ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት የወሰደችው እርምጃ ብልህነት የተሞላበት ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት የወሰደችው እርምጃ ብልህነት የተሞላበት ነው
አዲስ አበባ ፤ጥር 2/2016 (ኢዜአ)፦ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት የወሰደችው እርምጃ ብልህነት የተሞላበት መሆኑን የአልአረብ ፐብሊሺንግ ኩባንያ ዋና አዘጋጅ (ዶ/ር )ሃይታም ኤል ዞባይድ ገለፁ።
ሃይታም ዘአረብ ዊክሊ ድረገጽ ላይ ባሰፈሩት ረዘም ያለ ጽሁፍ የአለም ስርአት በእጅጉ መድልዎ የተሞላበት ነው። በማሳያነትም ሶማሊላንድ ነጻነቷን ማግኘት የነበረባት በአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1990ዎቹ መጀመሪያ አንደነበር በማንሳት ።
በእንግሊዝ የቅኝ ግዛት ጥላ ስር የቆየችው ሶማሊላንድ በ1960ዎቹ ነጻ ስትወጣ ከጣሊያን ሶማሊ ጋር እንድትቀላቀል የተደረገበት መንገድ ተንኮሎች እንደነበሩት በምልሰት ያስታውሳሉ።
እንደሌሎቹ የባህረሰላጤው ሃገራት የተትረፈረፈ የነዳጅ ሃብት ቢኖራት ኖሮ ልእለሃያላኑ ሀገራት ከሶማሊ ጋር እንድትቀላቀል አይፈርዱባትም ነበር ሲሉም ይሞግታሉ።
ቀደም ሲል አሜሪካን ጨምሮ ከ35 ያላነሱ ሃገራት እውቅና የሰጧት ሶማሊላንድ በግዴታ ወደ ሶማሊያ መዋሃዷ ዜጎቿ ለተቃውሞ ዳርጎ ነበር ፤ በ1990ዎቹ የዚያድባሬ አገዛዝን ተከትሎ የተቀሰቀሰው የሶማሊያ የእርስበእርስ ጦርነት የሶማሊላንድን ዳግም ውልደት እስኪያመጣ ድረስ ።
የዚያድባሬ አገዛዝ መገርሰስ የእርስበእርስ ጦርነት፣ የባህር ላይ ዝርፊያ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ያለመረጋጋት ማንገሱን ያተተው የዶክተሩ ጽሁፍ ሶማሊላንድ በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥም ሆና ዜጎቿን ማረጋጋት፣ የባህር ክልሏን መጠበቅ ብሎም ምርጫዎችን በማካሄድ የሉአላዊ ሃገር ተግባራትን ስትፈጽም እንደቆየች አትቷል።
የትኛውም ሃገርም ሆነ ባለሃብት የረጅም ጊዜ ትርፉን አስቦ እንደሚንቀሳቀስ ነጋሪ እንደማይፈልግ የገለጹት ዶክተሩ ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ብዛት፣ የገበያ አቅም፣ የመልማት እድል ብሎም የዲፕሎማሲ ትስስር አኳያ ለሶማሊላንድ ሊታለፍ የማይችል መልካም አጋጣሚ ነው።
ዶክተሩ ሃሳባቸውን ሲቋጩ እስካሁን በነበረው ሁኔታ የሞቃዲሾ አስተዳዳሪዎችን ጨምሮ አንዳንድ የኢትዮጵያ ጎረቤት ሃገራት ታማኝ የልማት አጋር ሆነው ተባብረው የመስራት ብሎም የመለወጥ እድላቸውን በተከተሉት የአስተዳደር ዘይቤና ስግብግብነት ምክንያት ያባከኑ መሆናቸው ያስታውሳሉ።
ከዚህ በተቃርኖ ኢትዮጵያ በተባበሩት አረብ ኤሚሬትስና በኤሽያ ሃገራት የኢንቨስትመንት መዳረሻ መሆኗን በመረዳት ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት መወሰኗ ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን ይሞግታሉ።