የሽግግር ፍትሕ - የአያሌ ችግሮች መፍቻ

የሽግግር ፍትሕ - የአያሌ ችግሮች መፍቻ

(ሙሴ መለሰ)

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች በደል፣ ግፍ እና መሠረታዊ የመብት ጥሰቶች ተከስተዋል። የቁርሾ እና የቂም በቀል አዙሪት፣ የተበዳይነት እና የብሶት ትርክት በሀገሪቱ ዋነኛው የፖለቲካ ማጠንጠኛ የሆነበት አንዱ ምክንያትም ይኸው ነው። 

በደሎችን በማከም ሰላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር መገንባትን ባለመ መልኩ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ለመተግበር ጥረቶች በመደረግ ላይ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ የነበረውን ኢ-ፍትሃዊነት በፍትሕ፣ በእርቅና በይቅርታ መፍትሔ ለመስጠት የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጭ ሰነድ ዝግጅት በጥር ወር 2015 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል።

ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት በወቅታዊ ሀገራዊ የደኅንነት እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ በቅርቡ ያወጣው መግለጫ እንዳመላከተውም በኢትዮጵያ የበዳይ ተበዳይ አዙሪት ለመስበር የሽግግር ፍትሕ አንዱ ተመራጭ ሥልት ነው።

ከአንድ ዓመት በላይ በዝግጅት ሂደት የቆየው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ መወሰኑን ተከትሎ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብርም ተካሂዷል።

የሽግግር ፍትሕ ታሪካዊ ዳራ

የሽግግር ፍትሕ ዘርፍ ታሪካዊ መነሻ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1939 እስከ 1945 ከተደረገው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ፍትሕን ለማስፈን የተደረገ እንቅስቃሴ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1945 በጀርመን ኑረንበርግ የተሰየመ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ችሎት የተቋቋመ ሲሆን፤ ችሎቱ የተቋቋመው ዋና የናዚ መሪዎችን የፍርድ ሂደት ለመከታተልና ውሳኔ ለመስጠት ነው።

በወቅቱ የናዚ መሪዎች በጦር ወንጀል፣ በሰብዓዊ ጥፋት እንዲሁም ወንጀሎችን ለመፈጸም በማሴር ተከሰዋል። ለአንድ ዓመት የቆየው የፍርድ ሂደትም በናዚ ሰዎች ላይ ያሳለፈው ውሳኔ “ታሪካዊ” እና “ታላቅ” የሚል አድናቆትን አግኝቶ ነበር።

የጦርነቱም የፍርዱም ተሳታፊዎች “ጨርሶ አይደገምም፤ Never again” የሚል ቃል ገብተው ነበር። በወቅቱ የጃፓን ወታደሮች የፍርድ ሂደት የሚታይበት የቶኪዮ ወታደራዊ ችሎትም ተቋቁሞ ነበር።

በኑረንበርግ እና በቶኪዮ የነበሩት ወታደራዊ ችሎቶች ለሽግግር ፍትሕ እሳቤ መጠንሰስ ቁንጮ ማሳያዎች እንደሆኑ ይነገራል።

በግሪክ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1945 እና በአርጀንቲና እ.አ.አ በ1983 የቀድሞ ወታደራዊ መንግሥት አባላት የፍርድ ሥርዓትም እንደ ሽግግር ፍትሕ ማሳያ ይጠቀሳሉ።

የሽግግር ፍትሕ ዘርፍ እ.አ.አ ከ1980 በኋላ ያለው እሳቤና ተፈጻሚነቱ እያደገ የመጣ ሲሆን፤ እ.አ.አ በ1970 እና 1980ዎቹ ትኩረቱን የሰብዓዊ መብቶች መከበርና መጠበቅ ላይ አድርጓል።

ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሽግግር ፍትሕ ተቀባይነት እንዲያገኝና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕጎችና ስምምነቶች እንዲቋቋሙ በር ከፍቷል።

በወቅቱ የሽግግር ፍትሕ እሳቤ ማዕከል የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በፖለቲካ ሽግግር እንዲሁም በሕግና ወንጀል ፍርዶች ወቅት እንዴት ይቃኛሉ? እንዴት ይታያሉ? የሚለው ጉዳይ ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ የሽግግር ፍትሕን አስመልክቶ የነበሩ ክርክሮች “ፍትሕ” ለሚለው ዓለም አቀፍ ጽንሰ-ሀሳብ መዳበርና መስፋት አስተዋጽዖ እንደነበረውም ይጠቀሳል።

በሂደት የሽግግር ፍትሕ እየሰፋ በተለይም እ.አ.አ በ1980ዎቹ መጨረሻና በ1990 መግቢያ ላይ ዴሞክራሲና የዴሞክራሲ እሳቤዎች ዓለምን እየተቆጣጠሩና ተጽዕኗቸው እየጨመረ ሲመጣ የሽግግር ፍትሕ ከዴሞክራሲ አንጻር መቃኘት ጀመረ።

በዚህም የሽግግር ፍትሕ የዴሞክራሲ እሳቤ አንዱ የጥናት ዘርፍ መሆን የቻለ ሲሆን፤ የሽግግር ፍትሕ “ጠባብ ከነበሩ የሕግ ጥያቄዎች ወደ የተረጋጉ የዴሞክራሲ ተቋማት መገንባትና የሲቪክ ተቋማት እንደገና ማደስ ወደሚል ሰፊ የፖለቲካ አመክንዮዎች አድማሱን አስፍቷል” ሲሉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የሽግግር ፍትሕን ማዕቀፍ ከፖለቲካዊ ሂደቶችና ዴሞክራሲያዊ ለውጦች ጋር ያቆራኙ አገራት ከአምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመሸጋገር ምቹ መደላድል እንደፈጠረላቸው በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉ ተመራማሪዎች ይጠቅሳሉ።

በዴሞክራሲያዊ ሂደት ውስጥ ያሉ የሽግግር ፍትሕ ፈተናዎች በርካታ ናቸው የሚሉት ምሁራን የዴሞክራሲ ሂደቱ ሳይጓተት ላለፉ ቁርሾዎች መፍትሔ መስጠት፣ ግጭቶችን የሚፈታ የዳኝነት ወይም የሦስተኛ ወገን የፍትሕ ሥርዓት መዘርጋት፣ የካሳ ክፍያዎችን መፈጸም፣ ያልሻሩ ቁስሎች እንዲሽሩና የባህል እርቆችን የተሟላ ማድረግ ከፈተናዎቹ መካከል የሚጠቀሱ እንደሆኑ ያነሳሉ።

ካናዳ፣ አውስትራሊያና ኒውዝላንድ አገራቱን የቆረቆሩ ነባር ዜጎች ይደርስባቸው ለነበረው ጭቆና ምላሽ ለመስጠት የሽግግር ፍትሕን ተጠቅመውበታል። በአሜሪካም “የዘር ፍትሕ Racial justice” አስመልክቶ በሚደረጉ ውይይቶችና ክርክሮች የሽግግር ፍትሕ ቋንቋና ሀሳብ ደጋግሞ ይነሳ ነበር።

የሽግግር ፍትሕ አንድ የወለደው ሀሳብ ቢኖር የ”እውነት ፈላጊ” ኮሚሽኖች (Truth commissions) ማቋቋም ነው። በአርጀንቲና እ.አ.አ በ1983፣ በቺሊ እ.አ.አ በ1990 እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ እ.አ.አ በ1995 የ”እውነትን አፈላላጊ” ኮሚሽኖች ተቋቁመዋል። 

ኮሚሽኖቹ በላቲን አሜሪካ፣ አፍሪካ፣ እስያና ምስራቅ አውሮፓ እንደ ሽግግር ፍትሕ “ምልክት” ይታዩ የነበረ ሲሆን፤ ይሁንና በዩጎዝላቪያ ለተፈጸሙ ወንጀሎች ቀጣናዊ የእውነት ፈላጊ ኮሚሽን ለማቋቋም ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢደረጉም በፖለቲካ መሰናክሎች ምክንያት ሳይሳኩ መቅረታቸውን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

የዴሞክራሲ ምሁራንና ባለሙያዎች አገራት በሽግግር ፍትሕ ማዕቀፎቻቸው ውስጥ ብሔራዊ ስትራቴጂዎቻቸውን ሲቀርጹ ያለፉ በደሎችንና ቁርሾዎችን እንደ አገሪቷ ተጨባጭ ሁኔታና ባህርይ መፍታትን በዋናነት ከግምት ውስጥ ሊያስገቡ እንደሚገባ ይመክራሉ።

ይህ ቁርሾን የመፍታት ሂደት ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ ከሕግ ተጠያቂነት የማምለጥ ዝንባሌን ለማስቀረት፣ በዜጎችና መንግሥታት መካከል ያለውን ግንኙነት እንደገና ለማደስና ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን ለመገንባት አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ ይገልጻሉ።

የሽግግር ፍትሕ ሰፊ የአስተሳሰብ ማዕቀፍ ዜጎች ሁሌም ኋላቸውን እያዩ ወይም ካለፉ ክስተቶች ጋር ከመጋፈጥ ወደፊት የተሻለ ነገር ይመጣል ብለው ተስፋ እንዲሰንቁ እንደሚያደርግም ይጠቅሳሉ።

እ.አ.አ በ2001 በሽግግር ፍትሕ፣ እርቅና ርትዕ ላይ የሚሰራ “ዓለም አቀፍ የሽግግር ፍትሕ ማዕከል” የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም የተመሠረተ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪ ዓለም አቀፍ የፍትሕ ግብረ-ኃይል ተቋቁሟል።

የሽግግር ፍትሕ በዘላቂ ልማት ግቦች መካከል ግብ 16 “የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አፋጣኝ የፍትሕ ጣልቃ-ገብነት እርምጃዎች በመውሰድ ዘላቂ ሰላምና ልማት ማምጣት” የሚለውን ለማሳካት አጋዥ ነው። 

የሽግግር ፍትሕ ትርጓሜዎች

እንደ ዓለም አቀፉ የሽግግር ፍትሕ ማዕከል ከሆነ የሽግግር ፍትሕ “ከግጭት የወጡ አገራት በመደበኛ የፍትሕ ሥርዓት በቂ ምላሽ ሊሰጡባቸው የማይችሏቸውን ከፍተኛ፣ የተደራጁና በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ምላሽ የሚሰጡባቸው መንገዶች ናቸው።” 

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሽግግር ፍትሕ ለፍትሕ ብቻ ትኩረት በማድረግ ፍትሃዊ የኃብትና አገልግሎት ክፍፍል ማድረግ ወይም ለኢ-ፍትሃዊነት ምላሽ መስጠት ሳይሆን “ከአቅም በላይ ለሆኑና ልዩ ባህርይ ላላቸው ፈተናዎች ምላሽ የሚሰጥበት አካሄድና መንገድ ነው” ሲል ይገልፀዋል።

የወንጀል ቅጣቶች፣ የእውነት ፈላጊ ኮሚሽኖች መቋቋም፣ ካሳ መክፈል፣ ሰዎች በግጭት ወቅት ያጡትን ወይም የተሰረቁትን ንብረትና ኃብት መተካት፣ በጅምላ መቃብር ውስጥ የተቀበሩ ሰዎች በክብር ለየብቻ እንዲቀበሩ ማድረግ፣ ይቅርታና ምህረት ማድረግ፣ መታሰቢያዎችን መገንባት፣ በግጭቶቹ ላይ ሳይንሳዊ ምርምር በማድረግ ግጭቶችና በደሎች እንዳይደገሙ በሚያደርግ መልኩ ትምህርቶችን ማስተማርና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ምላሽ የሚሰጡ ተቋማዊ የማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰድ በሽግግር ፍትሕ ውስጥ ከሚካተቱ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።

በሌላ በኩል በሽግግር ፍትሕ በፖለቲካዊ ሽግግር ውስጥ የሕግ የበላይነትን ማስፈን በዚህም ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት የሚደረግ ጉዞን ማፋጠን ያስፈልጋል የሚሉ ምሁራንም አሉ።

የሽግግር ፍትሕ በኢትዮጵያ 

በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት በደሎችን በማከም ሰላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር መገንባትን ባለመ መልኩ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ለመተግበር ጥረቶች በመደረግ ላይ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ ያሉ አለመግባባትና ግጭቶችን ለመፍታት የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ ትክክለኛ አማራጭ መሆኑ ይገለጻል።

የሽግግር ፍትሕ በሕዝቦች መካከል መተማመን እና ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር ሁሉንም የሚያሳትፍ፣ የሕግ ተጠያቂነት፣ ፍትሕ፣ እርቅና ካሳን ጭምር ታሳቢ የሚያደርግ እንደሆነ ተጠቅሷል።

በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ማዕቀፍ መዘርጋት አስፈላጊነት ታምኖበት ሁሉን አቀፍ አካታችና ተመጋጋቢ የሆነ ፖሊሲ ለማዘጋጀት ላለፉት ጊዜያት ሰፊ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል።

ኢትዮጵያ በዘመናት ሂደት ያጋጠሟትን ፈተናዎች በዘላቂነት ለመፍታት የሽግግር ፍትሕ ሂደት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ታምኖበታል።

የሽግግር ፍትሕ ሰላምና ፍትሕን አስተሳስሮ የመሄድ ጉዳይ እንደሆነና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የማይተካ ሚና እንዳለው እንዲሁም በሂደቱ የይቅርታና ምህረት ጉዳዮችን እንደሚያቅፍ የሕግ ምሁራን ይገልጻሉ።

በጦርነት የተጎዱ አካላትን ማቋቋም በሽግግር ፍትሕ እንደሚታይና በዚህም ዘላቂ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጋጋት ማምጣት እንደሚቻል ያስረዳሉ።

የተለያዩ አገራት ከነበሩባቸው በርካታ ቀውሶች ወጥተው ወደ ሰላም የመጡበት ሂደት መሆኑን በማውሳት የዘርፉ ባለሙያዎችን ባካተተ መልኩ በቁርጠኝነት ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባ ምክረ-ሀሳባቸውን ያስቀምጣሉ።

የሽግግር ፍትሕ ስልቶች ያለፉ በደሎችን፣ ቁርሾዎችን፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ አለመግባባትና ጥርጣሬን በአግባቡ በመፍታት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ምቹ መደላድል መፍጠር ዋነኛ ዓላማው ነው።

ቀደም ሲል ከነበረ አለመግባባት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲላቀቅ በማድረግ ቀጣይነት ያለው አብሮነትና መተማመን መፍጠር የሚያስችል የፍትሕ ማስገኛ ስልትም ነው።

አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ አገራት በሽግግር ፍትሕ ስልቶች አልፈው ከነበሩበት ውስብስብ ችግር በመውጣት የተሻለ ሰላም፣ መረጋጋት እና የሕግ የበላይነት ማስፈን ችለዋል።

ለአብነትም ኮሎምቢያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዩጋንዳና ሴራሊዮን ካለፉበት አስከፊ የእርስ በርስ ግጭትና አፓርታይድ ሥርዓት በሽግግር ፍትሕ መፍትሔ በመስጠት የተሻለ ሀገር መገንባት መቻላቸው በማሳያነት የሚቀርብ ነው።

በኢትዮጵያም በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ሊፈቱ የማይችሉ የረዥም ዓመታት ጥፋቶችን ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሽግግር ፍትሕ ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ መሆኑ ታምኖ እየተሰራበት ይገኛል።

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ዝግጅት

በኢትዮጵያ የነበረውን ኢ-ፍትሃዊነት በፍትሕ፣ በእርቅና በይቅርታ መፍትሔ ለመስጠት የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጭ ሰነድ ዝግጅት በጥር ወር 2015 ዓ.ም መጀመሩ ይታወቃል።

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ የሚያዘጋጅና ከተለያዩ ተቋማት የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ ምህረት መስጠትን፣ የሕግና ተቋማት ማሻሻያ ማድረግን፣ ማካካሻ መስጠትን፣ እውነትን ማፈላለግን እና ተጠያቂነትን ማስፈንም የሽግግር ፍትሕ ሰነዱ ዓላማ አድርጎ የሽግግር ፍትሕ የደረሰበትን ደረጃ ባገናዘበ መልኩ ፖሊሲው ሲዘጋጅ ቆይቷል።

ሰላምን በማረጋገጥ፤ በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት የማኅበረሰብን ትስስር መመለስ ያስፈልጋል የሚለው ጉዳይ ከፖሊሲው የትኩረት አቅጣጫ መካከል የሚጠቀስ ነው።

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን በተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪክ ተቋማት፣ የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ ከዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ቀጣናዊ ተቋማት ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በርካታ ውይይቶች ተደርገዋል።

የፖሊሲው ዝግጅት የሚመለከታቸውን አካላት ያሳተፈ፣ ዓለም አቀፍ ልምድን መሠረት ያደረገ ነው። በቅድመ-ፖሊሲ ማርቀቅ ሂደቱ ብቻ 60 የክልል እና 20 ሀገራዊ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች እንደተካሄዱበት ተልጿል።

በተጨማሪም መንግሥት የሽግግር ፍትሕ አማራጮችን አስመልክቶ ሕዝባዊ ውይይቶችን በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች አድርጓል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሚያዝያ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ባደረገው 30ኛ መደበኛ ስብሰባ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ጸድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ ወስኗል።

በሀገሪቱ በተለያዩ ዘመናት የተከሰቱ እና የቀጠሉ ተደራራቢ እና ሰፊ የተጎጂና የአጥፊ ወሰን ያላቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የእርስ በርስ ግጭቶች፣ ያልጠሩ ትርክቶች እና በደሎችን ለመፍታት የተለያዩ ሙከራዎች መደረጋቸውን አስታውሷል።

ሆኖም እነዚህ አሠራሮች በእውነት፣ በዕርቅ፣ በምህረት፣ በፍትሕ ላይ የተዋቀረ እና በግልፅ ፖሊሲ የሚመራ ሁለንተናዊ የሽግግር ፍትሕ ስልትን አካታች፣ ሰብዓዊ መብት ተኮር በሆነ እና በተሰናሰለ መንገድ ባለመተግበራቸው የሚፈለገውን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት አልቻሉም ብሏል።

ስለሆነም የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን በተደራጀ፣ በተቀናጀ እና ውጤታማ በሆነ መልኩ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመምራትና ለመተግበር እንዲቻል ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡንና ምክር ቤቱ ግብዓቶችን በማከል ፖሊሲው ከጸደቀበት ቀን እንስቶ ሥራ ላይ እንዲውል ውሳኔ አሳልፏል።

የባለድርሻ አካላት ሚና

በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲተገበር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብር ወሳኝ መሆኑ ዕሙን ነው። በፖሊሲው እንደተመላከተውም የሽግግር ፍትሕ ሥራዎችን ተግባራዊ የሚያደርጉ ተቋማት በርከት ያሉ ናቸው፡፡ 

በዚህ ሂደት የመንግሥት አካላት ሚናቸው ከፍተኛ ሲሆን ለአብነትም የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን፣ የፌዴራል እና የክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ሰላም ሚኒስቴር፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው።

ለምሳሌ የፍትሕ ሚኒስቴር የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓቱን በበላይነት የመምራት እና የማስተባበር ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም የሽግግር ፍትሕ ሂደቱ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲፈፀም ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር አንፃር ትልቅ የቤት ሥራ አለበት፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴርም የአገሪቱን የፋይናንስ ሥርዓት የማስተዳደር፣ የፌዴራል መንግሥት በጀትን የማዘጋጀት፣ የተፈቀደ በጀትን ለሚመለከተው አካል የመላክ፣ አፈጻጸሙን የመገምገም እና የመሳሰሉት ተግባራት እና ኃላፊነቶች ያሉት መሥሪያ ቤት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ትግበራ ጋር በተያያዘ የሚኖሩት ተግባርና ኃላፊነቶች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን የሽግግር ፍትሕ ሥርዓቱ አተገባበር በሕዝብ ተቀባይነት እንዲኖረው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ማኅበረሰቡን የማሳወቅ እና የማንቃት ሥራ እንዲሰሩ እንዲሁም በሽግግር ፍትሕ አተገባበር የቴክኒክ እና የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉ ማስተባበር ይጠበቅበታል።

የፌዴራል እና የክልል ፖሊስ ተቋማት የተለያዩ የሽግግር ፍትሕ ስልቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚቋቋሙ ተቋማት ወይም አደረጃጀቶች ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ጊዜ የሰላም እና የፀጥታ ችግር እንዳይገጥማቸው አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የተለያዩ የሽግግር ፍትሕ ስልቶችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ሕጎችን ቅድሚያ እና ትኩረት በመስጠት ከማጽደቅ፣ ለሽግግር ፍትሕ ሥርዓቱ ትግበራ የሚቋቋሙ ተቋማት ኮሚሽነሮች እና ዳኞች ሹመት ግልፅ በሆነ እና የሕዝብን ተሳትፎ በሚያረጋግጥ ሂደት እንዲከናወን ከማድረግ ወዘተ አኳያ ኃላፊነቱ ከፍተኛ ነው።

የሰላም ሚኒስቴር በበኩሉ የሽግግር ፍትሕ አተገባበርን አስመልክቶ ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር እና አዎንታዊ ሰላም እንዲገነባ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በመቀናጀት የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የአቅም ግንባታ ሥራ በመሥራት፣ የሽግግር ፍትሕ ዘላቂ ሰላምን ሊያመጣ በሚችል አግባብ በሁሉም ክልሎች ወጥ በሆነ መንገድ እየተተገበረ ስለመሆኑ በመከታተልና አስፈላጊውንም ድጋፍ በማድረግ ረገድ ትልቅ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል።

በአጠቃላይ ከሽግግር ፍትሕ ሥርዓት አተገባበር ጋር በተያያዘ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ሚና የሚኖራቸው የመንግሥት ተቋማት ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎችም አካላት ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው።

እነዚህ አካላት የሽግግር ፍትሕ ሂደት ትግበራው የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን ያከበረ፣ ተጎጂን ማዕከል ያደረገ እና የፖሊሲውን መርሆዎች ያከበረ መሆኑን በመከታተልና በመደገፍ፤ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ስለ ሽግግር ፍትሕ ሥርዓት እና ሂደት በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና የሽግግር ፍትሕ ሥርዓቱ አተገባበር በሕዝብ ተቀባይነት እንዲኖረው በማድረግ፤ ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆን የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

እንደ መውጫ

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር በቅርቡ ተካሂዷል። በዚሁ ወቅት እንደተገለጸውም መንግሥት የተሟላና ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚያስችል የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ለማዘጋጀት አስቀድሞ የገለልተኛ ሙያተኞች ቡድን በማዋቀር ሲሰራ ቆይቷል። 

ከ80 በላይ ሕዝባዊ የግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረኮች በማዘጋጀት ማኅበረሰቡ በስፋት ሃሳብ እንዲሰጥ በማድረግም የተገኙ ግብዓቶችን በፖሊሲው በማካተት እንዲፀድቅ መደረጉ ተገልጿል።

የፖሊሲው አጠቃላይ ዓላማ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አውድ መሠረት ያደረገ፣ የተቀናጀ እና የተናበበ የሽግግር ፍትሕ ሂደት የሚመራበት እና የሚተገበርበትን ሥርዓት በመዘርጋት ዘላቂ ሰላም፣ ዕርቅ፣ የሕግ የበላይነት፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ የሚረጋገጥበትን መደላድል መፍጠር መሆኑ በግልጽ መታወቅ ይኖርበታል።

የሽግግር ፍትሕ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት እንዲያመጣና ዜጎች ነገን በተስፋ እንዲጠብቁና በአገራቸው ላይ ብሩህ ተስፋ እንዲኖራቸው በተሟላ መልኩ መተግበር አለበት። ለዚህም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ድጋፍና ትብብር ወሳኝ ነው።

የሽግግር ፍትሕ ሂደቱና አገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ ካለችበት ችግር ወጥታ ወደ ቀጣዩ የእድገት ምዕራፍ እንድትሸጋገር ከማድረግ አኳያ እርስ በርስ የሚመጋገቡ ሲሆን፤ ከዚህ አንጻር ሁለቱ በሚጣጣሙባቸው አጀንዳዎችና ግቦች ላይ በጋራ በመሥራት ሁሉን አቀፍ ውጤት ማግኘትም ይቻላል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም