የዱርና የቤት እንስሳቱ ቤተሰባዊ ፍቅር

በፍሬዘር ጌታቸው (ወላይታ ሶዶ ኢዜአ)

አብዛኛውን ጊዜ አንዳንድ የዱር እንስሳት ለሥጋቸው፣ ለቆዳቸው፣ ለጥርሳቸው ወዘተ እየተባለ እንደሚገደሉ የአደባባይ ምስጢር  ነው።

መንግሥት ይህንን ጥቃት ለመከላከል የተለያዩ የዱር እንስሳት ፓርኮችን በማቋቋም ጭምር  የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ ይታያል። እርምጃው የዱር እንስሳቱን ከመጥፋት እንዲሁም መንግስት ዘርፉን በማስጎብኘት የሚያገኘውን ጥቅም ከመጨመር ባሻገር ሊኖረው የሚችለው ፋይዳ ብዙ ነው። የዱር እንስሳቱ ለአካባቢ ሥነ-ምህዳር የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ ሳይዘነጋ ማለት ነው። ሆኖም ግን አሁንም በሀገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም የዱር እንስሳት በሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋ ስጋት ላይ ናቸው። ለዛሬ የፅሁፌ ማጠንጠኛ የዱር እንስሳቱ ስጋትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን እነሱን በማላመድ ያልተለመደ ተግባርን እየፈፀመ ባለ ግለሰብ ላይ ይሆናል። 

ግለሰቡ ወጣት በረከት ብርሃኑ ይባላል፤ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ ነው። ወጣት በረከት አዘወትረን የምንሰማውን 'እንኳን ሰው ወፍ ያለምዳሉ' የሚለውን ብሂል በሚያስረሳ መልኩ እሱ አባባሉን 'እንኳን ሰው አውሬ ያለምዳሉ' ወደሚለው ቀይሮታል ማለት ይቻላል። በረከት “በጎሪጥ የሚተያዩ የዱር እንስሳትን በፍቅር እንዲኖሩ ያደረገበትን ሁኔታ በርካቶች በግርምት ሲመለከቱት ይታያል። የሰው ልጆች በተፈጥሮ ክፉ ሆነው አይወለዱም ዳሩ ግን በህይወት አጋጣሚ ከሚቀስሙት ክፉ ባህሪ የሚማሩትና የሚዋሃዱበት እንጂ ይላል በረከት።

''አብሪያቸው ለመሆን በመወሰኔ እውነተኛ ፍቅርን ከዱር እንስሳቱ ተምሬያለሁ'' የሚለው ወጣት በረከት ከሰባት ዓመት በፊት የዱርና የቤት እንስሳትን በተለይም ሰው ለመቅረብ የሚፈራቸውን ጭምር እንደ ዘንዶ፣ ጅብ፣ ዝንጀሮ፣ አዞ፣ ጦጣ፣ አሳማ እንዲሁም ውሻና  የመሳሰሉትን በማሰባሰብ በአንድ ላይ እንዲኖሩ እያደረገ በአንድ ላይ ማኖር እንደጀመረ ይናገራል። 


 

በዚህም ምክንያት ሰው ሰራሽ ሐይቅን በውስጡ የያዘ የወጣቶች መዝናኛ ፓርክ በወላይታ ሶዶ ከተማ ማቋቋሙን ገልጿል። የዱር እንስሳቱን ከአባያ ብላቴ እንዳመጣቸው የሚናገረው በረከት  በይበልጥ ግን በመኪናና መሰል አደጋዎች የተጎዱ የዱር እንስሳትን ከወደቁበት በማንሳት እንዲያገግሙ ለማድረግ በሚያደርግላቸው የእንክብካቤ ቆይታ ታዲያ የዱር እንስሳቱ ከቤት እንስሳት ጋር አብረው የማደር፣ አብረው የመዋል፣ አብረው የመብላት፣ በአንድ ላይ የመጫወት ዕድሉን እንዳገኙ ነው ለኢዜአ የተናገረው። የቤትና የዱር እንስሳቱ ህብረትና አንድነት የሚያስቀና እንደሆነም ወጣት በረከት ገልጿል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ የዱር እንስሳት ሀብት እንዳለ የሚናገረው ወጣት በረከት በውስጡ ለተፈጥሮ ያለውን ፍቅር ወደ ስራ መቀየሩን ነው የገለፀው። ከሌሎች የዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ጋር በመሆን ስራውን ለመሥራት ወስነው በመግባታቸው የከተማው አስተዳደር የሥራ ቦታና መነሻ ካፒታል እንደረዳቸው ገልፆ በዚህም በመበረታታት ያልተለመደ የስራ ዘርፍ ለመፍጠር ወጥነው መጀመራቸውን ይናገራል።

ስራውን ሲጀምር ቀላል ሁኔታ እንዳልገጠመው ያስታወሰው በረከት "ካባ ድንጋይ የሚፈነቀልበትን ስፍራ አልምቶና ችግኝ ተክሎ ወደ ዛፍ መቀየር እንዲሁም የሰው ሰራሽ ሐይቅ እንዲያመነጭ ማድረግ የማይቻል ይመስላል" ይላል። ቦታውን በባለሙያ በማስጠናትና ደባል አፈር ከሌላ ቦታ በማስመጣት ህልማቸውን እውን ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን አውስቶ ዓላማቸውን ለማሳካት የሄዱበት ርቀት ለሌሎች አስተማሪ መሆኑንም ይናገራል። ቦታውን አሁን ላይ የተለያዩ የዱርና የቤት እንስሳት በጋራ የሚኖሩበትና በርካታ የአገር ውስጥና ከሌላው ዓለም የሚመጡ ጎብኚዎች የሚዝናኑበትና የሚያርፉበት "ጁኒየር የወጣቶች መዝናኛ ፓርክ" መክፈት መቻላቸውን ነው የተናገረው።

እንስሳቶች የሚሰጣቸውን ስያሜ ሳይሆን ተቀራርበው የሚኖሩበትን የፍቅር ህይወት ለማየት የሚመጣው ጎብኚ የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም ማድረግ እንዳለበት በማመን የማረፊያ ቤቶች እና ተጨማሪ መዝናኛዎችን በማስፋፋት አሁን ላይ ጥሩ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አብራርቷል። በዚህም ''በፓርኩ ግቢ ውስጥ የወላይታ ሶዶ ከተማን ገጽታ የሚያሳይ ባለ ሰባት በር መግቢያና መውጫ ያለው ሆቴልና የጀልባ መዝናኛ አገልግሎት ለተጠቃሚዎች በመስጠት የተሻለ ስራ በመስራት ላይ እንገኛለን'' ብሏል።

ፓርኩን ለመጎብኘት ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ለአንድ ሰው 30 ብር፣ ለውጭ ዜጋ ደግሞ 100 ብር በማስከፈል አገልግሎት እየሰጡ ያነሳው ወጣቱ በአዘቦት ቀናት በቀን ከ400 በላይ ጎብኚ ፓርኩን እንደሚጎበኙ ፣ በሰንበት ቀናት እና በበዓላት ወቅት እስከ 1 ሺህ ድረስ ጎብኚዎች እንደሚመጡ ነው የተናገረው።  ያንን ሁሉ አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ ባደረጉት ብርቱ ጥረት ከቤተሰብና በጥቂቱም ቢሆን ከመንግሥት ጥገኝነት መላቀቃቸውን የሚናገረው ወጣቱ በህይወታቸው ጥሩ ኑሮ መኖር ከመጀመራቸውም በዘለለ በፓርኩ ውስጥ ላለው የእንስሳት እንክብካቤና ጎብኚዎችን የማስተናገድ ስራን ለሚያሳልጡ 22 ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር በመቻላቸውም ስኬታማ እንደሆኑም ያነሳል።

"አሁን እንስሳቶቹ ቤተሰቦቼ ሆነዋል በአንድ ቅጥር ግቢ ውስጥ አብሬያቸው ውዬ ነው የማድረው ይላል። ስራ ሩቅ አይደለም አጠገባችን እንዲያውም እጃችን ላይ ነው ያለው የሚለው ወጣት በረከት ሆኖም ሌላ አካል መጥቶ እንዲሰጠን እንጠብቃለን፣ ይኸ አስተሳሰብ የእድገታችን ፀር ነው '' ሲልም አፅንኦት ሰጥቶታል።

ኢትዮጵያ በዱር እንስሳት ሀብት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ የሚነሳ መሆኑን ጠቁሞ ሀብቱን ለማሳደግና ሳቢ በማድረግ ተደራሽነቱን ለማስፋት እንዲያመች የሎጅ ግንባታ ስራ እንቅስቃሴ ጀምሬያለሁ ባይ ነው። ፓርኩ ውስጥ 62 ምንጮች እንደሚገኙ የገለፀው ወጣት በረከት ማስፋፊያ ቦታ ቢሰጠው የተሻሉ ስራዎችን ለመስራት እቅድ እንዳለው ተናግሯል።

በሰዎች ዓለም ውስጥ ገዢ ሀይል ፍቅር ሊሆን እንደሚገባ ፓርኩ ትልቅ የፍቅር ተምሳሌት ፓርክ ‼  ነው የሚሉት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ ነዋሪ አቶ ታዲዮስ ታንቱ ናቸው። ፓርኩ በሂደት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስሟ እንዲጠራ ጉልህ ሚና ይኖረዋል የሚል ተስፋ እንዳላቸው በመግለጽ  የሚመለከታቸው አካላት ተገቢውን ትኩረትና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። 

ፓርኩን ሲጎበኙ ያገኘናቸው የአዲስ አበባ ነዋሪው አቶ ለገሰ ቶማስ በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየመነመነ ለመጣው የዱር እንስሳት ሀብት ማገገም የራሱን አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል ፓርክ መሆኑን ተናግረዋል። "ሁላችንም እንደዚሁ በእጃችን ያለውን ሀብት መጠቀም ካልጀመርን በቀር ሊለውጠን የሚመጣ ተዓምር አይኖርም'' ያሉት አስተያየት ሰጪው ከወጣት በረከት ሁሉም ብዙ ሊማር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም