በእስራኤልና ኢራን መካከል የሚታየውን አሳሳቢ ሁኔታ ሀገራት በአስቸኳይ ሊያስቆሙት ይገባል- አንቶኒዮ ጉተሬዝ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 7/2016(ኢዜአ)፡- አለም ተጨማሪ ጦርነት እንድታስተናግድ እድል ባለመፍጠር በእስራኤልና ኢራን መካከል የሚታየውን አሳሳቢ ሁኔታ ሀገራት በአስቸኳይ ሊያስቆሙት እንደሚገባ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አሳሰቡ።

ኢራን እስራኤል ከሳምንታት በፊት ሶርያ በሚገኘው ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ጥቃት አድርሳብኛለች በሚል ባሳላፍነው ቅዳሜ ሌሊት መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘሯ በተለያዩ የዓለም መገናኛ ብዙሃን መዘገቡ ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ በቀጣናውና በአለም ሀገራት የተፈጠረውን ከፍተኛ ውጥረት ለማርገብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የጸጥታ ምክር ቤቱን አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል።

በስብሰባውም አለም ተጨማሪ ጦርነት የምታስተናግድበት ምንም አይነት አቅም ስለሌለ ሀገራት በእስራኤልና ኢራን መካከል የሚታየውን አሳሳቢ ሁኔታ በአስቸኳይ ሊያስቆሙት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ችግሩ በቸልታ የሚታይ ከሆነ አስከፊ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል መናገራቸውን ያስነበበው ፍራንስ 24 የጸጥታው ምክር ቤት አባላት ሁኔታውን በአስቸኳይና ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ሊያስቆሙት እንደሚገባ ማሳሰባቸውንም ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም