ተመድ በሶሪያ በርዕደ መሬት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል የ397 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ጥሪ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ተመድ በሶሪያ በርዕደ መሬት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል የ397 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ጥሪ አቀረበ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 8/2015 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በሶሪያና ቱርክ ድንበር አቅራቢያ በደረሰው ርዕደ መሬት ሳቢያ ከቤታቸው የተፈናቀሉ ሶሪያውያንን ለማገዝ የ397 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ጥሪ አቀረቡ።
ዋና ጸሓፊው ጥሪውን ያቀረቡት ባሳለፍነው ሳምንት በቱርክና በሶሪያ ድንበር አቅራቢያ በደረሰው ርዕደ መሬት ሳቢያ ከቤታቸው የተፈናቀሉ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ ሶሪያውያንን ለማገዝ ነው።
በኒውዮርክ በሰጡት መግለጫ ሶሪያውያኑን ለማገዝ የተጠቀሰው የገንዘብ መጠን ለሶስት ወራት ጊዜ ብቻ የሚበቃ መሆኑን ጠቅሰው የሚመለከታቸው ሁሉ የድርሻቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ከአደጋው በኋላ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 50 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር አስቸኳይ ድጋፍ ማቅረቡን ገልጸው ተጨማሪ እገዛዎች አሁንም እንደሚያስፈልጉ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
በድርጅቱ ስር የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትና አጋር አካላት በጋራ በሚያቀርቡት ገንዘብ፤ አስቸኳይ ድጋፍ ለሚፈልጉ ሶሪያውያን የመጠለያ፣ የጤና፣ የምግብ እንዲሁም ሌሎች አስቸኳይ ድጋፎች እንደሚደረጉ አብራርተዋል።
ተመሳሳይ የድጋፍ ማዕቀፍ በቱርክ ድንበር ለሚገኙ ዜጎች እየተጠናቀቀ እንደሚገኝም ዋና ጸሓፊው ተናግረዋል።