የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ ስምምነት ለባህር በር መዳረሻና ለስትራቴጂካዊ ግንኙነት ቁልፍ እርምጃ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እና የሶማሌላንድ ስምምነት ለባህር በር መዳረሻና ለስትራቴጂካዊ ግንኙነት ቁልፍ እርምጃ ነው
አዲስ አበባ፤ ጥር 03/2016 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ የተፈራረሙት ስምምነት ለባህር በር መዳረሻ እና ለቀጣናው ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ቁልፍ እርምጃ መሆኑ ተመላከተ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሥምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
በሥምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ ወደብና የጦር ሰፈር መገንባት የሚያስችላትን ቦታ በሊዝ የምታገኝ ሲሆን ሶማሌላንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ የልማት ኩባንያ ድርሻ የምታገኝ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሥምምነትን በተመለከተ ሰፊ ትንታኔን ያቀረበው አፍሪካን ኒውስ ስምምነቱ በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ አውዶች ረገድ ግዙፍ ፋይዳዎች እንደሚኖሩት አመልክቷል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ ከማስቻሉ ጎን ለጎን ምርቶች የሚከማቹበት ተጨማሪ ወደብ በማስገኘት የገበያ ተደራሽነቷን እንደሚያሰፋው ነው የተመለከተው።
የሰፊ ህዝብ ባለቤትና ከፍተኛ ኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ የሆነችው ኢትዮጵያ ቁልፍ ስምምነት ማካሄዷን ያተተው ዘገባው ስምምነቱ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል ያለውን የማህበራዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊና ፖለቲካዊ ግንኙነት እንደሚያጠናክረው አብራርቷል።
በቀጣናው የኢኮኖሚና ተዛማጅ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አሊ ሆጂጅ በዘገባው ላይ እንዳመለከቱት ኢትዮጵያ የቀጣናው ግዙፍ ኢኮኖሚና ህዝብ ባለቤት እንደመሆኗ የእድገት ጉዞዋን የሚመጥን ዘርፈ ብዙ እርምጃዎችን መውሰድ ያስፈልጋታል።
ከሶማሌላንድ ጋር ያካሄደችው ስምምነትም የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ከማጠናከር ባለፈ በጅቡቲ ብቻ የነበረውን የወደብ ተጠቃሚነት በማስፋት የባህር በር እንድታገኝ ያስቻለ ቁልፍ ርምጃ መሆኑን አብራርተዋል።
ስምምነቱ ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሀገር ሆና በተቀላቀለችበት ወቅት የተካሄደ መሆኑም ትልቅ ስኬት ነው ያሉት ባለሙያው ኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የሚኖራትን ስትራቴጂካዊ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከብሪክስ አባል ሀገራት ጋር የሚኖራትን ሁለገብ ግንኙነት እንድታሰፋ የሚያስችል መሆኑን ነው የገለጹት።
በቀጣናውና በመካከለኛው ምሥራቅ በሚካሄዱ የንግድ እንቅስቀሴዎች ላይም በባለቤትነት ለመሳተፍ ይህ ስምምነት ቁልፍ መሆኑን ያተቱት ባለሙያው ሶማሌላንድ እንደ ሀገር እውቅና እንድታገኝና በአካባቢው የሚኖራትን ተሰሚነት የሚያሳደግ መሆኑን አስገንዝበዋል።