ዶክተር ሊያ ታደሰ በጤና ልማት ዘርፍ በሴት አመራርነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና አገኙ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) የካቲት 30/2015 የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በጤና ልማት ዘርፍ በሴት አመራርነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ በሩዋንዳ ኪጋሊ በተካሄደው በአፍሪካ ዓለም አቀፍ የጤና አጀንዳ ኮንፈረንስ (AHAIC)2023 ላይ እውቅና ተሰጣቸው።

ሚኒስትሯ በሩዋንዳ ኪጋሊ ትላንት በተካሄደው Africa Health Agenda International Conference (AHAIC) 2023 ላይ የተበረከተላቸውን Women in Global Health Award የእውቅና ሽልማት በተወካያቸዉ በኩል ተቀብለዋል።

እውቅናው በጤና ልማት ውስጥ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በመቋቋምና በመፍታት፣ የጤና አገልግሎት ጥራትና ፍትሀዊ ተደራሽነት እንዲሁም ሁሉን አቀፍ የጤና አገልግሎት ሽፋን ላይ ትኩረት ሰጥተው ለሚሰሩ አመራሮች የሚሰጥ መሆኑም ተመላክቷል።

ለመጪዎቹ ትውልዶች አርዓያ ለሆኑ የአፍሪካ ሴት መሪዎች የሚሰጠው ሽልማቱ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰም ለዜጎች የተሻለና ዘላቂ ጤናን ለማምጣት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ላበረከቱት የላቀ የመሪነት ሚና ከአምሪፍ ሄልዝ አፍሪካ እውቅናውን አግኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም