“ዮ-ማስቃላ''- ሁሉም የሚደሰትበት በዓል

በሳሙኤል አየነው 

የሰላም፣ የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የመቻቻልና የአንድነት ተምሳሌት የሆነው የጋሞ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል “ዮ-ማስቃላ” ከወርሃ መስከረም አጋማሽ ጀምሮ በተለያዩ ባህላዊ ሁነቶች በድምቀት ይከበራል ። በተለያየ ምክንያት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ተራርቀው የነበሩ ወገኖች ወደ የአካባቢያቸው በመመለስ ከቤተሰቦቻቸው ብሎም ከቀየው ህብረተሰብ ጋር አብረው የሚያከብሩት የዓመቱ ታላቅ በዓል ነው ።

ታዲያ በዓሉን በድምቀት ለማክበር ወንዶች ሰንጋ በሬ ለመግዛት እንዲሁም ለትዳር አጋሮቻቸውና ለልጆቻቸው ልብስና ጌጣ ጌጥ የሚሆን ገንዘብ መቆጠብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ሴቶችም ለባህላዊ ምግቦች፣ ለቅመማ ቅመም፣ ለቅቤና ለባህላዊ መጠጦች እህል ግዥ የሚሆን ገንዘብ ዓመቱን ሙሉ ሲቆጥቡ ይከርማሉ። መስከረም ወር ከገባበት ዕለት አንስተው ወንዶችም ሆኑ ሴቶቹ በቆጠቡት ገንዘብ በየፊናቸው ለበዓሉ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን ማቅረብ ይጀምራሉ።  ይህም የዝግጅት ጊዜ “እንግጫ” በመባል ይጥራል።

በ”ዮ--ማስቃላ” ጊዜ አብሮነት እንጂ ግለኝነት የሚባል ነገር በጋሞዎች ዘንድ ፈጽሞ አይታሰብም፤ አብሮ እርድ ማካሄድ፣ አብሮ መመገብ፣ አብሮ መጠጣት፣ አብሮ መጫወት የጋሞዎች መገለጫ ነው። እንደ ሌሎቹ በዓላት ሁሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖችም በዓሉን እንዴት እናሳልፍ የሚል ስጋት አያድርባቸውም። ምክንያቱም የሌለውም ካለው ጋር አብሮ የሚቋደስበት፣ የሚደሰትበት፣ የሚተሳሰብበትና የሰብአዊነት ልክ የሚንጸባረቅበት ልዩ ድባብ ያለው በዓል ነውና ዮ-ማስቃላ ። 

የጋሞ የሀገር ሽማግሌ አቶ አመሌ አልቶ ስለ “ዮ--ማስቃላ” በዓል በትንሹ እንዲያወጉን ጠይቀናቸው በዓሉ ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን እንስሳትና አዕዋፋት ሁሉ የሚደሰቱበት እንደሆነ ነግረውናል። በአካባቢው ቋንቋ ተፈጥሮ ሁሉ በዓሉን በደስታ እንደሚያሳልፍ ለመግለጽ “ካፎስ ካናስ ማስቃላ” በማለት የሚገለጽ ስሆን “ለሰው ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትም መስቀል ነው” እንደማለት ነው ብለዋል። በዓሉ ከመድረሱ ከሶስት ወራት አስቀድሞ በየአካባቢው ለእንስሳት የግጦሽ ሥፍራ ተከልሎ የሚዘጋጅ ሲሆን ችቦው በሚለኮስበት በደመራው ዕለት የቤት እንስሳት በሙሉ በዚያው የሚሰማሩ ይሆናል። ዓመቱን ሙሉ ሲያርሱ የነበሩ የእርሻ መሣሪያዎችም በበዓሉ ጊዜ ታጥበውና በቅቤ ታሽተው በክብር ይቀመጣሉ። ክብር ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትና ለእርሻ መሣሪያዎችም ይሰጣል።

በባህሉ መሠረት ችቦ በሚወጣበት ሰዓት አባት የራሱን ችቦ ለኩሶ የቤቱን ምሰሶ፣ የከብቶችን ጋጣና የበር ጉበኖችን ግራና ቀኝ በችቦው ጫፍ በማነካካት ወደ ውጭ ካወጣ በኋላ ወንድ ልጆች የየራሳቸውን ችቦ ተራ በተራ እየለኮሱ አባታቸውን ተከትለው “ዮ---ማስቃላ” እያሉ ወደ ደመራ ቦታ ያመራሉ። ከዚያም አባት በቅድሚያ ችቦውን ከለኮሰ በኋላ ልጆች ደግሞ ተከትለው ደመራውን ይለኩሳሉ። ከዚህ ፕሮግራም መልስ ወደ ቤት ተመልሰው የተዘጋጀውን ገንፎ በአንድ ወጭት ላይ “ዮ--ማስቃላ”እያሉ ሁሉም የቤተሰብ አባላት፣ ዘመድ አዝማድና ጎረቤት ተሰባስበው በጋራ ይመገባሉ። በ”ዮ--ማስቃላ” በዓል በዋናነት እርድ የሚከወን ሲሆን ቁርጥ፣ ጎረድ ጎረድ፣ ክትፎና የወጣ ወጥ ዓይነቶች ተሠርተው ለምግብነት ይቀርባሉ። ከባህላዊ ምግቦች ደግሞ የገብስ ቅንጬ፣ የቆጮና ገብስ ውህድ ቂጣ፣ የቡላ ፍርፍር፣ ሀረግ ቦዬ፣ እንዲሁም ከመጠጥ አይነቶች ደግሞ ቦርዴ፣ ጠላ፣ የማርና የቦርዴ ጠላ ውህድና ሌሎች ተወዳጅ ምግቦችና መጠጦች ይዘጋጃሉ።

በ”ዮ--ማስቃላ” በዓል ዕለት የሚቀራረቡ ጎረቤታሞች በጋራ ሆነው አማካይ በሆነ ሥፍራ ላይ የእርድ ሥነሥርዓት ያከናውናሉ። የእርድ ሥነ-ሥርአቱም በደመራው ዕለትና ማግስት እንደ ህብረተሰቡ ይሁንታ የሚፈጸም ይሆናል። ከማግስቱ ጀምሮ የተዘጋጀውን ሥጋ በጋራ እየበሉና እየጠጡ የበዓሉን ድባብ የሚያስቀጥሉ ሲሆን “ዱንግዛ” በተሰኘው የጋሞ ባህላዊ ጥበብ ልብስ ደምቀው በጌጣጌጥ አሸብርቀው ሁሉም በየአደባባዩ በባህላዊ ጫዋታዎች እየተደሰተ በዓሉን ያከብራል። ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና አብሮነት ካለ በአዲሱ ዓመት ምድሪቱ ተገቢውን ምርት እንደምትሰጥ ሁሉም ሰው በተሰማራበት መስክ ውጤታማ እንደሚሆን ይታመናል። ከዚም የተነሳ በአሮጌው ዓመት ሃዘን ላይ የነበሩ ወገኖች ሙሉ በሙሉ  ሀዘናቸውን በመተው በአዲስ መንፈስ ወደ መደበኛው ህይወት ይመለሳሉ። የተጣሉ ወገኖች ቂም ይዘው አዲስ ዓመትን መሻገር በጋሞዎች ዘንድ ነውር በመሆኑ በባህላዊ ሸንጎ ሥርአት /ዱቡሻ/ በጋሞ አባቶች አሸማጋይነት እርስ በርስ ተነጋግረው በመታረቅ አዲሱን ዓመት በጋራ ያበስሩታል።

በሌላ መንገድ “ዮ..ማስቃላ” በዓል ተጠብቆ ወጣቶች የሚተጫጩበት፣ የተጫጩት ደግሞ ጋብቻ የሚከውኑበት እንዲሁም ያገቡት በየገበያው ዕለት “ሶፌ” የሚባል ሥነ-ሥርዓት በማከናወን በማህበራዊ ህይወት ማህበረሰቡን በይፋ የሚቀላቀሉበት መሆኑን ጋሽ አመሌ አውግተውናል። ጋሞዎች ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በመሆን በአብሮነት ለሁለት ሳምንታት በደስታ ካሳለፉ በኋላ ወደ ግብርና ሥራቸው በመመለስ ቀደም ሲል በክብር ያስቀመጧቸውን የእርሻ መሣሪያዎች በማንሳት ወደ እርሻ ሥራ ይገባሉ። እስከ ታህሳስ ወር መውጫ ድረስ የበዓሉ ድባብ ሳይጠፋ ይቆይና በመጨረሻም የመሰናበቻ ድግስ ወይም “ጮዬ ማስቃላ” በማዘጋጀት በህብረት ከተመገቡና ከጠጡ በኋላ የዓመት ሰው ይበለን፣ ዓመቱ የሰላም፣ የጤና፣ የበረከት ይሁን በማለት በመመራረቅ “ዮ--ማስቃላ”ን ይሸኛሉ።

በዓሉ የህዝቡን ሰላም ፣አንድነትና አብሮነት የሚያንጸባርቅ ልዩ በዓል ነው በማለት የጋሞ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ሃላፊ አቶ ሞናዬ ሞሶሌ የጋሞ የሀገር ሽማግሌ የሆኑት የአቶ አመሌ አልቶን ሃሳብ ይጋራሉ። ባህላዊ እሴቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተጠብቆ እንዲቆይ “ዮ--ማስቃላ” ትልቅ ድርሻ አለው። የባህል እሴቶች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ በጥናትና ምርምር በማስገፍና የቋንቋና ባህል አውደ ጥናት በየዓመቱ እየተደረገ እንደሆነም ነግረውናል። አባቶች በልዩነት ውስጥ ያለንን አንድነት እንዳቆዩልን ሁሉ ወጣቶችም ኢትዮጵያዊ ለዛ ያላቸው የጋራ እሴቶች ሳይበረዙና ሳይከለሱ ጠብቀው ለትውልድ የማስተላለፍ ሃላፊነት አለባቸው የሚለውን የንግግራቸው ማሳረጊያ አድርገዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም