ሰው ሰራሽ አስተውሎት የመረጃ ስርጭትን በፍጥነት እየተለወጠ ባለበት አለም አፍሪካ ትክክለኛ ድምጿን እንድታሰማ ሀገራት ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ሰው ሰራሽ አስተውሎት የመረጃ ስርጭትን በፍጥነት እየተለወጠ ባለበት አለም አፍሪካ ትክክለኛ ድምጿን እንድታሰማ ሀገራት ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 8/2016(ኢዜአ)፦ ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ጋር በተገናኘ የመረጃ ስርጭት በፍጥነት እየተለወጠ ባለበት አለም አፍሪካ ትክክለኛ ድምጿን እንድታሰማ ለማድረግ ሀገራት ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ ቀረበ።
በአህጉሪቱ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ ላይ የሚመክረው 3ተኛው የአፍሪካ ሚዲያ ኮንቬንሽን በጋና አክራ እየተካሄደ ይገኛል።
አፍሪካዊ መረጃዎችን ለአርቴፍሻል አስተውሎት ግብአት በሚሆን መልኩ በማዘጋጀትና የአህጉሪቱን መጪ የቴክኖሎጂ ጉዞ በማፋጠን በኩል ሚዲያው ከፍተኛ ሚና እንዳለው በጉባኤው ተነስቷል።
የዘንድሮው ጉባኤ የሚዲያ ነፃነትና የመረጃ ተደራሽነት እንዲሁም ሚዲያውን በኢኖቬሽንና በሰው ሰራሽ አስተውሎት የማገዝ አጀንዳዎችን መያዙ ተገልጿል።
በተጨማሪም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ሀገራት የሚወስዱትን መፍትሄዎች ለብዙሃኑ መረጃ የማድረስ ሃላፊነታቸውን ሚዲያዎች እንዲወጡ ማድረግ ላይም ጉባኤው ይመክራል ተብሏል።
በ3ተኛው የአፍሪካ ሚዲያ ኮንቬንሽን ላይ የሀገራት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የአፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስራ መሪዎችና ከመላው አፍሪካ የተውጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች ተሳታፊ ናቸው።
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ ኢትዮጵያ በተለይ በሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፎች የምታከናውናቸውን ተግባራት በተመለከተ ልምዷን እንደምታካፍል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መረጃ ያመላክታል።