ዕልፍ ውበት ከኮይሻ ዕልፍኝ - ኢዜአ አማርኛ
ዕልፍ ውበት ከኮይሻ ዕልፍኝ
ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የቱባ ውበቶች መገለጫ ናት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዳሉትም ፈጣሪ በሰጣት የተፈጥሮ ሀብት የታደለች ናት በተለይም በተራሮች፣ በሸለቆዎች፣ በወንዞችና በሐይቆች፣ የተሞላች ሀገር ናት።
በአንድ በኩል ተፈጥሮ በብዙ ያደላት፣ ልጆቿም በትጋታቸው በየዘመናቱ ያደመቋት ብትሆንም በሌላ በኩል በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች እንዲሁም በመሰረተ ልማት መጓደል ፀጋዎቿን በአግባቡ ሳታስተዋውቅና ሳትጠቀምበት ቆይታለች።
ከአምስት ዓመታት በፊት የመጣውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ መንግስት ለብዝሃ ኢኮኖሚ በሰጠው ትኩረት ቱሪዝም አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ ሆኖ ብቅ ማለቱን ተከትሎ ጸጋዎቿ እየተገለጡ ይገኛሉ።
በዚህም የአገሪቱን የቱሪዝም አለኝታዎች በአግባቡ መለየትና ማልማት፣ የቱሪዝም መዳረሻዎችን መሠረተ-ልማት ማጠናከርና ተጨማሪ አዳዲስ መሠረተ-ልማቶችን መገንባት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ሆነዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሸገርና በገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ውጤታማ የቱሪዝም ልማት ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ዕውን ሆነዋል።
በገበታ ለሸገር ከተገነቡና ለአገልግሎት ከበቁ የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል የእንጦጦ፣ የአንድነትና የወዳጅነት ፓርኮች ይጠቀሳሉ። በወንዝ ዳርቻ ልማትም ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በገበታ ለሀገርም ጎርጎራ፣ ወንጪ-ደንዲና ኮይሻ ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው።
የኢትዮጵያን ውብ የተፈጥሮ ብልጽግና ሰዎች አይተው ይረኩ ዘንድ የኮይሻ ፕሮጀክት ውብ ሆኖ መሰናዳቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከሰሞኑ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አጋርተዋል።
የኮይሻ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት የብዝኃ-ቱሪዝም ባለቤት ለሆነችው ኢትዮጵያ ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር ነው።
የኮይሻ ኢኮ-ቱሪዝም በውስጡ ከያዛቸው በርካታ ሀብቶች መካከል የጨበራ ጩርጩራ ፓርክ አንዱ ሲሆን በማራኪ ጥብቅ ደን የተሸፈነ ብሔራዊ ፓርክ ነው።
በገበታ ለአገር በኮይሻ ፕሮጀክት ውስጥ ከሚለሙ የቱሪዝም መስህቦች አንዱ የሆነው ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ለአረንጓዴ ቱሪዝም ሁነኛ ማሳያ የሚሆን የሀገሪቱ ታላቅ የመስህብ ስፍራ ነው።
የመካከለኛው ኦሞ ሸለቆ አረንጓዴያማው ጌጥ ጨበራ ጩርጩራ ወደ 50 የሚጠጉ ከትናንሽ እስከ ትላልቅ ወንዞች መነሻ ሲሆን በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙትን ጨምሮ አያሌ የዕፅዋት ብዝኃ ሕይወትን የለበሰ ተፈጥሯዊ ፀጋ ነው።
የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ ዝርያው እየተመናመነ የመጣው የአፍሪካ የዝሆን ዝርያን ጨምሮ እንደ ጎሽ፣ ዲፋርሳ፣ ከርከሮ፣ ሳላ እና አጋዘን ያሉ የዱር እንስሳት የሚገኙበት ነው፡፡
ፓርኩ በደን ሽፋኑ ይበልጥ ጎልቶ ስሙ የሚነሳ ሲሆን፤ በፓርኩ ውስጥ የሚያቋርጡ በርካታ ወንዞችና አምስት ሃይቆችም ይገኛሉ። በጉያው ካቀፋቸው ፏፏቴዎች መካከል ባርቦ ፏፏቴ አንዱ ሲሆን የፏፏቴው ድምጽ ለፓርኩ ተጨማሪ ድምቀት ሆኖታል።
የገበታ ለአገር ፕሮጀክት አካል በሆነው የኮይሻ ፕሮጀክት ፓርኩን ለመጎብኘት የሚያስችል መሰረተ ልማት በማሟላት የአካባቢውን የቱሪዝም ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል።
የመሰረተ ልማት ግንባታዎቹ የፓርኩን ተፈጥሮ ሳይረብሽ ከፓርኩ ውጪ የሚከናወን ሲሆን ይህም ቱሪስቶች ፓርኩን በቀላሉ እንዲጎበኙት የሚያስችል ነው።
ሌላው የኮይሻ ውብት የግልገል ጊቤ ሶስት ግድብ የፈጠረውን ሰው ሰራሽ ሀይቅ ተንተርሶ የሚገኘው ሀላላ ኬላ ነው።
ሀላላ ኬላ በዳውሮ ዞን በኮረብታዎች፣ ሰንሰለታማ ተራራዎችና በግልገል ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ግድብ የተከበበ ስፍራ ነው።
በዳውሮኛ ቋንቋ "ኬላ" ማለት የድንጋይ ካብ ማለት ሲሆን ሃላላ ኬላ በ1532 ዓ.ም ተጀምሮ በ10 የዳውሮ ነገስታት ለ200 ዓመታት የተገነባ ነው። ስያሜውንም በመጨረሻው ንጉስ ሃላላ ስም ያገኘ ሲሆን ቅርሱ 500 ዓመታትን አስቆጥሯል።
ስፍራው ፀጥታ የሰፈነበት፣ የተረጋጋና መንፈስን የሚያድስ እንዲሁም ታሪክ፣ ባህልና መልከዐ ምድርን ማድነቅ ለሚፈልጉ ማረፊያና ማራኪ የቱሪስት መስህብ እንደሆነ ይነገርለታል።
ሀላላ ኬላ ሪዞርት የኢትዮጵያን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ለማጎልበትና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መዳረሻ ለመክፈት በማሰብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አማካኝነት በ2013 ዓ.ም ይፋ በሆነው የገበታ ለአገር ፕሮጀክት ስር ከሚገኙ የኮይሻ ቅርንጫፍ ስራዎች መካከል አንዱ ነው።
በርካታ የተፈጥሮ በረከቶች በአንድ ቦታ የሚገኙበት ሀላላ ኬላ ጎብኚዎች የሚመኙት አይነት አካባቢ፤ የሚውዱት አይነት የተረጋጋ የአየር ጠባይ ያለው ነው፤ የሀላላ ኬላ ሪዞርት።
ሪዞርቱ የተገነባው ኢትዮጵያ ያሏትን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብቶች በማጎልበት ማራኪነታቸውንና መስህብነታቸውን በመጨመር እንዲሁም ተደራሽነታቸውን በማስፋት ለእይታ እንዲበቁ ለማድረግ ነው።
በተጨማሪም ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ጎብኚዎች በእንቅስቃሴያቸው ሁሉ እንዲደሰቱና አዲስ ቆይታ እንዲኖራቸው ጥሩ እይታን ፈጥሮ አካባቢውን በሚገባ የሚያስተዋወቅ ነው።
የሪዞርቱ ንድፈ ሀሳብ የሃላላ ኬላ ግንብና የአካባቢውን ሕዝብ ታሪክ እንዲሁም የቱሪዝም ሀብትን ከማክበርና ከመጠበቅ ጋር የተቆራኘ ነው። ቱኩል በመባል በአካባቢው ነዋሪ የሚታወቀውን ባህላዊ የስነ ሕንጻ አሰራር ጥበብ በመከተል የቤቱ ውስጣዊ ክፍል አየር በደንብ እንዲያገኝ፣ ጣሪያቸው ከፍ ብሎ ተሰርቷል።
የሃላላ ኬላ ሪዞርት በሚያዚያ ወር 2015 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ ባለሀብቶችና እንግዶች በተገኙበት መመረቁ የሚታወስ ነው።
የኮይሻ እልፍኝ ሌላው ውበት የሆነው የልማት ስራ የኮይሻ የሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ነው።
የፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት 62 በመቶ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል፡፡ "በቅርብ ርቀት በጨበራ ጨርጩራ ብሔራዊ ፓርክ የሚገኘውን የጨበራ የዝሆን ዳና ሎጅን በምንመርቅበት በአሁኑ ወቅት የኮይሻ ግድብ ለአካባቢው የቱሪዝም ዕድል ተጨማሪ አስተዋፅኦ ያደርጋል" በማለትም በኮይሻ እልፍኝ ዕልፍ ውበት ዕልፍ ዕድል መኖሩን ተናግረዋል፡፡