አካባቢ ጥበቃ
የተፋሰስ ልማት የግብርና ልማት ስራቸውን ያቃናላቸው የሁለቱ ዞኖች አርሶ አደሮች
Jan 31, 2025 171
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የልማት አማራጮችን በማስፋት ተጠቃሚነትን እንዳሳደገላቸው ኢዜአ ያነጋገራቸው የካፋ እና ምዕራብ ሀረርጌ ዞኖች አርዞ አደሮች ገለጹ። በካፋ ዞን ሺሾ-እንዴ ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ወልደየስ ወልደማሪያምና በቀለ ወልደገብርኤል የእርሻ መሬት ለማስፋፋትና በተለያዩ ምክንያቶች የአካባቢ መራቆት በመከሰቱ የግብርና ምርታማነታቸው ቀንሶ እንደነበር አስታውሰዋል። ​ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራዎች ግን የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙና የአፈር ለምነት እንዲመለስ በማስቻላቸው በአትክልፍትፋ ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም በእንስሳት መኖ በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። ​   በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚና መሰረተ ልማት ዘርፍ አማካሪ (ዶ/ር) ኢንጂነር ምትኩ በድሩ ባለፉት ሦስት ዓመታት በስነ ህይወታዊና አካላዊ ስራዎች የተገኙ አበረታች ውጤቶችን ማስቀጠል ዘንድሮም የተፋሰስ ልማት ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል። በዘንድሮው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በ1 ሺህ 100 ንዑስ ተፋሰሶች ከ225 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማ ተገልጿል። ​ በኦሮሚያ ክልል የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ጭሮ ወረዳ አርሶ አደሮች በማህበር ተደራጅተው በአካባቢያቸው የሚገኝ ደን በመንከባከብና በመጠበቅ ከእንሰሳት መኖና በንብ ማነብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል። ​ አርሶ አደር አቡሌ መሀመድ አሊና ርሶ አደር አደም መሀመድ በማህበር ተደራጅተው በደን ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች በንብ ማነብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጸው፤ በደን ውስጥ መኖ በማልማት ለእንስሳቶቻቸው በቂ መኖ ማግኘት መቻላቸውን አአረጋገጠዋል። በኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ድርጅት የሐረርጌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ፋኪያ ጀማል እንዳሉት በምዕራብና ምስራቅ ሀረርጌ ዞኖች በአሳታፊ የደን ጥበቃና እንክብካቤ ከ2 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በ25 ማህበራት ታቅፈው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ​ ህብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት ለደን ጥበቃ ማድረግ ከጀመረ ወዲህ በደን ላይ የሚደርስ ጉዳት ቀመቀነሱን ገልጸው ህብረተሰቡ ደኑን በመጠበቅ በውስጡ የእንስሳት መኖ እና ንብ በማነብ እንዲሁም ከደን ውጤቶች ሽያጭ ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የምዕራብ ሐረርጌ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መገርሳ ዴሬሳ በዞኑ የግብርና እንሼቲቮችን ተግባራዊ በማድረግ እና ያልታረሱ መሬቶችን በማልማት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተከናወኑት ተግባራት ውጤታማ ሆነዋል በዞኑ 15 ወረዳዎች ለልማቱ ሲውሉ ያልነበሩና በበጋው የተፋሰስ ልማት የአፈር መሸርሸር የሚከላከሉ እርከኖች የተሰሩባቸው መሬቶች ለምነታቸው እየጨመረ በመምጣቱ አርሶ አደሩ ለልማቱ እንዲያውል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በአጠቃላይ በመኸር ወቅቱ ከ559 ሺህ 343 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ የአገዳ፣ ብርዕ እና ቅባት ሰብሎች መልማቱን ገልጸው ይህም ከቀዳሚው አመት ከ159 ሺህ ሄክታር በላይ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ ተግባራትን እናከናውናለን-የቤንች ሸኮ ዞን አርሶ አደሮች
Jan 30, 2025 69
ሚዛን አማን፤ጥር 22/2017 (ኢዜአ)፦በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትን እንደሚያከናውኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የቤንች ሸኮ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ። በዞኑ ባሉ ሁሉም መዋቅሮች የዘንድሮ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ሥራ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል። እንደ ዞን በሸይ ቤንች ወረዳ ማዝ ቀበሌ በተጀመረው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ላይ የተሳተፉት አርሶ አደር ታደሰ ኮኒ፥ መሬት ለምነቱን ሲያጣ መርታማነቱ እንደሚቀንስ ገልጸዋል። ይህን ለመከላከል የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በየዓመቱ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። የተፋሰስ ልማት በተከናወነባቸው አካባቢዎች ሙዝ፣ የመኖ ሣር እና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በመትከል ተጠቃሚ ለመሆን ጠንክረው እንደሚሰሩም ጠቅሰዋል። በተፋሰስ በሚለሙ አካባቢዎች የፍራፍሬ ችግኞችን መትከል የተራቆተ ቦታ ፈጥኖ እንዲያገግም ያደርጋል ያሉት ደግሞ አቶ በላይ ወልደየስ የተባሉ አርሶ አደር ናቸው። ከዚህ ቀደም በአካባቢው በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተሻለ ለውጥ ማምጣታቸውን ገልጸው፥ በየዓመቱ ተግባሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ዘንድሮ የተፋሰስ ልማት በሚሰራባቸው ዳገታማ ቦታዎች ሸንኮራ አገዳና ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ ሌሎች ችግኞችን ለመትከል መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል። በተፈጥሮ ሀብት ልማት ሥራው በግብርና ባለሙያዎች ምክረሀሳብ መሰረት ምርታማነትን የሚጨምሩና ገበያን ለማረጋጋት የሚያስችሉ የግብርና ሥራዎችን መሥራት ከሁላችንም ይጠበቃል ወይዘሮ ጣይቱ ሙሉጌታ የተባሉ ሌላዋ የተፋሰስ ልማት ሥራው ተሳታፊ ናቸው። የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና፣አካባቢ ጥበቃና ኅብረት ሥራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ በዞኑ በ34 ሺህ 480 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ተግባር እንደሚከናወን ገልጸዋል። ለዚህም በ96 ንዑስ ተፋሰሶች ላይ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ዛሬ በሁሉም መዋቅሮች ወደ ተግባር ተገብቷል ብለዋል። በለሙ ተፋሰሶች የፍራፍሬ ችግኝ በስፋት በመትከል አርሶ አደሩ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን መምሪያው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አስገንዝበዋል። የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መንገሻ የተፋሰስ ልማቱን በይፋ ሲያስጀምሩ እንደገለጹት፣የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ ሰውና እንስሳትን ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያድርግ ነው። የመሬት ለምነትን ለመጠበቅና የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው የተቀናጀ አፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ የደን ሽፋኑን ከማሳደግ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል - የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ
Jan 30, 2025 68
አዳማ፤ ጥር 22/2017(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አምስት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራ የደን ሽፋኑን ከማሳደግ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዘርፍ ምክትል ሃላፊ አቶ ኢሊያስ ከድር ለኢዜአ እንደገለጹት የተፈጥሮ ሀብትን በማልማት ለትውልድ ለማስተላፍ እየተሰራ ነው። በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት የክልሉ የተፋሰስና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራዎች ለግብርናው ምርታማነትና ለአካበቢ ስነ-ምህዳር መጠበቅ ወሳኝ ሚና እያበረከቱ ይገኛሉ ብለዋል። ይህም በመሆኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማት ስራው በክልሉ መንግስት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተመራ መሆኑንም አስረድተዋል። በተፈጥሮ ሀብት ልማት በአምስት ዓመታት ውስጥ ከተተከሉት የተለያዩ ዝርያ ያላቸው ችግኞች የጽድቀት ምጣኔያቸው የተሻለ መሆኑንም ተናግረዋል። ይህም የደን ሽፋኑን ቀደም ሲል ከነበረበት 17 በመቶ ወደ 27 ነጥብ 6 በመቶ ማሳደጉን ተናግረዋል። የተፈጥሮ ሀብት ልማቱ የደረቁ ወንዞች፣ ጅረቶችና ሃይቆችን ከመመለስ ባለፈ በድርቅ ተጋላጭ የነበሩ የክልሉ አካባቢዎች በእንስሳት መኖ እንዲያከማቹ ማገዙን አስረድተዋል። የተፋሰስ ልማቱ ምርታማነትን ከመጨመር ባለፈ በንብ ማነብ፣ በመኖ አቅርቦትና በተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ የስራ ፈጠራ እድልን እየፈጠረ መሆኑን ጠቅሰዋል። በዚህ አመትም ለ60 ቀናት የተፋሰስ ልማት ስራን ለማካሄድ መታቀዱንና ህዝቡ ለዚሁ ስራ በጉልበቱና በእውቀቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦም በገንዘብ ሲተመን ትልቅ መሆኑን አክለዋል። ዘንድሮ በ6 ሺህ 495 ተፋሰሶች ላይ በ3 ነጥብ 3 ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ እቀባ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል። ከተያዘው የጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ እየተከናወነ ያለው የተፋሰስ ልማቱ ስራ ሳይንስዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዲከናወን አመራሩና ባለሙያዎች እገዛ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ አድርገዋል - ኢንጂነር ምትኩ በድሩ(ዶ/ር)
Jan 30, 2025 78
ሺሾ-እንዴ፤ ጥር 22/2017(ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረጋቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚ አማካሪ ኢንጂነር ምትኩ በድሩ(ዶ/ር) ተናገሩ። በክልሉ የ"አፈር ሀብታችን ለብልጽግናችን" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው የዘንድሮው የበጋ ወቅት የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በካፋ ዞን ሺሾ እንዴ ወረዳ ተጀምሯል።   መርሃ ግብሩን ዛሬ በይፋ ያስጀመሩት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የኢኮኖሚ አማካሪ ኢንጂነር ምትኩ በድሩ(ዶ/ር) በክልሉ የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅና መንከባከብ የቆየ ልምድ አለ። ባለፉት ዓመታት ከ1 ሚሊዮን 745 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ በ1 ሺህ 64 ንዑስ ተፋሰሶች ላይ 185 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ማልማት መቻሉን ገልፀዋል። በለሙ አካባቢዎችም ከ28ሺህ 700 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች በመደበኛና በፕሮጀክቶች ወደ ስራ ገብተው እየተጠቀሙ መሆናቸውን ተናግረዋል። ለ45 ቀናት በሚቆየው በዚህ የተፋሰስ ልማት ያረጁ ቡናዎችን የመጎንደል፣ የጉድጓድ ዝግጅት፣ የእርከንና ሌሎች ሥነ አካላዊ ሥራዎች እንደሚከናወኑም ተመላክቷል።
በአካባቢያችን የተከናወነ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተጎዳ መሬት እንዲያገግም አስችሏል-የዞኑ አርሶ አደሮች
Jan 30, 2025 69
ጂንካ ፤ ጥር 22/2017 (ኢዜአ)፡-በአካባቢያቸው በተከናወነ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተጎዳ መሬት አገግሞ ምርት እየሰጠ መሆኑን የአሪ ዞን አርሶ አደሮች ገለፁ። በአሪ ዞን ባሉ ሁሉም የወረዳና የከተማ አስተዳደር መዋቅሮች የ2017 ዓ.ም የተፋሰስ ልማት ንቅናቄ በስፋት እየተከናወነ ነው። በዞኑ የሰሜን አሪ ወረዳ የሻማ ቡልቀት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሀሳቡ ዓለማ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአካባቢው የተፋሰስ ልማት ሥራ በስፋት መከናወኑን ተናግረዋል።   ሁሉም በንቃት በመሳተፍ በተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተጎዱና ምርት መስጠት የማይችሉ የእርሻ ማሳዎች አገግመው ምርት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል። አካባቢያቸው ተዳፋት በመሆኑ ከዚህ ቀደም የአፈር መንሸራተት እና የጎርፍ አደጋ ስጋት እንደነበረባቸው አስታውሰው፣ በተለይም ክረምት ሲመጣ የአደጋ ስጋቱ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል። ባለፉት ሦስት ዓመታት በአካባቢው በተፋሰስ ልማት በተሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የጎርፍና የአፈር መንሸራተት አደጋን መከላከል እንደተቻለም አመልክተዋል። "የተፋሰስ ሥራው ከዚህ ቀደም በጎርፍ ይታጠብ የነበረን ለም አፈር አስቀርቷል" ያሉት ደግሞ በወረዳው የገሊላ ዙሪያ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሀብታሙ ባህሩ ናቸው። ቀደም ሲል በአካባቢው የደን መመናመን፣ የምንጮች መድረቅና የእርሻ ማሳዎች ለምነት ማጣት ችግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል። እንደ አርሶ አደር ሀብታሙ ገለጻ፣ ባለፉት ዓመታት በህብረተሰቡ ተሳትፎ በአካባቢው በተሰሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች እነዚህ ችግሮች እየተፈቱ መጥተዋል። የተፋሰስ ልማቱ ካስገኘላቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅም አንጻር ዘንድሮውም ልማቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።   የአሪ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታፈሰ ተስፋዬ፤ ከዚህ ቀደም በዞኑ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ባመጡት ተጨባጭ ውጤት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ መሆኑን ነው የተናገሩት። ልማቱን አጠናክሮ ለማስቀጠልም በዘንድሮ ዓመት ህብረተሰቡን በማሳተፍ በ105 ንዑስ ተፋሰሶች ከ23 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፍርና ውሃ ልማትና ጥበቃ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል። በተጨማሪም በዞኑ በሚገኙ አራት ወረዳዎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች በእያንዳንዳቸው አንድ ተራራ ለማልማት መታቀዱን አስታውቀዋል።  
በብሔራዊ ፓርኩ የሚፈፀም ሕገ ወጥ አደንና ሰፈራን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው
Jan 29, 2025 87
ሳላማጎ፤ ጥር 21/2017 (ኢዜአ)፦ በማጎ ብሔራዊ ፓርክ የሚፈፀም ሕገ ወጥ አደንና ሰፈራን ለመከላከል ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የፓርኩ አስተዳደር አስታወቀ። ከአዲስ አበባ በ790 ኪሎ ሜትር ርቀት በውብ መልክዓ ምድርና በጥቅጥቅ ደኖች ማራኪ ገጽታ የተላበሰው የማጎ ብሔራዊ ፓርክ በደቡብ ክልል በታችኛው ኦሞ ሸለቆ ይገኛል። በ1970 ዎቹ ገደማ በፓርክነት የተቋቋመውና የበርካታ ብዝሃ ሕይወት መገኛ የሆነው ፓርኩ፤ ከ80 በላይ አጥቢ፣ ከ250 በላይ የአዕዋፍ እና 14 ዓይነት የዓሣ ዝሪያዎች አሉት። ዝሆን፣ የሜዳ አህያ፣ አንበሳ፣ ጎሽ፣ አምባራይሌ፣ አቦሸማኔ፣ ተኩላና የሌሎች አጥቢ የዱር እንስሳት የያዘ የመስህብ ስፍራ ነው። የማጎ ብሔራዊ ፓርክ አስተዳዳሪ አቶ አርቦር ሌለ ለኢዜአ እንደገለጹት ፓርኩ በሕገ ወጥ ሰፈራ፣ በእርሻ መሬትና በሌሎች ምክንያቶች ፓርኩ ጉዳት እያስተናገደ ነው። በዚህም የፓርኩ ይዞታ ከ2 ሺህ 142 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋት ወደ 1 ሺህ 942 ዝቅ ማለቱን ጠቁመዋል። በአርብቶ አደሩ ማህበረሰብ በኩል የሚፈጽምን ሕገ ወጥ አደን ለማስቆም በሚንቀሳቀሱ የፓርክ ስካውት አባላት ላይ ጥቃት እንደሚሰነዘር ገልጸዋል። በመሆኑም የፓርኩን ደህንነትና ብዝሀ ሀብት ለማስጠብቅ ህብረተሰቡንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በመጡ መሻሻሎች ወደ ጎረቤት አገራት የተሰደዱ የዱር እንስሳትም መመለስ መጀመራቸውን ነው ያነሱት። የፓርኩ የስካውት አባል አቶ ሻዳ ቡኬ በበኩላቸው፣ ሕገ ወጥ አደንን ለመከላከል በሚደረግ ጥረት በርካታ ስካውቶች የጥቃት ሰለባ እንደሚሆኑ ገልፀው፤ ድርጊቱን ለማስቆም የተጀመረው ጥረት ለውጥ እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል። ፓርኩን በዘላቂነት ለመጠበቅና ለሚፈለገው ቱሪስት መስህብነት ለማዋል ለፓርኩ ትኩረት መስጠት ይገባዋል ነው ያሉት። በበናፀማይ ወረዳ ጎልዲያ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ከበደ ቦጋለ፤ እንደ ጀግንነት የሚያስቆጥረው ግዙፍ የዱር እንስሳትን አድኖ የመግደል የአካባቢው ጎጂ ባህል እንዲቀረፍ በተደረገው ጥረት ጥሩ ለውጦች እየታዩ ነው ብለዋል። በአሪ ዞን የአልጋ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ዘውዱ አንክሲ በበኩላቸው የእርሻ ማሳ ለማስፋፋት ወደ ፓርኩ ይዞታ በህገ ወጥነት የመስፈር ሁኔታ እንደሚስተዋል ገልፀው፤ ይህን ሕገ ወጥ ድርጊት ለመከላከል የፀጥታ አካላት ጋር ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በሁለቱ ዞኖች ከ183 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ ይከናወናል
Jan 29, 2025 75
ሮቤ፤ ጥር 21/2017(ኢዜአ)፦ በባሌ እና ምስራቅ ባሌ ዞኖች ዘንድሮ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ከ183 ሺህ ሔክታር መሬት በላይ በሥነ-አካላዊ የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን የየዞኖቹ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጹ። የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራው በምሥራቅ ባሌ ዞን የተጀመረ ሲሆን በባሌ ዞን ደግሞ ስራውን ለመጀመር ዝግጅት መጠናቀቁ ተመልክቷል። የምሥራቅ ባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘላለም አለማየሁ እንዳሉት የዘንድሮው የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት በዞኑ በተለዩ 155 ንዑስ ተፋሰሶችን መሰረት በማድረግ ከ77 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ የሚያካልል ነው። በዞኑ ለአፈር መሸርሸርና ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ተዳፋታማና ተራራማ አካባቢዎችን የማልማት ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ ይከናወናል ብለዋል። የባሌ ዞን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ዳዲ በዞኑ በዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ሥራ 105 ሺህ 800 ሄክታር መሬትን መሰረት በማድረግ የተለያዩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች እንደሚከናወኑም አመልክተዋል። በዞኑ በዋና ዋና የአፈርና ውኃ መጠበቂያ ስትራክቸሮች፤ እርከን እንዲሁም የተጎዳ መሬትን ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ አድርጎ የማልማት ሥራ ለማከናወን መታቀዱን አብራርተዋል። የተፈጥሮ ሀብትን የመጠበቅ፤ የማልማትና የመጠቀም ጉዳይ ትውልድን የማስቀጠል አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰው ለዚህም የዞኑ ህዝብ በስፋት እንዲሳተፍ ቅስቀሳ እየተደረገ መሆኑንም እንዲሁ።
የመሬት ናዳ ዳግም እንዳይከሰት በተፋሰስ ልማቱ በንቃት እንሳተፋለን - የኬንቾ ወይዜ ቀበሌ ነዋሪዎች
Jan 28, 2025 82
ሳውላ፤ ጥር 20/2017(ኢዜአ)፡- በአካባቢያቸው የመሬት ናዳ ዳግም እንዳይከሰትና የተጎዳ መሬት መልሶ እንዲያገግም በተፋሰስ ልማቱ በንቃት በመሳተፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በገዜ ጎፋ ወረዳ የኬንቾ ወይዜ ቀበሌ ነዋሪዎች ገለጹ። የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የዘንድሮው የበጋ ተፋሰስ ልማት በገዜ ጎፋ ወረዳ በይፋ ባስጀመረበት ወቅት ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በገዜ ጎፋ ወረዳ ሐምሌ 15 ቀን 2016 ዓ/ም የተከሰተውን ዓይነት የተፈጥሮ አደጋ እንዳይደገም ለማድረግ አካባቢያቸውን ለመንከባከብ በተፋሰስ ልማት ስራዎች በንቃት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። የኬንቾ ወይዜ ቀበሌ አካባቢ ጥበቃ አርሶ አደሮች ማህበር ሰብሳቢ አቶ ተክሌ ባዝዴ እንደገለጹት፤ የአካባቢውን የተፈጥሮ ሃብት በመንከባከብ አደጋን መቀነስ ይቻላል። በአካባቢው ላይ የተፋሰስ ልማት ስራ መስራት ስለሚጠቅም ከሚመለከተው የወረዳው አካል ጋር በመሆን ይህን ቦታ ለማልማት የልኬት ስራ ሰርተናል ብለዋል። በስፍራው ሊከሰት የሚችለውን የመሬት ናዳ እና ጎርፍ ለመከላከል የአካባቢው ማህበረሰብ ተስማምቶ ወደ ስራ መግባቱንም ተናግረዋል።   ሌላዋ የማህበሩ አባል ወይዘሮ መሰለች አበበ በበኩላቸው፤ ያለንበት ስፍራ ላይ ያለውን የተጎዳ መሬት በማልማት አፈሩ እንዳይሸረሸር፣ ውሀውም እዚሁ እንዲቆይና ናዳ እንዳይከሰት ለመከላከል ለስራ ወጥተናል ብለዋል። ቀድሞ ይህ ቦታ ለምቶ ቢሆን ኖሮ አደጋው አይከሰትም ብየ አስባለሁ ያሉት አስተያየት ሰጪዋ፤ አሁን አካባቢውን በማልማት ችግሩን መከላከል እንደሚቻል መገንዘባቸውን ተናግረዋል።   ከማህበሩ አባላት መካከል ወጣት ስምኦን ስሜ እንደገለጸው፤ በተፋሰስ ልማቱ ዙሪያ የተለያዩ እጽዋትንና የእንስሳት መኖ በማልማት ተጠቃሚ ለመሆን እየሰሩ ይገኛሉ። የፋሰስ ልማቱ መሰራቱ መሬቱ እንዳይሸራተት ያደርጋል የሚል እምነት እንዳለው ገልጿል። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተያዘው ዓመት 421 ሺህ 378 ሄክታር የተጎዳ መሬት ላይ ለአንድ ወር የሚቆይ የተቀናጀ ተፋሰስ ልማት ስራ ጥር 15 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ መጀመሩን መዘገባችን ይታወሳል።
ለአካባቢ ብክለት መንስኤ በሆኑ ከ1 ሺህ 800 በላይ አገልግሎት ሰጭና አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል
Jan 27, 2025 97
አዲስ አበባ፤ ጥር 19/2017(ኢዜአ)፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ለአካባቢ ብክለት መንስኤ የሆኑ ከ1 ሺህ 800 በላይ አገልግሎት ሰጭና አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የ2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀም ገምግሟል፡፡ የባለስልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዲዳ ድሪባ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ለአካባቢ ጥበቃ እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ትኩረት በመስጠት የ10 እና 5 ዓመት ስትራቴጂያዊ እቅዶች ተዘጋጅተው ወደ ስራ ተገብቷል፡፡   በመዲናዋ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ባለፉት ስድስት ወራት ለ12 አልሚዎች ፈቃድ እንዲሁም ለስድስት ተቋማት ደግሞ እድሳት ተደርጓል ብለዋል፡፡ በዚህም 2 ሚልየን 3 መቶ ሺህ ሜትር ኪዩብ ድንጋይና የድንጋይ ውጤቶች ለመዲናዋ የመሰረተ ልማት ግንባታ በማቅረብ ከ19 ሚሊዬን 762 ሺህ ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ብለዋል፡፡ ባለስልጣኑ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ለሚያቀርቡ 65 አምራች ማህበራት የአማራጭ ኢነርጂ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ድጋፍና ክትትል ማድረጉን አንስተዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ በአካባቢ ጥበቃ ላይ በቂ ግንዛቤ ለመፍጠር ለ 132 ሺህ ዜጎች ሥልጠና መሰጠቱን ጠቅሰው፤ የብክለት ይወገድልኝ ጥያቄ ላቀረቡ 923 ሰዎች ምላሽ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡ በመዲናዋ የብክለት ምንጭ በሆኑ 8 ሺህ 772 አገልግሎት ሰጪ እና አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ ክትትል መደረጉን ገልጸዋል፡፡ በዚህም አካባቢን በተደጋጋሚ የሚበክሉ 1 ሺህ 801 ተቋማት ላይ ማሸግን ጨምሮ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውንም ተናግረዋል። እርምጃ የተወሰደባቸው ተቋማት የቆዳ፣ የብረታ ብረት እና የፕላስቲክ ፋብሪካዎች እንዲሁም ሆስፒታሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆቴሎች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከድምጽ ብክለት ጋር በተያያዘም 50 የሚሆኑ የምሽት ቤቶች መታሸጋቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ ማስተካከያ ካላደረጉ የንግድ ፈቃድ እስከ መሰረዝ የሚያደርስ ቅጣት ይጠብቃቸዋል ብለዋል፡፡
በሲዳማ ክልል በአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት የተገኘውን ውጤት ለማጠናከር ይሰራል
Jan 27, 2025 105
ሀዋሳ ፤ጥር 19/2017 (ኢዜአ):-በሲዳማ ክልል ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ልማት ስራ የተገኘውን የምርትና ምርታማነት መሻሻል ውጤቶችን ለማጠናከር በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ። በክልሉ የ2017 ዓ.ም የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራ “የአፈር ሀብታችን ለብልጽግናችን” በሚል መሪ ሀሳብ በቦርቻ ወረዳ አልዳዳ ደላ ቀበሌ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል። በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ አስፋው ጎኖሶ እንዳሉት፤ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሰቱ ችግሮች ለመከላከልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ወሳኝ ነው።   በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ስራዎች ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማድረጉን አንስተው፤ ይህን ለማጠናከርና የምግብ ዋስትናን ጥረት ለማሳካት ታስቦ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል። የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገቡን ተናግረዋል። የደን ሽፋን እንዲጨምር የአፈር ለምነትንና የውሃ አቅምን እንዲያድግ እንዲሁም ለእንስሳት መኖ የሚሆን ሳር ማግኘት መቻሉን ለአብነት አንስተዋል። ይህም በክልሉ ሁለንተናዊ የሆነ የምርትና ምርታማነት መጨመር ጉልህ ሚና እየተጫወተ በመሆኑ ልምዶችን እየወሰድን የማጠናከር ስራ ይሰራል ብለዋል።   በተያዘው ዓመት በ678 ንዑስ ተፋሰሶች ከ136 ሺህ 400 ሄክታር በላይ መሬት እንደሚለማ የቢሮው ምክትል ኃላፊና የተፈጥሮ ሀብትና መሬት አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቅረ ኢየሱስ አሸናፊ ገልጸዋል ። በተለይም ውሃን ማቆር የሚያስችሉ ተግባራት ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው ሲሆን የሀዋሳ ሀይቅን ጨምሮ ሌሎች ውሃማ አካላት ከጎርፍና ደለል መከላከልን ታሳቢ ያደረገ የስነ-አካላዊ ስራ እንደሚከናወንም አንስተዋል። የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ለሚቀጥሉት 30 ቀናት እንደሚተገበርም ተናግረዋል። ተዳፋታማ በሆነው የቦርቻ ወረዳ የአደላላ ደላ ቀበሌ በጎርፍ እየታጠበ መሬቱ ከምርት ወጥቶ እንደነበር ያስታወሱት ከልማቱ ተሳታፊዎች መካከል አርሶ አደር ኢሳያስ ባገ አሁን ለውጥ መኖሩን ገልጸዋል።   ''የተፋሰስ ስራን አትኩረን በመስራታቸው ዛሬ ለእርሻ መሬትና ለከብት ሳር ማግኘት ችለናል።'' ያሉት አርሶ አደሩ ውጤቱን ለማስቀጠልም ከሌሎች ጋር በመሆን እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል። ወይዘሮ አሽለ ስና በበኩላቸው ከዚህ ቀደም አካባቢው እጅግ የተጎዳና ምርት የማይሰጥ አየሩም ምቹ እንዳልነበረ አንስተው ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የተፋሰስ ስራ በአካባቢው ለውጥ መጥቷል ብለዋል። "በመሆኑም ስራውን ልምድ አድርገን እየሰራን ነው ዘንድሮም ከሌሎች ጋር በመሆን ወሩን ሙሉ እንሰራለን ጥቅሙ የእኛ ስለሆነ አጠናክረን እንቀጥላለን" ብለዋል።  
የተፋሰስ ልማቱ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገውን ሽግግር እያገዘ ነው- ከንቲባ ከድር ጁሃር
Jan 26, 2025 106
ድሬዳዋ፤ ጥር 18/2017(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚከናወነው የተፋሰስ ልማት ስራ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገርና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እያገዘ መሆኑን የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ። " የአፈር ጥበቃ ስራችን፤ ለብልፅግናችን" በሚል መሪ ሀሳብ በድሬዳዋ 38 የገጠር ቀበሌዎች የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል። የተፋሰስ ልማቱን በአራቱ የገጠር ክላስተሮች ተሰማርተው ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና የአስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ናቸው። በብዮ አዋሌ ክላስተር ተገኝተው የተፋሰስ ልማቱን ያስጀመሩት ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንደተናገሩት፤ አገራዊውን ለውጥ ተከትሎ በድሬዳዋ ውጤቶች ከተመዘገበባቸው ልማቶች መካከል የተፋሰስ ልማት አንዱ ነው። በአስተዳደሩ በህዝብ ንቅናቄ የተሰሩት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች ከተረጂነት ወደ አምራችነት ለመሸጋገር የሚከናወኑ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ማገዙን ገልጸዋል። እንደ ከንቲባ ከድር ገለፃ በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ከሚከናወነው የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ ጎን ለጎን የበጋ ወራት የበጎ ፍቃድ ተግባራት በትኩረት ይተገበራሉ። በመሆኑም ሁሉም በትጋት እንዲተገብረው ጥሪ አስተላልፈዋል። የአስተዳደሩ ግብርና፣ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በ50 ሺህ ሄክታር የተራቆቱ ተፋሰሶች ላይ የአፈርና የውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል። የተከናወኑት ልማቶች የጎርፍ ተጋላጭነት እና የአፈር መጠረግን በመከላከል በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና የስራ ዕድል ለመፍጠር እያገዙ ይገኛሉ ብለዋል። በተፋሰስ ልማቱ ላይ እየተሳተፉ ከሚገኙት አርሶአደሮች መካከል ወጣት አብዱልናስር ሙክታር ባለፉት ዓመታት የተሰሩት ልማቶች የጠፉ ምንጮችና የተፈጥሮ ደኖች እንዲመለሱ ማገዙን ተናግረዋል። ወጣቶች ተደራጅተው ልማቱን በመጠበቅ የእንሰሳት መኖ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው የዘንድሮውን ዕቅድ ለማሳካትም እንደሚተጉ ገልጸዋል።
በድሬዳዋ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ በይፋ ተጀመረ
Jan 26, 2025 85
ድሬዳዋ፤ ጥር 18/2017(ኢዜአ)፦ በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርየዘንድሮ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ዛሬ በይፋ ተጀምሯል። የተፋሰስ ልማት ሥራው "የአፈር ጥበቃ ስራችን ለብልፅግናችን" በሚል መሪ ሃሳብ በ38 የገጠር ቀበሌዎች ላይ ተጀምሯል። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደንና ከንቲባ ከድር ጁሃር ጨምሮ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች የተፋሰስ ስራዎችን አስጀምረዋል። የድሬዳዋ ግብርና፣ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ እንደተናገሩት፤ ዛሬ በተጀመረውና ለአንድ ወር በሚዘልቀው የተፋሰስ ልማት ሥራ 5 ሺህ 550 ሄክታር የተራቆቱ አካባቢዎች የአፈርና የውሃ ጥበቃ ይከናወናል። የገጠር መንገድ ጥገና፣ የመስኖ ውሃና የማሳ እንክብካቤ፣ የጤና እና የትምህርት ተግባራትን ከፍ የሚያደርጉ ስራዎች ይተገበራሉ ብለዋል። የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው የመሬት መራቆትን የሚቀንስና በጎርፍ የሚወሰድን 48 ሺህ 700 ቶን ለም አፈር የሚታደግ መሆኑን ገልጸዋል። ለአንድ ወር በሚቆየው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ላይ 41 ሺህ 300 የሚሆኑ የአስተዳደሩ ነዋሪዎች በባለቤትነት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። የብዬ አዋሌ ገጠር ወረዳ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ያሲን መሐመድ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት የአካባቢውን ስነምህዳር ከመለወጥ በተጨማሪ ለምርታማነት እና ለኑሮ ምቹ አካባቢ መፍጠር መቻሉን ተናግረዋል። እነዚህን የተገኙ ውጤቶች በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ በልማቱ ላይ መሳተፍ ጀምሯል ብለዋል።
በክልሉ የተፋሰስ ልማት ስራው የመሬት ለምነትን በመጨመሩ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ተጠቃሚ ሆነናል - የአካባቢው አርሶ አደሮች
Jan 25, 2025 155
ሐረር፤ ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡- በሐረሪ ክልል የተፋሰስ ልማት ስራው የመሬት ለምነትን በመጨመሩ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የአካባቢው አርሶ አደሮች ገለጹ። የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው በግብርናው ዘርፍ የሚከናወኑ የልማት ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ ምክንያት መሆኑንም የክልሉ ግብርና ልማት ቢሮ ገልጿል። በክልሉ የተፋሰስ ልማት ስራ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አንጻር አበርክቶው የላቀ በመሆኑ በየዓመቱ የበጋ ወቅት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በስፋት ይከናወናሉ።   በክልሉ ኤረር ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር ኢብራሂም አብዱሌ እንደተናገሩት በክልሉ የሚከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የአፈር ለምነትን በመጨመርና የከርሰ ምድር ውሃን በማጎልበት ምርትና ምርታማነታችን እንዲጨምር አድርጓል። በተለይ በተፋሰሱ ላይ የምናከናውነው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ስራ አካባቢውን ከሞቃታማነት ወደ ነፋሻማነት መለወጡን ተናግረዋል። የተፋሰስ ልማት ስራ የተራቆቱ አካባቢዎች አረንጓዴ እንዲሆኑና አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ናቸው ያሉት ደግሞ ሴት አርሶ አደር ፋጡማ ሙሜ ናቸው።   በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በተገኘው የከርሰ ምድር ውሃ አትክልትና ፍራፍሬን በማልማት ተጠቃሚነታችንን እያረጋገጥን እንገኛለን ብለዋል።   የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው በግብርናው ዘርፍ ለሚያከናወኑት የልማት ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ መምጣት ምክንያት መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነስረዲን አህመድ ናቸው። በተለይ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች አንድ ጊዜ ብቻ ሲያመርቱ የነበሩ አርሶ አደሮች በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ ማምረት እንዲችሉ አስችሏል ብለዋል። በክልሉ ለ30 ቀናት በሚቆየው የተፋሰስ ልማት ስራም ዛሬ መጀመሩን ጠቁመው በዚህም በ16 ተፋሰሶች ላይ 900 ሄክታር መሬት የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።   በተፋሰስ ልማት ሥራው ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት የተሰሩት የተፋሰስ ልማት ስራዎች በግብርና ምርትና ምርታማነት መጨመር ላይ ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው ብለዋል። በተጨማሪም በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ የተሰሩ ስራዎች የአርሶ አደሩን የስራ ባህል እየለወጡ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በሐረሪ ክልል "አፈራችን ለሀገራዊ ብልጽግናችን" በሚል መሪ ሃሳብ የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ መጀመሩ መገለጹ ይታወሳል።
በክልሉ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት የተገኘው ውጤት ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ሥራውን እንዲያጠናክር ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል
Jan 25, 2025 169
ከሚሴ፤ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት የተገኘው ተጨባጭ ውጤት ህብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ሥራውን ይበልጥ እንዲያጠናክር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የዘንድሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራ በአርጡማ ፉርሲ ወረዳ ወገሬ ደበሶ ቀበሌ ቦሩ ተፋሰስ ዛሬ ተጀምሯል። በማስጀመሪያው መረሃ ግብር ላይ የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው እንደገለጹት ፤ በክልሉ ባለፉት ዓመታት በተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራ በተጨባጭ አበረታች ውጤት አስገኝቷል። ይህም የተራቆቱ ተራራዎች ማገገማቸውን፣ የደን ሽፋኑ፣ ምርታማነት የአፈር ለምነትና እርጥበት ከመጨመሩ ባለፈ ተፋሰሶችን ዘላቂ በማድረግ ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሪያ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል። በልማቱ የተገኘው ተጨባጭ ውጤት ህብረተሰቡ በየዓመቱ ያለ ቀስቃሽ በራሱ ተነሳሽነት በነቂስ ወጥቶ እንዲሰራና ዘላቂ እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አስታውቀዋል። ተግባሩን አላቂ በማድረግ ለወጣቱ የሥራ እድል በመፍጠር ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። ዘንድሮም በተመረጡ ተፋሰሶች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጎ ሥራው በክልል ደረጃ መጀመሩን ገልጸዋል። ተፋሰሶችን ከአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ጋር በማስተሳሰር የተሻለ ጥቅም እንዲሰጡ ለማድረግ ችግኞች እየተዘጋጁ ነው ብለዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ በበኩላቸው፥ ዞኑ ውሃና ዝናብ አጠር በመሆኑ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ የህልውና ጉዳይ ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ባለፉት ዓመታት በዞኑ የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ አበረታች ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል። ተፋሰሶችን በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በመትከል ለወጣቶችም የሥራ እድል እየተፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል። በዞኑ ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተለዩ ስፍራዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ዛሬ ወደ ተግባር መገባቱን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀሰን ሰይድ ናቸው። ቀደም ሲል በተከናወነ ተግባራት የተጎዱ አካባቢዎችና ተራሮች ማገገማቸውን፣ ምርታማነት መጨመሩ፣ የደን ሽፋኑ መጨመሩንና የአፈር ለምነት መጠበቁን ገልጸዋል። በአርጡማ ፉርሲ ወረዳ የወገሬ ደቢሶ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር እንድሪስ ጀማል በሰጡት አስተያየት፤ ቀደም ሲል በተከናወነ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት ሥራ በተጨባጭ ተጠቃሚ በመሆናቸው ዘንድሮም በነቂስ ወጥተው ልማቱን መጀመራቸውን ተናግረዋል። በማስጀመሪያው መረሃ ግብር ላይ የክልል የዞን፣ የወረዳና የከተማ አመራር አባላትን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በተለያዩ የግብርና መስኮች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
Jan 25, 2025 83
አዳማ ፤ጥር 17/2017(ኢዜአ)፡-የሰብል ልማትን ጨምሮ በተለያዩ የግብርና መስኮች የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸው ተገለጸ። በግብርና ሚኒስቴር የአካባቢና አየር ንብረት ለውጥ ማስተባበሪያ ቡድን መሪ አቶ አዲሱ ነጋሽ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስር ኢትዮጵያ የተለያዩ እቅዶችን፣ ስትራቴጂዎችንና የማስፈፀሚያ ስልቶችን አዘጋጅታ እየተገበረች ትገኛለች። "እንደ አገር በሰብል፣ በእንስሳት ልማትና እፅዋት ላይ እየሰራን እንገኛለን" ያሉት ቡድን መሪው፤ በተለይ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የእንስሳት ዝሪያን በማሻሻልና ምርታማነቱን በመጨመር የሙቀት አማቂ ጋዞች መጠንን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በዚህም የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የኑሮ ሁኔታ በማሻሻል በአካባቢው ላይ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቋቋም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል። ስርዓተ ምግብን ለማረጋገጥ በቆላማ የአገሪቷ አካባቢዎች የፀሃይ ሃይልን በመጠቀም አነስተኛ መስኖን በማስፋፋት፣ ሰብልና የእንስሳት መኖን በማምረት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ እየተሰራባቸው ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በተፈጥሮና በሰው ስራሽ አደጋዎች የተጎዱና የተራቆቱ መሬቶች ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ እንዲያገግሙና ወደ ምርት እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑንም አንስተዋል። ኢትዮጵያ ካሏት 12 ተፋሰሶች ውስጥ ዘጠኙ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች መሆናቸውን ጠቁመው፤ የውሃ መጠናቸው እንዲጨምር፣ የአፈር መሸርሸርና የመሬት መራቆትን ለመቀነስ የተፋሰስ ልማት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። በተለይ በሰብል፣ በወተትና ወተት ተዋፅዖ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በአፈርና ውሃ እቀባ፣ በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብሮች እውቅና የተገኘባቸው ፕሮጀክቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። የድህረ ምርት ብክነትን ለመቀነስና በምግብ ራስን ለመቻል የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂን ተደራሽ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። የአየር ንብረት ለውጥ በአርብቶና አርሶ አደሩ አካባቢ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቋቋም ቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ስራዎች እየተከናወኑ ካሉት ፕሮጀክቶች መካከል መሆኑንም አስረድተዋል። የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በፋይናንስና አቅም ግንባታ ከሚደግፉ ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ለውጥና ማቋቋሚያ ፈንድ ጋር ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና ፋይናንስ በማስፈቀድ በትብብር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን መቀነስ የሚያስችሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅና ሀብት በማፈላለግ በመደበኛነት ከሚሰራው የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ስራዎች በተጨማሪ ሌሎች ስራዎች በፕሮጀክት እየተሰሩ መሆኑንም አመልክተዋል።    
በክልሉ የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የአርሶ አደሩን ምርታማነት ጨምረዋል- አቶ ሄኖክ ሙሉነህ
Jan 25, 2025 78
አዲስ አበባ፤ጥር 17/2017 (ኢዜአ)፡-በሐረሪ ክልል በተፋሰስ ልማት ስራዎች የአርሶ አደሩን ምርታማነት መጨመር መቻሉን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሄኖክ ሙሉነህ ገለጹ። በሐረሪ ክልል "የአፈር ሀብታችን ለብልፅግናችን" በሚል መሪ ቃል የተፋሰስ ልማት ስራ ዛሬ ተጀምሯል። የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሄኖክ ሙሉነህ የተፋሰስ ልማት ስራውን አስጀምረዋል። አቶ ሄኖክ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በተፋሰስ ልማት ስራው ላይ ከ30 እስከ 40 ሺህ አርሶ አደሮች ይሳተፋሉ። በክልሉ ከዚህ ቀደም የተከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የከርሰ ምድር ውሃ ተጠቃሚነትን በመጨመር በማድረግ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ መቻሉን አመልክተዋል። ተራቁተው የነበሩ ተራራዎች በደን እንዲሸፈኑ በማድረግ የተከናወነው ስራ ለትውልድ የለማና አረንጓዴ አካባቢ ለማስረከብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል። ከለውጡ ወዲህ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መደገፋቸው፤ ተራቁተው የቆዩ መሬቶች በፍጥነት እንዲያገግሙ ማስቻሉን ጠቁመዋል። በዚህም አርሶ አደሩ የመስኖ ልማት ስራውን በማጎልበት የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ነው ኃላፊው የገለጹት። አርሶ አደሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን ውጤት በተጨባጭ መመልከቱ የተሻለ የስራ ባህልን በመላበስ ከግብርና ስራው ጎን የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በስፋት እንዲያከናውን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አብራርተዋል። የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን በማከናወን የተፈጥሮ ሀብትን ጠብቆ ለም መሬትን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የሁሉም ኃላፊነት ነው ያሉት አቶ ሄኖክ፥ በዚህም ማህበረሰቡ በተፋሰስ ልማት ስራው ላይ በነቂስ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል። የሐረሪ ክልል ግብርና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ነስረዲን አህመድ በክልሉ በ16 ተፋሰሶች ላይ ከ900 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት በዕቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ መግለጻቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በትግራይ ክልል አደገኛ ኬሚካሎችን የሚጠቀሙ ህገወጥ የማዕድን አውጪዎችን የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥ ልዩ ችሎት ይቋቋማል - የመሬትና ማዕድን ቢሮ
Jan 24, 2025 99
ሽረ እንዳስላሴ፤ጥር 16/2017(ኢዜአ)፡-በትግራይ ክልል በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ አደገኛና የተከለከሉ ኬሚካሎችን የሚጠቀሙ የማዕድን አውጪዎችን የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥ ልዩ ችሎት እንደሚቋቋም በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የመሬትና ማዕድን ቢሮ ገለፀ። ''ልዩ ትኩረት ለማዕድን ልማት'' በሚል መሪ ሀሳብ ክልላዊ ሲምፖዚየም በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ዛሬ ተካሂዷል። በጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉ መሬትና ማዕድን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋአለም ሐድጉ እንደገለፁት፥ በክልሉ በማዕድን ምርት ላይ የሚስተዋለውን ህገ-ወጥ ድርጊት ለመከላከልና ህጋዊ መንገድ ለማስያዝ የተቀናጀ እንቅስቃሴ በመከናወን ላይ ነው። በማዕድን ምርት ለሰው፣ለእንስሳትና ለደን ጉዳት የሚያደርሱ የተከለከሉ አደገኛ ኬሚካሎች ጥቅም መዋሉን በጥናት በተረጋገጠባቸው ማዕድን አምራቾች ላይ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥ ልዩ ችሎት በሽረ እንዳስላሴና በአክሱም ከተሞች ማቋቋም አንዱ ህጋዊ መስመር የማስያዝ እንቅስቃሴ መሆኑን ተናግረዋል። በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ አደገኛና የተከለከሉ ኬሚካሎች ለማዕድን ማውጣት ተግባር እየዋሉ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን አመልክተዋል። በተለይ ሜርኩሪ፣ ሶድየምና ሲያናይድ የተባሉ አደገኛ ኬሚካሎችን የሚጠቀሙ ህገ-ወጥ ማዕድን አውጪዎች በስራ ላይ እንዳሉም በመቀሌና በአክሱም ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች የተደረገው ጥናት መጠቆሙን ገልጸዋል። በፌዴራል መንግስትና በጊዜያዊ አስተዳደሩ ፈቃድ የወሰዱ በማዕድን ማውጣት ተግባር ላይ የተሰማሩ ህገ ወጦች በአስቸኳይ ከተግባራቸው እንዲታቀቡ እንደሚደረግ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል። ስለሆነም ህገወጥ የማዕድን ማውጣት እንቅስቃሴ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ላይ ያሉ የተዛቡ አሰራሮችን በቅንጅት ማስቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በተለይ በክልሉ የሚገኙ መቀሌ፣ አክሱም፣ አዲግራትና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች በማዕድን ማውጣት ረገድ እየታየ ያለውን ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ ለማስተካከል የጀመሩትን እንቅስቃሴ ማጠናከር እንዳለባቸውም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም