ማህበራዊ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበራዊ
ቅን ኢትዮጵያ ማኅበር ዜጎችን ለበጎ ዓላማ እንዲሰለፉ የጀመረው ጥረት ሊጠናከር ይገባል
Aug 5, 2024 169
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ቅን ኢትዮጵያ ማኅበር ዜጎችን ለበጎ ዓላማ እንዲሰለፉ የጀመረው ጥረት ሊጠናከር ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ። ቅን ኢትዮጵያ ማኀበር በቅንነት፣ በጎ አሳቢነትና ሠላም ግንባታ ላይ ለተማሪዎች፣ ለወላጅ ተወካዮችና መምህራን ሲሰጥ የቆየው ሥልጠና ዛሬ ተጠናቋል። ሥልጠናው ለአንድ ሳምንት የተሰጠ ሲሆን "ተማሪ ለሀገር ሠላም" በሚል መሪ ኃሳብ ተካሂዷል። የሥልጠናው ተሳታፊዎችም በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሳቢያ፣ የአንድነት ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የተለያዩ የልማት ሥራዎችንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። የሥልጠናው ማጠቃለያ መርኃ ግብር በአድዋ ድል መታሰቢያ የተካሄደ ሲሆን የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል። ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ቅንነት፣ መልካምነትና መተሳሰብ እንደ አገር አብሮ ለመቆም፤ ለዘላቂ ሠላም መረጋገጥ ቁልፍ ሚና አለው። ሠላም ደግሞ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ መሰረት ነው ያሉት ከንቲባዋ ሁላችንም ተባብረን መሥራት አለብን ሲሉም ተናግረዋል። ቅን ኢትዮጵያ ማኅበርም የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ዜጎችን በማሰባሰብ ለበጎ ዓላማ እንዲሰለፉ የጀመረው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው ቀጣይነትም ሊኖረው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። የቅን ኢትዮጵያ ማህበር የቦርድ ሊቀ መንበር መሰረት ስዩም በበኩላቸው የሥልጠናው ተካፋዮች አገር ከእናንተ ብዙ ትጠብቃለች፤ የቀሰማችሁትን እውቀት ወደ መጣችሁበት አከባቢ በማስፋፋት ቅን ማኅበረሰብ የመፍጠር ጥረቱን ማጠናከር አለባችሁ ብለዋል። የቅን ኢትዮጵያ ማኅበር መሥራች አባል መሰለ ሃይሌ በኢትዮጵያ ቅንነት እንዲዳብር ማህበሩ የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል። ከረጅም ጊዜ አኳያ የቅንነት ባህል እንዲሁም የሠላም እሴቶች መገንባት ላይ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት የግንዛቤ ለውጥ እንዲመጣ እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል። ለአንድ ሳምንት ያህል "ተማሪ ለሀገር ሠላም" በሚል መሪ ኃሳብ የተሰጠው ሥልጠናም የዚሁ አካል ነው ያሉት አቶ መሰለ ይሄው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። በሥልጠና መርሃ ግብሩ ላይ ወላጆችን ወክለው ከተሳተፉ መካከል ከኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ሶኮሩ ወረዳ የመጡት ሙኢዲን አባቦራ አባሱራ፤ ሥልጠናው ለአገሬ በተነሳሽነትና ከልብ በመነጨ ስሜት በትጋት መስራት እንዳለብኝ ግንዛቤ የጨበጥኩበት ነው ብለዋል። ከአማራ ክልል ባህዳር ከተማ ጊዮን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተወከለችው ተማሪ ትንሳኤ እስጢፋኖስ በበኩሏ በሥልጠና ቆይታዬ አንድነታችንን የበለጠ የሚያጠናክሩ ኃሳቦችን ገብይቻለሁ ብላለች። ከአፋር ክልል ሎጊያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጣው ተማሪ ዑስማን መሀመድ በሰጠው አስተያየት በኢትዮጵያን በተሻለ መልኩ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ፣ በሠላም በኩልም የሚጠበቅብኝን ድርሻ ላይ በቂ ግንዛቤ ወስጃለሁ ብሏል።
በአለርት ሆስፒታል የሕክምና መሳሪያዎች የሚታደሱበት ማዕከል ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ
Aug 5, 2024 148
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ በአለርት ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና መሳሪያዎች የሚታደሱበት ማዕከል ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ። የመሰረት ድንጋዩን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባና በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጁንግ ካንግ አስቀምጠዋል። የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ጊዜ፤ እንደ አገር ያረጁ የሕክምና ግብዓቶችን መልሶ በመጠቀም ረገድ ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ የሕክምና መሣሪያዎች ታድሰው ዳግም አገልግሎት መስጠት እየቻሉ ለብክነት ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰው ዛሬ ግንባታው የተጀመረው ማዕከል ያረጁ የሕክምና መሳሪያዎችን አያያዝና አጠቃቀምን የሚያሻሽል መሆኑን ገልጸዋል። ግንባታው በኮሪያው ሪፐብሊክ ዓለም አቀፍ የጤና እንክብካቤ ፋውንዴሽን (ኮፊ) በተደረገ የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄድ መሆኑን አመላክተው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ተናግረዋል። ማዕከሉ ከኢትዮጵያ ባለፈ ለጎረቤት አገራት ጭምር አገልግሎት ጭምር አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ እንደሚገነባ ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ አምባሳደር ጁንግ ካንግ በበኩላቸው፤ ኮሪያ ሪፐብሊክና ኢትዮጵያ የጋራ ተጠቃሚነት ላይ መሰረት ያደረገ ጠንካራ ወዳጅነት ያላቸው አገራት ናቸው ብለዋል። ሁለቱ አገራት በተለያዩ የልማት መስኮች ላይ በትብብር እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል። ዛሬ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት ማዕከል በኢትዮጵያ የሕክምና መሳሪያዎችን በማደስና ወደ ሥራ በማስገባት የአገሪቱን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የሀዲያ ብሔረሰብ ባህላዊ የዳኝነትና የግጭት አፈታት ሥርዓት ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲሸጋገር እየተሰራ ነው
Aug 5, 2024 220
ሆሳዕና ፤ ሐምሌ 29/2016 (ኢዜአ)፡- የሀዲያ ብሔረሰብ ባህላዊ የዳኝነትና የግጭት አፈታት ሥርዓት ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲሸጋገር ለማስቻል በጥናት የተደገፉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የሀዲያ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ። በዞኑ የሌሞን ወረዳ ማህበረሰብን የሚወክሉ የበላይ ጠባቂ የሀገር ሽማግሌዎችን የመሰየም መርሃ ግብር ዛሬ በወረዳው ኃይሴ ቀበሌ ተካሂዷል። የመምሪያው ሃላፊ አቶ ታምሬ ኤርሚያስ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በሀዲያ የአካባቢውን ሰላም የሚያስጠብቁና የማህበረሰቡን የእርስ በርስ ትስስር ለማጎልበት የሚጠቅሙ በርካታ ባህላዊ እሴቶች አሉ። ህብረተሰቡ ግጭቶችን የሚያስወግድበትና ሰላም የሚያወርድበት ባህላዊ የዳኝነትና ግጭት መፍቻ ሥርአት ወይም የ"ጢጉላ ባህላዊ ግጭት አፈታት" ከባህላዊ እሴቶቹ አንዱ መሆኑንም ጠቁመዋል። ሥርአቱ ግጭትን በሰለጠነ መንገድ በውይይት በመፍታት ሰላምን ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸው፣ ባህላዊ እሴቱ ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲተላለፍና ተሰንዶ እንዲቀመጥ ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የጥናት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን አስረድተዋል። ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቱ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ታምሬ፣ ስርዓቱን የሚመራው ሰውም በየጊዜው በህዝብ እየተመረጠ የስልጣን ሽግግር እንደሚደረግ ገልጸዋል። አቶ ታምሬ እንዳሉት ባህላዊ የዳኝነት ስርዓቱ ለዴሞክራሲ መጎልበት ጭምር ጉልህ ሚና አለው። የሀድያ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ዳኛ ጥላሁን ዴታሞ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓት በዘመናዊ ፍርድ ቤቶች ያለውን የሥራ ጫና ከማቃለል አንጻር አስተዋጾው የጎላ ነው። ባህላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቱ እሴቱን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላፍ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል። በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ባህል ሽማግሌ አቶ ታደሰ ኮራ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውና ዘመናትን ያስቆጠሩ በርካታ ባህላዊ ዕሴቶች እንዳሉ ገልጸዋል። ግጭት በሰላማዊ መንገድ በውይይት የሚፈታባቸው ዕሴቶች ለሀገራዊ አንድነት እንደምሶሶ ናቸው ያሉት አቶ ታደሰ፣ ህብረተሰቡ ለዘመናት የተጠቀመባቸውን እነዚህን እሴቶች መጠበቅ ይገባናል ብለዋል። የአብሮነት እሴቶቻችንን በዘመናዊነት ሳይበረዙ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በሚሰሩ ሥራዎች ውስጥ የአገር ባህል ሽማግሌዎች ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አስረድተዋል። የሀገር ሽማግሌዎች ተቀራርበው በመስራት የሰላም እጦት ምክንያት የሆኑ ችግሮችን መፍታት እንደሚችሉ የጠቆሙት አቶ ታደሰ፣ እሳቸውም የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። "ሰላምን ማስጠበቅ የሚጀመረው ከአካባቢ ነው።" ያሉት ደግሞ በሌሞ ማህበረሰብ ዘንድ በሰብሳቢ ዳኝነት የተመረጡት ዳኛ ብርሃኑ ጡሞሮ ናቸው። የሀገር ሽማግሌዎች ጽንፍ ከመያዝና ከእኔነት አመለካከት ወጥተን ፍትሃዊ ፍርድ በመስጠት ለህዝብ ሰላምና አብሮነት መጠናክር ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብለዋል። የሀዲያን አንድነት ከማስጠበቅ ባለፈ በአጎራባች አካባቢ ካሉ ህዝቦች ጋር አብሮነትን በማጠናከር ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። በመርሃ ግብሩ ላይ የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ ተጋባዥ እንግዶች እና የባህል ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል።
ክልሉ የኮሌራና የወባ በሽታዎችን ለመከላከል ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ተግባር እየተከናወነ ነው
Aug 5, 2024 162
ባህር ዳር፣ሐምሌ 29/2016 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል የኮሌራና የወባ በሽታዎችን ህብረተሰቡን ያሳተፈ የመከላከል ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ። ቢሮው ያለፈው ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማና የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ የትውውቅ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል። የቢሮ ኃላፊው አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተደረገው የተቀናጀ ጥረት በዘርፉ አበረታች ስራ ማከናወን ተችሏል። በተለይም የኮሌራና የወባ በሽታዎችን ለመከላከል መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ለህብረተሰቡ በማዳረስ ለመቆጣጠር ጥረት መደረጉን አውስተዋል። በተያዘው በጀት ዓመትም የኮሌራ በሽታ ስርጭትን ለመግታት ህብረተሰቡ የግልና የአካባቢውን ንጽህና በመጠበቅ ራሱን ከበሽታው እንዲከላከል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። እንዲሁም ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ 22 ወረዳዎች ላይም የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭት እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል። አሁንም ተጨማሪ ርጭት ለማከናወን ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተው፤ ህብረተሰቡ ለወባ በሽታ አጋላጭ የሆኑ ስፍራዎችን ማፅዳት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል። የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ገበያው አሻግሬ በበኩላቸው፤ በዞኑ የወባ በሽታን ለመከላከል አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን የአልጋ አጎበር በማሰራጨትና ህብረተሰቡን በማስተባበር የመከላከል ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል። በአሁኑ ወቅትም በዘጠኝ ወረዳዎች የጸረ ወባ ኬሚካል ርጭትና ህብረተሰቡን ከበሽታው መከላከል በሚቻልበት አግባብ ግንዛቤን የማሰራጨት ስራ እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል። በመድረኩ ላይም የቢሮው፣ የዞንና የወረዳ የዘርፉ አመራሮች እንዲሁም አጋርና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
''ምድረ ቀደምት'' የሚለው መጠሪያ ኢትዮጵያን በልክ ይገልጻታል - የቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪዎች
Aug 5, 2024 225
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ ''ምድረ ቀደምት'' የሚለው መጠሪያ ኢትዮጵያን በልክ ይገልጻታል ሲሉ ኢትዮጵያን የጎበኙ የቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪዎች ተናገሩ። የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘችበትን 50ኛ ዓመት በተለያዩ መርኃ-ግብሮች እየተዘከረ ሲሆን፤ በቅርቡም ከ34 አገራት የተውጣጡ ከ240 በላይ የዘርፉ ተመራማሪዎች በኢትዮጵያ ቆይታ ነበራቸው። በቆይታቸውም የአድዋ መታሰቢያን፣ ብሔራዊ ቤተ-መዘክርና አንድነት ፓርክ ተዘዋውረው ጥንታዊ ቅርሶችና የቅሪተ-አካል ክምችቶችን ተመልክተዋል። ኢዜአ ያነጋገራችው ጎብኚዎች፤ኢትዮጵያ በሰው ዘር ምንጭነቷ ብሎም በዳበረ ጥንታዊ ቀደምት ታሪኳ ምድረ ቀደምት የሚለው መጠሪዋ በልክ ይገልጻታል ብለዋል። በአሜሪካ በሚገኘው ስቶክተን ዩኒቨርሲቲ ሥነ-ሕይወት ትምህርት ክፍል ተመራማሪ ፕሮፌሰሯ ማርጋሬት ሌዊስ፤ከፈረንጆቹ አቆጣጠር 1997 ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአፋር አካባቢ ምርምሮችን አድርገዋል። የምርምር ትኩረታቸውም ሉሲ በነበረችበት አካባቢ የነበሩ እንስሳት ላይ እንደሆነ የሚያነሱት ፕሮፌሰሯ፤ ኢትዮጵያን በብዙ መለኪያዎች ምድረ ቀደምት አገር እንደሆነች ያነሳሉ። በኢትዮጵያ የሚገኙ የቅድመ ሰው ዘርፈ-ቅሪተ-አካሎች ስለኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ ሳይሆን ስለመላው የሰው ልጆች የሚናገሩ እንደሆኑ ይገልጻሉ። ሌላው የሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪ ታንዛኒያዊ ፕሮፌሰር ጃክሰን ጃው፤ በሥነ-ምድር ጥናት ቀደምትነት የጊዜ ዑደትና የዕድሜ ቅደም ተከተል አኳያ ኢትዮጵያ ቀደምት የሰው ዘር መገኛ ናት ይላሉ። ኢትዮጵያ እስከ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ዕድሜ ያላቸው ቅሪተ-አካል የተገኘባት አገር መሆኗ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ቀደምት የሚያደርጋት ታሪኮች ባለቤትም እንደሆነ ተናግረዋል። በእንግሊዙ ሊቨርፑል ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር አመጣጥ ከፍተኛ ተመራማሪ ስፔናዊው ኢግናሲዮ ላሳጋባስተር (ዶ/ር)፤ የሉሲ ቅሪተ-አካል በኢትዮጵያ መገኘት እኔን ጨምሮ በርካታ ተመራማሪዎች በዘርፉ ጥናት እንዲሰማሩ አነቃቅቷል ይላሉ። ብሔራዊ ሙዚየምን ጨምሮ የቅደመ ሰው ዘር አመጣጥና የኢትዮጵያን ታሪኮች የያዙ ተቋማት የተደራጁበትን መንገድ አድንቆ፤ ኢትዮጵያ በቅሪተ-አካሎች ብቻ ሳይሆን በሌሎች አርኪዮሎጂካል ዘርፎች ምድረ ቀደምት የምትገኝ ሀገር ናት ብለዋል። በሌላ በኩል የታንዛኒያ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂስት ትምህርት ክፍል ባልደረባዋ ማሪየም ቡንዱላ (ዶ/ር) እና የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዋ ኬንያዊት ርብቃ ሙሪዩኪ፤ኢትዮጵያ ቅርሶቿን ያደራጀችበትን አግባብ አድንቀዋል። ቅርስን ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ማሻገር ትውልዱ በታሪኩ እንዲኮራ ብቻ ሳይሆን ከትናንት ማንነቱ እንዲማርበት የሚያስችል እንደሆነም ገልፀዋል። የ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ዓመት ዕድሜ ያላት የሰው ልጅ ቅሪተ-አካሏ ሉሲ ወይም ድንቅነሽ በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ኅዳር 24 ቀን 1974 በአፋር ክልል ''ሐዳር" የተባለ ሥፍራ ነበር የተገኘችው።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ የልማት ሥራዎች ከቻይና ድርጅት ጋር በትብብር ለመሥራት ተፈራረመ
Aug 5, 2024 129
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ የልማት ሥራዎች ከቻይናው ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንት ጋር በትብብር ለመሥራት ሥምምነት ተፈራረመ። ሥምምነቱን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የፋውንዴሽኑ ዳይሬክተር ይን ቼን ፈርመውታል። የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፤ ስምምነቱ በሰባት ፕሮግራሞች የገጠር ልማት ላይ ትኩረት በማድረግ ደሀና ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ብለዋል። ሰባቱ ፕሮጀክቶች የሚተገበሩበት ጊዜ እንዳላቸው አንስተው፤ የተማሪዎች ቁሳቁስ ድጋፍ ለማድረግ ዕቃዎቹ ወደብ ላይ መድረሳቸውን አስረድተዋል። ድጋፉ ገንዘብ፣ ቴክኒክና ቴክኖሎጂን ያካተተ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ መሆኑንም ጠቁመዋል። የተማሪዎች ምገባን በተለያዩ ክልሎች ማስፋት፣ ሴቶችን በኢኮኖሚ ማብቃት፣ በገጠር ለሚኖረው ማኅበረሰብ የሶላር ታዳሽ ኃይልን ተደራሽ ማድረግና የንጹህ መጠጥ ውኃ እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፎችን ያካተተ መሆኑን ገልፀዋል። ፕሮጀክቶቹ ሕብረተሰቡን ከተረጂነት በማላቀቅ በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል። የቻይናው ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንት በመጀመሪያ ዙር 320 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ የ10 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ፕሮጀክት መተግበሩንም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የፋውንዴሽኑ ዳይሬክተር ይን ቼን በበኩላቸው፤ ላለፉት አሥር ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ገልፀዋል። ፋውንዴሽኑ በተጠቀሱት ዘርፎች አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ለመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር የቁሳቁስ ድጋፍና ማዕድ አጋራ
Aug 5, 2024 110
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦የመከላከያ ሠራዊት ለመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር የቁሳቁስ ድጋፍና ማዕድ አጋራ። በድጋፍና የማዕድ ማጋራት ሥነ-ሥርዓቱ የመከላከያ ሠራዊት የሥራ ኃላፊዎችና የሠራዊቱ አባላት ተገኝተዋል። በመከላከያ ሠራዊት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄኔራል ሁሉአገርሽ ድረስ እንደገለፁት፤ የመከላከያ ሠራዊት የአልባሳት፣ የንጽህና መጠበቂያና ሌሎችንም ድጋፍ አድርጓል። የመከላከያ ሠራዊቱ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት በመሳተፍ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ተናግረዋል። የአገር መከላከያ ሠራዊት የአገርና የሕዝብ ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ ለአረጋውያንና ለአቅመ ደካሞች ያለውን በማካፈልና በልማት ሥራዎች በመሳተፍ የሕዝብ ልጅ መሆኑን እያስመሰከረ እንደሆነ ገልፀዋል። ሠራዊቱ በቀጣይ በሚችለው ሁሉ ለማኅበሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለጽ፤ ሌሎችም ለማኅበሩ ድጋፍ በማድረግ ወገናዊ አለኝታነታቸውን ማሳየት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። የመቄዶንያ በጎ አድራጎት ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት በማኅበሩ ታቅፈው የሚገኙ ወገኖችን በማሰብ የቁሳቁስ ድጋፍና ማዕድ በማጋራቱ አመስግነዋል። ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦች የመከላከያ ሠራዊቱን አርዓያ በመከተል ለማኅበሩ የሚችሉትን ሁሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ የልማት ሥራዎች ከቻይና ድርጅት ጋር በትብብር ለመሥራት ተፈራረመ
Aug 5, 2024 178
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ የልማት ሥራዎች በትብብር ለመስራት ከቻይናው ፋውንዴሽን ፎር ሩራል ዴቨሎፕመንት ጋር ሥምምነት ተፈራርሟል። ሥምምነቱን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) እና በኢትዮጵያ የፋውንዴሽኑ ዳይሬክተር ይን ቼን ፈርመውታል። የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)፤ ሥምምነቱ የተማሪዎች ምገባን ማስፋት፣ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፣ የሶላር ታዳሽ ኃይልን ተደራሽ ማድረግና የንፁህ መጠጥ ውኃ እንዲሁም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፎችን ያካተተ ነው ብለዋል። ፕሮጀክቶቹ ኅብረተሰቡን ከተረጂነት በማላቀቅ በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችሉ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የፋውንዴሽኑ ዳይሬክተር ይን ቼን በበኩላቸው ላለፉት አስር ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን ጠቁመዋል። ፋውንዴሽኑ በተጠቀሱት ዘርፎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።
የሠላም ሚኒስቴር በጎፋ ዞን በተከሰተው የመሬት መንሸራተት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ
Aug 5, 2024 146
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2016(ኢዜአ)፦ የሠላም ሚኒስቴር በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የ36 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ። በድጋፍ ርክክቡ ወቅት የሠላም ሚኒስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም በገዜ ጎፋ ወረዳ የተከሰተው የተፈጥሮ አደጋ እጅግ ልብ የሚሰብር በመሆኑ መላው የሀገራችን ህዝብ ማዘኑን ገልፀዋል። ከአሁን በኃላ ከሐዘን ድባብ በመውጣት በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበው መላው ኢትዮጵያውያን የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። ሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ሐዘኑን ከመግለፅ ባሻገር ተጎጂዎችን ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብ፣ ጥራጥሬ እና አልባሳት ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል። በተጨማሪም በጥሬ ገንዘብ ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ለሚደረገው ጥረት የ30 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ለማድረግም ቃል ገብቷል። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው በክልሉ ገዜ ጎፋ ወረዳ የህዝቡን ልብ የሠበረ አደጋ መከሰቱን ጠቁመው አደጋው ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሲያፅናና እና ሂደቱን በጥብቅ ሲከታተል መቆየቱን አስታውሰዋል። በአካል በመምጣት እና ድጋፍ በማድረግ ለህዝቡ ያላቸውን አጋርነት በመግለፃቸውም ርዕሰ መስተዳድሩ አመስግነዋል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እና ተጨማሪ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይፈጠር እንዲሁም የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የክልሉ መንግስት ከአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን እና ከፌደራል መንግስት ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል። በጊዜያዊ መጠለያ ለሚገኙ ተጎጂዎች አስቸኳይ ድጋፍ እየተደረገ ሲሆን ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ በሌላ ቦታ ለማስፈር የጥናት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አመላክተዋል። አሁን ላይ ከአስቸኳይ ድጋፍ ባሻገር ተጎጂዎችን ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት ሀብት የሚፈልግ በመሆኑ በቀጣይ ድጋፍ የሚያደረጉ እና መላው የሀገሪቱ ነዋሪዎች የገንዘብ፣ የቆርቆሮ እና የሚስማር ድጋፎች እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
አዲስ በተገነቡና ተጠግነው ለአገልግሎት በበቁ የውሀ ተቋማት ተጠቃሚ ሆነናል - የላዕላይ ማይጨው ወረዳ ነዋሪዎች
Aug 5, 2024 135
አክሱም ፤ ሐምሌ 29/2016 (ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል በላዕላይ ማይጨው ወረዳ አዲስ በተገነቡና ተጠግነው ለአገልግሎት በበቁ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋማት ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የውሃ ተቋማቱ ለአገልግሎት መብቃት ንፁህ የመጠጥ ውሃን በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ ከማገዙም በላይ ከተለያዩ ውሃ ወለድ በሽታዎች ተጋላጭነት እንደታደጋቸው ገልፀዋል። በላዕላይ ማይጨው ወረዳ ደብረቃል ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ ወይዘሮ ማዕሾ ተወልደብርሃን እንደተናገሩት፤ በቀበሌው ላለፉት 15 ዓመታት ሲያገለግል የነበረው በእጅ የሚሰራ የውሃ ጉድጓድ ለብልሽት በመዳረጉ ለችግር ተጋልጠው ቆይተዋል። ተበላሽቶ የቆየው የመጠጥ ውሃ ጉድጓድ ጥገና ተደርጎለት የተሟላ አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ገልጸዋል። በወረዳው የመዶገ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ነዋሪ አርሶ አደር ተክለወይኒ መውጫ በበኩላቸው፤ ለብልሽት ተዳርጎ የቆየው የውሃ ጉድጓድ ተጠግኖና በውሃ ኬሚካል ታክሞ ንፅህናው እንዲጠበቅ በመደረጉ ንፁህ የመጠጥ ውሃን በአቅራቢያችን በማግኘት ተጠቃሚ ሆነናል ብለዋል። ንጽህናው የተጠበቀ ውሃ በማግኘታቸውም ከውሃ ወለድ በሽታ ተጋላጭነት ነጻ መሆናቸውን ተናግረዋል። በቀበሌው ኩሒ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ውስጥ ለ500 አባወራዎችና እማወራዎች አገልግሎት የሚሰጥ የመጠጥ ውሃ ጉድጓድ በቂ ጥገና ተደርጎለት አገልግሎት መስጠት በመጀመሩ ንፅህናው የተጠበቀ ውሃ ተጠቃሚ ሆነናል' ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አወጣሽ ተክለአብ ናቸው። ጥገና የተደረገለትን የውሃ ጉድጓድ የአካባቢው ነዋሪ እንደሚጠብቀውና ሲበላሽም የመንግስት እጅ ሳይጠብቁ በራሳቸው ወጪ ለማሰራት በየወሩ ገንዘብ በማዋጣት በጋራ በተከፈተ የባንክ አካውንት እየቆጠቡ መሆኑን ገልፀዋል። የቀበሌው ነዋሪ ወጣት አርሶ አደር ተመስገን በየነ በበኩሉ፤ የተገነቡት የውሃ ተቋማት ከሁለት ኪሎ ሜትር በላይ በእግር ተጉዘን ንፅህናው ያልተጠበቀ ውሃ ከወራጅ ወንዝ ቀድቶ ከመጠቀም ገላግለውናል ብሏል። የቀበሌው ነዋሪዎች የተጠገኑና አዲስ የተሰሩ የውሃ ተቋማት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ተገቢውን ጥበቃ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጿል። በላዕላይ ማይጨው ወረዳ በ15 ገጠር ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የወረዳው አስተዳደር አመልክቷል። በወረዳው መስተዳደር የመጠጥ ውሃ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሙሉአለም መሰለ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በወረዳው በሚገኙ ቀበሌዎች ውስጥ የሚኖረውን ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ የውሃ ተቋማት ተገንብተዋል። ከአገልግሎት ውጪ ሆነው የቆዩ 243 በእጅ የሚሳቡ የውሃ ጉድጓዶች ጥገና ተደርጎላቸው ለአገልግሎት በቅተዋል ብለዋል። አዳዲስ በተገነቡና በተጠገኑ የውሃ ተቋማትም 210 ሺህ የሚሆን የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለም አስረድተዋል። ለተቋማቱ ግንባታና ጥገና ሥራ ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን፤ በአራት ት/ቤቶች ውስጥም አዲስ የከርሰ ምድር ውሃ ቁፋሮና በእጅ ድጋፍ የሚሰሩ የውሃ መሳቢያ መሳሪያዎች ተከላ መከናወኑንም ተናግረዋል። ከአገልግሎት ውጭ የነበሩትን የውሃ መሰረተ ልማት የመጠገንና አዲስ የመጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ በመካሄዱም የወረዳው የመጠጥ ውሃ ሽፋን ከነበረበት 54 ከመቶ ወደ 57 ከመቶ ከፍ እንዲል እንዳስቻለውም አመልክተዋል። በገጠር ቀበሌዎቹ የሚገኙ የመጠጥ ውሃ ተቋማትን የመንከባከብና የመጠበቁ ኃላፊነት የተጠቃሚው ህብረተሰብ በመሆኑ ተረክቦ እንዲያስተዳድረው ጭምር መሰጠቱን ገልፀዋል። ለዚህ ተግባር እንዲያግዝም ህዝቡ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ማዋጣቱንም ተናግረዋል።
በሸካ ዞን ከ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተገነባ ሆስፒታል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
Aug 4, 2024 195
ሚዛን ፤ ሐምሌ 28/2016(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሸካ ዞን ከ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ሆስፒታሉን መርቀው ከፍተዋል። ኢንጂነር ነጋሽ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የክልሉ መንግስት ካለው በጀት አብዛኛውን በማኅበረሰብ ተኮር ልማት ላይ በማዋል የልማት ጥያቄዎችን ለመመለሰ እየሠራ ነው። ዛሬ የተመረቀው የማሻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የዚሁ አንዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው ያልተሟሉ የውስጥ ግብዓቶችን በማሟላት የተቀላጠፈ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል። ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ሌሎች የልማት አውታሮችን ለመዘርጋት ክልሉ በቅርበት እንደሚሠራም አረጋግጠዋል። የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ሆስፒታሉ ከክልሉ መንግስት በተመደበ ከ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መገንባቱን አስታውቀዋል። በተጨማሪም ክልሉ ለሆስፒታሉ የትራንፎርመር ግዢ ሦስት ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉን ጠቁመዋል። ሆስፒታሉ በዞኑ ለሚገኙ ከ150 ሺህ ለሚልቁ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና ለአጎራባች ዞኖች ነዋሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥም አስረድተዋል። የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በበኩላቸው የሆስፒታሉ መገንባት የማሻ እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጥያቄ የመለሰ ነው ብለዋል። የማሻ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የግንባታ ሂደት በ2008 የተጀመረ ቢሆንም ሳይጠናቀቅ በመቋረጡ የሕዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱም በወቅቱ ተገልጿል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠል ይጠበቅበታል - ከንቲባ ከድር ጁሃር
Aug 4, 2024 232
ድሬዳዋ ፤ ሐምሌ 28/2016 (ኢዜአ)፡- የአስተዳደሩ ፖሊስ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ የጀመራቸውን አበረታች ተግባራት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር አሳሰቡ። የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለ14ኛ ጊዜ በሰላም ማስከበር የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ያሰለጠናቸውን ፖሊሶች ዛሬ አስመርቋል ። የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በስነ ስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት የስራ መመሪያ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ በአስተዳደሩ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ እንዲሰፍን አበረታች ተግባራት አከናውኗል ። የተገኙ ውጤቶችን አጠናክሮ በመቀጠልና ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን በመጠበቅ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እውን እንዲሆን ኃላፊነቱን በትጋት እንዲወጣ አሳስበዋል። ተመራቂ ፖሊሶችም በቀሰሙት ሙያዊ ዕውቀት በመታገዝ የህዝብን ሰላምና ፀጥታ በማስጠበቅ ሃላፊነታቸውን በትጋት እንዲወጡ አስገንዝበዋል ። ለስልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ላደረገው በሰላም ማስከበር የሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ምስጋና አቅርበዋል ። የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ በበኩላቸው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ፖሊስ የሚመራበትን ዶክትሪን በመንደፍ የተከናወኑ የሰላምና የፀጥታ ማስፈን ስራዎች አበረታች ውጤቶች አስገኝተዋል ብለዋል። ፖሊስ በተገበረው ሪፎርም በዘመናዊ አሠራርና አደረጃጀት እንዲሁም በቴክኖሎጂ የታገዙ ስራዎች ማከናወኑን ጠቅሰው እነዚህ ተግባራት የድሬዳዋ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከልነት እንዲረጋገጥ መሠረታዊ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን አመልክተዋል። የህግ የበላይነትን፤ የህዝብን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ መንገድ ለማስከበር የተጀመሩ አበረታች የለውጥ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል ። ተመራቂ ፖሊሶች የተጀመሩትን ውጤታማ ስራዎች ወደ ላቀ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግሩም አስታውቀዋል። የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እተጋለሁ ያሉት ደግሞ በላቀ ውጤት የተመረቁት ኮንስታብል ሳምሶን እሼቱ ናቸው ። የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፈቲህያ አደን ፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ለስልጠናው መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱት ተቋማትና ግለሰቦች የተዘጋጀውን ሽልማትና ምስክር ወረቀት አበርክተዋል። በስነ ስርዓቱ ላይ በሰላም ማስከበር የሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ፣ ወታደራዊ መኮንኖች፣ የኃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ፣ ዑጋዞችና አባገዳዎች እንዲሁም የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል ።
ክረምቱ ለሰዎች አለን የምንልበትና በጎ ነገር የምንሰራበት መሆን አለበት - ዶክተር መቅደስ ዳባ
Aug 4, 2024 213
አሶሳ፣ ሐምሌ 28/2016 (ኢዜአ)፦ የክረምቱ ወራት ለሰዎች አለን የምንልበትና በጎ ነገር የምንሰራበት መሆን አለበት ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ አስታወቁ። ዛሬ በአሶሳ ተገኝተው የበጎ ፈቃድ ሥራውን ያስጀመሩት የጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት አመራርና ሠራተኞች በክልሉ ከ25 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተመላክቷል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ በደም ልገሳ፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ነፃ ምርመራ፣ የቤት እድሳት እና በአረንጓዴ አሻራ እንደሚተገበርም ሚንስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናግረዋል። ሚኒስቴሩ ከዚሁ ጎን ለጎን 500 ለሚሆኑ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍም አድርጓል። የጤና ሚኒስቴር እና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የአመራር አባላቱ የአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል የአገልግሎት አሰጣት ሂደትንም ጎብኝተዋል። ሚኒስቴሩ በክልሉ የጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሻሻል ድጋፍ እንደሚያደርግም ዶክተር መቅደስ ገልጸዋል። ይህንን አብነት ወስዶ ሎሎቹም የበጎ ፈቃድ ሥራውን ማጠናከር እንዳለባቸው ያስታወቁት ሚኒስትሯ፤ በተለይም የክረምቱ ወራት ለሰዎች አለን የምንልበትና በጎ ነገር የምንሰራበት መሆን አለበት ብለዋል። የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻዲሊ ሐሰን ሚኒስቴሩ ባለፉት ዓመታት የጤና ተቋማትን መልሶ ለማደራጀት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል። የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ወልተጂ በጋሎ በበኩላቸው የተጀመረውን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለማስቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎቹ በአሶሳ አጠቃላይ ሆስፒታል የድንገተኛ ህክምና መስጫ ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጡ ሲሆን፤ በሆስፒታሉ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።
ለማሻ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ
Aug 4, 2024 170
ሚዛን አማን፤ ሐምሌ 28/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሸካ ዞን ከ400 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት ለሚገነባው የማሻ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ። የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ፕሮጀክቱን የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ናቸው። በመርሃ ግብሩ ወቅት የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው እንደተናገሩት፤ የውሃ ፕሮጀክቱ ግንባታ በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ሲጠናቀቅ 46 ሺህ ህዝብን ተጠቃሚ ያደርጋል። ከዋን ዋሽ ጋር በመተባበር ለሚሠራው የውሃ ፕሮጀክት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙን ጠቅሰው ፕሮጀክቱን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀዋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ፀጋዬ ማሞን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
ኮሌጁ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የሰለጠነ የሰው ሃይል ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ ነው
Aug 4, 2024 184
ጎንደር፤ ሐምሌ 28/2016(ኢዜአ)፦ የጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ክህሎት መር የስልጠና ስትራቴጂን በመከተል የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የሰለጠነ የሰው ሃይል ፍላጎት ለማሟላት እየሰራ መሆኑን ገለፀ፡፡ ኮሌጁ በ10 የሙያ ዘርፎች ከደረጃ አንድ እስከ አምስት ያሰለጠናቸውን 822 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡ የኮሌጁ ዲን አቶ ተስፋሁን መኮንን እንደተናገሩት፤ ኮሌጁ የአምራች ኢንዱስትሪውን የሰው ሃይል ፍላጎት በማጥናት በእውቀትና በክህሎት የበቁ ባለሙያዎችን በማፍራት ለዘርፉ እድገት አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡ ኮሌጁ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት በማጠናከርና በጥናት ላይ የተመሰረተ ክህሎት መር የስልጠና ስትራቴጂን በመተግበር የዘርፉን የሰው ሃይል ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ለማሟላት የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የቴክኖሎጂ ሸግግር ለማሳለጥም በዘርፉ የላቀ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸውን የሰለጠኑ ባለሙያዎች በማፍራት የልህቀት ማዕከል ለመሆን የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡ በ12 ሚሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ ወርክሾፖችን ከማቋቋም ጀምሮ የካይዘን ፍልስፍናን በመተግበር የቴክኖሎጂ ዕድገት የሚያፋጥን የሰልጣኞች የምዘና ስርዓት በማዘጋጀት እየተገበረ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የአገልግሎት ዘርፉን የሰው ሃይል ፍላጎት ለማሳካትም 3ሺ ለሚጠጉ ስራ ፈላጊዎች አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት የስራ እድል ትስስር እንዲፈጠርላቸው ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ በዛሬው ዕለት ለምረቃ ከበቁት መካከልም 322ቱ ሴቶች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ሁሉም ተመራቂዎች የስራ ብቃት ምዘና ወስደው በአጥጋቢ ውጤት ያለፉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ሁንዓለም አሻግሬ በበኩላቸው፤ ተመራቂዎች በቀሰሙት ሙያ ስራ ፈጣሪ በመሆን ሀገርና ህዝብን ለማገልገል ራሳቸውን ከወዲሁ ሊያዘጋጁ ይገባል ብለዋል፡፡ የሙያ ባለቤት መሆን የወጣቶች የመጀመሪያው የህይወት ምዕራፍ መሸጋገሪያ ድልድይ መሆኑን ጠቁመው፤ ተመራቂዎች በሰለጠኑበት ሙያ ስራ ፈጥረው ራሳቸውንና ሀገራቸውን በሚጠቅም ስራ እንዲሰማሩ የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍ እንደማይለያቸው ገልጸዋል፡፡ በሰው ሰራሽ አስተውሎት ሀገራችን የጀመረችውን የቴክኖሎጂ መርሃ ግብር ለመቀላቀል ጽኑ ፍላጎት አለኝ ያለው በኤሌክትሮኒክስ የሙያ ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነው ተመራቂ አማረ ጌታነህ ነው፡፡ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ የሆነችው ሌላኛዋ ተመራቂ በለጡ ሙሉዓለም በበኩሏ፤ መንግስት ከተሞችን ዘመናዊ ጽዱና አረንጓዴ ለማድረግ የጀመረውን ንቅናቄ በሰለጠነችበት የቅየሳ ሙያ ለማገልገል ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች፡፡ የጎንደር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በአሁኑ ወቅት በመጀመሪያና በመካከለኛ ደረጃ የሙያ ስልጠና ዘርፍ ከ3 ሺ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏል፡፡
የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለ14ተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ፖሊሶች እያስመረቀ ነው
Aug 4, 2024 153
ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 28/2016 (ኢዜአ)፡- የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለ14ተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን ፖሊሶች በሁርሶ የኮንቲንጀንት ወታደራዊ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት እያስመረቀ ነው። ተመራቂዎች የፖሊሲነት ሙያን በንድፈ ሀሳብና በተግባር በብቃት አጠናቀው መመረቃቸው በስነስርዓቱ ላይ ተገልጿል ። ለስልጠናው ስኬታማነት የሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አመራሮች ፣ መኮንኖችና ሠራተኞች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውም ታውቋል። በምረቃው ስነስርዓት ላይ የድሬደዋ አስተዳደር ምክርቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፈቲህያ አደን፣ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፣ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአስተዳደሩ ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ተገኝተዋል። የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ፣ የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት አዛዥ ኮሎኔል አዲሱ ተርፋሳ፣ መኮንኖችና የተመራቂ ቤተሰቦችም ተገኝተዋል። በተጨማሪም የአገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ተሳታፊ ሆነዋል። በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተመራቂዎች በስልጠናቸው ወቅት የቀሰሙትን የፖሊስነት ሙያና ምግባር በተለያዩ ትርኢቶች ለታዳሚዎች አሳይተዋል።
በአማራ ልማት ማህበር (አልማ) የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቁ
Aug 3, 2024 178
ደሴ ፤ ሐምሌ 27/ 2016 (ኢዜአ)፡-በደቡብ ወሎ ዞንና አካባቢው በአማራ ልማት ማህበር (አልማ) የተገነቡ 21 የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን በማህበሩ የደቡብ ወሎ ዞንና አካባቢው ማስተባበሪ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አበባው ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ አልማ የመንግስትን የልማት እንቅስቃሴ በመደገፍ እያገዘ ሲሆን፤ በዚህም ህዝብን ተጠቃሚ በሚያደርጉና ቅድሚያ በሚሰጣቸው ፕሮጀክቶች ላይ አተኩሮ እየሰራ ይገኛል። ማህበሩ ነባርና አዳዲስ አባላትን እንዲሁም የልማት አጋሮችን ጭምር በማስተባበር መንግስት ከሚሰራቸው የልማት ሥራዎች ጎን ለጎን የልማት ክፍተቶችን ለይቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ የትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራትንና የጤና አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። ፡ በዚህም 63 የትምህርትና የጤና የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ ውስጥ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ69 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነቡ 21 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት ክፍት መሆናቸውን አስታውቀዋል። ለአገልግሎት ከበቁት መካከል 14ቱ የአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደረጃ ማሻሻያና ማስፋፊያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ቀሪዎቹም የአንድ አዲስ ጤና ጣቢያ ግንባታ፣ የስድስት ጤና ጣቢያዎች ደረጃ ማሻሻያና ማስፋፊያዎች ናቸው ብለዋል፡፡ የተጠናቀቁት ፕሮጀክቶች ከ158 ሺህ በላይ ህዝብ ተጠቃሚ ያደርጋሉ ያሉት ኃላፊው፤ ቀሪ ፕሮጀክቶችንም በ2017 በጀት ዓመት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በደሴ ዙሪያ ወረዳ የቀበሌ 01 ነዋሪ አቶ ሀሰን አልይ በሰጡት አስተያየት፤ በአካባቢያቸው ያለው አንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከደረጃ በታች በመሆኑ በልጆቻቸው ትምህርት ላይ ጫና አሳድሮ መቆየቱን ገልጸዋል። ዘንድሮ በአልማ በተገነባ ባለ አንድ ወለል ህንጻ ግንባታ የትምህርት ቤቱ ደረጃ በመሻሻሉ ለመማር ማስተማር ስራው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል። ሌላው የቃሉ ወረዳ 023 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሁሴን እሸቱ እንዳሉት፤ አልማ በየአካባቢያቸው የሚገኘውን ትምህርት ቤት ደረጃ በማሻሻል ልጆቻቸው በተሻለ ትምህርት ቤት እንዲማሩ አመቻችቷል። ''እኛም በጉልበታችንና በገንዘባችን የድርሻችንን ተሳትፎ አድርገናል'' ብለዋል። በማህበሩ የደቡብ ወሎና አካባቢው ማስተባበሪያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ370 ሺህ ከሚበልጡ አባላት ከ111 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ከማስተባባሪያው ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ብሄረሰብ አስተዳደሩ ከ48 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከወባ በሽታ ለመጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል
Aug 3, 2024 198
ሰቆጣ፤ ሐምሌ 27/2016 (ኢዜአ)፡- በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከ48 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከወባ በሽታ ለመጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን የብሄረሰብ የአስተዳደሩ ጤና መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው የወባ መከላከልና መቆጣጠር ባለሙያ አቶ አበበ በለጠ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በብሄረሰብ አስተዳደሩ የወባ በሽታን የወባ መከላከልና ቁጥጥር ስራ ሲከናወን ቆይቷል። በዚህም ለወባ በሽታ ተጋላጭ በሆኑ ሰሃላ፣ ዝቋላና አበርገሌ ወረዳዎች በሚገኙ 25 ቀበሌዎች ከሰኔ 23 እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የፀረ ወባ ትንኝ መከላከያ ኬሚካል ርጭት መደረጉን ተናግረዋል። በዚህም 14 ሺህ 420 ቤቶች ላይ የፀረ ወባ ኬሚካል መርጨቱን አመልክተው፤ በተጨማሪም በጤና ሚኒስቴር በኩል 36 ሺህ 111 የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ቀርቦ መሰራጨቱን አስታውቀዋል። በተከናወኑት የመከለካል ስራዎች ከ48 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከወባ በሽታ እንዲጠበቁ መደረጉን አስረድተዋል። ህብረተሰቡም የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር በአግባቡ ሊጠቀም እንደሚገባና የወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ ሁኔታ ከሚፈጥሩ ስፍራዎችን የማዳፈን ስራ ማከናወን እንዳለበት አሳስበዋል። የዝቋላ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የጤና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ እስጢፋኖስ ወንዳየ እንዳሉት፤ የወባ ስግጭቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወረዳው ሦስት ቀበሌዎች ላይ የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት ከመደረጉም ባለፈ 22 ሺህ አጎበር ቀርቧል። በዚህም 2 ሺህ 556 ቤቶች ላይ ርጭት መደረጉን ገልፀው፤ የወባ መራቢያ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ቦታዎችን የማዳፈን ስራ የክረምት በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ እየተሰራ ነው ብለዋል። በወረዳው 01 ቀበሌ ነዋሪ አቶ መኳንንቴ ገብሩ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፉት የበጋ ወራት በአካባቢያቸው የወባ በሽታ ስርጭት ስጋት ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል። በአካባቢያቸው የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት መደረጉ ደግሞ የክረምት ወራትን ከወባ በሽታ ያለ ስጋት እንዲያሳልፉ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። ''በአካባቢያቸው ለወባ ትንኝ መራቢያ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ ቦታዎችን የማዳፈን ስራ እየሰራን ነው'' ብለዋል።
ምክር ቤቱ በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት የተጎዱ ወገኖች በዘላቂነት ለማቋቋም ድጋፉን እንደሚያጠናክር አስታወቀ
Aug 3, 2024 171
ሳውላ፤ ሐምሌ 27/2016 (ኢዜአ)፡- የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በዘላቂነት ለማቋቋም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ። ምክር ቤቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በቦታው ተገኝቶ በማጽናናት የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡ ድጋፉን ያስረከቡት የምክር ቤቱ አባልና የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ ኮሬ፤ በገዜ ጎፋ ወረዳ በተከሰተው አደጋ በደረሰው ጉዳት ምክር ቤቱ ማዘኑን ገልጸዋል። የደረሰው አደጋ እጅግ ከባድና ልብ የሚሰብር ነው ያሉት ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ ፤ ምክር ቤቱ በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውል የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ መስጠቱን አስታውቀዋል። በአደጋው የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም ምክር ቤቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማሃዲ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ምክር ቤቱ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ የተሰማውን ሀዘን ሲገልጽ መቆየቱንና ተጎጂዎችን ለማጽናናት በስፍራው መገኘታቸውን ተናግረዋል። ከፌዴራል መንግስት ጀምሮ መላው ኢትዮጵያውያን ባለን የመረዳዳት ባህልና እሴት መሰረት ለወገን ደራሽ መሆናቸውን በስፍራው እየተደረገ ያለውን ሰብዓዊ ድጋፍ ማየት ችለናል ብለዋል። በአደጋው ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች፣ ህጻናት አካል ጉዳተኞችና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካላት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል። የምክር ቤት አባላት በእረፍት ላይ በመሆናቸው እንጂ በአካል እዚህ ተገኝተው ሀዘናቸውን መግለጽ እንደሚፈልጉ የተናገሩት ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአባላት ተሳትፎ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ባንጉ ናቸው። አባላቱ ለወገናቸው ደራሽ መሆናቸውን ለመግለጽ ካሉበት ሆነው 340 ሺህ ብር በማዋጣት ለተጎዱ ወገኖች እንዲደርስ መላካቸውን ገልጸዋል። የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ከረዩ ባናታ በበኩላቸው፤ የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት እስከታችኛው ባለሙያ ድረስ አደጋውን ከሰሙበት ጊዜ አንስቶ ተጎጂዎችን ለመደገፍ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ክልሉና ዞኑ የተጎዱ ወገኖችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያከናውኑትን ስራ በመደገፍ እንደሚሰራም ተናግረዋል። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጅነር ዳግማዊ አየለ ድጋፉን ከተረከቡ በኋላ እንዳሉት፤ አደጋው ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ መላው ኢትዮጵያውያን ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ በስፍራው በመገኘት ላደረገው ድጋፍ በተጎጂዎቹ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ትውልድ የመገንባት ሚናን እየተወጣ ያለ ተቋም ነው
Aug 3, 2024 179
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአገሪቱ ሁለንተናዊ ታሪክ፣ እድገትና ትውልድ የመቅረጽ ጉልህ ሚና የነበረውና ይህን አጠናክሮ እየቀጠለ ያለ ተቋም እንደሆነ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ ገለጹ። የልጆችን የንባብ ባህል ለማዳበር ከዲጂታል ዓለም በተጨማሪ በወረቀት፣ ብራናና በሌሎች የተጻፉ ጽሑፎችን እንዲያነቡ ማድረግ ይገባል ያሉት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ናቸው። በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተዘጋጀ "ብላቴናት" የተሰኘ ባለቀለም የልጆች መጽሔት ዛሬ ተመርቋል። በመጽሔት ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ ሚኒስትሮች፣ የመገናኛ ብዙኃን አመራሮች፣ ደራሲያን፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መሀመድ እድሪስ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የእድሜውን ያህል አንጋፋና ጥበብ የተሸከመ የታሪክ ማኅደር የሆነ ተቋም ነው። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ እድገት እንዲሁም ብዝኃነታችን ለአንድነታችን መሠረት መሆኑን ያበሰረ ተቋም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ አገር ለመገንባት የሚያስችሉ ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱንም አንስተዋል። ተቋሙ የጀመረው ሥራ ለአገር የሚመጥን ትውልድ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑንም ነው የተናገሩት። ሌሎችም የተቋሙን አርዓያነት በመከተል ቀላል በሆነ መንገድ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የተለያዩ ሕትመቶች ለልጆች ተደራሽ ማድረግ አለባቸው ብለዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አባል ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ላለፉት ሺህ ዘመናት የመላው ዓለም እውቀት የተከማቸው በጽሑፍ በመሆኑ የዲጂታል ዓለሙን ከንባብ ባህል ጋር ማስተሳሰር ያስፈልጋል ብለዋል። ልጆች የንባብ ባህልን ካላዳበሩ ዓለም ካከማቻቸው እውቀት የተለዩ ስለሚሆኑ ወላጆች፣ መገናኛ ብዙኃን ልጆችን ከወረቀት ጋር ማቀራረብ እንዳለባቸው ተናግረዋል። የዲጂታል ቴክኖሎጂ አንድን ነገር በፍጥነት ለማግኘት እንዲሁም ከጽህፈት ጋር የተገናኘ ጥበብ የማስታወስ ችሎታን ለማሳደግ የሚጠቅሙ በመሆኑ ልጆች ሁለቱን አቀናጅተው እንዲሄዱ ማድረግ ይገባል ሲሉም አክለዋል። የንባብ ባህልን ለማሳደግ ልጆች በሚውሉበት ሥፍራ ጽሑፎችን ማስቀመጥ አስፈላጊ እንደሆነ አንስተው፤ ለዚህም ከወላጆች ጀምሮ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ መሳፍንት ተፈራ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ላለፉት ስምንት አሥርት ዓመታት አገርን ሲገነባና ትውልድ ሲያንጽ መቆየቱን አንስተዋል። በ83 ዓመት ጉዞው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በየሳምንቱ በልጆች አምድ አስተማሪ ይዘቶች ሲያቀርብ እንደቆየ ተናግረው፤ አገር ተረካቢ ህፃናት የሕትመት ሚዲያ እንዲኖራቸው "ብላቴናን" ለማሳተም መብቃቱን ተናግረዋል። መጽሔቱ በትምህርት ቤቶችና በሕዝብ ቤተ-መጽሐፍት አማካኝነት የሚሰራጭ ሲሆን፤ በአዟሪዎች ማግኘት የሚቻል መሆኑንም ገልፀዋል። ልጆች እየተዝናኑ እውቀት የሚገበዩበት፣ ስለአገራቸው ወጥ አረዳድ እንዲኖራቸው፣ በስነ-ምግባር እንዲታነፁና አንባቢ ትውልድ ለመፍጠር አቅም የሚፈጥሩበት መጽሔት መሆኑን ተናግረዋል። የይዘት ዝግጅቱ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች፣ በስነ-ጽሑፍ ባለሙያዎችና ሰዓሊያን የሚሳተፉበትና በቀጣይ ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ በሌሎች ቋንቋዎች ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል። የቅድመ መደበኛ መምህርት የሆነችው መምህርት ዙፋን ታምር እና የልጆች ፕሮግራም አዘጋጅና የልጆች መጽሐፍ ደራሲ አስረስ በቀለ በበኩላቸው፤ መጽሔቱ የልጆችን የንባብ ባህል ለማሳደግ የሚረዳ ነው። የ10ኛ ክፍል ተማሪዋ መልዕክተ ኃይሉ እና የስድስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ሜሮን ሀብታሙ መጽሔቱ በቀለማት የተዋበ ሆኖ መምጣቱ ንባብን የሚያበረታታ መሆኑን አንስተው፤ ሌሎችም በመሰል ተግባር በመሰማራት ትውልዱ በትክክለኛው መንገድ እንዲጓዝ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። "ብላቴናት" በመላ ሀገሪቱ የሚሰራጭ፣ በቀጣይ ኢትዮጵያውያን በብዛት በሚኖሩባቸው አገራት ተደራሽ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን፤ አምዶችን በመከፋፈል ከ3 እስከ 9 ዓመት በላይ የሚሆኑ ልጆችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑም ተገልጿል።