በደቡብ ምስራቅ ብራዚል በጣለ ከባድ ዝናብ በትንሹ ሰባት ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 15/2016(ኢዜአ)፦በደቡብ ምስራቅ ብራዚል በጣለ ከባድ ዝናብ በትንሹ ሰባት ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

ከሬዮዴጄኔሮ 65 ኪሎ ሜትሮችን በምትርቀው ፔትሮ ፖሊስ በደረሰው አደጋ በትንሹ ሰባት ሰዎች መሞታቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ገልጸዋል።

በአደጋው ለ16 ሰዓታት ያክል በጭቃ ተሸፍና ህይወቷን ማትረፍ የተቻለ የአራት ዓመት ታዳጊን ጨምሮ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ዝናቡን ተከትሎ ከተከሰተው የመሬት መንሸራተት ከ100 በላይ ሰዎችን ማዳናቸውም ተገልጿል።

መቀመጫውን በሰሜን አሜሪካ ያደረገው ፒቢኤስ(public broadcasting service) እንደዘገበው ረዘም ላለ ሰዓት በጣለው ዝናብ ምክንያት በከተማዋ የመሬት መንሸራተትን ጨምሮ ቤቶችም ፈራርሰዋል።

የከተማው ከንቲባ ክላውዲዮ ካስትሮ እንደገለጹት ካለፈው ሀሙስ ጀምሮ አደጋው ሊከሰት እንደሚችልና ነዋሪዎቹም እንዲጠነቀቁ መልዕክት ተላልፏል።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለማዳን በአነፍናፊ ውሾች ጭምር በመታገዝ የነፍስ አድን ስራዎችን እያከናወኑ ሲሆን እስከ አሁን አንድ ሰው የደረሰበት እንዳልታወቀ ተገልጿል።

የአየር ትንበያ ባለሙያዎች በፔትሮፖሊስ የተከሰተው ከባድ ዝናብ ኤስፒሪቶ ሳንቶ ወደተባለው አጉራባች ክልል ሊገባ እንደሚችልና አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም