ስፖርት
በገንዳ ውኃ ከተማ  ለወጣቶች ምቹ የስፖርት ማዘውተሪያ  የማልማት ስራ እየተከናወነ ነው
Feb 1, 2025 62
ገንዳ ውኃ ፤ ጥር 24/2017(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውኃ ከተማ ለወጣቶች ምቹ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ገለጸ። በከተማው ሰባት የአዋቂዎች እግር ኳስ ቡድኖች የሚሳተፉበት ውድድር ዛሬ ተጀምሯል። የገንዳ ውኃ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ አብዱልከሪም ሙሀመድ ውድድሩ ሲጀመር ባደረጉት ንግግር ፤ ስፖርት ሰላም፣ ልማትና አንድነትን የሚያጠናክር እሴት ነው ብለዋል። ስፖርት ለሰላም፤ ለልማትና ለጤና መሆኑን የሚገነዘብ ወጣት ከማፍራት ባሻገር ለወጣቶች ምቹ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን የማልማት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በከተማው ሀያ ስድስት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መለየታቸውን ጠቅሰው፤ ከእነዚህም ስድስት የሚሆኑትን የማልማት ስራ እየተካሄደ መሆኑንና ይሄው ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረኪዳን መንጋው በበኩላቸው፤ የስፖርት ዘርፉን በማጠናከር ጤናማ፤ ለሰላምና ልማት የሚተጋ ትውልድ የመፍጠር ተግባር እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል። "ስፖርት ፍቅርና አንድነትን የምናጠናክርበት መስተጋብራችን ነው" ያሉት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ልዑልሰገድ አሰፋ ናቸው። የሰላም መገለጫ የሆነውን ስፖርት በማዘመን ወጣቶች ለአካባቢያቸው ብሎም ለአገራቸው ሰላምና ልማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። በከተማው ሰባት የአዋቂዎች እግር ኳስ ቡድኖች የሚሳተፉበት ውድድሩ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ግንቦት 30/2017 ዓ.ም እንደሚቆይ ተመልክቷል።
አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ለተጫዋቾች ጥሪ አደረጉ 
Feb 1, 2025 49
አዲስ አበባ ፤ጥር 23/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ለ16ኛ የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት ለ29 ተጫዋቾች ዛሬ ጥሪ አድርገዋል። ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ከነገ ጀምሮ ልምምድ ማድረግ እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መረጃ ያመለክታል። ሉሲዎቹ ከዩጋንዳ ጋር የካቲት 14 እና የካቲት 19 ቀን 2017 ዓ.ም የደርሶ መልስ ጨዋታ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከዩጋንዳ ጋር ለሚያደርገው የማጣሪያ ዝግጅት እንዲረዳ ከጅቡቲ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር የካቲት 5 እና የካቲት 9 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንደሚያካሂድ ታውቋል። በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 16ኛው የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ መርሃ ግብሩ በሁለት ዙር እንደሚከናወን እና 38 ሀገራት እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል። ኢትዮጵያ ዩጋንዳን በደርሶ መልስ ካሸነፈች በሁለተኛው ዙር ከታንዛንያ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ አሸናፊ ጋር ትጫወታለች። 11 ሀገራት ከአዘጋጇ ሞሮኮ ውጪ በአህጉራዊው መድረክ ለመሳተፍ ይፋለማሉ። በአፍሪካ ዋንጫ ላይ 12 ሀገራት ይሳተፋሉ።
ፋሲል ከነማ ወደ ድል ተመልሷል 
Jan 31, 2025 68
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር ፋሲል ከነማ ድሬዳዋ ከተማን 2 ለ 1 አሸንፏል። ማምሻውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሀብታሙ ተከስተ እና አንዋር ሙራድ የማሸነፊያ ጎሎቹን አስቆጥረዋል። ሙኸዲን ሙሳ ለድሬዳዋ ከተማ ብቸኛውን ግብ ከመረብ ላይ አሳርፏል። ውጤቱን ተከትሎ ፋሲል ከነማ በሊጉ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል። በ20 ነጥብ ደረጃውን ከ14ኛ ወደ 9ኛ ከፍ አድርጓል። ቡድኑ በውድድር ዓመቱ አራተኛ ድሉን አሳክቷል። በአንጻሩ በሊጉ አራተኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ድሬዳዋ ከተማ በ19 ነጥብ ከ10ኛ ደረጃ 11ኛ ዝቅ ብሏል። ድሬዳዋ የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት ስድስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። ቀን ላይ በተደረገ ጨዋታ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ሀዲያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 አሸንፏል። ጨዋታዎቹን ተከትሎ የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ተጠናቋል። የ18ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከጥር 25 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶ ይካሄዳሉ። ኢትዮጵያ መድን ሊጉን በ32 ነጥብ እየመራ ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በ28 እና መቻል በ27 ነጥብ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። አዳማ ከተማ፣ ሃዋሳ ከተማ፣ ስሑል ሽሬ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ15ኛ እስከ 18ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ።
የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን እና ሀዲያ ሆሳዕና የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
Jan 31, 2025 67
አዲስ አበባ፤ ጥር 23/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የመጨረሻ ቀን ውሎ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን ከሀዲያ ሆሳዕና የሚያደርገው ጨዋታ የተመልካቾችን ትኩረት ስቧል። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳል። ኢትዮጵያ መድን በሊጉ ያደረጋቸውን ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ዘጠኝ ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሁለት ግቦችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ29 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሀዲያ ሆሳዕና ከባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ውስጥ በሶስቱ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያገናኝ አራት ግቦችን በማስተናገድ በ26 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ይዟል። ኢትዮጵያ መድን የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከተከታዩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ከፍ ያደርጋል። ተጋጣሚው ሀዲያ ሆሳዕና በጨዋታው ድል ከቀናው ደረጃውን የማሻሻል እድል ያገኛል። በ17ኛ ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር ድሬዳዋ ከተማ ከፋሲል ከነማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አላሸነፈም። አንድ ጊዜ ሲሸነፍ አራት ጊዜ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ አንድ ግብ ብቻ ሲያስቆጥር ሶስት ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ19 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ተጋጣሚው ፋሲል ከነማ በበኩሉ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በአምስቱ ጨዋታዎቹ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ሶስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። ፋሲል ከነማ በ17 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ17ኛ ሳምንት የሶስተኛ ቀን ጨዋታዎች ሃዋሳ ከተማ መቻልን 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ አንድ አቻ ተለያይተዋል።
በመዲናዋ ባለፉት ስድስት ወራት ከ113 ሺህ በላይ የሆኑ ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል
Jan 30, 2025 62
አዲስ አበባ፤ጥር 22/2017(ኢዜአ)፦በመዲናዋ ባለፉት ስድስት ወራት 113 ሺህ 326 ወጣቶችን የስራ ዕድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለፀ። ቢሮው የ2017 በጀት ዓመት የ6 ወር ዕቅድ አፈጻጸምን ከባለድርሻ አካላት ጋር ገምግሟል። የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን በዚሁ ወቅት፤ የከተማዋ ወጣቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል። በከተማው በተገነባው የመጀመሪያ ዙር የኮሪደር ልማት 50 ሺህ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማትም በተመሳሳይ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል። በስፖርት ዘርፉም ብቁና ተወዳዳሪ ስፖርተኞችን ለማፍራት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል። በዚህም ባለፉት አራት ዓመታት በከተማው ከ1 ሺህ 300 በላይ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች መገንባታቸውን ጠቅሰው፥ በሁለተኛ ዙር ኮሪደር ልማት 17 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እየተገነቡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። ከዚህ ባለፈም ወጣቱን በዕውቀት የበለፀገ፤ በስነ ምግባር የታነፀ፤ ንቁና ስራ ፈጣሪ እንዲሆን የሚያስችሉ በርካታ የግንዛቤ ፈጠራ ስራዎች መሰራታቸውን አብራርተዋል። ወጣቱ በማዕድ ማጋራት፣በአረንጓዴ አሻራ ልማት፣ በደም ልገሳ፣ በትራፊክ በጎፍቃድ አገልግሎትን ጨምሮ በሁሉም በጎ ተግባራት መስኮች በንቃት በመሳተፍ ማህበራዊ ተሳትፎውን እያረጋገጠ እንደሚገኝ ገልፀዋል። በቢሮው የዕቅድና በጀት ክትትል ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አበባየሁ ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት፥ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ለ110 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ 113 ሺህ 326 ወጣቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። ቢሮው ወጣቶችንና የስፖርት ቤተሰቡን በማሳተፍ የ15 አቅመ ደካሞችን ቤት ማደሱንና ለ330 አቅመ ደካሞች ደግሞ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉን ጠቅሰዋል። በስነ ተዋልዶ ጤና፣ በወቅታዊ ጉዳይ፣ በሰላምና ግጭት አፈታት ዙሪያ ከ1 ሚሊዮን 639ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መሰራቱንም አንስተዋል። ዜጎች በአካልና በአዕምሮ ጎልብተው ጤናማ እና አምራች እንዲሆኑ ለማስቻል ከ4 ሚሊዮን 509 ሺህ 896 የሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማህበረሰብ አቀፍ ስፖርት ተሳታፊ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች ተቋሙ በሁሉም መስክ አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ገልፀው፥ በግማሽ አመቱ ያልተሳኩትን ተግባራት በሁለተኛው ግማሽ አመት ስራ ጨምረው ለማሳካት እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
በስፖርት ፌስቲቫሉ 12 ተወዳዳሪዎች በወርልድ ቴኳንዶ የወርቅ ሜዳሊያ አገኙ 
Jan 30, 2025 60
አዲስ አበባ፤ጥር 22/2017(ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ፌስቲቫል ዛሬ ስድስተኛ ቀኑ ይዟል። በወርልድ ቴኳንዶ በወንዶች በተደረጉ ውድድሮች በ80 ኪሎ ግራም ፋሲል ላቀው ከደብረብርሃን ፣ በ74 ኪሎ ግራም ግዛቸው ደምሴ ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፣ በ68 ኪሎ ግራም አማኑኤል ዳንኤል ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፣ በ63 ኪሎ ግራም ፍቃዱ ዳንኤል ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፣ በ58 ኪሎ ግራም ተከታይ አደራው ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፣ በ54 ኪሎ ግራም ድሪባ ደበላ ከጅማ ዩኒቨርስቲ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝተዋል። በወርልድ ቴኳንዶ ሴቶች በ67 ኪሎ ግራም ዘይነባ ቦንታ ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ፣ በ62 ኪሎ ግራም ፀገነት ጎርፉ ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፣ በ57 ኪሎ ግራም አዜብ ጎንፋ ከሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ፣ በ53 ኪሎ ግራም ያብስራ በቀለ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፣ በ49 ኪሎ ግራም አደዋ ካሳ ከደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲ ፣ በ46 ኪሎ ግራም እየሩሳሌም ተሾመ ከፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ዩኒቨርሲቲ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ሆነዋል።   በወንዶች የሰላሌ፣ የመቅደላ አምባ ፣ የሐረማያ ፣ የዋቸሞ ፣ የአርሲ እና የደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲዎች የብር ሜዳሊያ ማግኘት ችለዋል። በሴቶች የወራቤ፣ የጂንካ ፣ ድሬዳዋ ፣ ሰመራ እና ፌዴራል ቴክኒኒክና ሙያ ዩኒቨርሲቲ ተወዳዳሪዎች የነሐስ ሜዳሊያ አግኝተዋል። በወርልድ ቴኳንዶ በወንድም በሴትም በድምሩ 24 የነሐስ ሜዳሊያዎችን አሸናፊ ዩኒቨርሲቲዎች ወስደዋል። በፌስቲቫሉ በቼዝ፣ በባህላዊ ስፖርት፣ እግር ኳስ እና አትሌቲክስ ጠንካራ ፉክክር እየተካሄደ እንደሚገኝ ይገኛል። የስፖርት ፌስቲቫሉ እስከ ጥር 27 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ከትምህርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ፌስቲቫሉ በኮቪድና በተለዩዩ ምክንያቶች ለዘጠኝ ዓመታት ከተቋረጠ በኋላ በድጋሚ መጀመሩ ተገልጿል።
በሊጉ የሶስተኛ ቀን ውሎ ሁለት ወሳኝ መርሃ ግብሮች ይደረጋሉ
Jan 30, 2025 60
አዲስ አበባ፤ጥር 22/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ወጥቷል። በአምስቱ ጨዋታዎች ሶስት ጎሎችን ሲያገባ በተመሳሳይ አራት ግቦች አስተናግዷል። ቡድኑ በ18 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ለይ ይገኛል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች መካል በአንዱ ድል ሲቀናው ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሰባት ግቦች ተቆጥረውበት በአምስት ነጥብ የመጨረሻውን 18ኛ ደረጃ ይዟል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ16ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሀዲያ ሆሳዕናን 1 ለ 0 በማሸነፍ በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው። በሌላኛው የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሃዋሳ ከተማ ከመቻል ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ሃዋሳ ከተማ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አላሸነፈም። ሁለት ጊዜ ሲሸነፍ በሶስቱ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አምስት ጎሎች አስተናግዷል። ቡድኑ በ12 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ተጋጣሚው መቻል በበኩሉ ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ያሸነፍ አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አንድ ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ አራት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ አራት ጎሎች ተቆጥረውበታል። መቻል በ27 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። መቻል የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ የሊጉን መሪነት በጊዜያዊነት ከኢትዮጵያ መድን ይረከባል። በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ17ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ወላይታ ድቻን 2 ለ 0 እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ባህር ዳር ከተማን 3 ለ 1 አሸንፈዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ 
Jan 29, 2025 74
አዲስ አበባ፤ጥር 21/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ወላይታ ድቻ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። ወላይታ ድቻ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቷል። በአምስቱ ጨዋታዎች ስድስት ጎሎችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ስድስት ግቦች አስተናግዷል። ቡድኑ በ20 ነጥብ 8ኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች አራት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል። በጨዋታዎቹ ስምንት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ግቦች ተቆጥረውበታል። ቡድኑ በ25 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በሌላኛው የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ኢትዮጵያ ቡና ከባህር ዳር ከተማ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። በጨዋታዎቹ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አንድ ግብ አስተናግዷል። ቡድኑ በ19 ነጥብ 10ኛ ደረጃን ይዟል። ባህር ዳር ከተማ ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ድል የቀናው በአንዱ ነው። አንድ ጊዜ ሲሸነፍ ሶስት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ሶስት ግቦችን ከመረብ ጋር ሲያገናኝ በተመሳሳይ ሶስት ጎሎች ተቆጥረውበታል። ባህር ዳር ከተማ በ23 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረጉ የ17ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አዳማ ከተማን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ መቀሌ 70 እንደርታ እና አርባምንጭ ከተማ ሁለት አቻ ተለያይተዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል
Jan 28, 2025 88
አዲስ አበባ፤ ጥር 20/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ይደረጋሉ። በመጀመሪያ ጨዋታ መቀሌ 70 እንደርታ እና አርባምንጭ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ። መቀሌ 70 እንደርታ ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች በሶስቱ ሲያሸንፍ ሁለት ጊዜ አቻ በመውጣት አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ምንም ግብ አላስተናገደም። ቡድኑ በ21 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት ተከታታይ አምስት ጨዋታዎች አራት ጊዜ ድል ሲቀናው አንድ ጊዜ ተሸንፏል። ቡድኑ በጨዋታዎቹ ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ግቦች ተቆጥረውበት በ22 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በሌላኛው የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር አዳማ ከተማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ። አዳማ ከተማ በሊጉ ካከናወናቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች መካከል ያሸነፈው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን ሶስት ጊዜ ሲሸንፍ አንድ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በአምስቱ ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን ሲያስቆጥር ስምንት ግቦችን አስተናግዶ በ15 ነጥብ 15ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ላይ ይገኛል። የአምናው የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበኩሉ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አንድ ጊዜ ተሸንፎ ሶስት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። በጨዋታዎቹ ሶስት ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያገናኝ በተመሳሳይ ሶስት ግቦችን አስተናግዶ በ15 ነጥብ ተጋጣሚውን በግብ ክፍያ በልጦ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የ17ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ጥር 23 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል። ሲዳማ ቡና እና ስሑል ሽሬ የሳምንቱ አራፊ ቡድኖች ናቸው። ኢትዮጵያ መድን በ29 ነጥብ ሊጉን ሲመራ መቻል በ27፣ ሀዲያ ሆሳዕና በ26 እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በ25 ነጥብ ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል። አዳማ ከተማ፣ ስሑል ሽሬ፣ ሃዋሳ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ15ኛ እስከ 18ኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የድሬዳዋ ከተማው መሐመድ ኑር ናስር፣ የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ፍጹም ጥላሁን፣ ሽመልስ በቀለ ከመቻል፣ የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ፣ የወላይታ ድቻው ያሬድ ዳርዛ እና የአርባምንጭ ከተማው አህመድ ሁሴን በተመሳሳይ ስድስት ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በጋራ ይመራሉ።`
የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር በሚቀጥለው ሳምንት ይጀመራል
Jan 27, 2025 81
አዲስ አበባ፤ጥር 19/2017(ኢዜአ)፦ስምንተኛው ዙር የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር በሚቀጥለው ሳምንት በወላይታ ሶዶ ከተማ እንደሚካሄድ የባህልና ስፓርት ሚኒስቴር አስታወቀ። የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር "የታዳጊ ስፖርተኞች ልማት ለአሸናፊ አገር" በሚል መሪ ሃሳብ በወላይታ ሶዶ ከተማ እንደሚካሄድ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገልጿል። በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሀመድ እንደገለፁት፤መንግስት ለስፖርቱ ዘርፍ እድገት ትኩረት ሰጥቷል። በተለይም ከለውጡ በኋላ እየተሰሩ ያሉ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ለስፖርቱ ዘርፍ ትልቅ ትኩረት መሰጠቱን የሚያመላክት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ በወላይታ ሶዶ ከተማ በሚካሄደው ውድድር ላይ እግር ኳስ፤አትሌቲክስ፤ ፤ውሃ ዋና፤ማርሻል አርትን ጨምሮ በ11 የስፖርት አይነቶች ምዘናው ይካሄዳል። 2 ሺ 656 ተወዳዳሪዎች የሚሳተፉበት የታዳጊ ወጣቶች ውድድርም ከጥር 27 እስከ የካቲት 5 ቀን 2017 እንደሚካሄድ አስታውቀዋል። ውድድሩ የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ስልጠና ፕሮግራምን ጥራት እና ውጤታማነት በመመዘን ክፍተቶችን መለየት አላማ አድርጎ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡ በውድድሩ የሚለዩ ተተኪ ስፖርተኞች ወደ ክለቦችና የስፖርት አካዳሚዎች የሚገቡበትን እድል ለመፍጠር እንደሚያስችልም አብራርተዋል። በሚኒስቴሩ የስፖርት ልማት ዘርፍ መሪ ስራ አስፈፃሚ ተስፋዬ በቀለ በበኩላቸው፤ተቋርጦ የቆየው የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር በተለይም ስፖርቱን ለማነቃቃት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡ በተለይም ውድድሩ በወላይታ ሶዶ መካሄዱ ያሉትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ለማነቃቃት በር እንደሚከፍት ነው የጠቀሱት፡፡ ከዚህ ባለፈ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ታዳጊዎች የሚሳተፉበት በመሆኑ እርስ በርስ ይበልጥ የሚተዋወቁበትን መድረክ ይፈጥራል ብለዋል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማጎልበት ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ራስን መጠበቅ ይገባል - ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ
Jan 26, 2025 89
አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2017(ኢዜአ)፦ ዜጎች የጎዳና ላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማጎልበት ራሳቸውን ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ሊጠብቁ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ አሳሰቡ። የጤና ሚኒስቴር ከአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጋር በመተባበር ያዘጋጁት "የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለጤናማ እናትነት" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተካሂዷል። በመርሀ ግብሩ የጤና የሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና ወጣቶች ተሳትፈዋል። የእናትነት ወርን ምክንያት በማድረግ ዛሬ የተካሄደው ስፖርታዊ እንቅስቃሴው ከቶታል ሶስት ቁጥር ማዞሪያ እስከ አለርት ኮምፕሬሄንሲቭ ሆስፒታል የእግር ጉዞ እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተደርጓል። ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በአካል ብቃት የዳበረ ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር መንግሥት በትኩረት እየሰራ ነው። ማህበረሰቡን ያሳተፈ የአካል ብቃት እንቅስቃሴም የዚህ አካል መሆኑን ጠቁመው፤ እናቶች ጤናቸውን በአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንዲያጎለብቱ ጠይቀዋል። ዜጎች የጎዳና ላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማጎልበት ራሳቸውን ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች ሊጠብቁ ይገባልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም