ሳይንስና ቴክኖሎጂ - ኢዜአ አማርኛ
ሳይንስና ቴክኖሎጂ
አየር ኃይል አሁን ለገነባው ከፍተኛ ወታደራዊ የዝግጁነት አቅም የሙያተኛው ድርሻ የጎላ ነው - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
Feb 1, 2025 42
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦አየር ኃይል አሁን ለገነባው ከፍተኛ ወታደራዊ የዝግጁነት አቅም የሙያተኛው ድርሻ የጎላ መሆኑን የአየር ሃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ። የኢፌዴሪ አየር ኃይል ሎጀስቲክስ የእውቅና እና የምስጋና መርሃ-ግብር በአየር ኃይል መኮንኖች ክበብ አካሂዷል። ዋና አዛዡ በመርሃ-ግብሩ በመገኘት ለተቋሙ የግዳጅ አፈፃፀም ስኬት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለነበራቸው ክፍሎች የእውቅና እና የምስጋና ሰርተፍኬት ሰጥተዋል። ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ የአየር ኃይል ሎጀስቲክስ የተቋሙን የማድረግ አቅም ወደ ላቀ ከፍታ ያሸጋገሩ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ጠቅሰው አየር ኃይሉ ለገነባው አሁናዊ ከፍተኛ የዝግጁነት አቅም የክፍሉ ሙያተኞች ድርሻ ከፍተኛ እንደነበረ ተናግረዋል ። የአየር ኃይል ምክትል አዛዥ ለአየር ሎጀስቲክስ ብርጋዲየር ጄኔራል ነገራ ሌሊሳ በበኩላቸው ተቋሙ አዳዲስ የአቪዬሽን ትጥቆችን ከመታጠቅ ባለፈ ያሉትን ጠግኖ ወደ ግዳጅ በማሰማራት ረገድ ክፍሉ ያከናወነው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይነትም በሁሉም መስክ የጀመርናቸውን ስራዎች በላቀ የስራ ተነሳሽነት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል። በመርሃ ግብሩ ላይ የተሰጣቸውን ግዳጅ እና ተልዕኮ በብቃት ከመፈፀም ባለፈ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችን ለሰሩ ክፍሎች የእውቅና እና የምስጋና ሰርተፊኬት እንደተሰጣቸው ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በክልሉ ልማትን የሚያጠናክሩ መረጃዎች ተደራሽ በማድረግ የተመዘገቡ ውጤቶችን የሚያጎለብቱ ተግባራት ይቀጥላሉ
Feb 1, 2025 41
ቦንጋ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የወል በሆነ መልኩ ልማትና ዕድገትን የሚያጠናክሩ መረጃዎች ተደራሽ በማድረግ የተመዘገቡ ውጤቶችን የሚያጎለብቱ ተግባራት እንደሚቀጥሉ የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለጸ። የቢሮው የበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት የተግባር አፈጻጸም ላይ የመከረ መድረክ በቦንጋ ከተማ ተካሄዷል። በዚህ ወቅት የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ የሺዋስ ዓለሙ፣ ቢሮው የመረጃ ተደራሽነትን ለማስፋት የመገናኛ ብዙሃን እና የኮሙኒኬሽን መዋቅሩን በማስተባበር በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል። ለአብነት ክልሉ ያሉ የልማት አቅሞች በማስተዋወቅ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝምና በሌሎች ሀብቶች እንዲመጡና ማህበረሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረጉን ጠቅሰዋል። እንደአገር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመቻቹ የተለያዩ ኢንሼቲቮችን ለህዝብ ለማስተዋወቅና ሀሳቡን ለማስረፅ በተከናወነው ስራ ተስፋ ሰጪ ለውጥ መምጣቱንም ጠቁመዋል። በተለይም የወል በሆነ መልኩ ዕድገትንና ልማትን የሚያጠናክሩ መረጃዎች ተደራሽ በማድረግ ረገድ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር በመተባበር በተደረገው ጥረት የተመዘገቡ ውጤቶችን የሚያጎልበቱ ተግባራት እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። በቀጣይም በዋና ዋና የልማት አጀንዳዎች፣ ሰላምን በሚገነቡና የሕዝቦች ትስስርን በሚያጠናክሩ ጉዳዮች ላይ በተቀናጀ መንገድ እንደሚሰራመ አቶ የሺዋስ አብራርተዋል። በመድረኩ የተሳተፉ የመገናኛ ብዙሃንና የኮሙዩኒኬሽን አመራር አባላት በሰጡት አስተያየት፤ከለዉጡ ወዲህ መንግስት ያመቻቸውን የመገናኛ ብዙሃን ነፃነት በመጠቀም በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። በቀጣይም የአገሪቱ የልማትና ብልፅግና ጉዛ የተሳካ እንዲሆን ህብረተሰቡን በማንቃትና እውነታውን በማሳወቁ ረገድ የሚጠበቅባቸውን አንደሚወጡ ገልጸዋል። ለአንድ ቀን በተካሄደው የምክክር መድረኩ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ተወካዮች፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የጥናትና ምርምር ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግና ችግሮችን ለመፍታት አቅም መሆን አለባቸው
Jan 31, 2025 62
ሀዋሳ ፤ጥር 23/2017 (ኢዜአ):- በምሁራን የሚሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግና ችግሮችን ለመፍታት አቅም ከመሆን ባለፈ መንግስት ለሚነድፋቸው ፖሊሲዎች ግብዓት መሆን እንዳለባቸው ተገለፀ። የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር "ብሔራዊ ጥቅሞቻችንና ቀጣናዊ ትስስር ለሚዛናዊ የህዝቦች ተጠቃሚነት" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ ተካሄዷል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ጅሀድ ናስር እንደገለፁት፤ በዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሚያደርጉት የጥናትና ምርምር ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግና ችግሮችን ለመፍታት አቅም ከመሆን ባለፈ መንግስት ለሚነድፋቸው ፖሊሲዎች ግብዓት ሊሆኑ ይገባል። በውይይት መድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስቴርን በመወከል የተገኙት በተቋሙ የብሔራዊ መግባባት ባለሙያ ወይዘሮ ሲሳይ ብርሌ እንዳሉት ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅና ቀጣናዊ ትስስርን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የምሁራን ሚና የላቀ ነው። የዛሬው ውይይትም ለሀገር እድገት ግብዓት የሚሆኑ የጥናት ውጤቶችንና አማራጭ ሀሳቦችን ምሁራን የሚያፈልቁበት አጋጣሚን የማመቻቸት ዓላማ እንዳለውና መሰል መድረኮችም በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚካሄዱ ተናግረዋል። የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) እንዳሉት ምሁራን ሀገርና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምርምር ስራዎችን መስራት ይጠበቅባቸዋል። መድረኩ ምሁራን ለቀጣናዊ ትስስሮችና ለሀገር ግንባታ ያላቸውን አበርክቶ ለማጉላት የዳበረ ምክረ ሀሳብ ማቅረብ እንዲችሉ ታስቦ መዘጋጀቱንም ጠቁመዋል። በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ተመራማሪ ዳኜ ሽብሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት በኢትዮጵያ ሰላምን፣ ልማትንና ብልጽግናን ለማምጣት ከቀጣናው ሀገራት ጋር ተባብሮና ተደጋግፎ መስራት ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ሰላም ለቀጣናው ሰላምና ልማት መጠናከር የላቀ ሚና ስላለው ለተግባራዊነቱም ቀጣናዊ ትብብር ላይ መስራት የግድ እንደሚል ተናግረዋል። በውይይት መድረኩ ላይ የሰላም ሚኒስቴርና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተወካዮችና የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተሳታፊ ሆነዋል።
11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ሆነዋል
Jan 31, 2025 63
አዲስ አበባ፤ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ የወሰዱ ዜጎች ቁጥር 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን መድረሱን የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም አስታውቋል፡፡ የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ የነዋሪዎችን የባዮሜትሪክ (የጣት አሻራ፣ የአይን አይሪስ እና የፊት ምስል) እንዲሁም የግል መረጃዎችን በመሰብሰብ አንድን ግለሰብ ልዩ በሆነ መልኩ እንዲታወቅ የሚያስችል ነው፡፡ ይህም ዘመናዊ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓትን በመገንባት ማንነትን የማረጋገጥ ሂደት ቀልጣፋ እና ደህንነቱ የተረጋገጠ እንዲሆን ያደርጋል። የፕሮግራሙ የስትራቴጂክ የኮሙኒኬሽን አማካሪ አቶ አቤኔዘር ፈለቀ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ፕሮግራሙ ከተጀመረ አመታት ማስቆጠሩን ተናግረዋል። በነዚህ አመታት ውስን በፕሮግራሙ የታቀዱ ውጥኖች ማሳካት የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል። እስከ አሁን ድረስ ከ1 ሺህ በላይ በሆኑ የምዝገባ ጣቢያዎች 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች መታወቂያውን መውሰዳቸውን አስታውቀዋል። ከ52 ተቋማት ጋር ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ትግበራና የአሰራር ትስስር መዘርጋት የሚያስችል ስራ መሰራቱንም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያን 12 የሚደርሱ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙም ገልጸዋል። የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም የሕግና ፖሊሲ ክፍል ኃላፊ ጋብሬላ አብርሃም በበኩላቸው፥ በ2017 ዓ.ም የብሔራዊ መታወቂያ ምዝገባ በተጠናከረ አግባብ እየተከናወነ ነው ብለዋል። በዚህም በተቋሙና በምዝገባ ሂደት አጋር በሆነው ኢትዮ ቴሌኮም አማካኝነት በአገር አቀፍ ደረጃ ምዝገባ እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል። ይህም በከተሞች ብቻ የነበረውን ምዝገባ በገጠር አካባቢዎችም ተደራሽ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፥ ይህም በዓመቱ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት እንደሚያስችል ጠቅሰዋል። ምዝገባውን በድንበር አካባቢዎችም ተደራሽ ለማድረግ በግል ተቋማት የሚከናወን ሱፐርኤጀንት የሚባል አሰራር ተግባራዊ እንደሚደረግ ጠቁመዋል። ፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ መደረጉ ሁሉን አቀፍ፣አካታችና አስተማማኝ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችልም ተመላክቷል። ዜጎች የዲጂታል መታወቂያ ዘርፈ ብዙ አስፈላጊነትን በመገንዘብ በአቅራቢያቸው በሚገኙ የመመዝገቢያ ጣቢያዎች በመመዝገብ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ተጠቃሚ እንዲሆኑም ኃላፊዎቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ባለፉት የለውጥ አመታት ለመጪው ቴክኖሎጂ ዝግጁ የሚያደርጉ ምቹ መደላድሎች ተፈጥረዋል-የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር
Jan 30, 2025 69
አዲስ አበባ፤ጥር 22/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት የለውጥ አመታት ለመጪው ቴክኖሎጂ ዝግጁ የሚያደርጉ ምቹ መደላድሎች መፈጠራቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን አለማየሁ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት ከለውጡ በኋላ ባሉት አመታት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ በመገባቱ በዘርፉ በርካታ ለውጦች መጥተዋል። እስካሁን ባለው 11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ለዲጂታል መታወቂያ መመዝገባቸውን ገልፀው፥ የዲጂታል ክፍያ አማራጮችን የማስፋት ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። በዚህም የቴሌኮምና ኤሌክትሮኒክስ ተደራሽነትን በማስፋት በኩል ውጤታማ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው፥ ኔትወርኩን ከ 2 ጂ ወደ 5 ጂ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል። ከ800 በላይ የመንግስት አገልግሎቶች በኦንላይን እየተሰጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል። አስተማማኝ የዲጂታል ስርዓት ለመፍጠር በተከናወኑ ተግባራት ጠንካራ የሳይበር ደህንነት ተቋም መገንባቱን አብራርተዋል። በአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ መርኃ ግብር ከ460 ሺህ በላይ ዜጎች ለስልጠና መመዝገባቸውንና ከእነዚህም ውስጥ ከ127 ሺህ በላይ የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን ገልፀዋል። በለውጡ አመታት ስታርት አፖችን ለማበረታታት የሚያስችሉና ለመጪው ቴክኖሎጂ ዝግጁ የሚያደርጉ ምቹ መደላድሎች መፈጠራቸውንና የተለያዩ የህግ ማዕቀፎች መዘጋጀታቸውንም አስረድተዋል። የለውጡ ሂደት የሚኒስቴሩን አቅም በማሳደግ ቴክኖሎጂን ከመቅዳት በራስ ወደ መፍጠር ያሸጋገረና ለገበያ የሚቀርቡ የፈጠራ ውጤቶች እንዲበራከቱ ማድረጉንም ጠቁመዋል። ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለአለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ የሚያስችል የጥራት መንደር መገንባቱንም ገልፀዋል።
የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወጣቱን ለፈጣን ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ብቁ ተወዳዳሪ የሚያደርግ ነው
Jan 29, 2025 72
ደብረ ብርሀን ፤ ጥር 21/2017 (ኢዜአ) ፡- የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወጣቱን ለፈጣን ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ብቁና ተወዳዳሪ የሚያደርግ መሆኑ ተገለጸ። በሰሜን ሸዋ ዞን የኢትዮ ኮደርስ የስድስት ወር ዕቅድ አፈፃፀምና ቀጣይ ተግባራት ላይ የመከረ መድረክ ዛሬ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሄዷል። የአማራ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ሙሉነህ ዘነበ በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት ፤ በክልሉ በ22 ከተሞች የኢትዮ ኮደርስ መርሃ ግብር እየተተገበረ መሆኑን አመልክተዋል። ስልጠናው የነገይቱን ኢትዮጵያን የሚረከቡ ወጣቶችን ለማዘጋጀት ያለመ መሆኑንና ለዚህም የክልሉ መንግስት በወጣቶች ተጠቃሚነት ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የሰሜን ሸዋ ዞን ስራና ስልጠና መምሪያ ምክትል ሀላፊ ነፃነት ንጉሴ በበኩላቸው፤ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በቴክኖሎጂ የዳበረ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመገንባት የጎላ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ከ14 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች በመርሀ ግብሩ ዙሪያ ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ 3 ሺህ 92 የሚሆኑት ስልጠናውን እንዲወስዱ መደረጉን አስረድተዋል። ክእነዚህም 2 ሺህ 153 የሚሆኑት ስልጠናውን በብቃት አጠናቀው ዓለም አቀፍ ሰርተፍኬት መውሰድ ችለዋል ነው ያሉት። የኮደርስ ስልጠና በተለይ የሴቶችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን አመልክተው፤ በቀጣይ ስልጠናው በስፋት እንዲሰጥ እንሰራለን ሲሉ አስታውቀዋል። ስልጠናው በዞኑ 56 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ የ11ኛ እና 12 ክፍል ተማሪዎች እየተሰጠ ነው ያሉት ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ፀጋዬ እንግዳ ወርቅ ናቸው። የደብረብርሀን መምህራን ኮሌጅ ተወካይ አቶ ቻለው አሳሳ በበኩላቸው፤ ለኮሌጁ ተማሪዎችና መምህራን ግንዛቤ ከመፍጠር ባለፈ 44 የሚሆኑት ስልጠናውን ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ ስልጠናውን በስፋት ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር እየተመቻቸ ነው
Jan 29, 2025 77
ቡታጅራ፤ ጥር 21/2017(ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ ለማድረግ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር እየተመቻቸ መሆኑን የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ፡፡ ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት እቅድ አፈፃፀምና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ዛሬ በቡታጅራ ከተማ ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ የቢሮው ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ እንዳመለከቱት፤ በክልሉ የሚገኙ ተቋማትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማዘመን ተገልጋዩ በቦታ ሳይገደብ ፍትሀዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ ጥረት እየተደረገ ነው። ተቋማት የሚያከናውኗቸው ሥራዎች እና የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች በድረገፅ እንዲያስተዋውቁ 15 ድረ-ገፆችን ማልማት መቻሉን ተናግረዋል። በተለያዩ ተቋማት የሚደረጉ ስብሰባዎችን በቪዲዮ ኮንፍረንስ እንዲከናወኑ በማድረግ ወጪን መቆጠብ መቻሉንም ገልጸዋል። በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተገነባ ተቋምና የሰው ኃይልን ማመቻቸቱን በመቀጠል በሁሉም መስክ ክልሉን ተወዳዳሪ ለማድረግ እንደሚሰራም ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ የጉራጌ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምስ ገብሬ በበኩላቸው፤ በዞኑ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ የተገልጋይ እርካታን ከማሳደግ አንጻር ለውጥ እየመጣ ይገኛል ብለዋል፡፡ እንዲሁም በዞኑ የፈጠራ ስራዎችን ከማበረታታት አንፃር ከ20 በላይ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ የፈጠራ ስራዎች እውቅና ማግኘት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ በከተማው ተቋማት በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተደገፈ ፍትሀዊና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን የገለጹት ደግሞ የወራቤ ከተማ አስተዳደር የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ባርሰባ ናቸው። ተግባሩን አጠናክሮ በማስቀጠል በዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ በመድረኩ የዞንና የልዩ ወረዳ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎችን ለዲጂታል መታወቂያ(ፋይዳ) መዝግቧል
Jan 29, 2025 81
አዲስ አበባ፤ ጥር 21/2017(ኢዜአ)፡-ኢትዮ ቴሌኮም እስካሁን 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎችን ለዲጂታል መታወቂያ(ፋይዳ) መመዝገቡን አስታወቀ። ከ427 ሺህ በላይ የመታወቂያ ካርዶች ታትመው ለህብረተሰቡ ተደራሽ መሆናቸውንም ገልጿል። የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ከስተመር ኤክስፒሪያንስና ኳሊቲ ኦፊሰር ሰለሞን አበራ እንዳሉት ኢትዮ ቴሌኮም ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም ከብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር ስምምነት በማድረግ በ275 ከተሞች የዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ እየተካሄደ ነው ብለዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ ለዲጂታል መታወቂያ ከተመዘገቡ 11 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም 5 ነጥብ 5 ሚሊየኑን መመዝገቡን ተናግረዋል። በዓመት እስከ 48 ሚሊየን መታወቂያዎችን ማተም የሚችሉ ማሽኖች በማስገባት የህትመት ስራን እያፋጠነ ነው ያሉት አቶ ሰለሞን አበራ፥ መታወቂያው ለ10 ዓመት ማገልገል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ እስካሁን ባለው ሂደት በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ ሃዋሳ፣ ነቀምትና ወላይታ ሶዶ ከተሞች መታወቂያ እየታተመ ለህብረተሰቡ ተደራሽ መሆኑን አንስተዋል። ኢትዮ ቴሌኮም የመታወቂያ ህትመት አገልግሎቱን እስከ የካቲት ወር አጋማሽ ድረስ በሁሉም አካባቢዎች ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የካርድ ህትመት ከተጀመረ ከሁለት ወር በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፥ 427 ሺህ የመታወቂያ ካርዶች ታትመው ለህብረተሰቡ እንዲደርሱ መደረጉንም ነው የገለጹት። በአዲስ አበባ 63 የካርድ መረከቢያ ቦታዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ በቴሌ ብር ክፍያ በመፈፀም የዲጂታል መታወቂያ ካርዱን መውሰድ እንደሚችሉም ተናግረዋል። በኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል መታወቂያ ካርዳቸውን ለመውሰድ ከመጡ ተገልጋዮች መካከል ጌታቸው ዓለሙ እና ባንቴ ጌትነት በበኩላቸው፥ ከምዝገባ ጀምሮ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል የኮደርስ ስልጠና ፕሮጀክትን ማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ - የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ
Jan 29, 2025 65
ጎንደር፤ ጥር 21/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል እየተከናወነ የሚገኘው የኢትዮ ኮደርስ የስልጠና ፕሮጀክትን ማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ገለጸ። በክልሉ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና መርሃ ግብር የ6 ወራት የስራ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተካሂዷል፡፡ በጎንደር ከተማ በተካሄደው በዚሁ መድረክ የተገኙት የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ አማረ አለሙ እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቱ ወጣቶች የዲጂታል ቴክኖሎጂ ክህሎትና እውቀት በማዳበር ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህም እውቀትና ክህሎትን በማስታጠቅና በማብቃት ዘመኑን የዋጀ ትውልድ መገንባት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ዜጎችን የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን አመልክተው፤ ከ205 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶችና ለሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መከናወኑን ጠቅሰዋል፡፡ ስልጠናውን የሚከታተሉ ሰልጣኞች 45ሺህ መድረሳቸውን ጠቁመው፤ ከ23ሺህ በላይ የሚሆኑት ስልጠናቸውን አጠናቀው ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው ሰርቲፊኬት መቀበለቻውን አስረድተዋል። ስልጠናው በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ በዳታ ሳይንስና በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎትና ብቃት በማሳደግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በክልሉ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ተደራሽ ለማድረግ ለተያዘው ዕቅድ ስኬታማነት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በየደረጃው ያለ የአመራር አባል ተልዕኮዎችን ተቀብሎ በመፈጸም ለፕሮጀክቱ መሳካት እንዲረባረብ መልዕክት አስተላልፈዋል። በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ፕሮጀክቱን የሚከታተልና የሚደግፍ አንድ ዐቢይ እና የቴክኒክ ከሚቴዎች ተዋቅረው ስልጠናውን ለማሳካት እየሰራ ነው ያሉት የዞኑ አስተዳደር ተወካይ አቶ ዳንኤል ወርቁ ናቸው፡፡ ኢትዮ ኮደርስ የወጣቶችን የዲጂታል ቴክኖሎጂ የአስተሳሰብ አድማስ ማስፋትና ማጎልበት የሚያስችል አለም አቀፍ ኢኒሼቲቭ መሆኑን ጠቁመው፤ የዲጂታል ክህሎት ስልጠና መርሃ ግብሩ እንዲሳካ የአመራር አባላት በትኩረት እየሰሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ስራና ስልጠና መምሪያ ሃላፊ አቶ እዮብ አግማስ በበኩላቸው፤ በዞኑ የስልጠና ማዕከላት ተቋቁመው በ92 የስልጠና አመቻቾች መርሃ ግብሩ እየተከናወነ ነው ብለዋል። በበጀት ዓመቱ የስልጠና ዕድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ ከታቀደው ውስጥ እስካሁን 5ሺህ 280 ስልጠና መውሰዳቸውን አስታውቀዋል፡፡ በመድረኩ በየደረጃው ያሉ አመራር አባላት በተገኙበት የስድስት ወራት የአፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ተገምግሟል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት በኢትዮጵያና በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግስታት ትብብር የ"አምስት ሚሊዮን ኮደርስ" መርሃ ግብር በመላ ሀገሪቱ እየተተገበረ ይገኛል፡፡
በክልሎች ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፉን ለማዘመን ቴክኖሎጂ መር አሰራሮች ተዘርግተዋል
Jan 29, 2025 56
አዳማ፤ ጥር 21/2017 (ኢዜአ)፦ የትራንስፖርት አገልግሎትን ዘርፉን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሰራሮች መዘርጋታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የክልልና የከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮዎች ገለጹ። ኢዜአ ያነጋገራቸው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ የኦሮሚያ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ሀላፊዎች የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር እየዘረጉ ነው። በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑርዬ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሳለጥና ተደራሽ ለማድረግ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል። በህዝብ መናኽሪያዎች ተገልጋዩን የሚያንገላቱና ከታሪፍ በላይ ክፍያን ለማስወገድ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል። በ11 መናኸሪያዎች የኤሌክትሮኒክ ትኬት(ኢ-ትኬት) አገልግሎት መተግበሩን ገልጸው፤ ይህን በሌሎች መናኸሪያዎች ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የመንጃ ፍቃድና የአሽከርካሪዎች ስልጠና አገልግሎቱን ከኪራይ ሰብሳቢነት የጸዳ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች እንደላ ገልጸዋል። የኦሮሚያ ትራንስፖርት ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ቸርነት በበኩላቸው አገልግሎቱን ለማዘመን በክፍያ፣ በተሽከርካሪ ስምሪት፣ በመንጃ ፍቃድ እድሳት፣ በተሽከርካሪ የቴክኒክ ፍተሻና የቦሎ አሰጣጥ የአንድ መስኮት አገልግሎት መጀመሩን አመልክተዋል። የመንጃ ፍቃድን ህጋዊነት ለመቆጣጠርም የ'ኦን ላይን' ምዝገባ ቋት መዘጋጀቱን ገልጸው፤ የአሸከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማትንና የቦሎ አገልግሎትን በሲሲቲቪ ካሜራ በመከታተል የሥነ ምግባር ችግሮች ቁጥጥር እየተደረገ ስለመሆኑ አስረድተዋል። በክልሉ በ290 መናኸሪያዎች ላይ የኢ-ትኬት አገልግሎት በማስጀመር ህብረተሰቡን ከእንግልትና አላስፈላጊ ወጪ መታደግ ተችሏ ብለዋል። የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወርቁ ደስታ፤ በመዲናዋ የትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማሳለጥ በተለይ የከተማ አውቶቢስ ሪፎርም ማድረጉን ጠቅሰዋል። የትራንስፖርት ምልልሱን በመጨመር ህብረተሰቡ በፍጥነት አገልግሎት ማግኘት የሚችልበት አሰራር መዘርጋቱን አስታውቀዋል። የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ብቃትን ለማሳደግም በቴክኖሎጂ የታገዘ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል። የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የስድስት ወር የዕቅድ አፈፈፃፀም ግምገማ ተጠሪ ተቋማት፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮዎች እና ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት መድረክ በቅርቡ በአዳማ መካሄዱ ይታወሳል።
በክልሉ በስድስት ወራት ውስጥ ከ30 ሺህ በላይ ዜጎች የኮደርስ ስልጠና ወስደዋል
Jan 29, 2025 45
ቡታጅራ፤ ጥር 21/2017 ዓ/ም (ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት 30 ሺህ 955 ዜጎች በኮደርስ ስልጠና መሳተፋቸውን የክልሉ ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ፡፡ ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት እቅድ አፈፃፀምና በቀጣይ ወራት የትኩረት አቅጣጫ ላይ የተዘጋጀ የምክክር መድረክ በቡታጅራ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ ሰላሙ አማዶ በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት 30 ሺህ 955 ዜጎች በኮደርስ ስልጠና ተሳትፈዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ከ15 ሺህ በላይ የሚሆኑት ስርተፊኬት መውሰዳቸውን ገልጸው ቀሪዎቹ ደግሞ በስልጠና ሂደት ላይ ይገኛሉ ብለዋል። በመንግሥት ተቋማት የሚገኙ ሰልጣኞች ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ሌሎች ወጣቶችም ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ መመቻቸቱን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ በበጀት ዓመቱ 49 ሺህ 571 የሚሆኑ ዜጎች የኮደርስ ስልጠና እንዲወስዱ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በመርሐ ግብሩ ላይ የቢሮው ከፍተኛ አመራር አባላት፤ የዞንና የልዩ ወረዳ የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ናቸው፡፡
የመንግሥት አገልግሎትን የሚያዘምኑ ከ800 በላይ የዲጂታል ስርዓቶች ለምተዋል - ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)
Jan 27, 2025 123
አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፡- የመንግሥት አገልግሎትን በማዘመን ቀልጣፋና ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ ከ800 በላይ የዲጂታል ስርዓቶች ለምተው ወደ ሥራ መግባታቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ። ከለውጡ ማግስት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በ2012 ዓ.ም ጸድቆ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወሳል። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) እንደገለጹት፥ የስትራቴጂው አምስት ዓመታት ትግበራ ጉልህ ውጤቶች የተገኙበት ነው። መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ለዲጂታል ስርዓተ ምህዳር ግንባታ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ በማድረግ በርካታ ስራዎች ማከናወናቸውን ገልጸዋል። የዜጎች የዲጂታል እውቀትና ክህሎት መጎልበቱ፣ በርካታ መሰረተ ልማት መገንባቱ፣ የኔትወርክ ትስስር መሻሻሉ፣ የኢንተርኔት ተደራሽነትና የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓት ማደጉ ከስኬቶች መካከል ናቸው ብለዋል። ለአብነትም በቴሌ ብር የክፍያ ስርዓት ከ3 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ዝውውር መፈጸሙን ጠቅሰዋል። የስትራቴጂው አንዱ ዋነኛ ትኩረት የመንግሥት አገልግሎቶችን ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ፍትሐዊ ማድረግ እንደሆነም ሚኒስትሩ አንስተዋል። በተለይም እያንዳንዱ አገልግሎት ከኋላ ቀር፣ ለሙስና ከሚያጋልጥና ግልፅ ካልሆነ ሂደት እንዲላቀቅና ወደ ዲጂታል እንዲሸጋገር በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል። ባለፉት አምስት ዓመታት የትግበራ ጊዜም በርካታ አገልግሎቶች ወደ ኦንላይን ስርዓት መግባታቸውን ነው ያነሱት። የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርም የመንግሥት አገልግሎትን የሚያዘምኑ ግልፅና ፈጣን የአገልግሎት ስርዓትን የሚፈጥሩ ከ800 በላይ ስርዓቶችን አልምቶ ወደ ስራ ማስገባቱን ጠቅሰዋል። ስርዓቶቹ የተገልጋዮችን ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት የሚቆጥቡ የመሆናቸውን ያህል፥ የተናበቡ፣ ብክነትን የማይፈጥሩና ለአጠቃቀም ምቹ እንዲሆኑ በየጊዜው መፈተሽ ቀጣይ የትኩረት ማዕከል ነው ብለዋል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግሥት ሀሚድ፥ የዲጂታል ሽግግር ጉዞው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማበልጸግና የሳይበር ግንዛቤን በማሳደግ ረገድ አበረታች ውጤት ማምጣቱን አንስተዋል። ሆኖም በሰው ኃይል ዝግጅት ማነስ፣ በተበታተነ መልኩ መስራት እና የዲጂታል ስርዓትን ደህንነት ሳያረጋግጡ የመጠቀም ክፍተቶች መኖራቸውን ጠቅሰው መስተካከል አለባቸው ብለዋል። የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑ የሳይበር መከላከል ስራን ለማጠናከር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አንስተው፥ ሆኖም የራሱ ስጋቶች እንዳሉት ጠቁመዋል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የዲጂታል ዕድገት የሚያመጣቸውን የሳይበር ደህንነት ስጋት ለመከላከል 24 ሰዓት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፥ ተቋማትም በራሳቸው ዝግጁ መሆን አለባቸው ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ እርጎን ከ10 ቀናት በላይ ሳይበላሽ ማቆየት የሚያስችል እርሾ አመረተ
Jan 27, 2025 193
አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፦ የባዮ እና ኢመርንጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ወተትን በሰዓታት ውስጥ ማርጋትና እርጎን ከ10 ቀናት በላይ ሳይበላሽ ማቆየት የሚያስችል እርሾ ማምረቱን ይፋ አደረገ፡፡ ከፍተኛ የቁም እንስሳት ሀብት ባላት ኢትዮጵያ ወተትን በነፍስ ወከፍ የመጠቀም ምጣኔ በዓመት ከ19 ሊትር አይበልጥም። በዚህም መንግስት የወተት ኃብት ልማት ስትራቴጂ ነድፎ የሌማት ትሩፋትን ጨምሮ የወተት ምርታማነትንና የነፍስ ወከፍ ፍጆታን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን በትኩረት እየሰራ ነው። የወተት ልማቱን ማሳደግ፣ የወተት ምርት ላይ እሴቶችን መጨመር እና የምርት ጥራትና ደኅንነት ማስጠበቅ ላይ ትኩረት ተሰጥቷል። በዘርፉ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማስፋት የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ከተቋቋሙት ተቋማት መካከል የባዮ እና ኢመርንጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አንዱ ነው፡፡ የኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ተስፋማሪያም በርሔ(ዶ/ር) እንደሚገልጹት የወተት ምርት አያያዝና አጠባበቅ አንዱ የትኩረት መስክ ነው። በዚህም ኢንስቲትዩት ባደረገው ሳይንሳዊ ምርምር ባወጣው ስድስት አይነት የእርጎ እርሾዎች ወተትን በፍጥነት ማርጋትና ደህንነቱ ተጠብቆ እንዲቆይ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። ባክቴሪያዎች ወተትን እንዲረጋም፤ እንዲበላሽም መንስኤ እንደሆኑ ገልፀው፤ እርሾው ወተት በሰዓታት ውስጥ ረግቶ ግን ለቀናት ሳይበላሽ እንዲቆይ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ በፊት ወተት ለመርጋት እስከ አራት ቀን የሚወስደውን ጊዜ ከአራት እስከ ስድስት ሰዓት ማሳጠር መቻሉን ገልጸዋል። የእርጎ እርሾ እርጎ ሳይበላሽ ከ10 ቀናት በላይ ማቀየት የሚያስችል መሆኑንም ገልጸው፤ ይህን የዜጎችን ጤና ከመጠበቅ ባለፈም ብክነት ለመከላከል የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የምርምር ውጤቱ በግልና በኢንዱስትሪ ዕርጎ ለሚያመረቱ አምራቾች ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኩባንያዎች ከባዮ እና ኢመርንጂንግ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር ውል በመግባት ምርቱን አምርተው ለገበያ ማቅረብ እንደሚችሉ ገልጿል።
ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሰረት የጣሉ ተግባራት ተከናውነዋል- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Jan 27, 2025 93
አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሰረት የጣሉ ተግባራት ተከናውነዋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ። ዛሬ የኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እና ውጥኖችን የተመለከተ ኤግዚቢሽንና ዐውደ ጥናት አካሂደናል ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው አስፍረዋል። መንግሥት ከለውጡ ማግሥት 2012 ዓ.ም ጀምሮ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ሀገራችን የቴክኖሎጂ ዕድገት ዕድሎችን እንድትጠቀም የሚያስችሉ ተግባራትን አከናውኗል ብለዋል። የዲጂታል መሠረተ ልማት በመሥፋፋቱ የፋይናንስና የክፍያ ስርዓት በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ መሆኑን ተናግረዋል። የመንግሥት አገልግሎቶችን የማዘመንና ወደ ዲጂታል የማሸጋገር እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ መጨመሩንም ገልጸዋል። የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስራዎች የተቀናጁ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ የሃብት ብክነትን የማያስከትሉ፣ የዜጎቻችንን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡና ፈጣን ለውጥ የሚያመጡ እንዲሆኑ መንግሥት የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። የመጀመሪያውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ እያጠናቀቅን በመሆኑም በቀጣይ 5 ዓመታት ስራ ላይ የሚውል የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ዝግጅት እያጠናቀቅን እንገኛለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአካታች የዲጂታል መሠረተ ልማትና ኢኮኖሚ ግንባታ ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበች ነው -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
Jan 27, 2025 91
አዲስ አበባ፤ጥር 19/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከለውጡ ማግስት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን በመተግበር አካታች ኢኮኖሚ ለመገንባትና የመንግሥት አገልግሎትን ለማሻሻል ወሳኝ መሠረት ማስቀመጧን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞን የተመለከተ ኤግዚቢሽንና አውደ ጥናትን በሳይንስ ሙዚየም በይፋ አስጀምረዋል። ኢትዮጵያ ከለውጡ ማግስት የቴክኖሎጂ ዕድገት ዕድሎችን ለመጠቀም እና ፈተናዎቹን ለማለፍ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እየተገበረች እንደምትገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። መንግስት የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ መሰረተ ልማት ማስፋፋቱን የጠቀሱት አቶ ተመስገን፥ የህግ እና የአሰራር ማዕቀፎችን ስራ ላይ በማዋል የመንግሥት ተቋማት አገልግሎትን በዲጂታል የማዘመንና ለዜጎች ፈጣንና ውጤታማ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል። በስትራቴጂው የትግበራ ዓመታት የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎትና ክፍያ እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ ንግድ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን አንስተዋል። የግሉ ዘርፍ የዳታ ማዕከላትን በማስፋፋት እና አዳዲስ የዲጂታል አገልግሎቶችን በማቅረብ ረገድ ያለው ተነሳሽነትና አስተዋጾም በእጅጉ ጨምሯል ነው ያሉት። በዚህም ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ወሳኝ መሰረት የጣሉ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል። በሌላ በኩል በዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ከተለዩ ቁልፍ የዲጂታል መሠረተ ልማቶች ውስጥ ዋነኛው በ2014 ዓ.ም መተግበር የጀመረው ዲጂታል የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ነው ብለዋል፡፡ ባለፉት የትግበራ ዓመታትም በሀገሪቱ ከ1 ሺህ በላይ የምዝገባ ጣቢያዎችን በመክፈት ከ11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች በላይ መመዝገባቸውን ተናግረዋል። መንግሥት የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ካውንስል በማቋቋም የዲጂታል ሽግግሩ የተቀናጀ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ የሃብት ብክነትን የማያስከትል፣ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እና ፈጣን ለውጥ የሚያመጣ እንዲሆን እየሠራ ነው ብለዋል። ሽግግሩን የሚያፋጥኑ የዲጂታል መንግስት ስትራቴጂ እና የኤሌክትሮኒክ ንግድ ስትራቴጂዎች የተዘጋጁ ሲሆን በቅርቡ ፀድቀው ወደ ሥራ እንደሚገቡም ጠቁመዋል። ስትራቴጂዎቹ የአገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣የንግድ አሰራርን በማዘመን እና የበለጠ አሳታፊ እና ዲጂታል ማህበረሰብ በመፍጠር ረገድ የሚኖራቸዉ ሚና ከፍተኛ እንደሆነም ገልጸዋል። የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የመጨረሻው የስትራቴጂው ትግበራ ዓመት ላይ መሆኑን በማንሳት፥ በቀጣይ እስከ 2030 የሚተገበር የ5 ዓመታት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂን ለማውጣት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከአንድ ሺህ በላይ ስታርትአፖች ክህሎት መር ዓለም አቀፍ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል
Jan 26, 2025 82
አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2017(ኢዜአ)፦ ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ስታርትአፖች ክህሎትን መሰረት ያደረገ ጥራት ያለውና ዘላቂ ዓለም አቀፍ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቪሽን ብቁ የሰው ኃይል በማፍራት የስራ ዕድል የሚፍጥሩ ሀገር በቀል ኩባንያዎችን ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ(ዶ/ር) እንደገለጹት በመንግስት ወጣቶችና ታዳጊዎች ያላቸውን ተሰጥኦ እንዲያወጡ የተሰራው ስራ ውጤታማ ነው፡፡ ለዚህም ምቹ ምሕዳር መፍጠር የተቻለ መሆኑን ገልጸው፤ እስካሁን ባለው ሂደትም ተሰጥኦን በመለየት፣ በማልማት፣ በማሳደግና በማበልጸግ ወደ ምርትና አገልግሎት የመቀየር ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል። የሳይንስና ቴክኖሎጂ እና የምርምር ተቋማት ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል። በመንግስት በኩልም እንደ 5ጂ ያሉ አስፈላጊ የመሰረተ ልማትና በፖሊሲ የታገዘ የድጋፍ ማዕቀፍ ተዘጋጅተው ተግባራዊ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ በተዘረጉ የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማቶች ለመጠቀም ትኩረት እንደተሰጠው ገልጸው፤ ለአብነትም በኔትዎርክ ማስፋፋት ስራ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ ኢ-ኮሜርስ፣ ኢ-ፋይናስና መሰል ለኢኮኖሚና ለሰው ሃብት ልማት ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በዚህም ክህሎትን መሰረት ያደረገ ጥራት ያለው፣ ዘላቂና አስተማማኝ ዓለም አቀፍ የስራ ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል። ከስድት አመት በፊት 50 የነበሩት ስታርትአፖች በአሁ ወቅት ከአንድ ሺህ በላይ መድረሳቸውን ጠቅሰዋል። ከነዚህም መካከል ከ92 በላይ የሚሆኑት ተጨማሪ ሃብትና የስራ ዕድል መፍጠር የቻሉ መሆናቸውን አንስተዋል። በስታርትአፖች የተፈጠሩ የስራ ዕድሎች በዋነኛነት በፋይናስ ቴክኖሎጂ፣ በአግሪ ቴክ (በግብርና)፣ በአገልግሎት፣ በትራንስፖርት፣ በአይሲቲ፣ በኢንዱስትሩ፣ በቱሪዝምና በሌሎች መሰል ዘርፎች መሆኑን አንስተዋል፡፡ በዘርፎቹ መተግበሪያዎችን በማልማት የኢ-ኮሜርስ የንግድ መተግበሪያዎችን እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም በዕውቀት የሚመራ ሀገራዊ ኢኮኖሚ ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡ በግብርናው ዘርፍም የእንስሳት ጤናን ለመጠበቅ የሚያስችል ክትባት በባዮቴክኖሎጂ ምርምር ዘርፍ በማምረት ከውጭ የሚገባን ምርት የመተካት በጎ ጅምር በስታርትአፖች እየታየ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ከኮዲንግ ኢንሼቲቭ አንጻር የኮምፒውተር ቋንቋ በአግባቡ የሚረዳ፤ የተረዳውንም ወደ ጽሁፍ የሚቀይር መተግበሪያ በማበልጸግ ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂ ማልማት የሚችሉ ወጣቶችን የማፍራት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች በኮዲንግ ኢንሼቲቭ ስልጠና የላቀ አግልግሎት መስጠት የሚያስችል የዲጂታል ዕውቀት በተለያዩ ተቋማት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡ ወጣቶቹም እየተሰጠ ያለውን የኮዲንግ ስልጠና ዕድል በአግባቡ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ትክክለኛ የአየር ፀባይ ትንበያን ተደራሽ በማድረግ በየዘርፉ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ የሚሰራው ሥራ መጠናከር አለበት - አብረሃ አዱኛ(ዶ/ር)
Jan 25, 2025 85
አዳማ፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- ትክክለኛ የአየር ፀባይ ትንበያን ተደራሽ በማድረግ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ የሚሰራው ሥራ መጠናከር እንዳለበት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብረሃ አዱኛ(ዶ/ር) ገለፁ። በመጪው በልግ የሚኖረውን የአየር ፀባይ ሁኔታ ትንበያ እና የበጋ ወቅት የአየር ፀባይ ትንበያን የሚገመግም የባለድርሻ አካላት መድረክ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብረሃ አዱኛ(ዶ/ር) በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት እየሰጠ ያለው የአየር ሁኔታ ትንበያ በተጨባጭ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያመላከተ ነው። መድረኩ የበጋ ወቅት የአየር ፀባይ ሁኔታ ትንበያ የሚገመገምበትና የመጪው የበልግ ወቅት የአየር ፀባይ ትንበያን በአግባቡ በመጠቀም ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል። የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለው ተፅዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሆኑን ጠቁመው ኢኒስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ትክክለኛ የአየር ፀባይ ሁኔታ ትንበያ ተደራሽ ለማድረግ የሚሰራውን ስራ ማጠናከር አለበት ብለዋል። በተለይ የአየር ጸባይ ትንበያን ተደራሽ በማድረግ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሚከናወኑ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች መጠናከር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። የመጪው የበልግ ወቅት ትንበያ መረጃን ለተጠቃሚዎች በአግባቡ ተደራሽ ለማድረግ ኢንስቲትዩቱና ባለድርሻ አካላት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው፤ ኢኒስቲትዩቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የአየር ፀባይ ትንበያ አቅሙን እያሻሻለና ተአማኒነቱን እያጎለበተ መምጣቱን ተናግረዋል። የአየር ፀባይ ትንበያን ለተጠቃሚዎች በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም ከቅድመ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን እየደገፈ ይገኛል ብለዋል። በተያዘው የበጋ ወቅትም ደረቅና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ እንዲሁም የቀንና የሌሊት ቅዝቃዜ እንደሚኖር ኢኒስቲትዩቱ በትንበያው ማመላከቱንም አስታውሰዋል። የመጪው በልግ የአየር ሁኔታ ትንበያን አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩን ጨምሮ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራን ነው ሲሉም ገልጸዋል። ተጠቃሚዎችም የቅድመ ማስጠንቀቂያ የአየር ፀባይ ሁኔታ ትንበያን መረጃ በአግባቡ በመጠቀም ሊደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ ቀድሞ መከላከልና መቀነስ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ተግባራዊ መደረጉ ሕብረተሰቡ በዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ያለው እምነት እንዲጨምር አድርጓል
Jan 25, 2025 97
አዲስ አበባ፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ተግባራዊ መደረጉ ሕብረተሰቡ በዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓቱ ላይ የነበረው እምነት እንዲጨምር ማድረጉን የአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ አስታወቀ። “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” ስትራቴጂ በዋናነት የዲጂታል መሰረተ ልማት በመገንባትና በማስፋፋት የሀገሪቱን የምጣኔ ሀብት እድገት ማፋጠንን ዓላማ ያደረገ ነው። ስትራቴጂው ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ለአምስት አመታት የሚቆይ ሲሆን ዘንድሮ የመጀመሪያው ዙር ይጠናቀቃል። የአዲስ አበባ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን አማረ ለኢዜአ እንደገለጹት የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ህብረተሰቡ በዲጂታል ኢኮኖሚና ግብይት ላይ የነበረው ንቃተ ህሊና እንዲያድግ አድርጓል። በተለይም የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች፣ የነዳጅ ግብይት፣ የመብራት፣ የቤት ኪራይ፣ የውሃና ሌሎች ክፍያዎችን ከመፈፀም አንፃር ስትራቴጂው የማህበረሰቡን መጉላላት ማስቀረቱን ጠቅሰዋል። የአየር ትኬቶችን ጨምሮ ትልልቅ የትራንስፖርት አገልግሎቶች በዲጂታል ቴክኖሎጂ መሰጠቱ ህብረተሰቡ በቴክኖሎጂው ላይ እምነት እንዲያሳድር አድርጓል ነው ያሉት። ባለፉት አምስት አመታትም ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ከማድረግና ከመጠቀም አንፃር ከፍተኛ ለውጥ መታየቱን ጠቅሰዋል። በመዲናዋ በአሁኑ ወቅት ከ400 በላይ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በዲጂታል ኢኮኖሚ ስርዓት ውስጥ ገብተው ጥቅም ላይ መዋላቸውንም ነው አቶ ሰለሞን ያነሱት። ከዚህ ውስጥም የአሽከርካሪ ተሽከርካሪ፣ የመንጃ ፈቃድ፣ የመሬት እና የሲቪል ማህበረሰብ ምዝገባና የማህበረሰብ አገልግሎቶች ተጠቃሽ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
ምክር ቤቱ የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግርን ለማሳካት ለሚደረገው ጥረት በልዩ ትኩረት እገዛ ያደርጋል - ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ
Jan 24, 2025 86
አዲስ አበባ፤ ጥር 16/2017(ኢዜአ)፡- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደ ሀገር የዲጂታል ኢኮኖሚ ሽግግርን ለማሳካት ለሚደረገው ጥረት በልዩ ትኩረት እገዛ እንደሚያደርግ የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ ገለጹ። ምክትል አፈ ጉባዔዋ ይህን ያሉት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ ለምክር ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች በተዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ የማጠቃለያ መርሀ-ግብር ላይ ነው። በሀገር ደረጃ ለወጣው ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ዕቅድ ስኬት በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ የምታደርገውን ሽግግር ዕውን ለማድረግ ከተለመደው አሰራር እና አስተሳሰብ ወጣ ባለ መልኩ ሀገርን ከፍ ለማድረግ በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ3 እስከ 4 ሚሊዮን ለሚጠጉ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን አስታውሰው፤ መጪውን የዲጂታል ዘመን ታሳቢ በማድረግም ክህሎታቸውን በማሳደግ በተሰማሩበት ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተጠናከረ ድጋፍ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት። ምክር ቤቱ በሚያከናውናቸው የህግ ማውጣት፣ የህዝብ ውክልና፣ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን አፈፃፀም ጥንካሬና ክፍተቶችን በመለየት ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል። ዘርፉን በትውልድ ቅብብሎሾ አለም ከደረሰበት ደረጃ ለማድረስ ከመደበኛ ሥራ ባሻገር በትብብር እና በቅንጅት መስራት እንደሚገባ ማስገንዘባቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ከምክር ቤቱ የሚጠበቀውን ኃላፊነት በመወጣት ከዘረፉ የሚጠበቁ ውጤቶችን ለማስመዝገብ እንሰራለን ሲሉም ገልጸዋል።
የኢንስቲትዩቱ ስራዎች የኪነጥበብ ዘርፉ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ እንዲሰራ የሚያነሳሱ ናቸው-አርቲስቶች
Jan 24, 2025 341
አዲስ አበባ፤ጥር 16/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ጅኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ያከናወናቸው ስራዎች የኪነጥበብ ዘርፉ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ እንዲሰራ የሚያነሳሱ መሆናቸውን አርቲስቶች ገለጹ። በ2014 ዓ.ም በአዲስ መልክ የተቋቋመው ኢንስቲትዩቱ በእንጦጦ የምርምር ማዕከልና በዋና ማዕከሉ በስፔስ እና በጅኦስፓሻል ዘርፍ የሚያከናውናቸው ዐቢይ ተግባራትን በዛሬው ዕለት በኪነ ጥበብ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሙያዎች አስጎብኝቷል፡፡ በጉብኝቱ ከተሳተፉ የኪነጥበብ ባለሙያዎች መካከል ተዋናይ ሰለሞን ሀጎስ እና አርቲስት ማህተመ ኃይሌ፥ ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የደረሰችበትን ደረጃ መመልከታቸውን ተናግረዋል። ባደጉት ሀገራት መጻኢ የቴክኖሎጂ ልህቀትን በሚጠቁም መልኩ የሳይንስ ፊልምና ሌሎች የኪነጥበብ ሥራዎች እንደሚሰሩ በማስታወስ፥ በእኛ ሀገርም መለመድ አለበት ብለዋል። በጉብኝቱ የተመለከቱት ሥራ በቀጣይ የኢትዮጵያ የኪነጥበብ ዘርፍ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቅሰው፥ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚያበረክቱም ጠቁመዋል። የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቤተልሄም ንጉሴ (ኢ/ር) እንደተናገሩት፤ኢንስቲትዩቱ በስፔስ እና በጅኦስፓሻል ዘርፍ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አበረታች ሥራ እያከናወነ ይገኛል። በሳተላይት አማካኝነት መረጃ በመሰብሰብ ለተቋማት የማድረስ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ማበልጽግና ማስፋፋት ላይ እየሠራ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡ በሳተላይት አማካኝነት የሚገኙ መረጃዎችን ለጥናትና ምርምር፣ ለግብርና ስራ፣ ለሚቲዎሮሎጂ፣ ለውሃ፣ ለመሬት እና መሰል የመረጃ አገልግሎቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል። የጉብኝቱ ዓላማ የኢንስቲትዩቱን ተግባራት በኪነ ጥበቡ ባለሙያዎች አማካኝነት ለህዝብ በማድረስና እንዲሁም በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ ምሁራን ግንዛቤ እንዲያገኙ ለማስቻል ነው ብለዋል፡፡