ኢኮኖሚ
ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ውጤት ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚያደርጋት ነው- የቱሪዝም ሚኒስቴር
Feb 1, 2025 52
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ውጤት ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ የሚያደርጋት መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። የሀገሪቱን እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር እንዲያስችሉ ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰሩ ካሉ ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ ነው። የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከለውጡ ወዲህ መንግስት ለቱሪዝም ልማት በተሰጠው ተኩረት በርካታ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች ተገንብተዋል። በአዲስ አበባ የተጀመረው ገበታ ለሸገር ፕሮጀክትን ጨምሮ የገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶችን ለአብነት አንስተዋል። በተጨማሪም ነባር የቱሪስት መዳረሻዎችን ደረጃውን በጠበቀ መልኩ በፍጥነት በማደስ ለጎብኚዎች ክፍት የማድረግ ስራም በትኩረት መከናወኑን አስታውቀዋል። በቱሪዝም ልማት ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት ኢትዮጵያን ለአፍሪካ ሀገራትም ጭምር ምሳሌ የሚያደርጋት መሆኑን አመልክተዋል። ለዚህም የኢጋድ አባል ሀገራት የሚመሩበት የዘላቂ ቱሪዝም ማስተር ፕላን አዲሰ አበባ ላይ ይፋ መደረጉ ትልቅ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ዘርፉ የታለመለትን አገራዊ ስኬት የበለጠ እንዲያስመዘግብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሪፎርምና መሰል የማሻሻያ ስራዎችን ተግባራዊ እያደረገ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የቱሪዝም ፖሊሲን የመከለስ ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቅርቡም አዲሱ የቱሪዝም ፖሊሲ ይፋ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን ያጠናክራል - አቶ ጌታቸው ረዳ
Feb 1, 2025 58
መቀሌ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦ አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከርና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበት እንደሚያግዝ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ገለጹ። አዲሱን የግብርናና የገጠር ልማት ፖሊሲ በዘርፉ ለተሰማሩ ባለድርሻ አካላት የማስተዋወቅ መርሀ ግብር ዛሬ በመቀሌ ከተማ ተካሂዷል። በዚሁ ጊዜ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ፤ ፖሊሲው በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከርና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ያግዛል ብለዋል።   ግብርናን ማዘመን ምርታማነትን ለማጎልበት የሚያግዙ ስራዎችን ማከናወንና ሜካናይዜሽን ላይ ማተኮር መሆኑን ጠቅሰዋል። ፖሊሲው የክልሉን እርሻ ለማጎልበት የሚደረገውን ጥረት ስለሚያጠናክር ለተግባራዊነቱ ባለድርሻ አካላት የተለየ ትኩረት ሊሰጡበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። በግብርና ሚኒስቴር የፖሊሲ ምርምርና ጥናት መሪ ስራ አስፈፃሚ ተስፋዬ መንግስቴ(ዶ/ር) በበኩላቸው በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ለውጦችን ለማምጣት የግብርና ኮሜርሻላይዜሽንን ማጠናከር ይገባል ብለዋል። በግብርና ዘርፍ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑንም አክለዋል። በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የፖሊሲና የስርዓተ ምግብ ዳይሬክተር አቶ ረታ ዋጋሪ፤ ፖሊሲው ተግባራዊ በሚደረግበት ወቅት የባለድርሻ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።   ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ብርሀነ ሀይለ የተባሉ የግብርና ባለሙያ፤ በግብርናው ዘርፍ እየታዩ ያሉት ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ይበልጥ ለማጎልበት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማጎልበት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል። በግብርና ዘርፍ የምርምር ስራ ላይ የተሰማሩት አባዲ ግርማይ(ዶ/ር) ደግሞ፤ የግብርና ዘርፍ ለኢኮኖሚው እድገት ያለው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ የተለየ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል። ፖሊሲው ለሀገሪቱ ዘላቂ ልማት ወሳኝ መሆኑን በመግለፅ ለተግባራዊነቱም የሁሉም አካላት ቅንጅታዊ ስራ አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የማህበራዊ ልማት ዘርፍ ሽግግር ሀላፊ ሴክሬታሪያት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት ናቸው።
በግማሽ ዓመቱ ከ12 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል - የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን
Feb 1, 2025 51
ዲላ፤ ጥር 24/2017 (ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በግማሽ ዓመቱ ከ12 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን አስታወቀ። ባለስልጣኑ የግማሽ አመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በዲላ ከተማ አካሂዷል። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሪክተር አቶ አማኑኤል ብሩ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ በግማሽ ዓመት ከ12 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል። በክልሉ ከ134 ሺህ ቶን በላይ እሸት ቡና ተሰብስቦ የደረቅ ቡና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በምርት ዘመኑ ተሰብስቦ የተከማቸ ቡናን በቀጣይ ሶስት ወራት አሟጦ ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ህገወጥ የቡና ዝውውርን ከመቆጣጠር በተጓዳኝ አቅራቢዎች ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ እንዲያቀርቡ በየደረጃው ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን አንሰተዋል። በዞኑ በግማሽ አመት ከ10 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን ያነሱት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ቡናና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ ቼካ ናቸው። በምርት ዘመኑም ከ200 በላይ ቡና አምራቾች ከ17 ሺህ ቶን በላይ የታጠበ ቡና ማዘጋጀት መቻላቸውን ጠቅሰው ይህንንም በቀጣይ ወራት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው ብለዋል። ይህም በበጀት ዓመቱ ከ28 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሐረሪ ክልል የተከናወነው የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት የቱሪስት ፍሰት እንዲጨመር አስችሏል- አቶ ተወለዳ አብዶሽ
Feb 1, 2025 46
አዲስ አበባ ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ):- በሐረሪ ክልል የተከናወነው የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት የቱሪስት ፍሰት እንዲጨመር ማስቻሉን የክልሉ ባህል ቅርስ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ገለጹ። ኃላፊው በሰጡት መግለጫ ከለወጡ ወዲህ በክልሉ የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት ከጁገል ዓለም አቀፉ ቅርስ መልሶ ልማት ጀምሮ የጅብ ትርዒት ማሳያ ፓርክ ግንባታዎች በዋናነት መከናወናቸውን ገልጸዋል። በክልሉ የተከናወኑ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት እና እድሳት ኢንሼቲቮች የመዳረሻዎችን ህልውና ከማስጠበቅ ባለፈ የቱሪስት ፍሰቱን እንዲጨምር ያስቻሉ መሆናቸውን አመልክተዋል። የውጪና የሃገር ውስጥ ጎብኚዎች በክልሉ መበራከታቸውንን ለአብነት አንስተዋል። በተያዘው አመት ብቻ 4 ሺህ 991 የውጭ አገር ጎብኚዎች ወደ ክልሉ መምጣታቸውን የገለፁት አቶ ተወለዳ የቱሪስት ፍሰቱ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ37 በመቶ እድገት ማሳየቱን ጠቁመዋል። 92 ሺ 581 የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መጎብኘታቸውንም ተናግረዋል። በኮሪደር ልማት የተፈጠሩ ምቹ የእግረኛ መንገዶች እና የአረንጓዴ ልማቶች ለቱሪስት ፍሰቱ ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል ነው ያሉት። በክልሉ የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ይበልጥ በማጎልበት የቱሪስተ ፍሰት እና ቆይታን ለማሳደግ የቱሪዝም ዘርፉ የሚፈልገውን የመሠረተ ልማቶች እና የሆቴል ቱሪዝም የማጠናከር ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። በሌላ በኩል በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው የኢኮ ፓርክን በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል። ሐረር የምትታወቅባቸውን የአብሮነት እሴቶችን ጠብቆ ለማቆየት የተለያዩ ህዝባዊ በዓላትና ሁነቶችን ወንድማማችነትን ይበልጥ አጉልቶ በሚያሳይ መልኩ መከበራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል
Jan 31, 2025 71
ሀዋሳ ጥር 23/2017 (ኢዜአ ):- በሲዳማ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የክልሉ እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ገለፀ። የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ለወረዳና ቀበሌ ባለሙያዎች በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ፓኬጆች ላይ ያተኮረ ሥልጠና እየሰጠ ነው ። በዚሁ ጊዜ የቢሮው ኃላፊ አቶ ተክሌ ጆምባ እንደገለፁት፤ በሲዳማ ክልል የወተት፣ የሥጋ፣ የዶሮ እና የዓሣ ሀብትን ጨምሮ በሰባት ፓኬጆች የአካባቢ አቅሞችን በመለየት የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብሩ እየተከናወነ ይገኛል። ባለፉት ሁለት ዓመታት አመርቂ ውጤቶች የተመዘገቡባቸው ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው የመርሀ ግብሩ ግብ ስኬታማ እየሆነ እንደሚገኝ አስረድተዋል ። የመርሀ ግብሩ ተግባራት ከዓመት ወደ ዓመት በመጠንና በአፈፃፀም ከፍ እያሉ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ ተክሌ ባለፈው በጀት ዓመት በሁሉም ፓኬጆች የተመዘገበውን ውጤት ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል። ለአብነትም ባለፈው በጀት ዓመት የታቀደውን 8 ሚሊዮን ዶሮዎችን ማሰራጨት ሲሆን በዚህ ዓመት ደግሞ ከታቀደው 10 ሚሊዮን እስካሁን 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዶሮ ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል። ባለፈው በጀት ዓመት 153 ሺህ ከብቶችን ዝርያ ማሻሻል ችለናል ያሉት አቶ ተክሌ ዘንድሮ 200 ሺህ የዝርያ ማሻሻል ስራ ለማከናወን ታቅዶ 117 ሺህ ከብቶችን ዝርያ ማሻሻል እንደተቻለም ጠቅሰዋል። በንብ ቀፎ ስርጭት፣ አርሶ አደር ማሳዎች ውስጥ በሚዘጋጁ የዓሣ ኩሬዎች እንዲሁም በሌሎች ተግባራት ውጤታማ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል። ሆኖም እያደገ የሚመጣውን የህዝቡን ፍላጎት ማሟላት እንዲቻል ከዚህም በበለጠ ፍጥነትና ጥራት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል። በመሆኑም በባለሙያዎች ዘንድ የሚስተዋሉ የክህሎት ክፍተቶችን ለመሙላት ብሎም በመርሀ ግብሩ ፓኬጆች ላይ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር በማሰብ ሥልጠናው መዘጋጀቱን አስረድተዋል። የዳሌ ወረዳ እንስሳት ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሻላሞ ሹራሞ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በፓኬጆች ላይ መንደሮችን በመፍጠር ሰፋፊ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል። አርሶ አደሩ በአሁን ወቅት ከሌማት ትሩፋት ሥራዎች የሚያገኘው ጥቅም እያደገ በመምጣቱ በዚሁ ልክ የአመለካከት ለውጥ እያመጣ ይገኛል ብለዋል።   በአራት ፓኬጆች ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት የአለታ ወንዶ ወረዳ እንስሳት ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማርቆስ ማልካቶ በተለይ የወተት ሀብት ልማት ሥራው አርሶ አደሩን የላቀ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በወረዳው አርሶ አደሮችን በህብረት ሥራ ማህበር በማደራጀት ለይርጋለም የግብርና ምርት ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁም ለአዲስ አበባ ገበያ በማቅረብ ገቢያቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግም ተችሏል ብለዋል ። ለሶስት ቀናት በሚቆየው የሥልጠና መድረክም 900 የሚሆኑ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን የክልል፣ የዞንና የወረዳ የዘርፍ አመራሮች ተገኝተዋል።
በደሴ ከተማ  የኮሪደር ልማት በፍጥነት እየተከናወነ ነው  - የከተማው አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ ሽመልስ ጌታቸው  
Jan 31, 2025 57
ደሴ ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡-የደሴ ከተማ አስተዳደር እየተከናወነ ያለው የአንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ እየተፋጠነ እንደሚገኝ የከተማው አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ሽመልስ ጌታቸው ገለጹ፡፡ የከተማ አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት ከቧንቧ ውሃ እስከ ወሎ ባህል አምባ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ተመልክተዋል፡፡ ምክትል ከንቲባው በወቅቱ እንደገለጹት፤ ከተማውን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ፡፡ በዚህም ህብረተሰቡን በማሳተፍ ከቧንቧ ውሃ እስከ ወሎ ባህል አምባ እየተሰራ ያለው የአንድ ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ ጥራቱን ጠብቆ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።   ለልማት ስራው መፋጠን የአመራር አባላቱ ያልተቋረጠ ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ አመልክተው፤ የልማት ስራው እስከዚህ ዓመት መጨረሻ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል። ልማቱ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ እድል እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለኮሪደር ልማቱ የህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎና አጋዥነት ውጤት እንዲመዘገብ እያረገ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጠል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የደሴ ከተማ አስተዳደር ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ አበበ በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡን በማሳተፍ ሰፋፊ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡   በተለይ የኮሪደር ልማቱ በተያዘለት ጊዜ በጥራት እንዲጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በህብረተሰቡ ከፍተኛ ድጋፍ እየተፋጠነ መሆኑንም አረጋግጠዋል። የልማት ስራው በአመራር አባላትና ባለሙያዎች የተጠናከር ክትትል በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በደሴ ከተማ እየተከናወነ ላለው የኮሪዳር ልማት ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተመላክቷል።  
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ
Jan 31, 2025 64
ሚዛን አማን፤ ጥር/23/2017 (ኢዜአ)፡-የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ገቢዎች ቢሮ ባለፉት ስድስት ወራት ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ። የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሕይወት አሰግድ በሰጡት መግላጫ ፤ በበጀት ዓመቱ የክልሉን መንግስት የልማት ወጪ 60 በመቶውን በራስ የገቢ አቅም ለመሸፈን ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው። የግብር ሕጎችን በማስከበርና የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ባለፉት ስድስት ወራት ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታውቀዋል። የተሰበሰበው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ጠቁመዋል። የክልሉን የገቢ አሰባሰብ ሂደት ከቴክኖሎጂ ጋር ለማጣጣም ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ በ31 የታክስ ማዕከላት የሲስተም ዝርጋታ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል። በአጠቃላይ በክልሉ ውስጥ ካሉት 70 የታክስ ማዕከላት በ66ቱ ላይ ሲስተም በመዘርጋት እንዲሠሩ መደረጉን አክለዋል። በዚህም በግማሽ የበጀት ዓመቱ 15 ሺህ የሚጠጉ የደረጃ 'ሐ' ግብር ከፋዮች ግብራቸው በ" ሲግታክስ" አሰርተው በቴሌብር አማካኝነት መክፈላቸውን ጠቁመዋል። በሌላ በኩል በግማሽ የበጀት ዓመቱ 186 ግብር ከፋዮችን ኦዲት በማድረግ የተገኘ 79 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል። በተመሳሳይ በገቢ ተቋም ውስጥ ሆነው በሕገ ወጥ ድርጊት የተሰማሩ 36 ባለሙያዎች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ መወሰዱንም ጠቅሰዋል። ደረሠኝ ሳይቆርጡ ሲያገበያዩ የተገኙ 205 የንግድ ድርጅቶች ላይ የማስተካከያ እርምጃ መወሰዱን ጠቁመዋል። በክልሉ በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ የታቀደው 9 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተመልክቷል።  
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቡና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ይገኛሉ
Jan 31, 2025 76
ዲላ፤ ጥር 23/2017 (ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቡና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የክልሉ ቡናና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ገለጸ። የኩታ ገጠም የቡና ልማት የመስክ ልምድ ልውውጥ በከልሉ ጌዴኦ ዞን ወናጎ ወረዳ ተካሂዷል። የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ብሩ በወቅቱ እንዳመለከቱት፤ በክልሉ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ የኩታ ገጠም የቡና እድሳት እየተከናወነ ነው። በበጀት ዓመቱ ከ10 ሺህ ሄክታር በላይ ያረጀ ቡናን በማንሳት በተሻሻሉ ዝሪያዎች ለመተካት የነቀላና ጉንደላ ስራ በንቅናቄ እየተከናወነ ነው ብለዋል። በተለይ አርሶ አደሩን በኩታ ገጠም በማደራጀት ያረጀ ቡና የማንሳት ስራን በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ለማስፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ምልከታውም የዚሁ አካል መሆኑን ገልጸዋል።   በቡና እድሳት የሚስተዋለውን የአመለካከትና የግብዓት በተለይም የተፈጥሮ ማዳበሪያና የተሻሻሉ የቡና ዝሪያዎች አቅርቦት በማመቻቸት የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ርብርቡ መጠናከር እንዳለበት አመልክተዋል። በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የቡና እድሳት ስራዎች ውጤት ማምጣቱን የገለጹት የጌዴኦ ዞን ቡናና ቅመማ ቅመም ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ ቼካ ናቸው። ይህም ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ጠቁመው፤ በዞኑ በተያዘው ዓመት ከ4ሺህ 200 ሄክታር ላይ የሚገኝ ያረጀ ቡና በማንሳት በተሻሻሉ ዝሪያዎች ለመተካት ወደ ተግባር መግባታቸውን ተናግረዋል። ከዚህ ውስጥም 342 ሄክታር የቡና ማሳ በኩታ ገጠም እየለማ ነው ብለዋል። በወናጎ ወረዳ የቱማታ ጭራቻ ቀበሌ አርሶ አደር ብርሃኑ አልማሴ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፈው ዓመት እሳቸውን ጨምሮ 54 አርሶ አደሮች ከ27 ሄክታር መሬት ያረጀ ቡናን በማንሳት የተሻሸሉ ዝሪያዎችን በኩታ ገጠም ማልማታቸውን አንስተዋል።   የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመጠቀምና የአረም ቁጥጥር ጨምሮ የተለያዩ እንክብካቤዎችን በማከናወን ቡናው በአጭር ጊዜ ምርት እንዲሰጥ እየሰራን ነው ብለዋል። ዘንድሮም ተጨማሪ በ36 ሄክታር መሬት ላይ ያረጀ ቡና በማንሳት በተሻሻሉ ዝሪያዎች ለመተካት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። በልምድ ልውውጡ በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራር አባላትና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።
ከሻይ ምርት ተገቢውን ጥቅም ለማግኘት የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር ይገባል
Jan 31, 2025 87
መቱ ፤ጥር 23/2017 (ኢዜአ)፡- በቡና ምርት እየተገኘ ያለውን ጥቅም ከሻይ ምርትም ለማግኘት የተጀመረው ጥረት ሊጠናከር እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በአዲስ የሻይ ልማት ፓኬጅ ላይ የሁለት ቀናት የአሰልጣኞች ስልጠና በመቱ ከተማ እየሰጠ ይገኛል።   በስልጠና ማስጀመሪያው ላይ የባለስልጣኑ የቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ዘርፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ደፈረስ፤ በኢትዮጵያ በቡናው ምርት እያስገኘ ያለውን ጥቅም በሻይም ለመድገም በትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል። የሻይ ልማት በኢትዮጵያ ከተጀመረ ዘጠና ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ተጠቃሚ መሆን እንዳልተቻለ ጠቅሰዋል። በነዚህ ዓመታት ሁሉ በሻይ ለምቶ የሚገኘው መሬት 3 ሺህ 729 ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑን አንስተው ይህም በግል የልማት ድርጅቶች እንጂ በአርሶ አደሩ ዘንድ የተሰራው ስራ ዝቅተኛ መሆኑን ገልጸዋል። አሁን ላይ መንግስት ትልቅ ትኩረት ከሰጣቸው የልማት አቅጣጫዎች አንዱ እንደመሆኑ ባለስልጣኑም በሚቀጥሉት አምስት አመታት 100 ሺህ ሔክታር መሬት በሻይ እንዲለማ እስፈላጊ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል። ይህን ለማሳካትም በክልሎች ያለውን የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ የአቅም ግንባታ ስራዎች በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የሻይ ልማት ለስራ ዕድል ፈጠራ፣ ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል። በተጨማሪም የሻይ ልማት ለውጭ ምንዛሪ ግኝት ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ለልማቱ የተሰጠው ትኩረት ሊጠናከር ይገባል ብለዋል። የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድሳኒ አሚን በበኩላቸው በከልሉ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 30 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የሻይ ችግኝ ለማልማት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። ለዚህም በክልሉ በተለይ ለሻይ ልማቱ ምቹ ሁኔታ ባላቸው ዞኖች የችግኝ ዝግጅት ስራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። የሻይ ተክል ምርት መስጠት ሲጀምር በየሁለት ሳምንቱ ለፋብሪካ የሚቀርብ በመሆኑ ከሌላው የግብርና መስኮች የበለጠ የአርሶ አደሩን ብሎም የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑንም ተናግረዋል። በኢሉባቦር ዞን በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት 15 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ሻይ የማልማት ስራ በትልቅ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቻላቸው አዱኛ ናቸው።    
ድሬዳዋን ይበልጥ  ውብ የመኖሪያና የሥራ ተመራጭ  ከተማ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
Jan 31, 2025 66
ድሬደዋ ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- ድሬዳዋን ይበልጥ ውብና ፅዱ የመኖሪያ እና የሥራ ተመራጭ ከተማ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት ገለጸ። ጽህፈት ቤቱ "ከብክነት ወደ ሀብት ምንጭነት " በሚል የሚካሄደውን የደቻቱ አሸዋማ ስፍራ ፕሮጀክት መተግበሪያ ስምምነት ዛሬ ከድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ምክር ቤት ጋር ተፈራርሟል። ስምምነቱን የተፈራረሙት የድሬደዋ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም እና የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሀሚድ አብደላ ጋር ናቸው። ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም በወቅቱ እንደተናገሩት ፤ ድሬዳዋን ውብ ፣ፅዱና ማራኪ የመኖሪያና የስራ ተመራጭ ከተማ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው። በተለይ በበጀት ዓመቱ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ይህንኑ ለማሳካት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል ። ከዚህ ጎን ለጎን በከተማው የሚወጣው ቆሻሻ በተቀናጀ መንገድ በማፅዳትና ወደ ጥቅም በመለወጥ ከተማዋ ፅዱና ውብ የመኖሪያ ስፍራ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። ዛሬ ከወጣቶች ምክር ቤት ጋር የተፈረመው ስምምነት በደቻቱ አካባቢ የሚገኘውን ስፍራ ፅዱና ውብ የንግድና የመኖሪያ ስፍራ ለማድረግ መሆኑን ተናግረዋል ። በፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው 60 ወጣቶቹ ከዛሬ ጀምሮ ወደ ስራ በመግባት የአካባቢውን ብክለት በመከላከል ስፍራው የስፖርትና የመዝናኛ ተመራጭ ስፍራ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አመልክተዋል። በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት ወደ ገቢ ምንጭነት በመለወጥ ሀብቱ በዘላቂነት እንዲጠበቅ የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ ቀጣይ ምዕራፍ እንዳለው ጠቁመዋል። የድሬደዋ አስተዳደር ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ወጣት ሀሚድ አብደላ በበኩሉ፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ የአስተዳደሩ ወጣቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ውስጥ ያላቸው ተሳትፎና ተጠቃሚነት እየጎለበተ መምጣቱን ተናግረዋል። ዛሬ ወደ ተግባር የተሸጋገረው ፕሮጀክትም የዚሁ ውጤት ማሳያ መሆኑን ጠቅሷል። በቆሻሻል ለብከለት የተጋለጠው የደቻቱ አሸዋማ ስፍራ ውብና ፅዱ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚተጉ የተናገረው ደግሞ የምክርቤቱ ፀሐፊና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ወጣት አማረ ጥላሁን ነው።
በጋምቤላ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት በኢኮኖሚና  በሰላም ግንባታ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል
Jan 31, 2025 53
ጋምቤላ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት በሰላም ግንባታ፣ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ዘርፎች አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች ተናገሩ ። ቋሚ ኮሚቴዎቹ የክልሉን ያለፉት ስድስት ወራት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈፃፀም ገምግመዋል። የቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት በሰላም ግንባታ፣ በኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ የልማት ዘርፎች አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል። የምክር ቤቱ የግብርና፣ የቆላማ አካባቢና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ገላዊት ታንገሺን ፤ በክልሉ የሌማት ቱሩፋትን ጨምሮ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ስራዎች አፈፃፀም ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል።   በተለይም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ከተረጅነት ለመላቀቅ የተጀመረውን ‘‘ኢንሸቲቭ’’ ስኬታማ ለማድረግ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው ብለዋል። በክልሉ በትምህርት ለትውልድ መርሃ ግብር ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን በመገንባት የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን የተናገሩት የምክር ቤቱ የሰው ሃብት፣ ማህበራዊ ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጋትሉዋክ ጋች ናቸው።   እንዲሁም አዲሱን ስርዓተ ትምህርት ተግባራዊ በማድረግ በኩልም በክልሉ ብሎም እንደ ሀገር የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የታለመውን ግብ ከማሳካት አኳያ መልካም ጅምሮች መኖራቸውን ተናግረዋል። በጤና ተቋማት የተዘዋዋሪ መድኃኒት መግዣ በጀት ውስንንት ስለመኖሩ ጠቁመው ፤ በዚህ ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አቶ ጋትሉዋክ አሳስበዋል። ሌላው የምክር ቤቱ የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኡፓራ አጉዋ እንደገለጹት፤ በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት ዘላቂ ሰላምን በማረጋገጥ ረገድ እስከ ወረዳ ስኬታማ ተግባራት ተከናውነዋል።   ሆኖም ጥራቱን የጠበቀ የፍትህ አገልግሎት ለዜጎች ተደራሽ በማድረግ ረገድ ያሉት ውስነቶች በቀጣይ ማስተካከል እንደሚገባ አመላክተዋል። የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች በየዘርፉ በተለያዩ አዳራሾች ትናንት የጀመሩት የስድስት ወር የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅድ አፈፃፀም ግምገማ ዛሬ ተጠናቋል።  
የኢትዮጵያ መርከቦች ወደብ ላይ በተቀመጠላቸው ጊዜ መጠቀማቸው ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ አስቀርቷል - የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ
Jan 31, 2025 71
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ መርከቦች ወደብ ላይ በተቀመጠላቸው ጊዜ በአግባቡ መጠቀማቸውን ተከትሎ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ሙሉ በሙሉ ማስቀረቱን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አስታወቀ፡፡ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል። በዚሁ ወቅት የባሕር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ(ዶ/ር) የ2017 በጀት አመት እቅድ ከ2016 በጀት አመት እቅድ በላቀ መንገድ መታቀዱን ተናግረዋል። በተሰራው ስራ ባለፉት ስድስት ወራት ከእቅድ በላይ አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቁመዋል። በሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ የድርጅቱን እና የኪራይ መርከቦችን በመጠቀም ከሁለት ሚልዮን ቶን በላይ ጭነት በባህር መጓጓዙን ገልጸዋል። በዩኒሞዳል የትራንስፖርት ስርአት ከ654 ሺህ ቶን በላይ ገቢ እቃ እና ከ 174 ሺህ ቶን በላይ ወጪ እቃ ማስተናገድ መቻሉን ጠቁመዋል። በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከተሰጡ አገልግሎቶች እና ከሌሎች የገቢ ምንጮች ከ46 ቢልዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል። ባለፉት ስድስት ወራት ኤክስፖርት ላይ የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበ ሲሆን በኮርፖሬት ስራዎችም ለረጅም ጊዜ ሳይዘጉ የቆዩ ሂሳቦችን መዝጋት ተችሏል ነው ያሉት። ያልተሰበሰቡ ሂሳቦችን ለመሰብሰብም የተሰራው ስራ ውጤት ማስገኘቱን በመግለጫቸው አስታውቀዋል። የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ግዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቅሰው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩንም አስረድተዋል። በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት የኢትዮጵያ መርከቦች ወደብ ላይ በተቀመጠላቸው ጊዜ በአግባቡ በመጠቀማቸው ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት መቻሉን ጠቁመዋል። የኮንቴነሮችን የወደብ ቆይታ ለመቀነስ የተከናወነው ስራ አበረታች ውጤት የተመዘገበበት መሆኑንም አብራርተዋል። በዚህም ካለፉት አመታት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን አና በቀጣይም ቀልጣፋ ስራ እንደሚሰራ አመላክተዋል።
በክልሉ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ66 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች በተለያዩ መስኮች የስራ እድል ተፈጥሯል
Jan 31, 2025 65
መቀሌ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- በክልሉ በበጀት ዓመቱ ስድስት ለ66 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች በተለያዩ መስኮች የስራ እድል መፈጠሩን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የወጣቶች ቢሮ አስታወቀ።   የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በመስኖ ልማት ዘርፍ እንዲሰማሩ ባመቻቸላቸው የስራ ዕድል ውጤታማነታቸውን በማረጋገጥ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው ማደጉን በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የእንደርታ ወረዳ ወጣቶች ገልጸዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የወጣቶች ቢሮ በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ ለ66 ሺህ 784 ወጣቶች በተለያዩ መስኮች የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ገልጿል።   ውጤታማ መሆን ከጀመሩ ወጣቶች መካከል በእንደርታ ወረዳ ''የማህበረ ገነት'' ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ፍፁምብርሃን ሰገድ አንዱ ነው። በጊዜያዊ አስተዳደሩ በተመቻቸለት የስራ እድል በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ቲማቲም፣ ቀይ ሽንኩርትና ቃሪያ በማልማት በዓመት ሶስት ጊዜ ምርት እየሰበሰበ መሆኑን ተናግሯል።   በወረዳው የገረብ ግባ ገጠር ቀበሌ ነዋሪው ወጣት ፀጋይ ግደይ በበኩሉ፣ ከቤተሰቡ የተሰጠውና ተጨማሪ አንድ ሄክታር መሬት በመከራየት አትክልትና ፍራፍሬ እያለማ የራሱ እና የቤተሰቡን ህይወት እየለወጠ እንደሚገኝ ገልጿል። እያለማው ካለው ምርትም ገቢ እያገኘ መሆኑንና ዛሬ ላይ በስሩ ስድስት ወጣቶችን ቀጥሮ እያሰራ መሆኑን አመልክቷል። ህገ-ወጥ ስደትን ከመምረጥ እዚሁ እየተመካከሩ መስራትና መለወጥ እንደሚመረጥ ወጣት ፀጋይ ተናግሯል።   የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የገለፀችው ደግሞ በእንደርታ ወረዳ የማህበረ ገነት ገጠር ቀበሌ የመስኖ ልማት ባለሙያ ወጣት ለምለም ገብረጨርቆስ ናት። አሁንም ለወጣቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንቅስቃሴ ከተደረገ ወጣቱ የመስራትና የመለወጥ ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው ብላለች። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለወጣቶች በሰጠው ትኩረት በእንደርታ ወረዳ ከ3 ሺህ 600 በላይ ወጣቶች በግብርና ልማት ዘርፍ ብቻ እየሰሩ እንዲለወጡ እየተደረገ መሆኑን የወረዳው መስኖ ልማት አስተባባሪ አቶ ዓምደ ገብረ ስላሴ አስታውቀዋል።   በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ 66 ሺህ 784 ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ወጣቶች ቢሮ የስራ እድል ፈጠራ ዳይሬክተር አቶ ዓብድል ዓዚዝ ዓብዱ ልቃድር ገልፀዋል። እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የስራ ዕድሉ ከተፈጠረላቸው ወጣቶች ከ32 ሺህ የሚልቁት ሴቶች ናቸው።
አገር አቀፍ ኤግዚቢሽን ባዛርና ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው
Jan 31, 2025 69
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ ከ350 በላይ ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት የሚሳተፉበት አገር አቀፍ ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቁ። የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽንና የአዲስ አበባ ህብረት ስራ ኮሚሽን በጋራ ያዘጋጁትን ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል። መርኃ ግብሩ ከጥር 28 እስከ የካቲት 3 ቀን 2017 "የህብረት ስራ ማህበራት ሚና ለኢትዮጵያ ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል። በመርኃ ግብሩ ከ50 ሚልዮን ብር በላይ ግብይት ይከናወንበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የተገለጸ ሲሆን አምራችና ሸማቾችን በማገናኘት የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ያስችላል ተብሏል። የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ በኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየሙ በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ሸማች ማህበራት ይሳተፋሉ። በኢግዚቢሽንና ባዛሩ ከ350 በላይ የግብርናና ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት እንዲሁም ከመቶ በላይ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይሳተፋሉ ብለዋል። ኢግዚቢሽኑ የህብረት ስራ ማህበራት የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት መሆኑንም ጠቅሰዋል። መርኃ ግብሩ የተሻለ ተሞክሮ ያላቸውን የህብረት ስራ ማህበራት አሰራር በመቀመርና ልምድ በመቅሰም የህብረት ስራ ማህበራትን እድገት ወደ ተሻለ ከፍታ ለማድረስና የሀገሪቱን የብልፅግን ጉዞ ለማረጋገጥ የሚያስችል ስራ የሚከናወንበት ነው ብለዋል። በመድረኩ አጠቃላይ የፋይናንስ ተቋማት እንደሚገኙ ገልፀው፤ ግብይቱ በዲጂታል አማራጭ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተጫነ አዱኛ በበኩላቸው በአዲስ አበባ ያሉ ከ120 በላይ ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በመድረኩ እንደሚሳተፉ አስታውቀዋል። እንዲሁም ከ110 በላይ የተለያዩ የምርት አይነቶች በኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየሙ ለግብይት እንደሚቀርቡ ገልጸዋል። ከስልሳ ሺህ በላይ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ በሚጠበቀው ኤግዚቢሽን፣ባዛርና ሲምፖዚየም ከሁሉም ክልሎች የግብርና ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣የሌማት ትሩፋት ውጤቶች እንደሚቀርቡ ተገልጿል። በኢግዚቢሽንና ባዛሩ ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶች እንዲቀርቡ ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል። ዘንድሮ የሚካሄደው ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ11ኛ በአዲስ አበባ ደረጃ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ መዘጋጀቱ በመግለጫው ተመላክቷል።  
ለሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል
Jan 31, 2025 59
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን የግድቡ ግንባታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ገለፀ። በግማሽ ዓመቱ 454 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍቅርተ ታምር ከኢዜአ እንዳሉት፣ ግድቡ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ደርሷል። ከግድብ ግንባታ ጀምሮ ሁሉም ዜጋ በዕውቀቱ፣ በጉልበቱና በገንዘቡ ድጋፍ በማድረግ ግድቡ ትውልዱ የመተባበር፣ የአንድነትና የመቻል ተምሳሌት እንደሆነ አረጋግጧል ብለዋል። ህብረተሰቡ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሁለንተናዊ ድጋፉን እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰው፤ ባለፉት ስድስት ወራት 454 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል ብለዋል። ፅህፈት ቤቱ ድጋፉ ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ እንዲቀጥል ከተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ አማራጮችን የድጋፍ ማሰባሰብ ስራ እንደቀጠለ ጠቁመዋል። በአባይ ተፋሰስ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች የጉልበት ድጋፍ እንዲሁም የምሁራን ተሳትፎ የዕውቀት ድጋፍ ማሳያ እንደሆኑ ጠቅሰዋል። ለጋራ ጥቅምና ዓላማ በህብረት መቆም ያለውን ውጤቱ ያስተማር ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸው፤ ህብረተሰቡ የነበረውን የነቃ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በሕገ ወጥ መንገድ ሊሸጥ የነበረ 1 ሺህ 400 ሊትር በላይ ነዳጅ ተያዘ
Jan 31, 2025 82
መተማ ፤ ጥር 23/2017 (ኢዜአ):- በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ በሕገ- ወጥ መንገድ ሊሸጥ የነበረ ከ1 ሺህ 400 ሊትር በላይ የቤንዚን ነዳጅ መያዙን የከተማ አስተዳደሩ ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ሙልዬ አየልኝ እንደገለጹት፤ ቤንዚኑ በህብረተሰቡ ጥቆማ ከማደያ በድብቅ ተቀድቶ ሊሰራጭ ሲል ተደርሶበት ትናንት ማምሻውን ነው የተያዘው።   ነዳጅን ጨምሮ የንግድ ግብይትን ፍትሃዊነት ለመከታተል ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ እየተሰራ ነው ብለዋል። የሕገ- ወጥ የነዳጅ ዝውውርን ለማስቆም ግብረ ሃይሉ ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀው፤ ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን እንዲቀጥል ጠይቀዋል። የገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽህፈት ቤት ተወካይ ኢንስፔክተር ሀይሌ ብርሃኑ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ሕገ- ወጥ ተግባራትን ለማስቀረት ከህብረተሰቡና ከተቋማት ጋር በጋራ እየተሰራ ነው። በሕገ-ወጥ መንገድ የነዳጅ ንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተሳተፉ ግለሰቦች ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል። ነዳጅና የሸቀጥ ምርቶች ለሸማቹ ህብረተሰብ በትክክል እንዲደርስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በስድስት ወራት ውስጥ ከ46 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ አገኘ
Jan 31, 2025 72
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ|)፦ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በግማሽ ዓመቱ ከተለያዩ ምንጮች 46 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገለፀ። የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ(ዶ/ር) የ2017 የስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ላይ በሰጡት መግለጫ ተቋሙ በስድስት ወራት ውስጥ በሺፒንግ አገልግሎት ከሁለት ሚሊዮን ቶን በላይ ጭነት በባህር ማጓጓዙን ገልጸዋል። በዩኒሞዳል የትራንስፖርት ስርዓት ከ654 ሺህ ቶን በላይ የገቢና ከ174 ሺህ ቶን በላይ የወጪ ዕቃዎች ማስተናገዱን ጠቁመዋል። በዚህም በስድስት ወራት ውስጥ ከሌሎች የገቢ ምንጮች 46 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል።   ባለፉት ስድስት ወራት ኤክስፖርት ላይ የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቁመዋል። በኮርፖሬት ስራዎችም ለረጅም ጊዜ ሳይዘጉ የቆዩ ሂሳቦችን መዝጋት መቻሉን ገልጸው፤ ያልተሰበሰቡ ሂሳቦችን ለመሰብሰብም የተሰራው ስራ ውጤት ማስገኘቱን በመግለጫቸው አስታውቀዋል። የተጀመሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ግዜ እየተጠናቀቁ ለአገልግሎት መብቃታቸውን ጠቅሰው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ለዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩንም አስረድተዋል።
በክልሉ በስድስት ወራት ውስጥ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
Jan 31, 2025 79
ጋምቤላ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ በጋምቤላ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከአንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ። ክልሉ የገቢ አቅም አሟጦ በመጠቀም ወጪዎችን በራስ አቅም ለመሸፈን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ቢሮው ገልጿል። የቢሮው ኃላፊ አቶ ቸንኮት ዴቪድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በተያዘው በጀት ዓመት ከ2 ቢሊዮን 963 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል። በዚህም ባለፉት ስድስት ወራት ከአንድ ቢሊዮን 486 ሚሊዮን ብር በላይ በመሰብሰብ የዕቅዱን 91 ነጥብ 66 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል። ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም ከ437 ሚሊዮን ብር በላይ ብልጫ ተናግረዋል። የክልሉ ገቢ አቅም አሟጦ በመሰብሰብ ወጪዎችን በራስ የመሸፈን አቅምን በማሳደግ የማህበረሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ፍላጎቶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። የታክስ አስተዳደር ስርዓቱን በማዘመን ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ በቀላሉ ግብር የሚከፍልበትን አሰራር በወረዳዎች የማስፋት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል። በቀጣይ ግማሽ በጀት ዓመት ለግብር ከፋዮች አዲሱን ልዩ መለያ /Qr Code/ ደረሰኝ ተግባራዊ በማድረግ ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል። ግብር ለህዝቡ የሚበጁ መሰረተ ልማቶችን ለማከናወን ያለውን ሁለንተናዊ ፋይዳ ጠቅሰው፤ ማህበረሰቡ ግብሩን በወቅቱ በመክፈል ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የወልዲያ ከተማ የመጀመሪያ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የፊታችን የካቲት ወር መጨረሻ ይጠናቀቃል
Jan 31, 2025 52
ወልዲያ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- በሰሜን ወሎ ዞን የወልዲያ ከተማ የመጀመሪያ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት የፊታችን የካቲት ወር መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ ከተማ አስተዳደሩ ገለፀ። የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ 15 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት እንደሚከናወን ገልጿል። የከተማዋ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዱባለ አብራሬ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኮሪደር ልማቱ የወልዲያ ከተማን ይበልጥ ውብ፣ ፅዱ እና ለነዋሪዎቿ ምቹ የሚያደርግና የስራ እድል የፈጠረ ፕሮጀክት ነው። ባለፈው ሕዳር ወር የተጀመረው የመጀመሪያ ምዕራፍ የአንድ ኪሎ ሜትር ኮሪደር ልማት 35 በመቶው መድረሱን ገልፀው፤ የፊታችን የካቲት ወር መጨረሻ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል። የመጀመሪያው ምዕረፍ ኮሪደር ልማት ለ125 ሰዎች የስራ ድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ ልማቱ በሕብረተሰቡ ተሳትፎ እንደቀጠለ ገልጸዋል። የመጀመሪያው ምዕራፍ ሲጠናቀቅ 15 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሁለተኛው ምዕራፍ ኮሪደር ልማት እንደሚቀጥል ገልጸዋል። ከጀነቶ በር እስከ ሸህ አልአሙዲ አደባባይ፤ ሸህ አልአሙዲ አደባባይ እስከ ስታዲየም፤ ከስታዲየም እስከ እቴጌ መናፈሻ እና ከፒያሳ እስከ ጉቦ በር የሚሸፍን መሆኑን አስታውቀዋል። ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት አለማየሁ ኃይሉና አዲሱ ንጉስ በኮሪደር ልማቱ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ኢኮኖሚና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዳሳደጉ ገልጸዋል። የአካባቢው ሰላም በመሻሻሉ የኮሪደር ልማት እየተፋጠነ መሆኑን ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በከተማዋ ዕድገት የሚያሳድግና የትራንስፖርት መጨናነቅን የሚቀርፍ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም