በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ ሀትሪክ የሰሩት ሰባት ተጫዋቾች 

አንድ እግር ኳስ ተጫዋች ለክለብህ ነው ወይስ ለአገርህ ግብ ብታስቆጥር ይበልጥ የሚያስደስትህ? ተብሎ ቢጠየቅ ለአገሬ የማስቆጥረው ግብ ትልቅ ዋጋ እሰጠዋለሁ ብሎ እንደሚመልስ አያጠራርጥርም።   

ተጫዋቾች ለአገራቸው የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አደረጉ፣ በብሔራዊ ቡድን መለያ የመጀመሪያ ግባቸውን አስቆጠሩ መባል ትልቅ ደስታና ክብር እንዲሰማቸው ያደርጋል።

ለአገራቸው ግብ በሚያስቆጥሩበት ወቅት አንዳንዴ በእንባ ሌላ ጊዜም በፈንጠዝያና በደስታ ስሜታቸውን ይገልጻሉ። በዚህም የተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ይገባሉ።

ተጫዋቾች በዓለም ዋንጫና ሌሎች አህጉራዊ ውድድሮች አገራቸውን ወክለው መጫወት ትልቁ ሕልማቸው ነው።

በእነዚህ ውድድሮች በአሰልጣኞች ጥሪ ሲደረግላቸው የመደሰትና የመጓጓት፣ ሳይካተቱ ሲቀሩ ደግሞ የማዘን ስሜት ይሰማቸዋል።

የመጀመሪያ ዙር ጥሪ ውስጥ ተካተው መጨረሻ ላይ የሚቀነሱ ተጫዋቾችም በቡድናቸው አለመካተታቸው ያስቆጫቸዋል።

በዓለም እግር ኳስ ውስጥ ከሚጠቀሱ ትልቅ ውድድሮች አንዱ የአውሮፓ ዋንጫ ሲሆን በዚህ ውድድር ላይ መሳተፍ የብዙ አውሮፓውያን ተጫዋቾች መሻት ነው።

በጀርመን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የአውሮፓ ዋንጫ ከ219 ክለቦች የተወጣጡ 622 ተጫዋቾች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ። 

ይህ ግዙፍ ስፖርታዊ መድረክ ከተጀመረ 64 ዓመቱን ደፍኗል።

የመጀመሪያው የአውሮፓ ዋንጫ (በቀድሞ አጠራሩ ኢሮፒያን ኔሽንስ ካፕ)  የተካሄደው እ.አ.አ በ1960 ነው። አዘጋጇ አገር ፈረንሳይ ነበረች። 

በውድድሩ ላይ አዘጋጇ አገርን ጨምሮ የቀድሞዎቹ ሶቪየት ሕብረት፣ ዩጎዝላቪያና  ቼኮዝሎቫኪያ ተሳትፈዋል። 

የዩጎዝላቪያው አጥቂ ሚላን ጋሊች የአውሮፓ ዋንጫ የመጀመሪያ ግብ ያስቆጠረ ተጫዋች ነው።

ሶቪየት ሕብረት ባነሳችው ዋንጫ ፈረንሳያዊው ፍራንስዋ ሁት፣ የሶቪየት ሕብረቶቹ ቫለንቲን ኢቫኖቭና ቪክቶር ፖንዴልኒክ እንዲሁም የዩጎዝላቪያዎቹ ሚላን ጋሊችና ድራዛን ጄርኮቪች በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን በማስቆጠር በጋራ የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ሆነዋል።

በ1960 አንድ ብሎ የጀመረው የአውሮፓ ዋንጫ ዛሬ 17ኛው ላይ ደርሷል። 

ከዚህ ቀደም በተደረጉ 16 የአውሮፓ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ስምንት ተጫዋቾች በአንድ ጨዋታ ሶስት ግቦችን በማስቆጥር ሀትሪክ ሰርተዋል።

በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀትሪክ የተሰራው እ.አ.አ በ1976 የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ባዘጋጀችው 5ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ነው።

በግማሽ ፍጻሜው የያኔዋ ምዕራብ ጀርመን ዩጎዝላቪያን 4 ለ 2 ስታሸንፍ ዲተር ሙለር ሶስት ግቦች በማስቆጠር ስሟን በደማቅ ቀለም አጽፏል።

ሙለር በውድድሩ በአጠቃላይ 5 ግቦችን በማስቆጠር ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመሆን አጠናቋል።

ቀጣዩ የሀትሪክ ተረኛ ሌላኛው የጀርመን የቀድሞ ተጫዋች ክላውስ አሎፍስ ነው። 

አሎፍስ እ.አ.አ 1980 ጣልያን ባዘጋጀችው 8ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ምዕራብ ጀርመን ኔዘርላንድን 3 ለ 2 ስታሸንፍ ሶስት ግቦችን ከመረብ ጋር አገናኝቷል።

ተጫዋቹ ኔዘርላንድ ላይ በሰራው ሀትሪክ የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኗል። 

ፈረንሳይ እ.አ.አ በ1984 አዘጋጅታ ራሷ በወሰደችው 7ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የቀድሞ የፈረንሳይ ኮከብ አጥቂ በሁለት ጨዋታዎች ሀትሪክ በመሥራት በውድድሩ አዲስ ታሪክ ጽፏል። 

ሚሼል ፕላቲኒ ፈረንሳይ ቤልጂየምን 5 ለ 0 እንዲሁም ዩጎዝላቪያን 3 ለ 2 ስትረታ በተመሳሳይ ሶስት ግቦችን አስቆጥሯል።

ፕላቲኒ በውድድሩ 5 ጨዋታዎችን አድርጎ 9 ግቦችን በማስቆጠር የኮከብ አግቢነት ሽልማቱን ወስዷል።

የቀድሞው አጥቂ ከፓርቹጋላዊ ክርስቲያኖ ሮናልዶ በመቀጠል የአውሮፓ ዋንጫ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ዝርዝር ላይ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ምዕራብ ጀርመን እ.አ.አ በ1988 ባዘጋጀችው 8ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ኔዘርላንዳዊው ኮከብ ማርኮ ቫን ባስተን አገሩ እንግሊዝን ስታሸንፍ 3 ግቦችን በማስቆጠር ሀትሪክ ሰርቷል።

ቫንባስተን ኔዘርላንድ ብቸኛውን የአውሮፓ ዋንጫን እንድታነሳ ቁልፍ አስተዋጽኦ ያበረከተ ተጫዋች ሲሆን በውድድሩ ሶቪየት ኅብረት ላይ በፍጻሜው ጨዋታ ላይ ያስቆጠረውን ግብ ጨምሮ በአጠቃላይ 5 ግቦችን ከመረብ ጋር በማዋሃድ የኮከብ አግቢነት ሽልማቱን አግኝቷል።

በአውሮፓ ዋንጫ ቀጣዮቹን ሀትሪክ ሰሪዎች ለማግኘት 12 ዓመት መጠበቅ ግድ ብሏል። 

እ.አ.አ በ2000 ቤልጂየምና ኔዘርላንድ በጣምራ ባዘጋጁት 11ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ሁለት ተጫዋቾችን በተመሳሳይ በአንድ ጨዋታ ሦስት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።

የክንፍ መስመር ተጫዋቹ ሰርጂዮ ኮንሴሳዎ ፖርቹጋል ጀርመንን 3 ለ 0 ባሸነፈችበት ጨዋታ ሀትሪክ ሰርቷል። 

ሌላኛው በውድድሩ ላይ ሀትሪክ የሰራው ተጫዋች ኔዘርላንዳዊው ኮከብ ፓትሪክ ክላይቨርት ነው። 

በጥሎ ማለፍ ጨዋታ ኔዘርላንድ ዮጎዝላቪያን 6 ለ 1 ስትረመርም ክላይቨርት ሶስት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።

ክላይቨርት በውድድሩ ላይ ከሰርቢያዊው ሳቮ ሚሎሶቪች ጋር በተመሳሳይ አምስት ግቦችን በማስቆጠር በጋራ የኮከብ ግብ አግቢነት ሽልማቱን ወስዷል።

ለመጨረሻ ጊዜ በአውሮፓ ዋንጫው ሀትሪክ የሰራው የቀድሞው የስፔን ኮከብ ዴቪድ ቪያ ነው።  

ቪያ እ.አ.አ በ2008 ኦስትሪያና ስዊዘርላንድ በጣምራ ባዘጋጁት 13ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ስፔን ሩሲያን 4 ለ 1 ስታሸንፍ ሶስት ግቦችን ከመረብ ጋር አገናኝቷል።

ስፔናዊው ኮከብ በአጠቃላይ በውድድሩ 4 ግቦችን በማስቆጠር የኮከብ አግቢ ሽልማቱን ወስዷል።

ዴቪድ ቪያ ለስፔን ባደረጋቸው 98 ጨዋታዎች 59 ግቦችን በማስቆጠር የአገሩ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው።

የአውሮፓ ዋንጫ ከዴቪድ ቪያ በኋላ ሀትሪክ የሰራ ተጫዋች ማግኘት የናፈቀው ሲሆን በውድድሩ በአንድ ጨዋታ ሶስት ግብ ያገባ ተጫዋች ከታየ 16 ዓመታት አልፈዋል።

በጀርመን እየተካሄደ ባለው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ እስከ አሁን በተደረጉ 18 ጨዋታዎች  47 ግቦች ተቆጥረዋል። 

በውድድሩ ላይ እስከ አሁን ሀትሪክ የሰራ ተጫዋች የለም። 

በአውሮፓ ዋንጫ በሚደረጉ ቀጣይ 33 ጨዋታዎች ሀትሪክ የሚሰራ ተጫዋች ይገኝ ይሆን? መልሱን ከጨዋታዎቹ። 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም