በኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የተፈረመው ስምምነት ለቀጣናው አዲስ ምእራፍ የሚያስተዋውቅ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 26/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የባህር በር አጠቃቀምን በሚመለከት የተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ ለቀጣናው አገራት አዲስ ምእራፍ የሚያስተዋውቅ መሆኑን የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ አንድሪው ኮሪብኮ ገለጹ።

ሰርቫይቭ ዘ ኒውስ በተባለው ድረገጽ ላይ የሰፈረው የተንታኙ ዘለግ ያለ ጽሁፍ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ የሶማሊላንድ ወደብን ለኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ አገልግሎት ለመጠቀም የገባችው ስምምነት ምጣኔ ሃብታዊና ማህበራዊ ትስስር ከማሳደግ ባለፈ ሌላ አላማ አለመያዙን አስረድተዋል።

ብዝሃ ባህልና ሃይማኖት የሚተገበርባት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ አጠቃቀምን በሚመለከት የደረሰችበት የመግባቢያ ሰነድ ወደ ሙሉ ትግበራ ሲገባ ከሶማሊላንድ ባለፈ ወደ ሌሎች የአካባቢው አገራት የሚሻገር ትሩፋት እንዳለው ያተተው የተንታኙ ጽሁፍ ጥቂት የማይባሉ አካላት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ስምምነቱን ጥላሸት እየቀቡት ይገኛሉ ብለዋል።

ስምምነቱን ተከትሎ የተቃርኖ አስተሳሰቦችን የሙጥኝ ብለው የያዙ ሰዎች ከምንም በላይ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተውን ስምምነትና መልካም ምሳሌ ይጸየፋሉ ሲሉ ወቅሰዋል።

ተንታኙ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር መሆኗን ባረጋገጠችበት እለት የተፈረመው ይሄ የመግባቢያ ሰነድ ለሶማሊላንድ ህዝብና መንግስት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን በማንሳት ሁነቱ ለአፍሪካ ቀንድ አገራት ህዝቦች በተለይም ለሶማሊላንድ ዜጎች አዲስ የሚባል የታሪክ ክስተት ሆኖ ሊመዘገብ የሚገባው ነው ብለዋል።

ስምምነቱ በትብብር የጋራ ተጠቃሚነትን ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ከመሆኑም ባሻገር  በሰጥቶ መቀበል መርህ በቀጣናው አካባቢ ያለውን የጸጥታ ችግር መቅረፍ እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በአለም ላይ በአንድ ቦታ እንደተቀመጠ የሚገኝ ነገር አለመኖሩን የሚያሳዩ ተጨባጭ ክስተቶች መኖራቸውን በማሳያዎች ያብራሩት ተንታኙ የአፍሪካ ቀንድ አገራት በእጅጉ ኋላ ከቀሩበት የኢኮኖሚ ደረጃ ተመንጭቀው መውጣት ካለባቸው መሰል ስምምነቶችን አድርገው እድገታቸውን ማስቀጠል የግድ ይላቸዋል ብለዋል። 

ኢትዮጰያ ካላት ሁለንተናዊ አቅም አንጻር መሰል ስምምነቶችን አድርገው የጥቅም ተጋሪ መሆን የሚችሉ አገራት መሪዎች ይሄንን ሁነት ቀለል አድርገው ሊመለከቱት እንደማይችሉ በማተት በጉዳዩ ላይ የሶማሊያ ፌደራል መንግስትና የሽብር ቡድኑ አልሽባብ አብረው ለመስራት ያደረጉት ያልተቀደሰ ጋብቻ መጨረሻው መጠፋፋት መሆኑን አስምረውበታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም