ፖለቲካ
የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬ ውሎው በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን አሳልፏል
Feb 1, 2025 48
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦የብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬ ውሎው በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን ማሳለፉን የፓርቲው የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ። የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ 2 ሺህ 100 ተሳታፊዎች በታደሙበት በደማቅ የመክፈቻ ስነ ስርዓት በትላንትናው ዕለት በይፋ ተጀምሯል። በጉባኤው 1 ሺህ 700 የድምፅ ተሳታፊዎች እንዲሁም የ15 ሀገራት ፓርቲዎች አመራርና ተወካዮችን ጨምሮ 400 የሀገር ውስጥና የውጭ እንግዶች በተጋባዥነት መገኘታቸውም የሚታወቅ ነው። የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ጉባኤውን አስመልክቶ ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ ጉባኤው ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ተወካዮችን ባሳተፈና በዴሞክራሲያዊነት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል። በዛሬው ዕለትም ጉባኤው መድረኩን የሚመሩ የፕሬዚዲየም አባላትን በመሰየም በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ በስፋት መወያየቱንና አጀንዳዎችን መርምሮ ማጽደቁንም ተናግረዋል። በዚህም የጉባኤው አዘጋጅ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት እና የስብሰባ ስነ-ስርዓት ደንብ ላይ በስፋት በመወያየት በሙሉ ድምፅ አጽድቋል ብለዋል። በመቀጠልም የማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም የኢንስፔክሽንና ስነምግባር ኮሚቴ ሪፖርቶች ለጉባኤው ቀርበው ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ መጽደቃቸውንም ገልጸዋል። በተመሳሳይ ጉባኤው በፓርቲው የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ላይ ሰፊ ውይይት በማድረግ በሙሉ ድምፅ አጽድቋል ነው ያሉት። ከአንደኛ ጉባኤ ማግስት በፓርቲው በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶች፣ ያጋጠሙ ፈተናዎች እና ፈተናዎችን ለማለፍ የተሔደበትን ርቀት በስፋት መገምገሙንም አንስተዋል። በዚህም የብልፅግና እሳቤ እስከ ታችኛው ህብረተሰብ ክፍል መድረሱ እና እሳቤው ባህል እየሆነ መምጣቱ የተረጋገጠበት ጉባኤ መሆኑን ገልጸዋል። ጉባኤው በነገው ዕለትም ቀጥሎ የሚካሄድ ሲሆን የፓርቲ ፕሬዝዳንትና ምክትል ፕሬዝዳንቶችን ጨምሮ የአመራር ምርጫ ይደረጋል ብለዋል። ለዚህም በዛሬው ዕለት አስመራጭ ኮሚቴ በመሰየም የዕለቱ ስብሰባ አሳታፊ እና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መጠናቀቁን ተናግረዋል። ጉባኤው ለመጪዎቹ ዓመታት የሚያገለግሉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሆነም ጠቁመዋል።
የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ዛፈር ሲራካያ ምን አሉ
Feb 1, 2025 39
  ኢትዮጵያ ከዓለማችን ጥንታዊ ስልጣኔዎች አንዷ ናት። ኢትዮጵያ በአፍሪካ የታሪክ ገጾች ውስጥ ጉልህ ታሪክ የጻፈች እንዲሁም በባህል፣ በታሪክ፣ በብዝሃነት፣ በእምነት፣ በቋንቋና ቅርስ የበለጸገችና በፈተናዎች ሳትበገር ዘመናትን የተሻገረች ሀገር ናት። ተርኪዬና ኢትዮጵያ የነጻነትና ሉዓላዊነት የአይበገሬነት መንፈስ የሚጋሩ ሀገራት ናቸው። ኢትዮጵያ እና ተርኪዬ በታሪክ ጥብቅ ቁርኝነት አላቸው። ተርኪዬ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር አጠናክራ ትቀጥላለች። ኢትዮጵያ እና ተርኪዬ በዘመናት መካከል የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸው እና ትብብራቸው እያደገ መምጣቱንና በርካታ ስኬቶች እያስመዘገበ ይገኛል። ተርኪዬ ለቀጣናው ሰላምና ልማት መረጋገጥ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በብልፅግና ፓርቲ ጉባዔ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ያነሷቸው ሃሳቦች ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ቀጣናውና የአፍሪካን ብልፅግናን ዕውን ማድረግ የሚያስችሉ ናቸው።
የካዛኪስታን የታችኛው ምክር ቤት እና የገዢው አማናት ፓርቲ አባል ሳማት ኑርታዛ ምን አሉ
Feb 1, 2025 49
  ኢትዮጵያ ለካዛኪስታን ታማኝ እና እውነተኛ አጋር ናት። ከኢትዮጵያ ጋር የሁለትዮሽ፣ የባለብዝሃ ወገን እና ሁሉን አቀፍ ትብብሯን ለማጠናከር ትሻለች። ኢትዮጵያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ለቀጣናው እና ዓለም አቀፍ ደህንነት ቁልፍ አበርክቶ አድርጋለች። የብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ከፍቷል። ብልጽግና ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ረገድ ስኬታማ ተግባር አከናውኗል። አማናት ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለውን ግንኙነት እና ካዛኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጎልበት ይሰራል። አማናት ለዓለም ሰላም እና ብልጽግና ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በትብብር መስራት ይሻል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጪነት ብልጽግና ፓርቲ የለውጥ እና የሽግግር ተምሳሌት መሆን ችሏል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና ባለ ራዕይ መሪነት፤ ውጤታማ አስተዳደር ሀገርን ከቀውስ በማውጣት ለዘላቂ ልማት መሰረት መጣል እንደሚቻል በግልጽ ያመላከተ ነው።
የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ለብልጽግና ፓርቲ 2ኛ ጉባዔ የመልካም ምኞት መልዕክት ላከ
Feb 1, 2025 62
አዲስ አበባ፣ ጥር 24፣ 2017(ኢዜአ)፦የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ የድጋፍና የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፏል፡፡ ኢትዮጵያ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት እያስመዘገበችው ላለው ሁለንተናዊ እድገት የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ (CPC) ያለውን አድናቆት ገልጿል። ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጦ ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያ ተስማሚ የሆነ የእድገትና የዘመናዊነት መንገድ እንድትከተል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ ለአብነትም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ የዜጎችን ኑሮ በማሻሻል፣ በአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃን በማሳደግ፣ የሀገራዊ ምክክር ቅድመ-ዝግጅት በማገባደድና ማህበራዊ አንድነትን በማጎልበት ረገድ የተመዘገቡ ውጤቶች ጉልህ መሀኖቸውን ጠቅሷል። እነዚህ ስኬቶች ኢትዮጵያን “የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት” እንድትሆን እያስቻሉ ነው ሲልም እውቅና ሰጥቷል፡፡ በቀጣይ ዓመታት ብልጽግና ፓርቲ ሀገሪቱን ወደ “አዲስና የላቀ ስኬት” መምራቱን እንደሚቀጥል ያለውን እምነት ገልጿል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል ላለው ጥልቅ ትብብር አጽንኦት በመስጠትም የሁለቱ ፓርቲዎች መሪዎች ከዚህ ቀደም የደረሱባቸውን ስምምነቶች ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡ በቀጣይ የቻይናን እና የኢትዮጵያን ትብብር በሁሉም ዘርፎች በማስፋት በማንኛውም ሁኔታ የማይናወጥ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ሆኖ የበለጠ እንዲጠናከር ጥሪ አቅርቧል። ሁለተኛው የብልፅግና ፓርቲ ጉባኤ የኢትዮጵያን ቀጣይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ የሚቀርፅበት ወሳኝ ሁነት እንደሆነ እና ለሀገራዊ ልማት ወሳኝ የሆኑ ቀጣይ ግቦችን እንደሚቀመጡ እምነት እንዳለው በመጥቀስ ለጉባኤው ስኬት መልካሙን ሁሉ ተመኝቷል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ሰላምና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል -የጉባዔው ተሳታፊዎች
Feb 1, 2025 60
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦ ብልጽግና ፓርቲ በሁለተኛ መደበኛ ጉባኤው የኢትዮጵያን ሰላምና ልማት የሚያረጋግጡና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችሉ ውሳኔዎች እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል ሲሉ የጉባዔው ተሳታፊዎች ገለጹ። ብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን "ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ሀሳብ በአድዋ ድል መታሰቢያ ከትናንት ጀምሮ እያካሄደ ይገኛል፡፡ ብልጽግና ፓርቲ በመጀመሪያው ጉባኤ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን በፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ መክፈቻ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ተሳታፊዎች ተናግረዋል። የጉባኤው ተሳታፊ የሆኑት መሰረት መስቀሌ በሰጡት አስተያየት ብልጽግና ፓርቲ በመጀመሪያ ጉባኤው ለህዝብ የገባውን ቃል ወደ ተግባር ቀይሮ ማሳየቱን ተናግረዋል። ፓርቲው የህዝቦችን ህብረ ብሄራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ እና የኢትዮጵያን ተደማጭነት ያጎለበቱ በርካታ የዲፕሎማሲ ስራዎችን በማከናወን ውጤት ማስመዝገቡን አንስተዋል። በልማት ስራዎች በተለይም በግብርናው ዘርፍ በተከናው አስደማሚ ተግባራት በሀገሪቱ ተከታታይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል። በትምህርት ጥራት ማስጠበቅና በጤና አገልግሎት አሰጣጥ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ተግባራት መከናወናቸውን ለአብነት አንስተዋል። ሌላው የጉባዔው ተሳታፊ አቶ ንጉሴ ገመዳ በበኩላቸው ከፓርቲው የመጀመሪያ ጉባኤ በኋላ የአድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ በርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። በተለይም በኮሪደር ልማት በአዲስ አበባ ከተማና በክልል ከተሞች እየተከናወነ ያለው ስራ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ ገጽታ ከፍ ያደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተግባሩ ከተሞችን ለኑሮና ለስራ ምቹ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ተሳታፊዎቹ በፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ በኢትዮጵያ የተጀመሩ የልማት ስራዎች በፍጥነት ተጠናቀው ወደ አገልግሎት እንዲገቡ የሚያስችሉ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለው እንደሚጠብቁም ገልጸዋል። ብልጽግና ፓርቲው በሀገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የሰላምና ልማት ግንባታ ስራዎች የበለጠ ተጠናክረው የሚቀጥሉበትን ውሳኔ እንደሚያሳልፍም እንዲሁ። ከጎረቤት ብሎም ከአለም ሀገራት ጋር ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የበለጠ የሚጠናከርበትና በኢኮኖሚ የበለጸገች አገር መገንባት የሚያስችሉ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ብለው እንደሚጠብቁም አንስተዋል። ትናንት የተጀመረው የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ እስከ ነገ እንደሚቀጥል መገለጹ ይታወቃል።
የሰላም መሰረት፣ የብልፅግና ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማውረስ ተግተን እንሰራለን- የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
Feb 1, 2025 58
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦ የሰላም መሰረት፣ የብልፅግና ተምሳሌት የሆነች ያበበች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማውረስ ተግተን እንሰራለን ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተናገሩ። ሀገር ለማበልጸግ በዘመቻ የተጀመሩ ንቅናቄዎች ባህል ሆነው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል። የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባዔ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ገቢራዊ የተደረጉ አዳዲስ እሳቤዎችና ኢኒሸቲቮች ከዘመቻ ያለፈ ባህል የመፍጠር ልምምድና ክንውን ይፈልጋሉ ብለዋል። ለአብነትም የጽዱ ኢትዮጵያን ንቅናቄ፣ ምርታማነት የመጨመር እና ፕሮጀክቶችን በፍጥነት የመጨረስ አዳዲስ ልምምዶች በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ባህል፣ ትዕምርትና እሴት ሆነው መከወን እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ባህል ማድረግ አለብን ካሏቸው ጉዳዮች መካከልም ማወቅ፣ ማላቅ፣ መፍጠር፣ መፍጠን፣ ማስተሳሰር ጽንሰ ሃሳቦችን አብራርተዋል።   ብልፅግና ጊዜ የለኝም በሚል ስሜት የሚሰራ፣ በውጤት የሚያምን እንዲሁም ጀምሮ መጨርስን፣ ተናግሮ መፈጸምን ባህል አደርጎ እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል። የፓርቲው ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባዔ የማንሰራራት ዘመን የሚበሰርበት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመጀመሪያው ጉባዔ የተገቡ ቃሎች ተፈጽመው ሪባን የምንቆርጥበት ዘመን ነው ሲሉ አመላክተዋል። በዚህም በቀጣይ ወራት ለኢትዮጵያ ህዝብ ብስራት እናበስራለን ብለዋል። በዚህ ዓመት የታየው የኮሪደር ልማት በሚቀጥለው ዓመት አታዩትም፤ በዚህ ዓመት ያያችሁት ፕሮጀክት በሚቀጥለው ዓመት ጨርሰን አስውበን አሳምረን አልቀን በአዲስ መልክ ታዩታላችሁ እንጂ የዘንድሮውን በሚቀጥለው ዓመት አንደግመውም ብለዋል። ለዚህ ደግሞ አዲስ የስራ ባህል መፍጠር፣ አሰራርና የተሻለ አመራር የመምረጥ የጋራ ውሳኔ ከጉባዔው ይጠበቃል ብለዋል።   ብልጽግና ከ15 ሚሊየን በላይ አባላት በመያዝ በአፍሪካ ግዙፉ ፓርቲ መሆኑን ገልጸው፤ ከቁጥር በዘለለ ግን አባላቱ እንደ ሻማ ቀልጠን ለትውልድ ዕዳ ሳይሆን ምንዳና ብልፅግና ለማውረስ መሰረት መጣል አለብን ብለዋል። አዲሱ ትውልድ ልማትና ብልጽግና እንደሚሻ በማሰብ ለፍሬ መትጋት እንደሚገባ አንስተዋል። የብልጽግና አጀንዳ ሰላምና አንድነት በመሆኑ ለሰላም፣ ለአንድነትና ለልማት እጁ የተዘረጋ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከግጭት ይልቅ መነጋገርና መሰልጠንን ማስቅደም እንደሚገባ አስገንዘበዋል። ብልፅግና ባለፉት ዓመታት ብዙ ፈተናዎች ቢገጥሙትም ይህን ተሻግሮ ማሸነፍ የሚችል አቅም መፍጠሩን ገልጸው፤ የኢትዮጵያን ልማትና ሰላም እናረጋግጣለን ብለዋል። በአጠቃላይ የሰላም መሰረት፣ የብልጽግና ተምሳሌት የሆነች፣ ያበበች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማውረስ ብልፅግና ተግቶ ይሰራልም ብለዋል።
ብልፅግና ፓርቲ ከጉባኤ እስከ ጉባኤ ያስመዘገባቸውን አመርቂ ውጤቶች ዘላቂነት የሚያረጋግጡ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል- የጉባዔው ተሳታፊዎች
Feb 1, 2025 47
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦ ብልፅግና ፓርቲ ከጉባዔ እስከ ጉባዔ ያስመዘገባቸውን አመርቂ ውጤቶች ዘላቂነት የሚያረጋግጡ አቅጣጫዎችንና ውሳኔዎችን እንደሚያስቀምጥ የጉባዔው ተሳታፊዎች ገለጹ፡፡ ብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤውን " ከቃል እስከ ባህል " በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው። ብልጽግና ሀገር በቀል እሳቤ ነድፎ የመጣ የመጀመሪያው ፓርቲ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት እና የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጸዋል፡፡ ብልጽግና ፓርቲ ከጉባኤ እስከ ጉባኤ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች እንዲሁም በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሀገርን ቀጣይነት የሚያረጋግጡ ተጨባጭ ውጤቶችን አስመዝገቧል፡፡ የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛው መደበኛ ጉባኤ ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን የሚያስተሳስሩ ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት ስለመሆኑም በጉባኤ መክፈቻ ላይ ተጠቁሟል፡፡ የጉባኤው ተሳታፊዎች በመክፈቻ መርሐ ግብር ላይ በሰጡት አስተያየት፤ ብልጽግና ፓርቲ ከጉባኤ እስከ ጉባኤ ያስመዘገባቸውን አመርቂ ውጤቶች ዘላቂነት የሚያረጋግጡ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ተናግረዋል፡፡ የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ኃላፊ ሲሳይ ዳምጤ በሰጡት አስተያየት ፓርቲው ባለፉት ዓመታት በሁሉም መስኮች አንጸባራቂ የሚባሉ ድሎችን ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡ በህዝቡ የተጠየቁ ጥያቄዎችን በመመለስ ላይ ያለ ፓርቲ መሆኑን ጠቁመው የኢትዮጵያን ብልጽግና በጠንካራ መሰረት ላይ ለማነጽ እየተጋ ያለ ፓርቲ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞ ዞን የቦረዳ ወረዳ አስተዳዳሪና የጉባኤው ተሳታፊ አሸናፊ ሻሌ በበኩላቸው ብልጽግና ሰላምን፣ ልማትን እና የህዝቦችን ህብረ ብሄራዊ አንድነት ከማረጋገጥ አኳያ አመርቂ ስራዎችን መስራቱን ገልጸዋል፡፡   በኢትዮጵያ አስደማሚ ለውጦች እንዲመዘገቡ በማስቻልም የህዝብን ተጠቃሚነት በተግባር በማረጋገጥ ላይ ያለ ፓርቲ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ በሁለተኛ መደበኛ ጉባኤው የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚስቀጥሉ ውሳኔዎች እንደሚጠበቁም ተናግረዋል፡፡ እንደሀገር የተጀመሩ ለውጦችን ዘላቂነት ማስቀጠል የሚችሉ በሳል ውሳኔዎች እንደሚጠበቁም ጠቁመዋል፡፡ አቶ አሸናፊ ሻሌ በበኩላቸው በሁሉም መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ፓርቲው አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ ተናግረዋል፡፡   ኢትዮጵያ በጀመረችው የልማት መንገድ የህዝቦቿን ተጠቃሚነት ይበልጥ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ውሳኔዎች እንደሚጠበቁ ጠቅሰው ለተፈጻሚነቱም እንደሚተጉ ገልጸዋል፡፡ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የመጡት የጉባኤው ተሳታፊ አስራት መኩሪያ እንዳሉት ብልጽግና የፖለቲካ አካታችነትን በተግባር ያረጋገጠ ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል፡፡   በኢትዮጵያ የብሔራዊነት ትርክት እንዲጸና ብሎም ወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲጠናከር አልሞ የጀመራቸው ስራዎች ውጤት ማስመዝገብ መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ከምዕራብ ሀረርጌ ዞን በዴሳ ከተማ በጉባኤው በመክፈቻው መርሐ ግብር ላይ የተገኙት ፋጡማ ጠሃ አህመዶ በበኩላቸው ብልጽግና ቃል በተግባር ያሳየ ፓርቲ መሆኑን ገልጸዋል።  
ለፓን አፍሪካዊነት ማበብ ወሳኝ ሚና የነበራቸው ኢትዮጵያና ሞሮኮ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ አጋርነታቸው እየጎለበተ መጥቷል- ፕሮፌሰር መሀመድ ሳዲኪ
Feb 1, 2025 58
አዲስ አበባ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፦ ለፓን አፍሪካዊነት መጎልበት ወሳኝ ሚና የነበራቸው ኢትዮጵያና ሞሮኮ በጋራ ተጠቃሚነትና መሻት ላይ የተመሰረተ አጋርነታቸው እየጎለበተ መምጣቱን የሞሮኮው ናሽናል ራሊ ኦፍ ኢንዲፔንደንትስ(አር ኤን አይ) ፓርቲ ተወካይ ፕሮፌሰር መሀመድ ሳዲኪ ገለጹ። ትናንት ማምሻውን በተደረገው የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የፓርቲያቸውን መልዕክት ያስተላለፉት ፕሮፌሰር መሀመድ ሳዲኪ ኢትዮጵያ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት የጀመረችውን አስደናቂ የልማት ጉዞ እንዲሁም በሀገራዊም ሆነ በአፍሪካ አቀፍ አንድነትና ሰላም ላይ ያላትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።   ኢትዮጵያና ሞሮኮ የጥንታዊ ታሪክ ባለቤቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሁለቱ ሀገራት ከ1960ዎቹ ጀምሮ የፓን አፍሪካዊነት እሳቤ እንዲያብብ ወሳኝና ንቁ ተሳትፎ ነበራቸው ብለዋል። የኢትዮ-ሞሮኮ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት፣ የመበልጸግ ርዕይ እና ረጂም ዘመን ያስቆጠረ ታሪካዊ አጋርነት ላይ የተመሰረተ ትብብር ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ ሁለቱ አገራት በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የጋራ ፍላጎት እንዳላቸው አንስተዋል። ከቅርብ ዓመታት ውስጥ የሞሮኮው ንጉስ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የኢትዮ-ሞሮኮ ፖለቲካዊ ወዳጅነት ወደላቀ ደረጃ እንዲሸጋገርና ስትራቴጂካዊ አጋርነታቸው እንዲጎለብት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ አጋጣሚ ነበር ብለዋል። በዚህም ሁለቱ ሀገራት በተለይም በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሁሉን አቀፍ የትብብር መስኮች ላይ እየሰሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል። የሁለቱ አገራት አጋርነትና ትብብር በደቡብ-ደቡብ ማዕቀፍ የጋራ ፈተናዎችን ለመከላከል እንዲሁም ለማህበረሰቡ የተሻለ አህጉራዊ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና አካታች የአስተዳደር ስርዓት እንዲሰፍን ያግዛል ብለዋል። የሁለቱ አገራት የግል ዘርፍ ተዋንያን በኢኮኖሚው መስክ እመርታ የሚጫወቱት ወሳኝ ሚናም አንስተዋል። አፍሪካ መልከ ብዙ ዕምቅ ጸጋ ቢኖራትም በነባራዊ ዐውድ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የምግብ ዋስትና፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ስራ አጥነትና መሰል ትኩረት የሚሹ ፈተናዎችን እንዳሉባት አንስተዋል። የጋራ ፈተናዎችን ለማሸነፍ ደግሞ የጋራ አቅሞቻችንን በማቀናጀት በትብብር መስራት ግድ ይለናል ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ጊዜው አፍሪካን የፈተና ሳይሆን የዕድል ቤት ለማድረግ የምንሰራበት ነው ብለዋል።   ኢትዮጵያና ሞሮኮ ከኢኮኖሚያዊ ትብብር ባሻገር ፖለቲካዊ ትብብር ለማጠናከር ያላቸውን መሻት ገልፀው፤ የሁለቱ ሀገራት ገዥ ፓርቲዎች ለፖለቲካዊ ትብብሮች መጠናከር ቁልፍ የመሪነት ሚና እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል። በዚህም ፓርቲያቸው የሁለቱ ሀገራት ሁሉን አቀፍ ትብብር ይበልጥ ወደላቀ ደረጃ እንዲሻጋገር ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በቀጣይነት ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳቦች የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን ብልፅግና ለማረጋገጥ ይበጃሉ- የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር
Jan 31, 2025 95
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በብልፅግና ፓርቲ ጉባዔ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ያነሷቸው ሃሳቦች ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ቀጣናውና የአፍሪካን ብልፅግናን ዕውን ማድረግ የሚያስችሉ ናቸው ሲሉ የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ዛፈር ሲራካያ አደነቁ። የብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ ጠቅላላ ጉባኤ "ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ቃል ከተለያዩ ሀገራት የመጡ እህት ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ተጀምሯል፡፡ የተርኪዬ ኤኬ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ዛፈር ሲራካያ በጉባዔው ላይ ባደረጉት ንግግር የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን(ዶ/ር) ጠንካራና ሁሉን አቀፍ ቁም ነገር አዘል መልዕክት አድንቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የጠቀሷቸው ሃሳቦች መተግበር ከተቻለ ወደፊት የበለጸገች ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የበለጸገ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ብሎም የበለጸገች አፍሪካን ዕውን ማድረግ እንደሚቻል እርግጠኛ ነኝ ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃላቸውን ወደ በገቢር እንደሚለውጡ ተስፋቸውን ገልጸው፤ በብልጽግና ጉባዔ ውሳኔዎችም ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካና ለዓለም ሰላምና ልማት የሚበጁ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉ እምነታቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከዓለማችን ጥንታዊ ስልጣኔዎች አንዷ እንደመሆኗ በአፍሪካ የታሪክ ገጾች ውስጥ ጉልህ ታሪክ የጻፈች እንዲሁም በባህል፣ በታሪክ፣ በብዝሃነት፣ በእምነት፣ በቋንቋና ቅርስ የበለጸገችና በፈተናዎች ሳትበገር ዘመናትን የተሻገርች ምድር ናት ብለዋል። ከኢትዮጵያ አስደናቂ ታሪኮች መካከል ለዘመናት ሉዓላዊነቷን አስከብሯ መኖሯ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ክፍለ ዓለማት የነጻናት ታጋዮች ፋና ወጊነቷ እንደሆነ ጠቅሰዋል።። ተርኪዬና ኢትዮጵያ የነጻነት እና ሉዓላዊነት የአይበገሬነት መንፈስ እንደሚጋሩ ጠቅሰው፤ ሁለቱ ሀገራት በታሪክም ከመሰረቱ ጥብቅ ቁርኝነት እንዳላቸው አንስተዋል። ረጁም ዘመናት ባስቆጠረው የሀገራቱ ወዳጅነት ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው በ1920ዎቹ መጀመሩን ገልጸው፤ ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት የርኪዬ የመጀመሪያውን ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮ ነበር ብለዋል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በንግድ፣ በባህል፣ በትምህርት እና በሌሎች መስኮች ያላቸው ትብብር በየዘመኑ እያበበና እየጎለበተ የመጣና መልከ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች ያስመዘገበ እንደሆነ ገልጸዋል። ኤኬ ፓርቲ ኢትዮጵያ እንደ የፍሪካ ህብረት መገኛነቷም ልዩ ትኩረት እንደሚሰጣት እና የሁለትዮሽ የልማት ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አበክሮ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካዊ መፍትሄ በሚለው መርህ መሰረት በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ተርኪዬ ያላትን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ጠቁመው፤ ተርኪዬ ለቀጣናው ሰላምና ልማት መረጋገጥ ትብብሯን ምንጊዜም ትቀጥላለች ብለዋል።
በአፍሪካን ሰላምና ብልጽግናን ዕውን ለማድረግ የሀገራትን ተቀራርቦ መስራት ይሻል- የታንዛኒያ እና ሩዋንዳ እህት ፓርቲዎች
Jan 31, 2025 72
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ አፍሪካን ከውስብስብ ችግሮቿ በማላቀቅ ወደ ተሟላ ሰላምና ብልጽግና ለማሻገር የሀገራት ይበልጥ ተቀራርቦና ተባብሮ መስራትን እንደሚሻ የታንዛኒያ እና ሩዋንዳ እህት ፓርቲዎች ገለጹ። የሁለቱ ሀገራት የፓርቲ ተወካዮች ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያላቸውን የፓርቲ ለፓርቲ አጋርነትና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚሰሩም አረጋገጠዋል። የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል። በጉባኤው ላይ የተለያዩ አገራት አህት ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች የታደሙ ሲሆን በመድረኩም መልእክት አስተላልፈዋል። የታንዛኒያው ቻማ ቻማ ፑንዱዚ ፓርቲ ዋና ጸሀፊ ኢማኑኤል ቺምቢ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሳል የአመራርነት ጥበብ ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል። የታንዛንያ ፕሬዝዳንት ሳምያ ሱሉህ ሀሳን፤ የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ስኬታማ እንዲሆን የመልካም ምኞት መግለጫቸውን መላካቸውን አንስተው ሁለቱ አገራት ለጋራ ልማትና ብልጽግና ትብብራቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ገልጸዋል። የሀገራቱ የረጅም ጊዜ ግንኙነት በፓርቲ ለፓርቲ ትብብርም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል። ዓለማችን በአየር ንብረት ለውጥ፣ በግጭት፣ በድርቅና በምግብ እጥረት እየተፈተነች ነው ያሉት ዋና ጸሀፊው፤ አፍሪካን ከእነዚህ ችግሮች ለማውጣት አህጉራዊ ትብብርን ማጠናከር ይገባል ብለዋል። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎችና የተመዘገቡ ውጤቶች የሚደነቁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ዌላርስ ጋሳማጌራን፤ በበኩላቸው የሩዋንዳ ፕረዚዳንት ፖልካጋሜ የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ስኬታማ እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል ብለዋል። ከሁቱ አገራት ጠንካራ ግንኙነት ባለፈ በፓርቲ እና ለፓርቲ መካከል የትብብር ግንኙነቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል። የሁለቱ እህት ፓርቲዎች መካከል ያለው አጋርነትም የፖለቲካ መስተጋብራቸውን እንዲያጎለብቱ ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ አፍሪካን ከውስብስብ ችግሮች በማላቀቅ ሰላምና ብልጽግናዋን ዕውን ለማድረግ አገራት ይበልጥ ተባብረውና ተቀራርበው መስራት እንዳለባቸውም አንስተዋል። በሩዋንዳ እና በኢትዮጵያ መካከል የሁለትዮሽ የትብብር ግንኙነቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የኢትዮጵያና የሩስያ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን አጋርነት ተጠናክሮ ይቀጥላል- የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ
Jan 31, 2025 58
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያና የሩስያ የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን አጋርነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ገለጸ። "ከቃል እስከ ባህል" ከዛሬ ጥር 23 እስከ ጥር 25/2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የዩናይትድ ሩስያ ፓርቲ ሱፕሪም ካውንስል ቢሮ አባልና የሩስያ ፌዴሬሽን ሴናተር አንድሬ ክሊሞቭ ፓርቲውን ወክለው መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም፤ ለብልጽግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባዔ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። ጉባዔው ለኢትዮጵያ ቀጣይ እድገት አሻጋሪ እንደሚሆንና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ቦታ እንደሚያስቀጥል ባለሙሉ ተስፋ ነኝ ብለዋል። ኢትዮጰያና ሩስያ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ታሪካዊና በበርካታ መስኮች ላይ የተመሰረተ አጋርነት እንዳላቸው ጠቁመዋል። ይህንንም አጋርነት በሁለትዮሽና ባበለብዙ ወገን በተለይም ብሪክስንና የአፍሪካ ሩስያ አጋርነት መድረክን በመጠቀም ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል። ገዢው የዩናይትድ ሩሲያ ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለው ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር እንሰራለንም ብለዋል። ብልጽግና ፓርቲ በቀጣይ ተጨማሪ ስኬትን እንዲጎናጸፍ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
ብልጽግና ፓርቲ ቃል የገባቸውን ተግባራት የፈጸመበት መንገድ እጅግ የሚደነቅ እና ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው - የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ ዋና ጸሀፊ ፒተር ላም
Jan 31, 2025 57
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- ብልጽግና ፓርቲ በመጀመሪያው ጉባኤ ቃል የገባቸውን ተግባራት የፈጸመበት መንገድ እጅግ የሚደነቅ እና ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ ዋና ጸሀፊ ፒተር ላም ገለጹ። የብልጽግና ፓርቲ እህት ፓርቲ የሆነው የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ ዋና ጸሀፊ ፒተር ላም የአጋርነትና የመልካም ምኞት መግለጫቸውን አቅርበዋል። ብልጽግና ፓርቲ በመጀመሪያው ጉባኤ ቃል የገባቸውን ተግባራት የፈጸመበት መንገድ እጅግ የሚደነቅ እና ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን ተናግረዋል። ይህ ተሞክሮ የበርካታ አፍሪካ ሀገራት ገዥ ፓርቲዎች ለህዝባቸው ቃል የገቡትን ለመፈጸም ተሞክሮ የሚወስዱበት መሆኑንም ገልጸዋል። ብልጽግና ፓርቲ እድገትን በማረጋገጥና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በመገንብት ያከናወናቸው ተግባራት ኢትዮጵያ በከፍተኛ የልማት መንገድ ላይ መሆኗን የሚያመላክቱ መሆናቸውን ተናግረዋል። ይህም በፖለቲካና በኢኮኖሚ መስኮች የተመዘገበው ስኬት የሚደነቅ እንደሆነ የሚያመላክት ነው ብለዋል።   ዋና ጸሀፊው በአዲስ አበባ የተገነባው የኮሪደር ልማት ስራ እጅግ አስደማሚ እና የከተማዋን ገጽታ ውብ ያደረገ መሆኑን ለአብነት አንስተዋል። በተጨማሪም የተያዘን ግልጽ ራእይ ወደ ተግባር መቀየር ደግሞ የበለጠ አስፈላጊ መሆኑን ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑንም ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ ከደቡብ ሱዳን ነጻነት ጊዜ ጀምሮ ከጎኗ ያልተለየች ወዳጅ ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ የሀገሪቱ መሪዎች ድጋፍም ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል። የሁለቱ ሀገራት ወዳጅነት ተጠናክሮ መቀጠሉን ያነሱት ሃላፊው፤ ደቡብ ሱዳን ባለፈው አመት የናይል ቤዚን ትብብር ማእቀፍን ማጽደቋ ሌላው የሀገራቱ ወዳጅነት ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል። በትምህርት ዘርፍ ያለውን ወዳጅነት ለማጠናከርም ከስድስት መቶ በላይ የደቡብ ሱዳን ተማሪዎች በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት እድል ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
የናይጄሪያው ኤፒሲ ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ ይቀጥላል
Jan 31, 2025 55
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- የናይጄሪያ ኤፒሲ ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ። "ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ሃሳብ ከዛሬ ጥር 23 እስከ ጥር 25/2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆየው የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በድምቀት መካሄድ ጀምሯል። በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የናይጄሪያው ኤፒሲ ፓርቲ ምክትል ሊቀ-መንበር አልሀጅ አሊቡካር ዳሎሪ ፓርቲያቸውን በመወከል መልዕክት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም ኢትዮጵያና ናይጄሪያ በርካታ ዓመታት የዘለቀ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ይህም ግንኙነት በመከባበርና በጋራ እሴት ላይ የጸና መሆኑን ተናግረዋል። ሁለቱ ሀገራት የጋራ ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ጠቅሰው ይህም አጋርነት በተለያዩ የትብብር መስኮች የተመሰረተ መሆኑን ገልጸዋል።   ለአብነትም በዲፕሎማሲ፣ በንግድና በባህል ልውውጥ ያላቸውን አጋርነት አንስተዋል። በተመሳሳይ የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን ኤፒሲና ብልጽግና ፓርቲ የጋራ ግብ ያላቸው ፓርቲዎች ናቸው ሲሉም ተናግረዋል። ሁለቱም ፓርቲዎች ልማትን ለማረጋገጥና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንዲሁም የበለጸገች ሀገር ለመፍጠር እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ምንም እንኳን እንደ ሀገር የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሙን መፍትሄው ትብብር ነው ሲሉም አክለዋል። በመሆኑም ፓርቲያቸው ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ብልጽግና ፓርቲ ዛሬ የሚያካሂደው ጉባኤ ልማትና አንድነትን ለማምጣት ያለንን ቁርጠኝነት በጋራ የምናወድስበት ነው ሲሉም ጠቁመዋል።
በአፍሪካ የአንድነት መሰረት እንዲጸና ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ በማድረግ ኢትዮጵያ የላቀ ሚናዋን እየተወጣች ነው - የደቡብ አፍሪካው ናሽናል ኮንግረንስ ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል ኑዶሎ ኪቤት
Jan 31, 2025 87
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- በአፍሪካ የአንድነት መሰረት እንዲጸና ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ በማድረግ ኢትዮጵያ የላቀ ሚናዋን እየተወጣች ነው ሲሉ የደቡብ አፍሪካው ናሽናል ኮንግረንስ ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል ኑዶሎ ኪቤት ገለጹ። የብልጽግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ መካሄድ ጀምሯል። በጉባኤው ላይ የተለያዩ ሀገራት አህት ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች የታደሙ ሲሆን በመድረኩም መልዕክት አስተላልፈዋል። የደቡብ አፍሪካው ናሽናል ኮንግረንስ ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ አባል ኑዶሎ ኪቤት፤ በመልዕክታቸው በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና እውን እንዲሆን በመስራት ላይ ላሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና አመራራቸው አድናቆታቸውን ገልጸዋል።   በአፍሪካ የአንድነት መሰረት እንዲጸና ልማትና ብልጽግና እንዲረጋገጥ የኢትዮጵያ ሚና የላቀ መሆኑን አስታውሰው አሁንም አጠናክራ መቀጠሏን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ምሳሌ ብቻ ሳትሆን የአንድነትና የጥንካሬ መሰረት መሆኗንም አስታውሰዋል። በመሆኑም የደቡብ አፍሪካ ናሽናል ኮንግረንስ ፓርቲ ለሀገራዊና አህጉራዊ ልማት መሳካት ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በቅርበት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል። የአፍሪካ የልማት አጀንዳዎች እንዲሳኩ አህጉራዊ ሰላም፣ የዳበረ ዴሞክራሲና ልማት እንዲረጋገጥ የጋራ ጥረታችን ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል። የአፍሪካ ነፃነት የሚረጋገጠው የዜጎቿ ሰላምና ነፃነት እውን ሲሆን ነው ያሉት ኑዶሎ ኪቤት፤ ለዚህ ስኬት ሀገራት ይበልጥ ተባብረውና ተቀራርበው መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
የብልፅግና ጉባዔ በፓርቲዎች ጉባዔ ታሪክ መላው ብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ኖሮት የሚደረግ ብቸኛው ጉባዔ ነው- የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
Jan 31, 2025 66
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ፓርቲዎች ጉባዔ ታሪክ መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ኖሮት የሚደረግ ጉባዔ የብልፅግና ጉባዔ ብቻ ነው ሲሉ የፓርቲው ፕሬዝዳንት እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ። የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባዔ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የፓርቲው ፕሬዝዳንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገር በቀል ዕሳቤ ነድፎ የመጣ ፓርቲ ብልፅግና መሆኑንም ተናግረዋል።   ብልፅግና ፓርቲ ለ2ኛ ጊዜ ጉባዔ ያዘጋጀበት ዋናው ምክንያት ያለፈባቸውን ጉዞ በማጠቃለል አዲስ የጉዞ ጅማሮን የሚያስኬድ የተሰናሰለ ሃሳብ የሰነቀ አመራር፣ አሰራርና ደንቦች በጉባዔ መጽደቅ ስላለባቸው መሆኑንም አስገንዝብዋል። በምክክርና ውይይት የሚፈልቅ ሃሳብም ኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት ዓመታት የምትጓዝበትን መንገድ የሚቀይስ መሆኑን ገልጸዋል። ከጉባዔውም በጉባዔው ሂደትም ሆነ ውጤት ዴሞክራሲያዊና አሳታፊነትን እርግጠኝነቱን ለመፈተሽ የሚያስፈልግ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ፓርቲዎች ጉባዔ ታሪክም መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ኖሮት የሚደረግ ጉባዔ የብልፅግና ጉባዔ ብቻ ነው ብለዋል። ሁለተኛው የፓርቲው ጉባዔም "ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ሃሳብ በቃል የሚነገርና የሚሰነድን በልምምድ ባህል የማድረግ ትኩረት መሰነቁን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ለሃምሳና ስልሳ ዓመታት የነበረው የፓርቲ ፖለቲካ ልምምድ የምንጠላውን አብዝተን መውቀስ፣ ልናፈርስና ልንንድ የፈለግነውን ነገር በብዙ ማስረጃ መክሰስ ላይ የተመሰረተ አንጂ ልንገነባ የፈለግነውን ለውጥ ማመላከት ላይ ውስንነት ነበረብን ብለዋል። በመሆኑም ብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበሩ ኋላ ቀር አሰራርና ልምምዶችን በማፍረስ በአዲስ እሳቤ የለውጥ ስራዎችን አስቀጥሏል ብለዋል። የደረጀ ሃሳብ የሌለው የፖለቲካ ፓርቲ የፈለገውን በማፍረስ ለውጥ መፍጠር ቢችልም ለውጥ መምራት ካልቻለ ግን የሚያልመውን ለመትከል ይቸገራል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም