መከላከያ ሠራዊት-የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የመጨረሻ ምሽግ

በዋጋ ለተቀበሉት ኪዳን ያለጥርጥር መታመን፣ ለእውነትና ለፍትሕ በርትዕ መቆም የአላማ አይነተኛ ፍቺ ነው። የዚህም ነጸብራቅ ደግሞ ሰራዊት ነው። የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የካቲት 1993 ያሳተመው አማርኛ መዝገበ ቃላት ሰራዊት የሚለውን ቃል “ለአንድ አላማ በአንድ ቡድን ውስጥ የተሰባሰበ ብዙ ህዝብ” የሚል ፍቺ ሰጥተቶታል። 

ከጥሬ ቃላቱ ጥቅል ትርጉም እንደምንረዳው ሰራዊት ለህዝቦች ሉዓላዊነት እና አንድነት በአላማ የቆመ የአሸናፊነትን አርማን ስንቁ በማድረግ የሚጓዝ የህዝብ ልጅ ማለት ነው። በዚህ አላማና ርዕይ የተሰራው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትም የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና የዜጎቿን ደኅንነት የማረጋገጥ ታሪካዊ ኃላፊነት የተሸከመ ህዝባዊ ሰራዊት ነው። 

የመከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ የገጠሟትን እና የሚገጥሟትን ፈተናዎች ድል በማድረግ ከፍታዋን አስጠብቆ የኖረ እና የሚኖር ሰራዊት ነው። የሰራዊቱ ግብና ተልዕኮ የሉዓላዊነት ሥጋት፤ የህዝብ ሠላምና ደህንነት እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን በደም ዋጋ በማስከበር የህዝብ የሃገር ሉአላዊነትን ማስቀጠል ነው። 

የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአንድ ወቅት ስለሰራዊቱ ሲናገሩ መከላከያ ሰራዊት ያለ ሰላም እንዳይደፈርስ የሚጠብቅ፣ የጠፋን ሰላም ለማምጣት የሚተጋ፣ የመጣ ሰላምን ለማጽናት የሚሰራ ዋነኛ ዓላማውም ሰላምን ማስፋትና የሃገር ብልጽግናን ባልተቋረጠ መንገድ እውን ማድረግ ብቻ ነው ማለታቸው ይታወሳል።   

ዘመን በማያዝለው ልጆቿ ክንድ ጠላቶቿን ድል እየነሳች በአሻናፊነት የጸናችው ኢትዮጵያ ጀግናው ሰራዊቷ ከራሷ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ብሎም በአለም አቀፍ ወታደራዊ ተልዕኮዎች ብቃቱንና ሰላም አስከባሪነቱን ያስመሰከረ መሆኑም ይታወቃል።

ለዚህም ከ60 ዓመታት በፊት የሰራዊቱን ታሪካዊ ጀግንነት ያስመሰከረው የኮሪያ ጦርነት፣ የኮንጎና ሩዋንዳ ዘመቻ የጎረቤት ሀገራት ሶማሊያ እና ሱዳን ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ሕያው የታሪክ ምስክሮ ናቸው ። ሰራዊቱ በተሠማራባቸው የግዳጅ ቀጣናዎች ከጠላት ነፃ ያወጣውን ማህበረሰብ በመንከባከብ፣ በጉልበቱ የልማት ሥራዎችን ማገዝም የሰርክ ልማዱ ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአህጉር አቀፍና ቀጣናዊ የተልእኮ ስፍራዎች ያበረከታቸው ሰው ተኮር ድጋፎች የሰራዊቱን አለኝታነት በገሃድ የሚናገሩ ሀቆች ናቸው። ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር በሚል መርህ የታነፀው ሠራዊቱ ምን ጊዜም አሸናፊና በየአውደ ውጊያው ሁሉ ባለድልም ነው። 

በየጊዜው የሚነሱ ጸረ ሰላም ሃይሎችን በመደምሰስ የኢትዮጵያን ልማትና አንድነት የሚያስጠብቀው ይህ ሰራዊት አሁንም በአሸባሪው ሸኔና በፅንፈኛ ሃይሎች ላይ የማያዳግም እርምጀ እየወሰደ ይገኛል። ሠራዊቱ ከየአካበቢው የህብረተሰብ ክፍልና ፀጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን በወሰዳቸው ርምጃዎች የፅንፈኛውና አሸባሪው ቡድን እኩይ አላማ በዘለቄታዊነት እየከሸፈ ነው። 

በወታደራዊ ሳይንስ በተቀመረው ሰልታዊ ውጊያ የጥፋት ቡድኖችን ህዋስ ለይቶ በመምታት ውጤታማ ስራ እያከናወነ የሚገኘው ሰራዊቱ ህገ-ወጥ የሰዎች፣ የገንዘብና የኮንትሮባንድ ዝውውርን በመቆጣጠር የእኩይ ቡድኖችን እስትንፋስ እየቆረጠም ይገኛል።  በግዳጅ ቀጣና ህዝባዊ መድረኮች የሚነሱ ሀሳቦችን ወደ ውጤት በመቀየርም የልማትና የሰላም ተግባራትን አጠናክሮ እያስቀጠለ ነው።

ኢትዮጵያዊ ወኔን በመላበስ ዘመኑ የደረሰበትን ትጥቅ፣ ዕውቀትና ክህሎት በመያዝ የታሪካዊ ጠላቶችን እኩይ አላማ እያመከነ በደም የተጻፈ ወርቃማ ገድሉን በከፍታ ሰንደቅ ሰቅሏል። የዚህ ባለ ደማቅ ታሪክ እና የአሸናፊነት ተምሳሌት የሆነ ሰራዊት አባል መሆን ደግሞ ድርብ ክብር ነው። 

የአሸናፊነት እና የጀግንነት ተምሳሌት የሆነው ሰራዊት ወኔ የተጋባባቸው የኢትዮጵያ ወጣቶችም ሰራዊቱን  ለመቀላቀል ያሳዩት ተነሳሽነት ልብ የሚያሞቅ ነው። በሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ ጎጆ ከአራቱም አቅጣጫ የተሰበሰቡት የሰራዊቱ አባላት ህልማውቸና ጉዟቸው ወደ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና ነው። ለዚህ ደግሞ ከትውልድ ትውልድ ደም እየተቀረጸ የመጣው ኢትዮጵያዊ ጀግንነት ጉልበት ሆኖት የማይሻገረው ተራራ ድል የማይነሳው ግዳጅ የለም።

ከራስ በፊት ለህዝብና ለሀገር በሚል እሴት የታነፀው ሠራዊቱ በህዝባዊ አመለካከትና ተግባሩ ሁሌም የሚመሠገን ዛሬም ለአህጉር እና አለም አቀፍ ተልእኮዎች ተመራጭ ሃይል ነው። 

የሀገር አለኝታ የሆነውን ሠራዊት በልዩ ልዩ መልኮች መደገፍ፣ አሳሳች መረጃዎችን መከላከል፣ በአለም አቀፍ መድረኮች የሰራዊቱን ገጽታ መገንባት ከአውደ ውጊያው እኩል መዘጋጀትና መዋጋት ያንተ፣ ያንቺ ፣የኔ፣ የኛ የሁላችንም ሃላፊነት ነው። 
 
ባለፈው ጥቅምት በተከበረው 116ኛው የሰራዊት ቀን ላይ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ማክበር ኢትዮጵያን ማክበር ነው ሲሉ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድማርሻል ብርሃኑ ጁላ  መግለጻቸውም ይሄንኑ ተልዕኮ ታሳቢ ስላደረገ ነበር።

ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ያሉበት ትንሿ ኢትዮጵያ መሆኑንና የአገር አደራ የተረከበ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የመጨረሻ ምሽግ መሆኑን መግለጻቸውም አይዘነጋም።

የጀግናው መከላከያ ሠራዊት አባላትም “ለኢትዮጵያ የአሸናፊነቷ ሚስጥሮች፤ የማንዝል ብርቱ ክንዶች ደጀን የህዝብ ልጆች” እኛ ነን እያሉ ዘላለማዊ ቃል ኪዳናቸውን በከፍታ ያውለበልባሉ።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም