በአዲስ አበባ ከሚያዚያ 16 ጀምሮ የነዳጅ ግብይት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ መንገዶች ብቻ ይፈጸማል-ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከሚያዚያ 16 ጀምሮ የነዳጅ ግብይት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ መንገዶች ብቻ ይፈጸማል-ባለስልጣኑ
አዲስ አበባ መጋቢት 28/2015(ኢዜአ)፡ በአዲስ አበባ ከሚያዚያ 16 ጀምሮ የነዳጅ ግብይት ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ መንገዶች ብቻ እንደሚፈጸም የነዳጅና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።
የነዳጅና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መንገዶች ብቻ የሚፈፀምበትን የድርጊት መርሐ ግብር በተመለከተ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ተወያይቷል።
የውይይቱ ዓላማ በመዲናዋ የሚገኙ ሁሉም የነዳጅ ማደያዎችና ኩባንያዎች በአሰራሩ ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ እንዲይዙ ለማስቻል መሆኑ ተነግሯል።
በዚህ ወቅት የነዳጅና ኢነርጂ ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሳህረላ አብዱላሂ፤ ባለስልጣኑ የነዳጅ ግብይትን በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።
በዚህም ቀደም ብሎ ከነዳጅ ማደያና አከፋፋይ ኩባንያዎች ጋር ሲሰራ መቆየቱን ገልፀው፤ አሁን ደግሞ ለሙሉ ትግበራው ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ውይይት ተደርጓል ብለዋል።
በአዲስ አበባ የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ስርዓቱ በአማራጭነት ለሙከራ እየተተገበረ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከሚያዚያ 16 ጀምሮ የነዳጅ ግብይት በአስገዳጅ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መንገዶች ብቻ እንደሚፈጸም ተናግረዋል።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ማንኛውም የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ ብቻ የሚፈጸም መሆኑን ተገንዝቦ ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አተገባበር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሀምሌ አንድ ጀምሮ በአስገዳጅነት እንደሚተገበርም ጠቁመዋል።
በኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ሞባይል መኒ ኦፊሰር ብሩክ አድሃነ፤ የነዳጅ ግብይትን በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መንገዶች በማድረግ ረገድ በቴሌ ብር ውጤታማ ስራ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል።
ለዚህም ባለፉት ዘጠኝ የሙከራ ወራት በቴሌ ብር ብቻ ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ የነዳጅ ግብይት መፈጸሙን አንስተዋል።
የነዳጅ ግብይቱን በአግባቡ በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ መንገዶች ለማከናወን የሚያስችል ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መገንባቱንም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ ነዳጅ ማደያዎች ማኅበር አባል የሆኑት አቶ ሚካኤል ገብረስላሴ እና የማህበሩ የቦርድ አባል አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ የነዳጅ ግብይት ስርዓቱ በኤሌክትሮኒክስ ክፍያ መንገዶች ብቻ መሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።
በተለይ ለነዳጅ አዳዮች ጥሬ ገንዘብ በመቁጠር የሚያባክኑትን ጊዜ ከመቅረፍ አንፃር እንዲሁም በማደያዎች የሚቀመጥ የግብይት ገንዘብ እንዳይኖር በማድረግ የደህንነት ስጋትን እንደሚፈታ ተናግረዋል።
በተጨማሪም መንግስት የነዳጅ ምርት ከመነሻው እስከ መድረሻው ያለውን ስርጭት ሂደት መረጃ እንዲኖረው እና ነጋዴዎችም ግብርና ታክስ እንዳያጭበረብሩ በማድረግ ቴክኖሎጂው ትልቅ ሚና አለው ነው ያሉት።