከሰት የሚችለው የጎርፍና የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ቀድሞ ለመከላከል ሥራዎች እየተሰሩ ነው። ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ለአደጋው ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን የመለየት ሥራ አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል። በዚህም በዞኑ ካዎ ኮይሻ፣ ኪንዶ ዲዳዬ፣ ኦፋ፣ ቦሎሶ ሶሬ እና ቦሎሶ ቦምቤ ወረዳዎች ለመሬት ናዳ ተጋላጭ እንደሆኑ መለየታቸውን ገልጸዋል። ድጉና ፈንጎ፣ ዳሞት ወይዴ፣ ሆብቻ፣ ሁምቦና እና አበላ አባያ ወረዳዎች ደግሞ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ መሆናቸውንም አስታውቀዋል። በአሁኑ ወቅት የክረምቱ ዝናብ እየተጠናከረ መምጣቱን ተከትሎ የአደጋ ስጋት በሆኑ አካባቢዎች ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከስጋት ነፃ ወደ ሆኑ አካባቢዎች የማስፈር ሥራ መጀመሩን ገልፀዋል። ሥራውን በሃላፊነት የሚያስተባብር ግብረ ሃይል ተቋቁሟል ያሉት አቶ ዳዊት፣ የቅድመ ጥንቃቄ ሥራው ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ጀምሮ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። እስካሁንም ካዎ ኮይሻ እና ኪንዶ ዲዳዬ ወረዳዎች ውስጥ ለመሬት ናዳ የተጋለጡ ነዋሪዎችን ወደ ሌሎች አካባቢዎች የማስፈር ሥራ ተሰርቷል ብለዋል። ባለፈው ዓመት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በአበላ አባያ ወረዳ ከአንድ ሺህ በላይ አባውራዎችን ከስጋት ነፃ ወደ ሆነ ቦታ በማስፈር በቋሚነት የማቋቋም ሥራ መሠራቱንም አስታውሰዋል። የአበላ አባያ ወረዳ ነዋሪ አቶ አባይነህ ባላ በበኩላቸው አካባቢያቸው ለጎርፍ ተጋላጭ በመሆኑ በየጊዜው በእርሻ ማሳቸውና በንብረት ላይ ጉዳት ሲደርስ እንደነበር አስታወሰዋል። ዘንድሮ ችግሩን አስቀደሞ ለመከላከል ከአካባቢያቸው ህብረተሰብ ጋር በመተባበር የውሃ መሄጃ ትቦዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ሌሎች የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ይህም ድንገተኛ የውሃ ሙላት ሊያደርስባቸው ከሚችለው ጉዳት ራሳቸውን ለመጠበቅ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል። አካባቢያቸው ለመሬት ናዳ አደጋ የተጋለጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ ደስታ ደንጎ የተባሉ የቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ነዋሪ ናቸው። ከዞን አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽህፈት ቤት በተላኩ የአደጋ ቅድመ መከላከል ኮሚቴ አባላት ሙያዊ ድጋፍ የቅድመ መከላከል ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተለይ የተፈጠረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እሳቸውን ጨምሮ ህብረተሰቡ ከጎርፍና ከመሬት መንሸራተት አደጋ ራሱን ለመጠበቅ በቅድመ መከላከል ሥራዎች በንቃት እንዲሳተፍ ማድረጉን ገልጸዋል።      
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በቡታጅራ ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት አስጀመሩ
Aug 3, 2024 153
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በቡታጅራ ከተማ የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት አስጀመሩ። አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር የክረምት የበጎ ፈቃድ ተግባራት ሥራዎችን ለማስጀመር ቡታጅራ ከተማ ገብተዋል። አፈ-ጉባኤው በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በተጠሪ ተቋማት የሚሰሩ የአቅመ ደካሞችን ቤት ዕድሳት ያስጀመሩ ሲሆን በቀጣይ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረግና የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ይከናወናሉ።   አፈ-ጉባኤው ቡታጅራ ከተማ ሲደርሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰውን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። በመርኃ ግብሩ ላይ ለመሳተፍ አፈ-ጉባኤውን ጨምሮ የምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባዔ ወ/ሮ ዛህራ ኡመድ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤትና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል። መርኃ ግብሩ የምክር ቤቱና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የምክር ቤቱ ተጠሪ ተቋማት ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም የክብር እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።   የምስራቅ ጉራጌ ዞን በክረምቱ ለመትከል የያዘው 24 ሚሊዮን የችግኝ ተከላ እቅድ አካል የሆነው የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር ይከናወናል። ምክር ቤቱ የክረምት ወራት የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር፣ የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤቶች አድሶ የማስረከብ እና ሌሎች ሀገራዊ የበጎ አድራጎት መርኃ ግብሮችን ላለፉት ዓመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ሲያከናውን መቆየቱ ተገልጿል።  
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከ8 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስመረቀ ነው
Aug 3, 2024 133
ባህር ዳር፤ ሐምሌ 27/2016 (ኢዜአ)፦የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያሰተማራቸውን ከ8 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ዛሬ እያስመረቀ ነው። በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ አባል ወይዘሮ አስቴር ዘውዴን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የተመራቂ ወላጆች ተገኝተዋል። ዩኒቨርሲቲው እያስመረቀ ያለው በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያሰተማራቸውን 8 ሺህ 524 ተማሪዎችን ሲሆን ከተመራቂዎቹ መካከል በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ 3 ሺህ 708፣ በሶስተኛ ዲግሪ 82፣ በስፔሻሊቲና ሳብ ስፔሻሊቲ 62 የህክምና ዶክተሮች ይገኙበታል።   እንዲሁም በማሪታይም፣ በአመራርነትና በሌሎች መርሃ ግብሮች የሰለጠኑ ተማሪዎችን እንደሚገኙበት ተመላክቷል። ከአጠቃላይ ተመራቂ ተማሪዎች መካከልም 3 ሺህ 34ቱ ሴቶች መሆናቸውም ታውቋል። ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ከ28 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ መሆኑም ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።    
በመንግስትና በተለያዩ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ እያገኘን ነው- በጎፋ ዞን በመጠለያ የሚገኙ ተፈናቃዮች 
Aug 2, 2024 129
ሳውላ ፤ሐምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፦በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሳቢያ ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ያሉ ወገኖች ሁለንተናዊ ድጋፍ እያገኙ መሆናቸውን ተናገሩ። በወረዳው ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በቅርቡ የደረሰ ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ይገኛሉ። አስተያየታቸውን የሰጡት እነዚህ ተፈናቃዮች ከዕለት ደራሽ በተጨማሪ የጤናና የስነ ልቦና ድጋፍም እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል ወጣት ኢዮብ ባሌ በአደጋው ወላጅ አባቱን፣ ታላቅ እህቱን እንዲሁም የአጎቱን ልጅ በሞት እንደተነጠቀ ተናግሯል። ቤተሰቦቹ በዕለቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ የተጎዱ ወገኖቻቸውን ለመታደግ በሄዱበት ወቅት ለሁለተኛ ጊዜ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሕይወታቸው ማለፉን ተናግሯል። መንግስትና የተለያዩ አካላት ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ጠቅሶ፣ "የምግብ፣ የአልባሳት፣ የንጽህና መጠበቂያና ሌሎች ቁሶችን በበቂ ሁኔታ እያገኘን ነው" ብሏል።   በአደጋው ሲደግፋቸው የነበረውን የመጀመሪያ ልጅ በሞት የተነጠቁት ወይዘሮ አየለች ሶምባ በበኩላቸው ማሳቸውም በመሬት መንሸራተት ተገምሶ መወሰዱን ተናግረዋል። በአደጋው ጥልቅ ሀዘን ውስጥ ቢገኙም የተለያዩ አካላት እያደረጉላቸው ባለው ድጋፍና እገዛ እየተጽናኑ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተጨማሪም ነፃ የሕክምና አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውንም አክለዋል። ወይዘሮ አየለች እንዳሉት ከሰብአዊ ድጋፎች ባሻገር የሕክምና እርዳታን ለተጎጂዎች የሚሰጡ በርካታ የህክምና ባለሙያዎች በቅርበት እየረዷቸው ይገኛሉ። በሜሪ ስቶፕስ ኢንተርናሺናል ኢትዮጵያ የደቡብ ቀጠና ምክትል ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ አለምብርሀን አሰፋ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ በመጠለያ ጣቢያው አቅራቢያ የሕክምና ማዕከል በማቋቋም ነፃ የህክምናና የስነ ልቦና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።   የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለም በአደጋው ምክንያት ንብረታቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ያጡና ስጋት ካለባቸው ቦታዎች የተፈናቀሉ ዜጎች በሦስት ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ እንዳሉ ተናግረዋል። አደጋው ከተከሰተበት ዕለት ጀምሮ ለእነዚህ ወገኖች አስፈላጊው ሰብዓዊ ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ እርዳታዎች እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።   በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ እንዳሉት፣ ለተጎጂዎች በተቀናጀ መንገድ ሁሉም አይነት ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው። ከደረሰባቸው የሥነ-ልቦና ቀውስ ፈጥነው እንዲያገግሙም የስነ ልቦና ህክምና እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው፣ በዘላቂነት ከሥጋት ነፃ በሆኑ ሥፍራዎች ለማስፈርም የቦታ ልየታ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም ህብረተሰቡን የማወያየት ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል።  
በአማራ ክልል የእናቶች ጡት ማጥባት ሳምንት እየተከበረ ነው
Aug 2, 2024 119
ባህር ዳር፤ ሐምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ''ክፍተትን በመሙላት ሁሉንም እናቶች ጡት እንዲያጠቡ እናድርግ'' በሚል መሪ ሃሳብ የእናቶች ጡት ማጥባት ሳምንት እየተከበረ ነው። የክልሉ ጤና ቢሮ የማህበረሰብ ጤና አገልግሎትና የመጀመሪያ ደረጃ ጤና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ወንድሜነህ ልየው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፤ የእናቶች ጡት ማጥባት ሳምንት ከሐምሌ 25 እስከ ነሐሴ 1/2016 ዓ.ም እየተከበረ ነው። የዓለም የእናቶች ቀን እናቶች ጡትን በማጥባት የልጆቻቸውን ዘላቂ ጤናና የአካል ጥንካሬ እንዲያስጠብቁ መነቃቃትን በሚፈጥር አግባብ እየተከበረ መሆኑን አስታውቀዋል። እናቶች እስከ ስድስት ወር ያሉ ህጻናትን ምንም ተጨማሪ ምግብ ሳያስፈልጋቸው በአግባቡ እንዲያጠቡ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑንም ገልጸዋል። የእናት ጡት የተሟላ የምግብ ንጥረ ነገሮችን የያዘ መሆኑን አመልክተው፤ እናቶች ልጆቻቸውን በአግባቡ በማጥባት ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችንና የአካል ጉዳትን ቀድመው እንዲከላከሉ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል። በተለይም ዕድሜያቸው ከስድስት ወር በታች የሆኑ ህጻናት የእናታቸውን ጡት ብቻ በአግባቡ እንዲጠቡ በማድረግ ጤናው የተጠበቀና አምራች ዜጋ በመፍጠር ረገድ ድርሻው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።   የዓለም የጡት ማጥባት ሳምንት በዓለም ለ32ኛ፣ በኢትየጵያ ደግሞ ለ16ኛ ጊዜ እየተከበረ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
የመምህራን ቅጥር ባልተከናወነበት መደብ ክፍያ ሲፈፅሙና ሲቀበሉ የተገኙ በጽኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጡ
Aug 2, 2024 118
ሆሳዕና ፤ሀምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፦በሀዲያ ዞን ሻሾጎ ወረዳ የመምህራን ቅጥር ባልተፈጸመበት መደብ ክፍያ የፈጸሙ የወረዳው የፋይናንስ አመራርና ባለሙያዎች እንዲሁም ደመወዝ ሲቀበሉ የተገኙ ግለሰቦች በጽኑ እስራትና በገንዘብ መቀጣታቸው ተገለጸ። ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ያሳለፈው በሀድያ ዞን በሻሸጎ ወረዳ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በተሳተፉ ሶስት የፋይናንስ ባለሙያዎችና ሁለት የጥቅም ተጋሪ በሆኑ ግለሰቦች ላይ ነው። የሀድያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዳኛ ጥላሁን ዴታሞ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የፅኑ እስራትና ገንዘብ ውሳኔው የተላለፈው በሻሾጎ ወረዳ የመምህራን ቅጥር ባልተፈጸመበት መደብ በ19 መምህራን ስም ክፍያ ፈጽመው በተገኙ ሶስት የፋይናንስ አመራርና ባለሙያዎች ላይ ነው። በተጨማሪም መምህራን ሳይሆኑና ሳይቀጠሩ በጥቅም ተጋሪነት በባንክ አካውንታቸው በየወሩ ደመወዝ ሲቀበሉ የነበሩና በቁጥጥር ስር የዋሉ ሁለት ግለሰቦችም ውሳኔው እንደተላለፈባቸው ገልጸዋል። ቀሪዎቹ አድራሻቸው በውል ያለመታወቁን ጠቁመው፤ ግለሰቦቹ በተገኙበት ተይዘው የሚቀርቡና ውሳኔ የሚተላለፍባቸው መሆኑንም አስረድተዋል። የፍርድ ውሳኔ ከተሰጣቸው መካከል የወረዳው የፋይናንስ ጽህፈት ቤት ምክትል የነበረው ግለሰብ ኃላፊነቱን ወደጎን በማለት የህዝብና የመንግስት ሀብትን ለአደጋ በመዳረግ በተጠረጠረበት የሙስና ወንጀል መሰረት ዐቃቤ ህግ ክስ መመስረቱን ጠቅሰዋል። ግለሰቡ ተጠርጥሮ የተከሰሰበት ከባድ የሙስና ወንጀል መሆኑንና ለፖሊስ እጅ እንዳልሰጠም በክስ ጭብጡ ላይ መመላከቱን ገልጸዋል። ወንጀሉ ከባድ ስለሆነ በሌለበት የ11 ዓመት ጽኑ እስራትና 10 ሺህ ብር እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ማስተላለፉንም አመልክተዋል። እንዲሁም ፋይናንስ ክፍያ ኦፊሰርና ፔሮል አዘጋጅ የነበሩ ሁለት ባለሙያዎች ደግሞ የሙስና ወንጀልን ለመከላከል የወጣውን አዋጅ በመተላለፍ እያንዳንዳቸው በ7 ዓመት ከ8 ወር ጽኑ እስራትና የ5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ እንደተላለፈባቸው ዳኛ ጥላሁን ተናግረዋል። መምህራን ሳይሆኑና ሳይቀጠሩ በጥቅም ተጋሪነት ሰንሰለት በመፍጠር በስማቸው በባንክ አካውንት በየወሩ የሚገባውን ገንዘብ ለዘጠኝ ወራት ሲቀበሉ ከነበሩት 19 ግለሰቦች እስከ አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ሁለቱ ክሱን ለማስተባበል ባለመቻላቸው የሦስት ዓመት ጽኑ እስራትና ሦስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንደተወሰነባቸው ገልጸዋል። ቀሪዎቹ አድራሻቸው በውል የማይታወቅ መሆኑን የጠቀሱት ዳኛ ጥላሁን፤ በፖሊስ ተይዘው በቀረቡ ጊዜ የፍርድ ውሳኔ እንደሚሰጣቸውም አመልክተዋል። በዚህም ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከተጠናቀቀው 2016 ዓ.ም ከ5 እስከ 11 ወራት በተፈፀመ ያልተገባ ክፍያ ከ730 ሺህ 239 ብር በላይ የመንግስትና የህዝብ ሃብት እንዲመዘበር መደረጉን ከቀረበው ክስ መረጋገጡን አስረድተዋል። ፍርድ ቤቱ የተፈጸመውን ወንጀል በሰውና በሰነድ ማስረጃ ያረጋገጠ ሲሆን፤ ተከሳሾችም ማስተባበል ባለመቻላቸውንና ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን ተናግረዋል። ሰራተኛው በስራ ገበታው ላይ ስለመገኘቱ ሙሉ መረጃ ለማግኘት የሚያስችል አሰራርን በመዘርጋትና የውስጥ ኦዲትን በማጠናከር መሰል ወንጀሎችን መከላከል እንደሚቻልም በምክረ ሃሳባቸው አመላክተዋል። የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ላልተገባ ዓላማ እንዳይውል መከላከል ከሁሉም ይጠበቃልም ብለዋል።          
ኮሚሽኑ በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የ14 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረገ
Aug 2, 2024 125
ሳውላ፤ ሐምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች 14 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ አደረገ። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት በመድረሱ የተሰማቸውን ኅዘን ገልጸው፣ በአደጋው ለተጎዱ ወገኖች መጽናናትን ተመኝተዋል። ኮሚሽኑ ለተጎጂዎች የተላከ 12 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ እና 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስ ይዞ ወደስፍራው መምጣቱንም ገልጸዋል። ኮሚሽኑ በቀጣይም በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ቀጣይ እንቅስቃሴ የድርሻውን እንደሚወጣ ምክትል ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል። ድጋፉን የተረከቡት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል። በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን ለማቋቋም በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
በአዲስ አበባ አንድ ባለሀብትን በማገት 20 ሚሊዮን ብር የተቀበሉ 7 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ
Aug 2, 2024 104
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ባለሀብትን በማገት 20 ሚሊየን ብር የተቀበሉ 7 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ መደረጉን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ። አጋቾቹ 20 ሚሊዮን ብር የተቀበሉት 100 ሚሊዮን ብር ካልከፈላችሁ በሚል ከብዙ ድርድር በኋላ እንደነበር አገልግሎት መስሪያ ቤቱ አስታውቋል። አቶ እንግዳው ውዱ የተባሉት ግለሰብ ቡና ወደ ውጭ በመላክ ሥራ ላይ የተሠማሩ ባለሀብት ናቸው፡፡ ግለሰቡ ያላቸውን የሀብት ሁኔታ ሲያጠኑ የቆዩት በእገታው የተሳተፉ ግለሰቦች፤ ስለባለሀብቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለማጥናት አንድ ተሸከርካሪ በቀን እስከ 1300 ብር ተከራይተው በአዲስ አበባ ውስጥ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡   አጋቾቹ ሲያደርጉት የነበረውን ጥናት አጠናቀው ባለሀብቱ እንዲታገቱ ውሳኔ ላይ ከደረሱ በኋላ፤ ግለሰቡን በአዲስ አበባ በተለምዶ ቦሌ ቡልቡላ 93 ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሲወጡ መንገድ በመዝጋት አግተው ከአዲስ አበባ ወደ አዋሽ መልካሳ በመውሰድም በታጋቹ ስልክ ለቤተሰብ በመደወል 100 ሚሊዮን ብር እንዲከፍሉ መደራደራቸውን የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህ ጥቆማ የደረሰው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፤ ታጋቹን በሙሉ ጤንነት፣ እንዲከፍል ከተጠየቀው ገንዘብ ጋር ለመመለስ እና አጋቾችን በቁጥጥር ስር በማዋል በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የመረጃ ኦፊሰሮችን ክትትል እንዲያደርጉ እና ከፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ኦፕሬሽን እንዲያካሂዱ ስምሪት መስጠቱን አመልክቷል፡፡ ይህ በህቡእ ተደራጅቶ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሰባት አባላት ያሉት የአጋቾች ስብስብ፤ የታጋቹን የአቶ እንግዳው ውዱን ቤተሰቡ 100 ሚሊዮን ብር እንደኪፈል በተደጋጋሚ በሞባይል ስልክ በመደወል ሲወተውት መቆየቱንና አንከፍልም ካሉ ግን ግለሰቡን በመግደል ሬሳውን በር ላይ እንደሚጥሉ ማስጠንቀቃቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይሁንና የታጋቹ ቤተሰቦች 100 ሚሊዮን ብር መክፈል እንደማይችሉ፤ የቤተሰቡን አባወራ ሕይወት ለመታደግ ሲሉ 20 ሚሊዮን ብር እንደሚከፍሉ ያሳውቃሉ ይላል መግለጫው፤ አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተል የአጋቾችን መውጫ እና መግቢያ እንዲሁም የግንኙነት መረብ በሚስጥር ሂደቱን ይከታተል እንደነበር በማመልከት፡፡ ታዲያ በዚህ መሀል አጋቾቹ የገንዘብ ቅብብሉ በዲጂታል አልያም በባንክ ከሆነ እንያዛለን በሚል ታጋቹን ለመልቀቅ የተስማሙበትን 20 ሚሊዮን ብር ለአያያዝ እንዲመች በሚል በወርቅ እና በዶላር ቀይረው እንዲያቀብሏቸውእና ታጋቹን ለመልቀቅ ይስማማሉ፡፡ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አክሎም፤ ይህን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉት የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ አመራሮችና ኦፊሰሮች አጋቾችና የታጋች ቤተሰብ ገንዘቡን በምሽት ሲቀባበሉ በቅርበት ሆነው ካረጋጋጡና ታጋቹ ከአዋሽ መልካሳ አዳማ ከተማ ድረስ እንዲመጡ ተደርገው መለቀቃቸውን እና ከቤተሰብ ጋር መቀላቀላቸውን ካረጋገጡ በኋላ ከኦሮሚያ እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በዚህ የአጋች ታጋች የወንጀል መረብ ውስጥ ያሉትን በሙሉ በቁጥጥር ስር ውል እንዲውሉ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ስር እንዲውሉና በህግ እንዲጠየቁ ያደረጋቸው በአጋችና ታጋች ወንጀል ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩ ተጠርጣሪዎች ይበልጣል ካኻሊ ግሩም፣ጎሳዬ ወንድሙ አባተ፣ ስንታየሁ ሞገስ ገብረየሰ፣ አብርሃም ታደሰ ማሞ ፣ደነቀው ቢታው ተገኝ፣ ሙሉቀን ከበደ ታዬ እና የሺዋስ ደበበ ደግፈው የተባሉ ግለሰቦች መሆናቸውን መረጃው ጠቁሟል፡፡ አጋቾቹ እራሳቸውን ለመደበቅ እና ከሕግ ተጠያቂት ለማምለጥ ከሶስት በላይ ሓሰተኛ ስሞችና መታወቂያዎችን ለመጠቀም ቢሞክሩም፤ ከፀጥታና ደኅንነት አካላት መሰወር እንዳላስቻለቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በመረጃው አመልክቷል፡፡ የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ መግለጫ አክሎም፤ በዚህ አጋች ታጋች ወንጀል ውስጥ ተሳትፈው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች ጋር ለዚሁ እኩይ ዓላማቸው የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ፣ተተኳሾች እና የተለያዩ ሰነዶች መያዛቸውን አስታውቋል፡፡ የወንጀሉ ተሳታፊዎች ቀደም ሲል በተመሳሳይ የአጋች ታጋች ወንጀሎች ንፁሃንን በማስገደድ በግፍ የሰበሰቡት በርካታ የኢትዮጵያ ብር እና የአሜሪካ ዶላሮች ጭምር መያዛቸውንም አመልክቷል፡፡ በአጋቾቹ ተይዘው የነበሩት በቡና ላኪነት የሚተዳደሩት እና 100 ሚሊዮን ብር ቤተሰቦቻቸው የተጠየቁት አቶ እንግዳው ውዱ በሰላም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲቀላቀሉ፤ አጋቾቹ የተቀበሉት የ20 ሚሊዮን ብር ግምት ወርቅና 30 ሺ ዶላርም በቁጥጥር ስር ውሎ ለቤተሰቡ እንዲመለስ መደረጉን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ በመረጃው ጠቁሟል፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት አጋቾች ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፤ እገታ በመፈፀም ገንዘብ መቀበል እንዲሁም በቤተሰብ በኩል ተጠይቀው እንዲከፍሉ እየተገደዱ ያሉ የህብረሰተብ ክፍሎች ለፀጥታና ደኅንነት አካላት ጥቆማ በመስጠት ወንጀለኞችና ግፈኞች በህግ ተጠያቂ እንዲሆን ለማድረግ የፀጥታና ደኅንነት አካላት እያደረጉ ያሉትን የተቀናጀ ኦፕሬሽን መረጃ በመስጠት እንዲደግፉና አንዲተባበሩ ጥሪ ያቀረበው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፤ በኦፕሬሽኑ ለተሳተፉ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡ እርምጃው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ አረጋግጧል፡፡              
በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ 
Aug 2, 2024 105
ጎፋ ሳውላ፤ ሐምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብና የዓይነት ድጋፍ ተደረገ። በክልሉ የመሬት መንሸራተትና ናዳ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ከአደጋ ስጋት ነጻ ወደሆኑ አካባቢዎች ለማዘዋወር እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል። ድጋፉን ዛሬ ያደረጉት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የቱሪዝም ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ናቸው። ከድጋፉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሁለት ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።   የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ አደጋው የደረሰባቸውን ወገኖች ለማጽናናት መምጣታቸውን ተናግረዋል። ሚኒስቴሩ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ኅዘኑን መግለጹን ጠቁመው፣ በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች መጽናናትን ተመኝተዋል። ሚኒስቴሩ አሁን ካደረገው ድጋፍ በተጨማሪ ተጎጂዎች መልሰው እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፉን ያጠናክራል ብለዋል።   የቱሪዝም ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማትም ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሦስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል። የቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ “የደረሰው አደጋ አስደንጋጭና ልብ የሚሰብር ነው'' ብለዋል ። ሚኒስቴሩ በሥሩ ካሉት የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንና የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር በመሆን ድጋፉን ማሰባሰቡን ተናግረዋል።   የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሺፈራው ተሊላ በበኩላቸው አገልግሎቱ በደረሰው አደጋ ተጎጂዎችን ለማጽናናትና ድጋፍ ለማድረግ በሥፍራው መገኘቱን ነው የገለጹት። ለተጎጂዎች መርጃ እንዲሆንም አምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማበርከቱን አስታውቀዋል። በተጨማሪም በአካባቢው ጉዳት የደረሰበትን የኤሌክትሪክ ትራንስፎርመር ለመተካት አዲስ ትራንስፎርመር ይዘው መምጣታቸውን ተናግረዋል። አገልግሎቱ ተጎጂዎች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ የጀመረውን ድጋፍ እንደሚያጠናክርም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።   የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መስከረም አበበ እንዳሉት በደረሰው ጉዳት የሊጉ አባላት የተሰማቸውን ኅዘን ገልጸው፣ ሊጉ በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ 100 ሺህ ብር ድጋፍ ማበርከቱን ተናግረዋል። ሊጉ በቀጣይም ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን በማመላከት።   ድጋፉን ከተቋማቱ የተረከቡት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ ናቸው። ኢንጂነር አክሊሉ ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ በክልሉ መንግሥት ስም አመስግነዋል። በክልሉ የመሬት መንሸራተትና ናዳ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ከአደጋ ስጋት ነጻ ወደሆኑ አካባቢዎች ለማዘዋወር ከፌዴራል መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።      
ድርጅቱ በገዜ ጎፋ ወረዳ ለተቋቋሙ ጊዜያዊ የሕክምና መስጫ ማዕከላት ድጋፍ አደረገ
Aug 2, 2024 109
ጎፋ፤ ሀምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፡- የአለም ጤና ድርጅት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ለተቋቋሙ ጊዜያዊ የህክምና መስጫ ማዕከላት የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ድጋፍ አደረገ። ድርጅቱ ድጋፍ ያደረገው በገዜ ጎፋ ወረዳ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ከቄያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የህክምና እርዳታ ለመስጠት ለተቋቋሙ ጊዜያዊ የህክምና መስጫ ማዕከላት ነው። ድጋፉ በወረዳው የተቋቋሙ አምስት ጊዜያዊ የህክምና አገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ለማጠናከር እንደሚያግዝም በድርጅቱ የሀዋሳ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር በረከት ያለው ገልጸዋል። ድጋፉ በጠቅላላው 50 ሺህ ዶላር የሚገመት እገዛ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው፣ በድጋፉ የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችና የመጠለያ ድንኳኖች ተካተዋል ብለዋል። በተጨማሪም ለሥራው አጋዥ የሆኑ ሁለት ተሽከርካሪዎች ለሁለት ወር በኮንትራት አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍ መደረጉን ነው ያስረዱት። ድጋፉን የተረከቡት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ ተቋሙ ላደረገው ድጋፍ በዞኑ አስተዳደርና በተጎጂዎች ስም ምስጋና አቅርበዋል።  
በጅማ ዞን  በመሬት መንሸራተት አደጋ  ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለማቋቋም ድጋፍ ይደረጋል
Aug 2, 2024 117
ጅማ፤ሀምሌ 26/2016 (ኢዜአ):- በጅማ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለማቋቋም ድጋፍ እንደሚደረግ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም (ዶ/ር) አስታወቁ። የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በጅማ ዞን በጎማ እና ጌራ ወረዳዎች ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተከሰቱ የመሬት መንሸራተት አደጋዎችን በስፍራው ተገኝተው ተመልክተዋል። የስራ ኃላፊዎቹ በዞኑ አንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለው የመሬት መንሸራተት አደጋ እየሰፋ ሄዶ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ለመከላከል ሰራው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አመልክተዋል። የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም (ዶ/ር) በጉብኝቱ ወቅት እንዳሉት፤ አሁንም አደጋው እየሰፋ እንዳይሄድ የቅድመ ጥንቃቄ ስራ መሰራት አለበት። ለዚህ ደግሞ ኮሚሽኑ ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመሆን የተጀመሩ የቅድመ መከላከል ስራዎች እንዲጠናከሩ አስፈላጊው ስራ ይሰራል ብለዋል። በተለይም የአደጋው ተጋላጭ የሆኑ ወገኖችን ከስጋት ቀጣና የማራቅ እና አደጋው የደረሰባቸውን ደግሞ መልሶ የማቋቋም እና የመደገፍ ስራ በቅንጅት እንደሚሰራ ገልፀዋል። በመሬት መንሸራተቱ ተጎጂ የሆኑ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑንም ኮሚሽነሩ አመልክተዋል።   የጅማ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ቲጃኒ ናስር በበኩላቸው የመሬት መንሸራተት አደጋው በዞኑ አልፎ አልፎ በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል። የዞኑ አስተዳደርም በመሬት መንሸራተት አደጋው የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማዳበር ጭምር አስፈላጊውን ጥንቃቄ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። በዞኑ በጌራና ጎማ ወረዳዎች ባለፉት ዓመታት የተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋም በርካታ ሰዎችን ከቀያቸው ማፈናቀሉን አስታውሰዋል። ምንም እንኳን የጉዳቱ መጠን የተለያየ ቢሆንም ችግሩ በዞኑ በሰባት ወረዳዎች መታየቱን የገለጹት አስተዳዳሪው በጌራ ወረዳ ብቻ 284 ነዋሪዎች ተጋላጭ ሲሆኑ 81 ቤቶች በአደጋው ፈርሰዋል ብለዋል። አደጋው የደረሰባቸው ወገኖች በበኩላቸው ቤታቸው በመፍረሱ ለችግር መዳረጋቸውን ገልጸዋል። የጎማ ወረዳ ነዋሪ አቶ ገዛኸኝ ነጋሽ፣ የመሬት መንሸራተት አደጋው ቤታቸውን ያፈረሰባቸው በመሆኑ ለችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል።   የደረሰባቸው ተፈጥሮአዊ አደጋ ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀላቸው በመሆኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም ጠይቀዋል። በወረዳው የሊሙ ሻይ አካባቢ ነዋሪ አቶ በቀለ ደስታ በበኩላቸው ቤታቸው በናዳው ቢፈርስባቸውም የከተማው አስተዳደር የቤት መስሪያ ምትክ ቦታ የሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም አደጋው ሊስፋፋ ስለሚችል በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ቅደመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያሳሰቡት ነዋሪው ችግሩ በመንግስት በኩልም ትኩረት የሚፈልግ ነው ብለዋል። በጉብኝቱ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) እና ሌሎችም የፌዴራል መንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።  
የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የሚሰሩ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ የፋርማሲ ባለሙያዎች ሙያዊ ኃላፊነታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል
Aug 2, 2024 96
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦በሀገሪቱ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ የሚሰሩ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ የፋርማሲ ባለሙያዎች ሙያዊ ኃላፊነታቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የኢትዮጵያ መድኀኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ገለጹ። የኢትዮጵያ ፋርማሲ ማህበር” የፋርማሲ ባለሙያዎች የመጀመሪያ ደረጃ የጤና እንክብካቤን ከማጠናከር አንጻር ያላቸው ሚና” በሚል መሪ ሃሳብ 44ኛውን ዓመታዊ ጉባኤ ማካሄድ ጀምሯል።   በጉባዔው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ መድኀኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ ማህበሩ የፋርማሲ ዘርፉ ውጤታማ እንዲሆን የሚሰራቸው ስራዎች የሚበረታቱ እና ሊጠናከሩ የሚገቡ ናቸው ብለዋል። የፋርማሲ ባለሙያዎች ጤናማ ማህበረሰብን ለመፍጠርና የጤናው ዘርፍ አበረታች ለውጥ እንዲያመጣ ትልቅ አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በተለይም የፋርማሲ ባለሙያዎች በሀገሪቱ ያለው መሰረታዊ የጤና አጠባበቅ ስርአት ውጤታማና ተደራሽ እንዲሆን ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ተናግረዋል። ከዚህም ባሻገር የህክምና ግብቶች ጥራታቸውንና ደህንነታቸውን ጠብቀው በበቂ ሁኔታና ጤናማ በሆነ መንገድ ለማህበረሰቡ እንዲደርሱ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስታውቀዋል። የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በመንግስት የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ የፋርማሲ ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፋቸውን ከምንጊዜውም በላይ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል። በሀገሪቱ ጤናማ የሆነ ማህበረሰብን ለመፍጠር ፋርማሲስቶች ሙያዊ ስነ ምግባርን የተላበሰ አገልግሎት ለህብረተሰቡ መስጠት ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል። የኢትዮጵያ የፋርማሲ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ሰይፉ በበኩላቸው ማህበሩ በሀገሪቱ የሚሰጡ የጤና እንክብካቤ አገልግሎቶች እንዲጠናከሩ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ማህበሩ ይህንኑ ተግባሩን አጠናክሮ ለማስቀጠል 44ኛውን ጉባኤ ምክንያት በማድረግ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ለሁለት ቀናት የሚቆይ ምክክር ማካሄድ መጀመሩን አስታውቀዋል ። ጉባኤው መንግስት የጤና ተደራሽነት ለማረጋገጥ "ጤና ለሁሉም" በሚል መሪ ሃሳብ የሚሰራቸው ተግባራቶች ውጤታማ እንዲሆኑ ከፋርማሲ ባለሙያዎች ምን ይጠበቃል የሚሉ ነጥቦችን በመለየት በዘርፉ የተሻለ ስራ ለመስራት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም