የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአርሶ አደሩን ምርታማነት የሚያሳድጉ ዘጠኝ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች በምርምር አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአርሶ አደሩን ምርታማነት የሚያሳድጉ ዘጠኝ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች በምርምር አገኘ
ባህር ዳር ፤ ሚያዝያ 15/2016(ኢዜአ)፦ የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአርሶ አደሩን ምርታማነትን የሚያሳድጉ ዘጠኝ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎች በምርምር መገኘታቸውን አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አስማረ ደጀን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት ከአምስት እስከ ስድስት ዓመታት በተካሄደ ምርምር የተገኙት የሰብል ዝርያዎቹ በሽታና ድርቅን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት መስጠት የሚችሉ ናቸው።
በምርታማነታቸውና ፈጥኖ በመድረስም ከተለምዶው የተሻሉ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ዝርያዎቹ በብሄራዊ ዝርያ አፅዳቂ ኮሚቴ ተገምግመው መለቀቃቸውን ገልጸው፤ ከመካከላቸውም ሁለት የማሽላ፣ ሶስት የበቆሎና ቀሪዎቹ ደግሞ የአኩሪ አተር፣ ሽምብራ፣ ድንችና ጥቁር አዝሙድ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ከእነዚህም ውስጥ የማሽላ፣ የአኩሪ አተር፣ የሽምብራና የጥቁር አዝሙድ ዝርያዎች ከጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል የወጡ እንደሆኑ ጠቅሰው፤ የበቆሎ ሰብል ዝያዎቹ ደግሞ ከሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከል በማላመድ እንደተገኙ አስረድተዋል።
እንዲሁም ከአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል አንድ የድንች ዝርያ፣ ከደብረ ብርሃን ግብርና ምርምር ማዕከል ደግሞ አንድ የማሽላ ሰብል ዝርያዎች በምርምር የተገኙ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ከጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል የተገኘው የማሽላ ዝርያ በሄክታር 41 ነጥብ 5 ኩንታል፣ ከደብረ ብርሃን ምርምር ማዕከል የወጣው ደግሞ በሄክታር 52 ኩንታል ምርት መስጠት እንደሚችሉ ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።
በተጨማሪም ከዚሁ ምርምር ማዕከል የተለቀቀው አዲሱ የጥቁር አዝሙድ በሄክታር 9 ኩንታል በላይ ምርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ከሰቆጣ ግብርና ምርምር ማዕከል የተለቀቁት ሶስት የበቆሎ ዝርያዎች ደግሞ በሽታና ድርቅን ተቋቁመው በእርጥበት አጠር አካባቢዎች በሄክታር እስከ 48 ኩንታል ምርት እንደሚሰጡ አስረድተዋል።
እንዲሁም ከአዴት ግብርና ምርምር ማዕከል የተለቀቀው አዲሱ የድንች ዝርያ በሄክታር 425 ኩንታል ምርት እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ ቀደም ብለው ከተለቀቁት የድንች ዝርያዎች በምርታማነት ደረጃ በ37 በመቶ የምርት ብልጫ እንዳለው አስታውቀዋል።
ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን በማፍለቅ፣ በማባዛትና የወጡትን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ ለምርታማነት ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከተቋቋመ ከ1992ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን 173 አዳዲስ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን በማውጣት ለሰብል ምርታማነት ማደግ የድርሻውን መወጣቱም ተመልክቷል።