ጀርመን በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት እንዲሳካ ድጋፍ ታደርጋለች - አምባሳደር ስቴፋን አወር

አዲስ አበባ ሰኔ 10/2015 (ኢዜአ) ፦ ጀርመን በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ሂደት እንዲሳካ ድጋፍ እንደምታደርግ በአገሪቷ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስቴፋን አወር ገለጹ።

ጀርመን ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የሰብአዊ ድጋፍ በእጥፍ ማሳደጓንም አመልክተዋል።

ጀርመን  ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በፖለቲካው፣ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ የትብብር መስኮች ያላቸው አጋርነት እየተጠናከረ መምጣቱን አምባሳደር ስቴፋን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ጀርመን በአቅም ግንባታ፣ በግብርና ምርታማነት እንዲሁም በማህበራዊ ልማትና በመልካም አስተዳደር  ዘርፎች ለኢትዮጵያ የምታደርገው የልማት ትብብር ማደጉን አመልክተዋል።    

ጀርመን በተለይም በልማት ኤጀንሲዋ(ጂ አይ ዜድ) በኩል ለኢንዱስትሪው እድገት ወሳኝ የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የአቅም ግንባታ ድጋፍ ማድረጓን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ሙያዊ ድጋፍ እንዲሁም የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ነው አምባሳደሩ የገለጹት።

በኢትዮጵያ ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን ለመደገፍ ሰው ተኮር የሆኑ ፕሮጀክቶችን ለአብነትም የሰብአዊና የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ጀርመን ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የሰብአዊ እርዳታ ወደ 82 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ከፍ በማድረግ በእጥፍ ማሳደጓንና ይሄም "ጀርመን በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀምጣታል" ብለዋል።

በሌላ በኩል ጀርመንና ኢትዮጵያ በንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነቱን ለማጠናከር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ይህንንም እውን ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።  

የሁለቱን አገራት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ለአብነትም በጀርመን የባህል ተቋምና በሌሎችም ኢንስቲትዩት  እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በማሳየነት ጠቅሰዋል።  

በኢትዮጵያ በተለይም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተጀመረው የሰላም ስምምነት ቀጣይነት እንዲኖረው ጀርመን ፍላጎት እንዳላት ገልጸው ለዚህም ድጋፍ እያደረገች ትገኛለች ነው ያሉት አምባሳደር ስቴፋን።  

የኢትዮጵያ መንግሥት የሽግግር ፍትህ ለማረጋገጥ የጀመረው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደሩ ጀርመን ሂደቱ የተሳካ እንዲሆን ድጋፍ ታደርጋለች ብለዋል።

ጀርመን የአፍሪካ ሕብረት እንዲጠናከር በተለይም በአፍሪካ አገራት መካከልም የፖለቲካና ምጣኔ ኃብታዊ ውህደት እንዲረጋገጥ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቁመዋል። 

ኢትዮጵያና ጀርመን ግንኙነታቸውን የጀመሩት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1905 ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም