በአውሮፓ ዋንጫ አገራቸውን ውክለው የተጫወቱ አባትና ልጆች

በይስሐቅ ቀለመወርቅ

ለመነሻ

በእግር ኳሱ ዓለም የጣልያናውያኑ የማልዲኒ ቤተሰቦች የእግር ኳስ ተጨዋችነት ታሪክ ለሦስት ትውልድ የዘለቀ መሆኑ ይነገርለታል።

የሴዛር ማልዲኒ ልጅ የሆነው ፓውሎ ማልዲኒ እንዲሁም የፓውሎ ማልዲኒ ልጆች ክርስቲያን ማልዲኒ እና ታናሽ ወንድሙ ዳንኤል ማልዲኒ ከአባት እስከ ልጅ፣ ከልጅ እስከ የልጅ ልጅ ለደረሰው የእግር ኳስ ተጨዋችነት ውርርስ ማሳያ ናቸው።

ለዛሬም በአውሮፓ ዋንጫ ታሪክ ሀገራቸውን ወክለው የተጫወቱ አባትና ልጅ ተጨዋቾችን በወፍ በረር  እንቃኛለን። ለዚህ ጽሁፍ ሁሉም የተጠቀምነት የአውሮፓዊያን ዘመን አቆጣጠር ነው።

ዳኒ ብሊንድ እና ልጁ ዴሊ ብሊንድ (ኔዘርላንድ) ፡- እነዚህ ኔዘርላንዳውያን አባትና ልጅ በተለያየ ጊዜ አገራቸውን ወክለው እግርኳስ ተጫውተዋል። 


 

በ62 ዓመቱ ላይ የሚገኘው ዳኒ ብሊንድ፤ በተጨዋችነት ዘመኑ በተከላካይ ሥፍራ የሚጫወት ሲሆን ለአገሩ ክለቦች ስፓርታሮተርዳም እና አያክስ ተጫውቷል። በአሰልጣኝነት ሕይወቱም የአያክስ እና የኔዘርላንድ ብሔራዊ ብድንን በረዳትና በዋና አሰልጣኝነት አሰልጥኗል። 

በ1992 በስዊድን፣ በ1996 ደግሞ በእንግሊዝ አስተናጋጅነት በተከናወነው የአውሮፓ ዋንጫ አገሩን ወክሎ ተጫውቷል።

በ34 ዓመት ዕድሜው ላይ የሚገኘው ልጁ ዴሊ ብሊንድ ደግሞ በተከለካይና በአማካይ ተከላካይ ቦታ የሚጫወት ሲሆን ለአገሩ ክለቦች ለሆኑት ግሮኒገን እና አያክስ ተጫውቷል። በተጨማሪም ለእንግሊዙ ማንችስተር ዩናይትድ እና ለጀርመኑ ባየርሙኒክ ከተጫወተ በኋላ አሁን ለስፔን ክለብ ጂሮና እየተጫወተ ይገኛል።

በ2020 በአስራ አንድ ሀገራት በተከናወነው የአውሮፓ ዋንጫ ለሀገሩ ኔዘርላንድ በመሰለፍ ተጫውቷል።  

ኢንሪኮ ቼሳ እና ልጁ ፌድሪኮ ቼሳ (ጣሊያን)፡- እነዚህ ሁለት ጣልያናውያን አባትና ልጅ ሲሆኑ ሀገራቸውን ጣልያንን በተለያዩ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች ወክለው ተጫውተዋል። 


 

በ53 ዓመቱ ላይ የሚገኘው ኢንሪኮ ቼሳ፤ በተጨዋችነት ዘመኑ ከጣሊያኖቹ ክለቦች ሳምፕዶሪያ፣ ፓርማና ፊዮረንቲና ጋር ዋንጫዎችን አሸንፏል።  

በ1996 ደግሞ በእንግሊዝ አስተናጋጅነት በተከናወነው የአውሮፓ ዋንጫ ሀገሩን በመወከል ለጣልያን ብሔራዊ ቡድን ተሰልፏል።

የ26 ዓመት ልጁ ፍድሪኮ ቼሳ በበኩሉ አሁን ላይ ለጁቬንትስ በክንፍ ተጨዋችነትና በአጥቂነት እየተጫወተ ሲሆን፤ በጣልያን ብሔራዊ ቡድን ከ19 ዓመት በታች፣ ከ20 ዓመት በታችና ከ21 ዓመት በታች ተጫውቷል።

ከ2018 ጀምሮ ለጣልያን ዋናው ብሔራዊ ቡድን መሰለፍ የጀመረ ሲሆን፤ በ2020 የተደረገውን የአውሮፓ ዋንጫ ከጣልያን ጋር አሸንፏል።

በጀርመን አስተናጋጅነት እየተከናወነ በሚገኘው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ደግሞ፤ በሉቺያኖ ስፓሌቲ የቡድን ስብስብ ውስጥ በመካተት ለጣልያን ብሔራዊ ቡድን እየተጫወተ ይገኛል።

ሰርጂዮ ኮንሲሳኦ እና ልጁ ፍራንሲስኮ ኮንሲሳኦ(ፖርቹጋል)፡- እነዚህ ሁለት ፖርቹጋላውያን አባትና ልጅ ሲሆኑ በተለያየ ጊዜ ሀገራቸውን በእግር ኳስ ወክለው ተጫውተዋል።


 

የ49 ዓመቱ ሰርጂዮ ኮንሲሳኦ በተጨዋችነት ዘመኑ የክንፍ ተጨዋች የነበረ ሲሆን በአምስት ከተሞች ለ10 ክለቦች ተጫውቶ አሳልፏል።

በተለይ የሀገሩ ክለብ  ከሆነው ፖርቶና ከጣልያኑ ላዚዮ ጋር የተለያዩ የዋንጫ ክብሮችን አግኝቷል።

በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ለፖርቹጋል የተጫወተ ሲሆን በ2000 በኔዘርላንድና በቤልጂየም አስተናጋጅነት በተከናወነው የአውሮፓ ዋንጫ ለሀገሩ ተሰልፎ ተጫውቷል።

የ21 ዓመቱ ልጁ ፍራንሲስኮ ኮንሲሳኦ ደግሞ አሁን ላይ ለፖርቶ በክንፍ ተጨዋችነት እየተጫወተ ይገኛል።

በብሔራዊ ቡድን ደረጃም ለፖርቹጋል ከ16 ዓመት በታች፣ ከ17 ዓመት በታች፣ ከ18 ዓመት በታችና ከ21 ዓመት በታች የተጫወተ ሲሆን፤ ከ2024 ጀምሮ ለፖርቹጋል ዋናው ብሔራዊ ቡድን እየተጫወተ ነው።

በጀርመን አስተናጋጅነት እየተከናወነ በሚገኘው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ፤ በሮቤርቶ ማርቲኔዝ በሚሰለጥነው የፖርቹጋል የቡድን ስብስብ ውስጥ በመካተት እየተጫወተ ይገኛል።

ጆርጅ ሀጂ እና ልጁ ኢያኒስ ሃጂ (ሮማንያ)፡- እነዚህ የሮማንያ የእግር ኳስ ተጨዋቾች አባትና ልጅ ሲሆኑ ሀገራቸው ሮማንያን በተለያዩ ዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ውድድሮች ወክለው ተጫውተዋል። 


 

የ59 ዓመቱ ጆርጅ ሀጂ በአጥቂ አማካይ ሥፍራ የተጫወተ ሲሆን በ1980ዎቹና፣ በ1990ዎቹ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ኮከብ ተጨዋቾች መካከል ስሙ ይነሳል።  

በተጨዋችነት ዘመኑም ለሪያልማድሪድና ለባርሴሎና ለሁለት ተቀናቃኝ ክለቦች ከተጫወቱ  ተጨዋቾችም አንዱ ነው።

ለሀገሩ ክለቦች ኮንስታንታ፣ ስፖርቱል ስቱዴንቴስ እና ስቲዋ ቡካሬስት የተጫወተ ሲሆን የጣልያኑ ክለብ  ብሬስካ ካልሲዮ እና የቱርኩ ክለብ ጋላታስራይ ሌሎች የተጫወቱባቸው ክለቦች ናቸው። 

ከ1983 እሰከ 2000 ለሀገሩ ሮማንያ ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን፤ በ1984 በፈረንሳይ፤ በ1996 በእንግሊዝና በ2000 በኔዘርላንድና በቤልጂየም አስተናጋጅነት በተከናወነው የአውሮፓ ዋንጫ ለሀገሩ ተሰልፎ ተጫውቷል።

የ25 ዓመት ልጁ ኢያኒስ ሀጂ የእሱን ፈለግ በመከተል ኳስ ተጨዋች የሆነ ሲሆን፤ እንደ አባቱ በአጥቂ አማካይ ሥፍራና በተጨማሪም በክንፍ ተጨዋችነት ይጫወታል ። 

በ16 ዓመቱ ለሮማንያው ክለብ ቪያትሮል ኮንስታንታ በመጫወት የጀመረ ሲሆን ለጣልያኑ ፌዮረንቲና፣ ለቤልጂየሙ ጌንክ እና ለስኮትላንዱ ሬንጀርስም ተጫውቷል።  

አሁን ላይ ለስፔኑ ክለብ አላቪስ በውሰት እየተጫወተ ሲሆን ለሮማንያ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ከ2018 ጀምሮ እየተጫወተ ይገኛል።

በጀርመን አስተናጋጅነት እየተከናወነ በሚገኘው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ደግሞ በሮማንያ ብሔራዊ ቡድን በመካተት እየተጫወተ ነው።

ፒተር ሹማይክልና ካስፐር ሹማይክል (ዴንማርክ )፡- እነዚህ ሁለት ዴንማርካውያን አባትና ልጅ በተለያየ ጊዜ ሀገራቸውን በእግር ኳስ ወክለው ተጫውተዋል።


 

የ60 ዓመቱ ፒትር ሹማይክል በግብ ጠባቂነት ለስምንት ዓመታት በማንችስተር ዩናይትድ የተጫወተበት ስኬታማ የክለብ ቆይታው ነበር።

በተለይም በ1999 ከማንችስተር ጋር የፕሪሚየርሊግ፣ የኤፌካፕና የአውሮፓ ሻምፒዎንስ ሊግ ዋንጫ ያነሳበት በክለብ ተጨዋችነት ጊዜው የጎላ ስኬቱ ነው፤ ከ1987 እስከ 2001 ለዴንማርክ ብሔራዊ ቡድን ተጫውቷል።

በ1988 በያኔዋ ምዕራብ ጀርመን አስተናጋጅነት በተከናወነው የአውሮፓ ዋንጫ እና በ2000 በኔዘርላንድና በቤልጂየም አስተናጋጅነት በተደረገው የአውሮፓ ዋንጫ ለሀገሩ ዴንማርክ ተሰልፎ ተጫውቷል።

የ37 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኘው ልጁ ካስፐር ሹማይክል ልክ እንደ አባቱ በግብ  ጠባቂነት የሚጫወት ሲሆን ከተጫወተባቸው ክለቦች መካከል ከሌስተር ሲቲ ጋር ያሳለፈው ጊዜ የሚረሳ አይደለም።

በ2015 ከሌስተር ጋር የእንግሊዝ ፕሪሚየርሊግ ዋንጫን ያነሳበት ተጨዋቹ በክለብ እግር ኳስ ተጨዋችነቱ ካሳለፋቸው ጊዜያት ቀዳሚው እንደሆነ ይናገራል።

ከ2013 ጀምሮ ለዴንማርክ ዋናው ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ እየተጫወተ ሲሆን በ2020 በአስራአንድ ሀገራት በተከናወነው የአውሮፓ ዋንጫ፤ ለሀገሩ ዴንማርክ በመሰለፍ ተጫውቷል።  

ሊሊያን ቱራምና ልጁ ማርኮስ ቱራም( ፈረንሳይ)፡- እነዚህ ፈረንሳውያን አባትና ልጅ የእግር ኳስ ተጨዋቾች ሀገራቸው ፈርንሳይን በተለያዩ  ዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ወክለው ተጫውተዋል።


 

የ52 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኘው ሊሊያን ቱራም፤ እግር ኳስ መጫወት የጀመረው ለፈርንሳዩ ክለብ ሞናኮ በመጫወት ነበር ።  

የጣልያኖቹ ክለቦች ፓርማና ጁቬንትስ እንዲሁም የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ቀሪ የተጫወተባቸው ክለቦች ናቸው ።

በ1998 ሀገሩ ፈረንሳይ አዘጋጅታ በነበረው 16ኛው የዓለም ዋንጫ በግማሽ ፍፃሜ ከክሮሽያ ጋር ስትገናኝ ሁለት ጎሎችን በማስቆጠር ሀገሩ ወደ ፍፃሚ ገብታ የዋንጫ ባለቤት እንዲትሆን አድርጎል።

በ2000 ለመጀመሪያ ጊዜ በኔዘርላንድና ቤልጂየም ጣምራ አዘጋጅነት በተከናወነው የአውሮፓ ዋንጫ፤ ለሀገሩ ፈረንሳይ ተሰልፎ በመጫወት ዋንጫ አንስቷል።

በ26 ዓመት ዕድሜ ላይ የሚገኘውና ለጣልያኑ ክለብ ኢንተር ሚላን የሚጫወተው ልጁ ማርኮስ ቱርሃም ደግሞ፤ ለፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን በተለያየ የዕድሜ ደረጃ ተጫውቷል።

ለፈረንሳይ ከ17 ዓመት በታች፣ ከ18 ዓመት በታች፣ ከ19 ዓመት በታችና ከ20 ዓመት በታች ተሰልፎ ተጫውቷል።

ከ2020 ጀምሮ ለፈረንሳይ ዋነው ብሔረዊ ቡድን እየተጨወተ ይገኛል።

በጀርመን አስተናጋጅነት እየተከናወነ በሚገኘው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ደግሞ፤ በፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በመካተት እየተጫወተ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም