ዓለም አቀፍ ዜናዎች - ኢዜአ አማርኛ
ዓለም አቀፍ ዜናዎች
የቀድሞው ሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ የ11 ዓመት እስራት ተፈረደባቸው
Jan 30, 2025 67
አዲስ አበባ፤ ጥር 22/2017(ኢዜአ)፦ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ በሙስና በመደለል ከግብፅ መንግስት ጉቦ የተቀበሉት አሜሪካዊው የቀድሞው የኒው ጀርዚ ሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ የ11 ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል። በኒው ዮርክ በ12 ዳኞች የተሰየመው ችሎት የፍርድ ውሳኔውን ትናንት ማስተላለፉን የአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ኤንቢሲ ዘግቧል። ችሎቱ ከዚህ ቀደም የ71 ዓመቱን የሕግ ባለሙያና ፖለቲከኛ በ16ቱም የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ ብሏቸዋል። የአሜሪካ ፌደራል ዐቃቤ ሕጎች የቀድሞውን ሴናተር ጉቦ ተቀብለው የግብጽ ወኪል ሆኖ በመስራት፣ ፍትሕ እንዲዛባ በማድረግና የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወንጀል መክሰሳቸው ይታወቃል። ዐቃቤ ሕጉ ሜኔንዴዝ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ በነበሩበት ወቅት የግብጽን ፍላጎት በማንጸባረቅ፣ ለዚህም ከግብጽ መንግስት ገንዘብ ማግኘታቸው በሰነድና በሰው ማስረጃ አረጋግጧል። የቀድሞው ሴናተር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተገናኘ በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደረግ በኒው ጄርሲ በንግድ ስራ ላይ ከተሰማሩ 3 የግብጽ ሰዎች እጅ ወርቅ እና ጥሬ ገንዘብ ጉቦ ተቀብለዋል። ይህም ሴናተሩ ራሳቸውን ለግብጽ መንግሥት ወኪል አድርገው በመቆም ሰርተዋል የሚል ክስ ሲቀርብባቸው እንደነበረ ይታወቃል። በዚህም በዘረፋ፣ ጉቦ በመቀበል፣ ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም፣ በሴራ፣ ፍትህን በማደናቀፍና መሰል 16 ወንጀሎች ላይ ተሳትፎ ማድረጋቸው ተገልጿል። በ16 የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ የተባሉት ሜኔንዴዝ የግብፅ መንግስት በሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት የአሜሪካ መንግስት ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ረድተዋል የሚል ክስ እንደቀረባበቸውም እንዲሁ። ሜኔንዴዝ የውጪ መንግስታትን ፍላጎት ለማስፈጸም ከተቀበሏቸው ስጦታዎች መካከል 100 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ወርቅና ቅንጡ መርሰዲስ መኪና የተጠቀሱ ሲሆን፣ በመኖሪያ ቤታቸውም 480 ሺህ ዶላር ጥሬ ገንዘብ በቤታቸው መገኘቱን የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ከዚህ ቀደም በስፋት ዘግበውታል። የቀድሞው ሴናተር ከግብጽ የንግድ ባለቤቶች ጋር የጥቅም ትስስር እንደነበራቸው ተጠቁሟል። በክሳቸው ላይ ከግብጽ በተጨማሪ ከሌሎች የውጭ መንግስታት ጉቦ መቀበላቸው በምርምራ እንደተረጋገጠም ተመላክቷል። እ.አ.አ በ2021 የ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤች አር 6600 ረቂቅ ሕግ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ (ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው የኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2022’ ወይም ‘ኤስ.3199’ የተዘጋጀው በ70 ዓመቱ ፖለቲከኛና የሕግ ባለሙያ ቦብ ሜኔንዴዝ ዋና አርቃቂነት ነው። በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ረቂቅ ሕጎቹ በሕግ አውጪው አካል ድምጽ ተሰጥቶባቸው እንዳይጸድቁ ለማድረግ ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላትን በማናገር፣ደብዳቤ በመጻፍ፣ፊርማ በማሰባሰብና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ በማድረግ ጥረት አድርገዋል። ሕጉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት የሚጎዳና ሉዓላዊነቷን የሚጥስ እንደነበር በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገለጽ ቆይቷል። እነዚህ ሕጎች እንዲፀድቁ ግብጽ ግፊት ስታደርግ እንደነበር ይታወቃል።
አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት የመውጣቷን ውሳኔ ማጤን አለባት - የአፍሪካ ህብረት
Jan 22, 2025 169
አዲስ አበባ፤ ጥር 14/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት የመውጣት ውሳኔዋን እንድታጤነው ጠይቀዋል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጉዳዩን አስመልክተው መግለጫ አውጥተዋል። በመግለጫቸውም አሜሪካ ከድርጅቱ አባልነት ለመውጣት መፈለጓ እንዳሳዘናቸው ሙሳ ፋኪ ገልጸዋል። ውሳኔውን መለስ ብሎ በማጤን በአባልነቷ ትቀጥላለች የሚል ተስፋ እንዳላቸውም አስታውቀዋል። አሜሪካ የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ማዕከል(አፍሪካ ሲዲሲ) መስረታ ላይ ቀደምት እና ጠንካራ ደጋፊ ነበረች ሲሉም በመግለጫቸው አስታውሰዋል፡፡ አሁን ላይ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዓለም አቀፉን የህብረተሰብ ጤና ደህንነት እንደ አንድ የጋራ ጥቅም የማረጋገጥ ተልዕኮውን ለመወጣት በዓለም ጤና ድርጅት ላይ ጥገኛ መሆኑን የገለፀው ህብረቱ፤ የድርጅቱ ቁልፍ መስራች አባል የሆነችው አሜሪካ ከተቋሙ የመውጣት ውሳኔዋን በድጋሚ እንድታጤነው ጠይቋል።
26ኛውን የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤን ኢትዮጵያ ታዘጋጃለች - ግብርና ሚኒስቴር
Jan 15, 2025 183
አዲስ አበባ፤ ጥር 7/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ 26ኛውን የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤ ልታስተናግድ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ። የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት ጉባኤ በየዓመቱ በግንቦት ወር በፈረንሳይ ፓሪስ የሚካሄድ ሲሆን በየሁለት ዓመቱ ደግሞ በየአህጉራቱ እንደሚካሄድ ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ በአፍሪካ ደረጃ 25ኛው ጉባኤ እአአ በ2023 ቦትስዋና ያስተናገደች ሲሆን 26ኛውን ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ መመረጧንም አስታውቋል። ጉባኤው "የእንስሳት ጤና ለምግብና ስነ-ምግብ ዋስትና መረጋገጥ እና ለሕብረተሰብ ጤና" በሚል መሪ ሀሳብ ከጥር 27 እስከ 30/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡ ለጉባኤው መሳካት ከዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት ዋናው ጽህፈት ቤት፣ የአፍሪካ እና የምስራቅ አፍሪካ ተወካዮች ጋር የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች ሲደረጉ መቆየታቸውም ተገልጿል። የግብርና ሚኒስቴርም ግብረ-ሃይል በማቋቋም ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡ በጉባኤው ከየአፍካ ሀገራት የጤና ኃላፊዎችና ቋሚ ተወካዮች፣ ከዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት፣ በየአህጉሩ ያሉ የእንስሳት ጤና አመራሮች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የልማት አጋሮች፣ የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች እንደሚታደሙም ተጠቁሟል። የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ(ዶ/ር) በጉባኤው በአፍሪካ የእንስሳት ጤና አገልግሎት፣ ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን መቆጣጠርና መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ብሎም ከበሽታ ነጻ የሆነ አህጉር ለመፍጠር የሚረዱ ውይይቶች ይደረጋሉ ብለዋል። በጉባኤው በእንስሳት ጤናና ልማት፣ በምግብና ስነ-ምግብ ዙሪያ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚገኙና የተለያዩ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉበት ገልጸዋል። በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እየተሰሩ ያሉ እንደ ዝርያ ማሻሻል፣ መኖ፣ የእንስሳት ጤና እና የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ በስፋት ውይይት ይደረግባቸዋል፤ አቅጣጫዎች ይቀመጡበታል ሲሉም ተናግረዋል። የእንስሳት ጤና በንጥረ ነገር የበለጸገ ምግብ ለማምረት እንደሚረዳ፣ መቀንጨርን ከመከላከል አንጻር የእንስሳት ጤና ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳለውም የምናይበት መድረክ ነው ሲሉም ገልጸዋል። ጉባኤው ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራትና በአህጉር ደረጃ ካሉ ሀገራት ጋር ድንበር ዘለል የእንስሳት በሽታዎችን ለመቆጣጠር፣ የገበያ ተደራሽነትን ለማስፋት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋልም ብለዋል። ሀገራት ያላቸውን የእንስሳት በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስትራቴጂና ተሞክሮ፣ ኢትዮጵያም በእንስሳት ጤና፣ መሰረተ ልማት እና ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን ለዓለም የምታስተዋውቅበት፣ ልምድ የምንጋራበት መድረክ ነው ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል። ከመቶ ዓመት የዘለለ የእንስሳት ጤና አገልግሎትና የምርምር ተቋማት፣ በእንስሳት ጤና ላይ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ፣ ክትባትና መድሃኒት የሚያመርቱ፣ በእንስሳት ጤና የሰው ሃይል የሚያፈሩ ተቋማት መኖራቸው መልካም አጋጣሚዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የሚካሄደው የዓለም የእንስሳት ጤና ድርጅት የአፍሪካ ጉባኤ የእንስሳት ጤና እንዲጠበቅ ብሎም ዘርፉ እንዲነቃቃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ማለታቸውም በመረጃው ተመላክቷል።
አፍሪካ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ማሳየት ችላለች
Jan 3, 2025 261
አዲስ አበባ፤ ታኅሳሥ 25/2017 (ኢዜአ) አፍሪካ በተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2024 የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ማሳየቷ ተገለፀ። አሕጉሪቱ የወሰደቻቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ደግሞ ለተገኘው ጥንካሬ በምክንያት ተነስተዋል። የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ያወጡት ትንበያ እንዳመለከተው አፍሪካ በዓመቱ የ 3 ነጥብ 6 በመቶ ዕድገት ታስመዘግባለች። እንዲያም ሆኖ የዋጋ ግሽበት እና የብድር ዕዳ መጨመር ዋነኛ የሕጉሪቱ ፈተና ሆነው መቀጠላቸውን የአፍሪካ ቢዝነስ ዘገባ አመልክቷል።
የአሜሪካ 39ኛ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር በ100 ዓመታቸው አረፉ
Dec 30, 2024 283
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 21/2017 (ኢዜአ)፡- የአሜሪካ 39ኛው ፕሬዝዳንት የነበሩት ጂሚ ካርተር በ100 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የቀድሞ ፕሬዝዳንቱ በመጨረሻው ጊዜያቸው በፔሊንስ ጆርጂያ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው “በቤተሰቦቻቸው ተከበው ነበር” ሲል ካርተር ሴንተር በሰጠው መግለጫ አስታውቋል። ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ካርተርን “ውድ ጓደኛ” እና “ልዩ መሪ” ሲሉ የተሰማቸውን ሀዘን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል። ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው አሜሪካውያን ለቀድሞው ፕሬዝዳንት “የምስጋና እዳ አለባቸው” ብለዋል። የአሜሪካ መንግሥት የቀድሞ ፕሬዝዳንቱን ሥርዓተ ቀብር ለመፈጸም ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ የሲ.ኤን.ኤን ዘገባ አመልክቷል። የቀድሞ ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር ባለቤት ሮዛሊን ካርተር እ.ኤ.አ. በ2023 ወርሃ ኅዳር በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሁለቱ ጥንዶች ለ75 ዓመታት አብረው በትዳር አብረው ኖረዋል። ካርተር እ.ኤ.አ. ከ1977 እስከ 1981 አሜሪካን በፕሬዝዳንትነት መርተዋል። ፕሬዝዳንት ካርተር እ.ኤ.አ. በ1980 በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የካሊፎርኒያ ገዢ በነበሩት ሮናልድ ሬገን ሲሸነፉ የካርተር ማእከልን እ.ኤ.አ. በ1982 አቋቁመው ወደ በጎ አድራጎት ተግባር ተሰማርተው ነበር። የካርተር ማእከልም ከኢትዮጵያ ጋር በሽታን በከላከልና በመቆጣጠር፣ የምግብ ምርትን በማሳደግ፣ ግጭትን በማስወገድና በምርጫ ታዛቢነት በመሳተፍ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ነበረው።
ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተሸፍኗል- ሚኒስቴሩ
Dec 24, 2024 277
ደሴ፤ ታኅሣሥ 15/2017 (ኢዜአ)፦ በአገር አቀፍ ደረጃ ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት መሸፈኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) ገለጹ፡፡ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር)ን ጨምሮ ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ተጀምሯል። ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ወቅት እንዳሉት የበጋ መስኖ ስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ የዜጎችን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ምርት በስፋት ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ነው፡፡ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ትኩረት መስጠቱን ጠቁመው፤ በዘንድሮው የበጋ ወራት ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ በስንዴ ለማልማት እየተሰራ ይገኛል፡፡ እስካሁን በተደረገ እንቅስቃሴም ከ2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር የሚበልጥ መሬት በስንዴ ዘር መሸፈን እንደተቻለ ነው የተናገሩት። ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎች ግብዓቶችን በበቂ መጠን እያቀረበ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የአማራ ክልል ገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና ግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም 254 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት ከ9 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ገልፀዋል፡፡ እስካሁን ከ120 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቁመዋል። በክልሉ በተሻሻለ አሰራር ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ በቂ ምርት ለገበያ እንዲቀርብ ጭምር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ህብረት ጉባዔ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለመገንባት ዝግጅት አድርገናል -በጎ ፍቃደኞች
Dec 22, 2024 291
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 13/2017(ኢዜአ)፦በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለመገንባት ዝግጁ መሆናቸውን በጎ ፍቃደኞች ገለጹ። ኢትዮጵያ 38ኛውን የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰለጠነ የሰው ኃይል በመታገዝ በብቃት ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት ማድረጓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል። ኢትዮጵያ የህብረቱ መቀመጫና የአፍሪካ መዲና እንደመሆኗ ጉባኤውን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ በሁሉም መስክ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቋም ተገልጿል። በጉባኤው ላይ የሚሳተፉ እንግዶችን ለማስተናገድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዕጩና ነባር ዲፕሎማቶች እንዲሁም ለበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል። የስልጠናው ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ እየተገነባ ያለውን የአዲስ ዓለም አቀፍ የኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል እንዲሁም የኮሪደር ልማት ስራዎችንና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን ጎብኝተዋል። በጎ ፍቃደኛ ወጣት ምርትነሽ ካሳሁን ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ እድል በማግኘቴ ደስተኛ ነኝ ብላለች። በኢትዮጵያ የተፈጠረው ሠላምና መረጋጋት እንዲሁም ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለገጽታ ግንባታው ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግራለች። በጎ ፍቃደኛ ወጣት ባቻክ ኡጁሉ በበኩሉ በጉብኝቱ የተመለከተው የልማት እና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ነው ያስታወቀው። ያገኘሁት ዕድል ለአገሬ የሚጠበቅብኝን አስተዋጽኦ ለማበርከት መልካም አጋጣሚ ፈጥሮልኛል ብሏል፡፡ ከስልጠናው ባገኘሁት ዕውቀት በመታገዝ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ በሚጠበቀው ደረጃ ለማስተዋወቅ ቁርጠኛ ነኝ ሲልም አክሏል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮንፍረንስ፣ ሁነትና የመንግሥት ፕሮቶኮል ዳይሬክተር እሸቱ ለገሰ በበኩላቸው፥ በአፍሪካ ህብረት ጉባዔ ላይ የሚሳተፉ እንግዶች ኢትዮጵያ የደረሰችበትን ደረጃ እንዲገነዘቡ የሚያስችል አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ መከናወኑን አስታውቀዋል። በተለያዩ ቋንቋዎች የኢትዮጵያን ገጽታ የሚያስተዋውቁ በጎ ፍቃደኞች ስልጠና በመውሰድ ላይ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ዛሬ የተደረገው ጉብኝት ሰልጣኞች በቂ ግንዛቤ ጨብጠው አገራቸውን እንዲያስተዋውቁ ያለመ መሆኑን ነው የገለጹት። የውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በረከት ድሪባ በ38ኛው የህብረቱ ጉባኤ የሚሳተፉ እንግዶች የኢትዮጵያን ገጽታ በላቀ ደረጃ እንዲረዱ በቂ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል። በጎ ፍቃደኞቹ የውጭ ጉዳይ ዲፕሎማሲን ጨምሮ እንግዶችን ተቀብሎ በማስተናገድ ረገድ ልምድ ባላቸው አሰልጣኞች ግንዛቤ እንዲጨብጡ በመደረግ ላይ መሆኑን ነው ያስታወቁት። ኢትዮጵያ ከኮንፍረንስ ቱሪዝም ይበልጥ እንድትጠቀም የሰለጠነ የሰው ኃይል ወሳኝ በመሆኑ መሰል ስልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
በኬኒያ የተለያዩ አካባቢዎች እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ በርካቶችን ከቄያቸው አፈናቀለ
Dec 1, 2024 1362
አዲስ አበባ፤ህዳር 22/2017(ኢዜአ)፦በኬኒያ የተለያዩ አካባቢዎች እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ በርካቶችን ከቄያቸው ማፈናቀሉ ተገለጸ። የኬንያ መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ ተጨማሪ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። በኬኒያ የተለያዩ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ከባድ ዝናብ እየጣለ ነው። የአደጋ ምላሽ ቡድን አባላት በሚጥለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በደረሰው የጎርፍ አደጋ የተጎዱ ከ240 በላይ አባወራዎችን አደጋ ከደረሰበት ሥፍራ ማንሳት መጀመራቸውን የሀገር ውስጥና ብሔራዊ አስተዳደር ሚኒስቴር በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በሰጠው መግለጫ ማስታወቁን ዥንዋ ዘግቧል። ሚኒስቴሩ በቪክቶሪያ ሀይቅ ተፋሰስ እና በሰሜን ምዕራብ ክልሎች ከፍተኛ ዝናብ በመጣሉ የጎርፍ አደጋ መከሰቱን በመግለጫው አስታውቋል። "የአደጋ ምላሽ ቡድኑ ከብሔራዊ የመንግስት አስተዳደር ጋር በመተባበር በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ያለውን ሁኔታ በመከታተል ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ እየሰጡ ነው" ሲል ዘገባው አመልክቷል። በሳምንቱ መጨረሻ እርጥበት አዘል አውሎ ነፋሶች ይጠበቃል ሲል ያመለከተው ዘገባው፤ የሰሜን እና ምስራቃዊ ኬንያ እንዲሁም የባህር ዳርቻ እና የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የጎርፍ ማስጠንቀቂያዎች መሰጠታቸውንም አክሏል። ይሁን እንጂ በሚቀጥለው ሳምንት ዝናቡ ሊቀንስ የሚችልባቸው ሁኔታዎች እንደሚኖሩ የሚኒስቴሩን መግለጫ ጠቅሶ ዥንዋ አስታውቋል። ሚኒስቴሩ በተጨማሪም ሀይቅ ዳር በሆነችው ኪሱሙ 200 የሚጠጉ አባዎራዎች መጎዳታቸውን አመልክቶ፤ 100 ሄክታር ማሳ ላይ የተዘሩ ሰብሎች መውደማቸውን ጠቁሟል። "ለደህንነታቸው ሲባል ለጊዜው ወደ ሌላ ቦታ የሚዘዋወሩ የጎርፍ ተጋላጭ አካባቢ ነዋሪዎች የአደጋ ምላሽ ከሚሰጡ ቡድኖች ጋር እንዲተባበሩ ሚኒስቴሩ ማሳሰቡን" ዘገባው አመክቷል። 2024 መጀመሪያ ላይ የጣለው ያልተለመደ ዝናብ ኤልኒኖ ተብሎ ከሚጠራው የአየር ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ለአየር ንብረት ለውጥ በጣም ተጋላጭ በሆነችው በኬንያ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተሉን ዘገባው አስታውሷል። በኬኒያ በመጋቢት እና ሰኔ መካከል በጣለው ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ከ300 በላይ ሰዎችን ህይወት መቅጠፉን ያመለከተው ዘገባው፣ በዚህ ወቅት 188 ሰዎች ቆስለዋል፣ 38 የሚሆኑት ሌሎች ሰዎች ደግሞ ደብዛቸው መጥፈቱን ዘገባው ጠቁሟል። በነዚሁ ጊዚያት በጎርፉ ምክንያት ከ293 ሺህ 200 በላይ ሰዎች ተፈናቅለው ወደ 306 ሺህ 520 የሚጠጉ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ከብሔራዊ የአደጋ መከላከል ማእከል ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ዥንዋ ዘግቧል።
እየተባባሰ የመጣው የሶማሊያ ፖለቲካዊ ቀውስ
Nov 27, 2024 1184
አዲስ አበባ፤ ህዳር 18/2017(ኢዜአ)፦ በሶማሊያ ፓርላማ ዛሬ ከፍተኛ ብጥብጥ ተከስቷል። የሶማሊያ መንግስት አካሄድን የተቃወሙ የሀገሪቱ የፓርላማ አባላት ቁጣቸውን በፓርላማ ውስጥ ሲገልጹ ታይተዋል። የሶማሊያ ፓርላማ ባወጣው መግለጫ የሀገሪቱ መንግሥት የሶማሊያ ጦር አልሸባብን ከመዋጋት ይልቅ በጎሳ ክፍፍል እንዲወጠር በማድረግ የያዛቸውን ቦታዎች እንኳ እንዳያስተዳድር አድርጓል ብሏል። በሀገሪቱ ሙስና ስር እየሰደደ ከመምጣቱም ባሻገር መንግስት ጦሩን ለፖለቲካ ፍጆታ እየተጠቀመ መሆኑንም ነው ፓርላማው በመግለጫው ያስታወቀው። ይህም በሀገሪቱ የጎሳ ክፍፍል እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል። ከሶማሊያ ህገ መንግስት ባፈነገጠ መልኩ የሀገሪቱ መንግስት የክልላዊ አስተዳደሮችን መብቶች እየተጋፋ መሆኑንም እንዲሁ። የሶማሊያ መንግስት ሶማሊያውያንን በጎሳ ለመከፋፈል የሚያደርገው ሙከራ በአስቸኳይ እንዲቆምም ጠይቀዋል። የሀገሪቱ መንግስት ከመሰል አደገኛ አካሄዱ ካላቆመም ሶማሊያ የመፍረስ አደጋ እንደሚገጥማት የፓርላማ አባላቱ ባወጡት መግለጫ አስጠንቅቀዋል።
የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት ፎረም የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ዓላማን ለማሳካት የሚያስችል ነው - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)
Nov 10, 2024 1891
አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2017(ኢዜአ)፦ የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት ፎረም የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ዓላማን ለማሳካት የሚያስችል ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ። በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) የተመራ ልዑክ በሩሲያ-ሶቺ ከተማ በተካሄደው የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት ፎረም የሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ ተሳትፏል፡፡ ጉባዔው በሩሲያ እና አፍሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት ያጎላ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) በመድረኩ ገልጸዋል። የሩሲያ-አፍሪካ አጋርነት ፎረም የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ዓላማን ለማሳካት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ቁርጠኛ መሆኗን በመድረኩ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል። በአፍሪካ እና ሩሲያ መካከል በተለይም በውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እና ንግድ ዘርፎች ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ማጠናከር እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ የጋራ ተጠቃሚነትን ከፍ ለማድረግም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን ትብብር ማሳደግ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ምርታማነትን ማሳደግ፣ እንደ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም፣ ኢንዱስትሪን ማስፋት የአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን በመፍታት ረገድ ቁልፍ መስኮች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማሻሻያ ለማድረግ እና አፍሪካ በድርጅቱ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና እንድታገኝ ሩሲያ ድጋፍ ለማድረግ ያላትን ዝግጁነት ኢትዮጵያ በደስታ ትቀበለዋለችም ነው ያሉት፡፡ ሚኒስትሩ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከበርካታ የአፍሪካ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡
አገራት ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ ፍትሃዊ ዓለም ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት በጋራ ሊቆሙ ይገባል
Oct 24, 2024 2783
አዲስ አበባ፣ጥቅምት 14/2017( ኢዜአ)፦የመንግሥታቱ ድርጅት አባል አገራት ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ ፍትሃዊ ዓለም ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥሪ አቀረበ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀን የድርጅቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተከብሯል። በመርኃ-ግብሩ ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ መልዕክት የድርጅቱ ረዳት ዋና ፀሐፊ እና የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ዶክተር ራሚዝ አላክባሮቭ አስተላልፈዋል። ዋና ፀሐፊው በመልዕክታቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ከተመሠረተ አንስቶ ላለፉት 79 ዓመታት ለዓለም አቀፍ ችግሮች መፍትሔ በማበጀት የላቀ ሚናውን መወጣቱን አስታውሰዋል። የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር፣ የዓለም አቀፍ ሕግ እሴቶችና መርሆዎች በእያንዳንዱ ሰው ክብር እንዲሁም ሰብአዊ መብቶች ውስጥ ስለመሆኑ አንስተው፤ በቀጣይም ለዓለም ዘላቂ ሰላምና ሰብአዊ መብት መከበር ሁለገብ መፍትሔ ያስፈልጋል ብለዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት አባል አገራት ሁሉንም ተጠቃሚ ያደረገ ፍትሃዊ ዓለም ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት በጋራ እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል። የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የትምህርት ጉዳዮች አማካሪ ጋኦጋካላ ሌመንያኔ፤ የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አጋርነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልፀዋል። በተለይም በሰላምና ደህንነት፣ በዘላቂ ልማት እና ሰብአዊ መብቶች ዙሪያ እና ሌሎችም ጠንካራ ትብብር መፈጠሩን አንስተዋል። በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዳይሬክተር ጄኔራል ሰሙንጉስ ገብረሕይወት፤ ኢትዮጵያ በዓለም የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ትልቅ አስተዋጽዖ ማበርከቷንና አሁንም መቀጠሏን አንስተዋል። ኢትዮጵያ በሚሊየን የሚቆጠሩ ስደተኞችን በመቀበል እያስተናገደች ስለመሆኗ አንስተው በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሆና መመረጧም ይበልጥ ተቀራርባ ለመስራት የሚያግዛት መሆኑን ገልጸዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀን ድርጅቱ እ.አ.አ 1971 ባሳለፈው የውሳኔ ሀሳብ ቁጥር 2782 መሠረት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየዓመቱ ጥቅምት 24 ይከበራል። እለቱ እ.አ.አ 1945 የተቋቋመውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ምሥረታ በማሰብ የሚከበር ሲሆን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ አገራትና ተቋማት የመንግሥታቱን ድርጅት እሴቶች እንዲሁም ዓላማዎች በሚያስተዋውቁ ዝግጅቶች እና ተግባራት ይከበራል።
የሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ መጨረሻ
Oct 17, 2024 2019
በኒው ዮርክ በ12 ዳኞች የተሰየመው ችሎት የ70 ዓመቱ የሕግ ባለሙያ እና ፖለቲከኛ በ16ቱም የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ ብሏቸዋል። ለሁለት ወራት የቆየው የክስ ሂደት የሜኔንዴዝን የፖለቲካ ቆይታ እንዲያበቃ ማድረጉን የአሜሪካው የፖለቲካ ዲጂታል ጋዜጣ ፖለቲኮ ዘግቧል። የአሜሪካ ፌደራል ዐቃቤ ሕጎች የቀድሞውን ሴናተር ጉቦ ተቀብለው የግብጽ ወኪል ሆኖ በመስራት፣ ፍትሕ እንዲዛባ በማድረግ እና የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወንጀል ከሰዋል። የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ ሜኔንዴዝ የአሜሪካ ሴኔት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ በነበሩበት ወቅት የግብጽን ፍላጎት በማንጸባረቅ፣ ለዚህም ከግብጽ መንግስት ገንዘብ ማግኘታቸው በሰነድና በሰው ማስረጃ አረጋግጧል። የሴናተሩ ባለቤት የሆኑት ናዲኔ ሜኔንዴዝ እ.አ.አ. በማርች 2020 ገደማ ባለቤቷ ሴናተር ሜኔንዴዝ ከአንድ የግብጽ ጦር ጄኔራል ጋር እንዲገናኙ ፕሮግራም ማዘጋጀቷንና በፕሮግራሙ ላይም ሴናተሩ ከግብፅ ጄኔራል ጋር ተገናኝተው በወቅቱ ታላቁ የኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ በግብፅ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ይካሄድ ስለነበረው ድርድር መወያየታቸው የምርመራ መዝገቡ ያመለክታል። ግብጽ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይን ዋንኛ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋነኛ የትኩረት ማዕከል አድርጋ ስትሰራበት መቆየቷ መዝገቡ ያሳያል። ሴናተሩ ከግብፅ ጄኔራል ጋር በተገናኙ በቀጣዩ ወር ውስጥ (በኤፕሪል 2020 ወይም ገደማ)፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ላይ ለሚሳተፉት የአሜሪካ ግምጃ ቤት የቀድሞ ዋና ፀሐፊ ስቴቨን ሙንቺንና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደብዳቤ መጻፋቸውን ይገልጻል። በደብዳቤው ላይ ኢትዮጵያና ሱዳን በግድቡ ዙሪያ ያደርጉት የነበረው ድርድር መቋረጥ እንዳሳሰባቸው ለመግለጽ ደብዳቤውን መጻፋቸው ተመላክቷል ። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በሕዳሴ ግድቡ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሳድግ መጠየቃቸውን በምርመራ ሰነዱ ላይ ሰፍሯል። በ16 የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ የተባሉት ሜኔንዴዝ የግብፅ መንግስት በሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት የአሜሪካ መንግስት ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ረድተዋል የሚል ክስ እንደቀረባበቸውም የቢቢሲ መረጃ ያመለክታል። ሜኔንዴዝ የውጪ መንግስታትን ፍላጎት ለማስፈጸም ከተቀበሏቸው ስጦታዎች መካከል 100 ሺህ ዶላር የሚያወጣ ወርቅና ቅንጡ መርሰዲስ መኪና የተጠቀሱ ሲሆን፣ በመኖሪያ ቤታቸውም 480 ሺህ ዶላር ጥሬ ገንዘብ መገኘቱን ጠቁሟል። የቀድሞው ሴናተር ከግብጽ የንግድ ባለቤቶች ጋር የጥቅም ትስስር እንደነበራቸው ተጠቁሟል። በክሳቸው ላይ ከግብጽ በተጨማሪ ከሌሎች የውጭ መንግስታት ጉቦ መቀበላቸው በምርምራ እንደተረጋገጠም ተመላክቷል። ሴናተሩ ጥፋተኛ ከተባሉም በኋላ በሰጡት አስተያየት ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል የገባሁትን ቃለ መሐላ አላፈርስኩም ማለታቸው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በፍርድ ቤት ክርክር ሂደት ውስጥ የሜኔንዴዝ ጠበቆች ለጥፋቶቹ ሁሉ ተጠያቂ ሚስታቸው ናዲን ናት ሲሉ ይወቅሳሉ። የግል ጥቅሞችን ለማግኘት ጥፋቶቹን ፈጽማለች በማለትም ተከራክረዋል። ጥፋተኛ በተባሉባቸው ክሶች ምክንያት ከሰኔቱ እንዲሰናበቱ ግፊት በርትቶባቸው የነበሩት ሜኔንዴዝ ከስልጣናቸው መልቀቃቸው ይታወሳል። ሴናተሩ ጥፋተኛ በተባሉባቸው ወንጀሎች የቅጣት ውሳኔ ከተላለፈባቸው ለበርካታ ዓመታት በእስር ሊቆዩ እንደሚችሉ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን በመግለጽ ላይ ናቸው። በ2025 ለምን ያህል ጊዜ ይታሰራሉ? የሚለው ጉዳይ ምላሽ እንደሚያገኝ ተገልጿል። ሜኔንዴዝ እ.አ.አ በ2015 በፌደራል የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለው የነበረ ቢሆንም ዳኞች የፍርድ ውሳኔ ላይ ባለመድረሳቸው ክሳቸው ውድቅ እንዲሆን መደረጉ የሚታወስ ነው። እ.አ.አ በ2021 ቶም ማሊኖውስኪ፣ በያንግ ኪም፣ ግሪጎሪ ሚክስ ፣ ዴቪድ ሲሲሊን፣ ብራድ ሼርማንና ማይክል ማካውል ደጋፊነት የተዘጋጀው ‘ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ አክት’ ወይም ኤች አር 6600 ረቂቅ ሕግ መዘጋጀቱ ይታወቃል። ሕጉ በወቅቱ የኮንግረሱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ተወያይቶበት ለኮንግረሱ መርቶት ነበር። በወቅቱ የ‘ኤችአር 6600’ ተጓዳኝ ወይም አጋዥ (ኮምፓኒየን ቢል) የሆነው የኢትዮጵያ ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ ፕሮሞሽን አክት ኦፍ 2022’ ወይም ‘ኤስ.3199’ የተዘጋጀው በ70 ዓመቱ ፖለቲከኛና የሕግ ባለሙያ ቦብ ሜኔንዴዝ ዋና አርቃቂነት ነው። ሕጉ ሴኔቱ እ.አ.አ በ2022 ሊመለከታቸው በጊዜ ሰሌዳው ከያዛቸው ረቂቅ ሕጎች አንዱ ሆኖ እንዲካተት ተወስኖም ነበር። በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ረቂቅ ሕጎቹ በሕግ አውጪው አካል ድምጽ ተሰጥቶባቸው እንዳይጸድቁ ለማድረግ ሴናተሮችና የኮንግረስ አባላትን በማናገር፣ደብዳቤ በመጻፍ፣ፊርማ በማሰባሰብና በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ዘመቻ በማድረግ ጥረት አድርገዋል። ሕጉ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት የሚጎዳና ሉዓላዊነቷን የሚጥስ እንደነበር በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገለጽ ቆይቷል። እነዚህ ሕጎች እንዲፀድቁ ግብጽ ግፊት ስታደርግ እንደነበረም ይታወቃል። ሴናተሩ ከተከሰሱበት ወንጀል አንዱ ከግብጽ ጉቦ ተቀብለው በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ኢትዮጵያ ጫና እንዲደረግባት ማድረግ ይገኝበታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ለመጉዳት እየተንቀሳቀሰች ከምትገኘው ግብጽ በቀጣናው ትርምስ ለመፍጠር እየሰራች ትገኛለች። ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር ለማግኘት ከሶማሊላንድ ጋር ስምምነት መፈራረሟ ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ ግብጽ አላስፈላጊ የዲፕሎማሲ ትኩሳት ለመፍጠር እና የአገርን ስም የማጠልሸት ተግባር እየፈጸመች ትገኛለች። ግብጽ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና እያደረገች ያለው ያልተገባ እንቅስቃሴ ቀጣናውን ውጥረት ውስጥ የማስገባት እኩይ ዓላማ ያለው ነው። ኢትዮጵያ ግብጽ ወደ ቀጣናው የምትልካቸው የጦር መሳሪያዎች እንደ አልሻበብ ያሉ የሽብርተኛ ቡድኖች እጅ ሊወድቁ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላት በተደጋጋሚ ጊዜ ስትገልጽ ቆይታለች። ኢትዮጵያ የግብጽን ቀጣናውን የማተራመስ እና ሽብርተኝነትን የመደገፍ አካሄድ የቀጣናውን ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል ነው። ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት አስታውቃለች። የሶማሊያ መንግሥት ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ እንደሚገኝ መንግስት መግለጹ ይታወቃል። ኢትዮጵያ በቀጣናው የብሔራዊ ደህንነቷን አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሁሉ በአንክሮ እየተከታተለች ትገኛለች። ኢትዮጵያን የመጉዳት እና የአባይ ወንዝን እኔ ብቻ በብቸኝነት የመጠቀም አባዜ የተጠናወታት ግብጽ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን ከህዳሴ ግድቡ ግንባታ እና ከልማት ሕልሟ ልታስቆም አልቻለችም። ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ፍትሐዊነት እና እኩልነት በተሞላባት እና ዓለም አቀፍ ሕግን ባከበረ መልኩ የመጠቀም አቋምን በተደጋጋሚ ጊዜ ብታወሳውቅም ግብጽ ይሄን ጥሪ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ሉዓላዊ አገራት የተፈጥሮ ሀብታቸውን ለዜጎች ጠቀሜታ የማዋል ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ጽንሰ ሀሳብ ተቃርና ቆማለች። ግብጽ የቅኝ ግዛት ዘመን የትብብር ማዕቀፎችን መሰረት አድርጋ እኔ ብቻ ልጠቀም በሚል ኢ-ሚዛናዊ እሳቤ በውሃ ሀብት የመልማት ጥረቶች እውን እንዳይሆኑ እክል እየፈጠረች ትገኛለች። ግብጽ ኢትዮጵያ የዜጎቿን ሕይወት ለመቀየር የምታደርጋቸውን ጥረቶች ሙሉ ለሙሉ ውድቅ የሚያደርግ ሀሳብ ማንጸባረቋን በግልጽ ተቃውማ አቋሟን አሳውቃለች። ግብጽ ጊዜ ያለፈባቸውን የቆዩ ማዕቀፎች ተጠቅማ የናይል ወንዝን እኔ ብቻ ልቆጣጠር የሚለውን ተቀባይነት የሌለው ሀሳብ ትታ ዓለም አቀፍ የሕግ አሰራርና ሁሉን አሸናፊ የሚያደርግ የድርድር አማራጭን እንድትከትል ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ጊዜ ጥሪ ማቅረቧ ይታወቃል። ግብጽ በቅርቡ ወደ ትግበራ በገባው የናይል ትብብር ማዕቀፍ ስምምነት በማጽደቅ በቀጣናዊ ልማት እና ትብብር ገንቢና እንድትወጣም ጠይቃለች። ከተፋሰሱ አገራት ጋር ወደ ሰላማዊ የትብብር አማራጭና ውይይት ዳግም እንድትመልስም አሳስበለች። ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በቀጣናው በጋራ የመልማት እና በጋራ የማደግ ፍላጎቷን እውን ለማድረግ የጀመረችን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ተደማጭነት በማስፋት ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ጉልህ ስራዎች መከናወናቸውንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ አማራጭ የወደብ እና የባህር በር ለማግኘት የጀመረችው ጥረት እንደምትገፋበትም አመልክተዋል።
ኤጀንሲው ታዳሽ ኃይልን በሦስት እጥፍ ለማሳደግ እየሰራ ነው
Sep 24, 2024 3094
አዲስ አበባ ፤መስከረም 14/2017 (ኢዜአ)፦ዓለም አቀፍ ኢነርጂ ኤጀንሲ ታዳሽ ኃይልን በሦስት እጥፍ ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የሮይተርስ ዘገባ አመለከተ ። የኤጀንሲው ሪፖርት እ.ኤ.አ. በ2030 ዓለም አቀፍ የታዳሽ ኃይልን በሦስት እጥፍ በማሳደግ የነዳጅ ፍጆታን በመቀነስ የአየር ንብረት ለዉጥ ግቡን ማሳካት እንደሚቻል አመልክቷል። በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እርምጃ ለመውሰድ በኒውዮርክ የአየር ንብረት ሳምንት ላይ ለታደሙ ከመንግሥት እና ከንግዱ ዘረፍ ለተውጣጡ ኃላፊዎች ሪፖርት ማቅረቡን ዘግቧል። በዱባይ አምና በተካሄደው COP 28 የአየር ንብረት ጉባኤ 200 የሚጠጉ ሀገራት እንደ የንፋስና ፀሀይ ያሉ የታዳሽ ኃይሎችን በሦስት እጥፍ በማሳደግ በ2050 ዜሮ የካርበን ልቀት ላይ ለመድረስ መስማማታቸውን ዘገባው አስታውሷል። አገራት በ2030 ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ በመተግበር ጥቅም ላይ ለማዋል 25 ሚሊዮን ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ መስመሮችን ለመገንባት እና ለማዘመን የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም አንስቷል። በዚህም በ2030 ዓለም 1 ሺህ 500 ጊጋዋት የኃይል ማከማቻ አቅም እንደሚያስፈልጋት ሮይተርስ በዘገባው ጠቅሷል። አገራት በCOP 28 የኃይል አጠቃቀምን የሚረዱትን የኃይል ቆጣቢ እርምጃዎችን በእጥፍ ለማሳደግ ቃል የገቡ ሲሆን፤ዉጤታማነቱ መንግሥታት ለፖሊሲዎቻቸዉ ቅድሚያ እንዲሰጡ መጠየቃቸውን አመላክቷል። በፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት መሰረት የተቀመጡ ግቦችን ለማሳካት ሀገራት ታዳሽና የኢነርጂ ውጤታማነት ግቦችን በአገራዊ ዕቅዳቸው ውስጥ ማካተት አለባቸው ሲል ዓለም አቀፉ ኢነርጂ ኤጀንሲ ማሳሰቡን ዘገባው ያመለክታል። ከዓለም አቀፉ የኢነርጂ ዘርፍ የተለቀቀው የልቀት መጠን ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱንም ዘገባው አንስቷል። የታዳሽ ኃይል አቅምን በሶስት እጥፍ ማሳደግና የኃይል አጠቃቀምን ለመቀነስ የኃይል ቆጣቢ እርምጃዎችን በእጥፍ ማሳደግ በአሥር ዓመታት መጨረሻ የዓለም ሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን በ10 ቢሊየን ሜትሪክ ቶን ሊቀንስ ይችላል ተብሎ ከሚጠበቀው ጋር ሲነጻጸር መሆኑን ሪፖርቱን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
የሱዳንን ግጭት ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ተጠየቀ
Sep 24, 2024 2774
አዲስ አበባ ፤መስከረም 14/2017 (ኢዜአ)፦የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ እና የአሜሪካ መሪዎች የሱዳንን ግጭት ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ እንዲወሰድ ማሳሰባቸውን ሱዳን ትሪቡን ከዋሽንግተን ዘግቧል። የሁለቱ አገራት ፕሬዘዳንቶች በሱዳን ጉዳይ ላይ ትናንት ውይይት ማድረጋቸውን ዘገባው ጠቁሟል። የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ፕሬዘዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ እና የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ከውይይታቸው በኋላ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። መሪዎቹ በመግለጫቸው በሰላማዊ ሰዎች ላይ እደረሰ ባለው መፈናቀል ረሀብና ጭካኔ የተሞላበት ግጭት ቆሞ ዘላቂ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ማለታችውን ዘግቧል። "ለሱዳን ግጭት ምወታደራዊ መፍትሄ የለም" ያለው መግለጫው ጦርነቱ ባስቸኳይ እንዲቆም፣ ወደ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲመለስ እና በሲቪል የሚመራ አስተዳደር እንዲሸጋገር ጥሪ አቅርቧል። በዳርፉር እየተባባሰ የመጣው ብጥብጥም እንዳሳሰባቸው መሪዎቹ መግለጻቸውን ዘገባው አመልክቷል። ሁለቱም ወገኖች ግጭት አቁመው ወደ ድርድር የማይመጡና የዓለም አቀፉን የሰብዓዊ ህግ የማያከብሩ ከሆነ የተለያዩ ማዕቀቦችን ከመጣል ጀምሮ በዘር ማጥፋት ወንጀል በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀል ተጠያቂ እንዲሆኑም ጠይቀዋል። ሰላማዊ ዜጎችን በተለይም ሴቶችን፣ ህጻናትን እና አረጋውያንን መጠበቅ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑንም አዘስገንዝበዋል። በግጭት መስመሮች የእርዳታ አቅርቦትን ለማመቻቸት ሰብዓዊ ፋታዎች እንዲፈጠሩ የሁለቱ አገራት መሪዎች መጠየቃቸውን ሱዳን ትሪቡን በዘገባው አመልክቷል።
የዓለም ፋይናንስ አሰራር ጥልቅ ማሻሻያ ያስፈልገዋል - አንቶኒዮ ጉተሬዝ
Sep 23, 2024 1854
አዲስ አበባ፤ መስከረም 13/2017 (ኢዜአ):- የዓለም ፋይናንስ አሰራር ጥልቀት ያለው ማሻሻያ እንደሚያስፈልገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ። የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ነባራዊውን ዓለም የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት ብለዋል። ከ79ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ጎን ለጎን የዋና ፀሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢኒሼቲቭ የሆነው የመጪው ጊዜ ጉባዔ (Summit of the Future) በኒውዮርክ እየተካሄደ ይገኛል። የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ አሰራር የእይታ ለውጥ ማምጣት፣ የተገቡ ቃልኪዳኖችን መፈጸምና የረጅም ጊዜ ችግሮችን መፍታት ላይ የጉባዔው ዋንኛ ማጠንጠኛ ጉዳዮች ናቸው። የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጉባኤው ላይ የተሰበሰብነው የባለብዝሃ ወገን ስርዓትን ከተጋረጠበት የሕልውና አደጋ ለመታደግ ነው ብለዋል። ጉባኤው ዓለም አቀፍ ተቋማት የተመድ ቻርተር እሴቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ ይበልጥ ሕጋዊ፣ ፍትሐዊና ውጤታማ መሆን የሚያስችላቸው ጥልቅ ማሻሻያዎች በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ሀሳቦችን እንዲያነሳ ጠይቀዋል። የ21ኛው ክፍለ ዘመን ፈተናዎች የ21 ክፍለ ዘመንን መፍትሔዎች ይሻሉ ያሉት ዋና ፀሐፊው ሁሉን አሳታፊና ለሰብዓዊነት ቅድሚያ የሚሰጡ ማዕቀፎች እንደሚያስፈልጉ አመልክተዋል። በበርካታ ውስብስብና አሳሳቢ ፈተናዎችና ስጋቶች እያለፈች የምትገኘው ዓለም የገጠሟት ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች በዘላቂ ልማት ላይ አሉታዊ ተጽእኖዎችን ማሳደሩን ነው የገለጹት። ይህም በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት እድገት ላይ ጋሬጣ እንደሆነ ተናግረው ይህ ፍትሐዊ ካልሆነው የፋይናንስ አቅርቦት ጋር ተዳምሮ ተደራራቢ ጫናዎችን መፍጠሩን አመልክተዋል። በቅኝ ግዛት ዘመን የተዘረጋው የዓለም የፋይናንስ ስርዓት የአገራቱን የዘላቂ ልማት ትልሞችና ፈተናዎች ባማከለና ከወቅቱን የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታ ጋር በተጣጣመ መልኩ ጥልቅ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የፋይናንስ ስርዓቱን ለመለወጥ የተጀመሩ ተስፋ ሰጪ ስራዎች ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም አጽንኦት ሰጥተዋል። የተመድ የጸጥታው ምክር ቤትም ሁለን አሳታፊና አካታች ያደረገ ፍትሐዊ ለውጥ ማድረግ እንዳለበት ገልጸው የአፍሪካ፣ እስያ፣ ፓሲፊክና ላቲን አሜሪካ በምክር ቤቱ ውክልና ሊያገኙ ይገባል ነው ያሉት። ዓለም አቀፍ የትብብር መድረክን ፍትሃዊ፣ አሳታፊና ትስስርን አጎልባች እንዲሆን ቁርጠኝነት የተሞላባቸውን እርምጃዎች መውሰድ እንደሚያስፈልግ አክለዋል። ትናንት በመጪው ዘመን ጉባዔ መክፈቻ ቀን አገራት ዓለም አቀፍ የዲጂታል ማዕቀፍና የቀጣይ ትውልድ የመርሆዎች መግለጫን ያካተተ ታሪካዊ የተባለለት ‘Pact for the future’ (የቀጣይ ዘመን ስምምነት) ማጽደቃቸው የሚታወስ ነው። ጉባዔው የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ዛሬ ማምሻውን ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በአፍሪካ በዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የተጠረጠሩ ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች ተለዩ
Sep 16, 2024 1581
አዲስ አበባ፤ መስከረም 6/2017(ኢዜአ)፡- የዓለም ጤና ድርጅት ከዘንድሮው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ በዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የተጠረጠሩ ከ25 ሺህ በላይ ሰዎች በሽታ መለየታቸውን አስታወቀ። የአፍሪካ በሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲሲ) በበኩሉ ለዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ምላሽ 600 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያሰባስብ የስፑትኒክ ዘገባ አመለክቷል። ከጥር 1 እስከ መስከረም 8/ 2024 ድረስ ከ720 በላይ በበሽታው ምክንያት ሞት መመዝገቡን ተገልጿል። እንደ ዓለም ጤና ድርጅት እስከ መስከረም 8/2024 በአፍሪካ ከበሽታው ጋር የተያያዙ 5ሺህ 789 የበሽታ ምልክቶች በቤተ ሙከራ ሲረጋገጥ 32 ሰዎች መሞታቸውን ዘገባው አመልክቷል። በሽታው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፤ በአገሪቱ ከበሽታው ጋር በተያያዘ ከተጠረጠሩ 21 ሺህ 835 ጉዳዮች 717 ሰዎች መሞታቸውን በዘገባው ተጠቅሷል። የዓለም ጤና ድርጅት የዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍልና በአጎራባች አገሮች የሚያደርሰውን ጉዳት ከፍ አድርጎ መገምገሙን አመላክቷል። ድርጅቱ የወረርሽኙ ጉዳት በናይጄሪያና በሌሎች የምዕራብ፣ የመካከለኛው እና የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት መጠነኛ እንደሆነ መታሰቡንና በአፍሪካ እና በተቀረው ዓለም ስላለው ሁኔታ ተመሳሳይ ግምገማ መስጠቱንም በዘገባው ተገልጿል። እንደ ስፑትኒክ ዘገባ በአጠቃላይ ከጥር 1/2022 እስከ ሐምሌ 31/2024 በዓለም ከዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ 103ሺህ 48 የተረጋገጡ ጉዳዮች፤ 229 ሞትን ጨምሮ በ121 አገራት ተመዝግበዋል። የአፍሪካ በሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) በበኩሉ ለዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ምላሽ 600 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያሰባስብ ገልጿል። የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር ዣን ካሴያን ገንዘቡ ከአፍሪካ ህብረት ሀገራት፣ ከልማት አጋሮች፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ከግሉ ዘርፍ ለማሰባሰብ እንደታቀደ አመልክተዋል። እንደ ጋቪ እና ዘ ፓንዴሚክ ፈንድ ካሉ ድርጅቶች ጋር ውይይት እየተካሄደ መሆኑንና ፤ የቴክኖሎጂ ዝውውሮች የክትባት ወጪዎችን 90በመቶ ሊቀንስ እንደሚችል ዳይሬክተሩ መግለጻቸውን ዘገባው አመልክቷል። በተጨማሪም የምዕራቡ ዓለም ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ትምህርት መውሰዱንና በዝንጀሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝም አፍሪካን እንዳልተዉ ማሳየት እንደሚጠበቅበት ማስገንዘባቸውን አንስቷል። ገንዘብ የማሰባሰብ ጥረት የዓለም ጤና ድርጅት ባለፈው ወር በዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ ዓለም አቀፍ ድንገተኛ የጤና አደጋ መሆኑን ካወጀ በኋላ የመጣ መሆኑን በዘገበው ተጠቅሷል።
አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት አሜሪካ ዛሬ ድጋፏን ታሳውቃለች
Sep 12, 2024 949
አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2017 (ኢዜአ)፡- አፍሪካ በተባበሩት መንግስትት የጸጥታው ምክር ቤት ሁለት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት አሜሪካ ድጋፏን ኒውዮርክ በሚገኘው የድርጅቱ የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት ዛሬ እንደምታሳውቅ በድርጅቱ የሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ ገለጹ። ከአፍሪካ በተጨማሪ አንድ ተዘዋዋሪ መቀመጫ ታዳጊ የደሴት (Highlands) ሀገራት እንዲኖራቸው አሜሪካ እንደምትደግፍ አምባሳደሯ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። አገራቸው አፍሪካ በጸጥታ ምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫዎች እንዲኖራት ድጋፍ ማድረጓ ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት በላቀ ሁኔታ እንደሚያሳድገውም አምባሳደሯ ጠቁመዋል። የአፍሪካ ሕዝብ ከቢሊዮን በላይ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ. በ1946 የተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ለአኅጉሪቷ ቋሚ መቀመጫ ሳይሰጣት፣ ከ70 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ ምክር ቤቱ 15 አባላት ያሉት ሲሆን፤ ቋሚ መቀመጫ የሰጠው ግን ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው አምስቱ ሀገራት ለአሜሪካ፣ ለቻይና፣ ለፈረንሳይ፣ ለሩሲያና እንግሊዝ መሆኑን ጠቅሶ፣ድርድሮችን ለማበረታታት፣ ማዕቀብ ለመጣል፣ የሰላም አስከባሪ ማሰማራትን ጨምሮ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ለማድረግ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን አለው። በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት ነፃ ወጥተው በሂደት ተመድን ቢቀላቀሉም፣ ፀጥታው ምክር ቤት ካሉት አሥር ቋሚ ያልሆኑ መቀመጫዎች ለአፍሪካ የሰጠው ሦስት ተቀያያሪ መቀመጫዎችን እንደሆነም ዘገባው አመልክቷል፡፡ በግጭት የሚታመሱ አገሮች ያሉባት አፍሪካ፣ ድምጿ በቋሚነት እንዲሰማ፣ በሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ጉልህ ሚና እንድትጫወት ዛሬ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት፣ ለዚህም ተመድ የፀጥታውን ምክር ቤት መልሶ እንዲያዋቅር ስትወተውት ቆይታለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2010 አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የአኅጉሪቱ መሪዎች ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ ጥያቄያቸው እስካሁን መልስ አላገኘም፡፡ ሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2016 ዓ.ም የተመድ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በነበራቸው ውይይትም፣ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ የፀጥታው ምክር ቤት ያረጀ አወቃቀሩን መልሶ እንዲያዋቅርና አፍሪካን በቋሚ አባልነት እንዲያካትት በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ “ዓለም እየተለዋወጠች ባለችበት ወቅት አፍሪካ የምክር ቤት ቋሚ አባል መሆን አለባት፣ እስካሁን አለመወከሏም ትክክል አይደለም፤” ሲሉ የተናገሩት ጉተሬስ፣ በምክር ቤቱ ያለው ስብጥር አሁን እየተቀየረ ካለው ዓለም ጋር ተመጣጥኖ መሄድ አቅቶታል ብለዋል፡፡ “ከአንድ ቢሊዮን በላይ ሕዝብ የያዘን አኅጉር በቋሚነት ያላካተተ የሰላምና ፀጥታ አካል አንቀበልም፣ ሰላምና ደኅንነትን በተመለከተ የአፍሪካን አመለካከት ዋጋ የሚያሳጣ አንቀበልም” ሲሉም ለጉባዔው አሳስበዋል፡፡ አፍሪካ ዛሬ በምክር ቤቱ ሁለት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ድጋፏን በአምባሳደሯ በኩል የምታሳውቀው አሜሪካ አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ብትደግፍም ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት እንዲኖራት እንደማትፈቅድም ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ መናገራቸውን ዘገባው አመላክቷል። አፍሪካ በምክር ቤቱ ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት አሜሪካ መደገፏ አፍሪካ በምክር ቤቱ በቋሚነት ትወከል የሚለውን ዘመቻ እንደሚያግዘው አምባሰደሯ አስረድተዋል። እንደ ሮይተርስ ዘገባ ምክር ቤቱ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ካላቸው ከአምስቱ ቋሚ አገሮች በተጨማሪ አሥር መቀመጫዎችን ለየቀጣናው ቢሰጥም፤ ሀገራቱ ቋሚ መቀመጫ የላቸውም፡፡ በምክር ቤቱ አፍሪካ ሦስት፣ እስያ ፖስፊክ ሁለት፣ ላቲን አሜሪካና ካሪቢያን ሁለት፣ ምዕራብ አውሮፓና ሌሎች ግዛቶች ሁለት እንዲሁም ምሥራቅ አውሮፓ አንድ መቀመጫ እንዳላቸው በመረጃው ተጠቅሷል።
አብዱልመጂድ ቴቡኔ በድጋሚ የአልጄሪያ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ
Sep 9, 2024 1414
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 4/2016 (ኢዜአ)፦ አብዱልመጂድ ቴቡኔ የአልጄሪያ ፕሬዝዳንት ሆነው በድጋሚ ተመርጠዋል። በአልጄሪያ ትናንት በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የ78 ዓመቱ ፖለቲከኛ 95 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን የአገሪቷ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል። አብዴላሊ ሃሳኒ ቼሪፍ 3 በመቶ እና ዩሱፍ ኦውቺቼ 2 በመቶ ድምጽ ማግኘታቸውን ዘ ኢስት አፍሪካን እና አልጀዚራ ኮሚሽኑን ዋቢ አድርገው ያወጡት ዘገባ ያመለክታል። በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡ ከ24 ሚሊዮን በላይ ዜጎች መካከል 48 በመቶው ብቻ ድምጽ መስጠታቸው ተገልጿል። በምርጫው ላይ ከ800 ሺህ በላይ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ የአልጄሪያ ዳያስፖራዎች ድምጽ ሰጥተዋል። ውጤቱን ተከትሎ አብዱልመጂድ ቴቡኔ ለቀጣይ አምስት ዓመታት አልጄሪያን በመምራት ይቀጥላሉ። ቴቡኔ ከእ.አ.አ 2019 አንስቶ አልጄሪያን በፕሬዝዳንት እየመሩ እንደሚገኝ የዘ ኢስት አፍሪካን ዘገባ ያመለክታል።
ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲሰሩ የማሻሻያ ስራዎች ተጀምረዋል - አንቶኒዮ ጉተሬዝ
Sep 5, 2024 1589
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2016 (ኢዜአ)፡- የመንግስታቱ ድርጅት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲሰሩ የማሻሻያ ስራዎች መጀመሩን የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ገለጹ፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ50 የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የታደሙበት የቻይና-አፍሪካ የትብብር ጉባዔ ትናንት በቤጂንግ ተከፍቷል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የቻይናን ያልተቋረጠ ድጋፍ ታደንቃለች ብለዋል። በጉባኤው ላይ የተገኙት የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ከሲጂቲኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ አፍሪካ የቅኝ አገዛዝ ድርብ ተጠቂ መሆኗን ጠቅሰው ጉዳቱ የሚጀምረው ራሱ የቅኝ አገዛዝ ካደረሰባት ጫና መሆኑን አስታውቀዋል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተቋቋሙ ዓለም አቀፍ ተቋማት ያደረሱባት የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ሌላው ጫና መሆኑን ተናግረዋል። የቅኝ አገዛዙ ድርብ ጫና በፈጠረባቸው ፈተና በርካታ የአፍሪካ አገራት ህልውናቸውን በራሳቸው አቅም ማስቀጥል የማይችሉ እንደነበሩ ገልጸዋል። በዚህም አፍሪካ በዓለም አደባባይ በበቂ ሁኔታ መወከል አለመቻሏን በማንሳት ተግባሩን ነጥለን ካየነው በተለይም አህጉሪቱ በኢኮኖሚና በፋይናንስ ዘርፍ የደረሰባት መገለል በጣም አሳሳቢ መሆኑን ተናግረዋል። ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትን ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ለመሸፈን አለመፈለጋቸውና አገራቱ በተቋማቱ ውስጥ በሚፈለገው ልክ አለመወከላቸው ችግሩን አባብሶታል ብለዋል። ይሀንን ችግር ለመፍታት የመንግስታቱ ድርጅት ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን አሰራር ለማሻሻል ስራዎች መጀመሩን ጠቅሰዋል። ማሻሻያው በማደግ ላይ የሚገኙ አገራትን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲተገበር እየሰራን ነው ብለዋል። ቻይና ዘላቂነት ያለውን የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካትና የራሷን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ፍላጎት ለሟሟላት ከፍተኛ ኃላፊነት ወስዳ እየሰራች መሆኑን ዋና ፀሐፊው አስረድተዋል። የቻይና አፍሪካ ግንኙነት የደቡብ-ደቡብ ትብብርን የሚያንጸባርቅ መሆኑን በመጥቀስ ቻይና አፍሪካ የምትፈልገውን ኢንቨስትመንት በማቅረብ በኩል የሚጠበቅባትን ሚና እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል። አፍሪካ በመሰረተ ልማት፣ ትምህርትና ጤና ዘርፍ ያሉባትን ጉድለቶች ለመሙላት በምታደርገው ጥረት የቻይና እገዛ ከፍተኛ ቦታ ይይዛል ብለዋል። ቻይና ለአፍሪካ አገራት እያደረገች ያለው እገዛ ትልቅ እድል ይዞ መምጣቱን የተናገሩት ዋና ፀሐፊው አጀንዳ 2030ን ለማሳካት የቻይና አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቦታ እንዳለው ተናግረዋል። ዘላቂነት ያለውን የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን ማሻሻል ዋነኛው እርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል። ለሦስት ቀናት በሚካሔደው የቻይና-አፍሪካ የትብብር ጉባዔ እአአ እስከ 2027 በሚኖረው የቻይና እና አፍሪካ ግንኙነት የትብብር ሰነዶች ላይ ውይይት ተደርጎ ስምምነት እንደሚፈረም ይጠበቃል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይና-አፍሪካ ትብብርን ይደግፋል - አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
Sep 5, 2024 1183
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30 /2016(ኢዜአ)፡- የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይናና አፍሪካ ትብብርና አጋርነትን እንደሚደግፍ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ገለጹ። የቻይና-አፍሪካ ጉባኤ ዛሬ በቤጂንግ መካሄድ ጀምሯል። የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ላይ ዓለም በግጭቶችና ማህበራዊ ቀውሶች ውስጥ እያለፈች እንደምትገኝና ተግዳሮቶቹ ለእድገትና ልማት ትልቅ ፈተና መሆናቸውን ገልጸዋል። የአፍሪካ አገራት በእዳ ቀውስ ፈተና ውስጥ መግባታቸውንና ለዘላቂ ልማት መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ መቸገራቸውን አመልክተዋል። ኢ-ፍትሐዊና ጊዜው ያለፈበት ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓት ማሻሻያ እንደሚያስፈልገውና የፋይናንስ ተቋማት ፍትሐዊ በሆነ መልኩ የፋይናንስ አቅርቦትን ተደራሽ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት ፈታኝ የገበያ ሁኔታዎች ተቋቁመው የዘላቂ ልማት ግቦችን እንዲያሳኩ የሚያደርግ የፋይናንስ ድጋፍ ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ገልጸዋል። ይህም የአገራትን የፋይናንስ ተደራሽነት በማሳደግ የመካከለኛና የረጅም ዘመን መፍትሔ እንዲያበጁ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል። በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስርዓቱ ፍትሐዊ ማሻሻያ ለማድረግ የአፍሪካና ቻይና ሚና ቁልፍ መሆኑን ነው ዋና ፀሐፊው የገለጹት። ከዚህ አኳያም የደቡብ-ደቡብ ትብብር የአገራትን አቅም ለመገንባትና የልማት ግቦችን በጋራ እውን ለማድረግ የሚያስችል ማዕቀፍ እንደሆነ ተናግረዋል። ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላት አጋርነት የደቡብ-ደቡብ ትብብር ዋንኛ ምሰሶ ነው ብለዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይና-አፍሪካ ትብብርና አጋርነት እንደሚደግፍ ዋና ፀሐፊው ገልጸዋል።