በጂንካ ከተማ የተመረተው 23 ኪሎ ግራም የሚመዝነው የስኳር ድንች "በአፍሪካ ትልቁ ስኳር ድንች" በሚል ተመዘገበ - ኢዜአ አማርኛ
በጂንካ ከተማ የተመረተው 23 ኪሎ ግራም የሚመዝነው የስኳር ድንች "በአፍሪካ ትልቁ ስኳር ድንች" በሚል ተመዘገበ
ጂንካ መጋቢት 4/2015 (ኢዜአ):- በጂንካ ከተማ ደሙዝ ሰፈር የተመረተው እና 23 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ስኳር ድንች በአፍሪካ የድንቃ ድንቆች መዝገብ "በአፍሪካ ትልቁ ስኳር ድንች" በሚል መመዝገቡ ተገለጸ።
በአዲስ አበባ በተካሄደው የእውቅና ስነስርዓት ላይ የአፍሪካ ድንቃ ድንቆች መዝገብ ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ አለም ለስኳር ድንቹ ባለቤት አቶ ኢሳያስ ጊዜአለው የእውቅና ምስክር ወረቀት አስረክበዋል።
ከዚህ ቀደም በአፍሪካ 10 ኪሎ ግራም የሚመዝን ስኳር ድንች መቅረቡን አቶ አሸናፊ ለኢዜአ ገልጸዋል።
“ነገር ግን 23 ኪሎ ግራም የሚመዝን ስኳር ድንች በአፍሪካ ደረጃ ሲቀርብ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው” ብለዋል።
በዓለም የድንቃ ድንቅ መዝገብ 37 ኪሎ ግራም የሚመዝን ስኳር ድንች መመዝገቡንና በደሙዝ ሰፈር የተገኘው ስኳር ድንች በ14 ኪሎ ግራም ዝቅ ብሎ ከዓለም የ”ሁለተኛነት” ደረጃ ላይ እንደሚያስቀምጠው አመልክተዋል።
የስኳር ድንቹ ባለቤት አቶ ኢሳያስ ጊዜያለው ስኳር ድንቹ በአፍሪካ ድንቃ ድንቆች መዝገብ ላይ በመስፈር የኢትዮጵያን ስም በማስጠራቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ስኳር ድንቹ እውቅና እንዲያገኝ የዜና ሽፋን ለሰጠው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምስጋቸውን አቅርበዋል።
ኢዜአ የካቲት 19 ቀን 2015 ዓ.ም “በጂንካ ከተማ ደሙዝ ሰፈር 23 ኪሎ ግራም የሚመዝን አንድ የስኳር ድንች መመረቱ ተገለጸ” በሚል መዘገቡ የሚታወስ ነው።