ትውልደ አፍሪካውያን ተጨዋቾች የበዙበት የአውሮፓ ዋንጫ

በይስሐቅ ቀለመወርቅ 

በዓለም እግር ኳስ ውስጥ ከሚጠቀሱ ትልቅ አህጉራዊ የእግር ኳስ ውድድሮች አንዱ የአውሮፓ ዋንጫ ነው። በዚህ ውድድር ላይ መሳተፍ የብዙ አውሮፓውያን ተጫዋቾች ምኞት ነው።

በጀርመን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ከ219 ክለቦች የተወጣጡ 622 ተጫዋቾች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

ከተጨዋቾቹ መካከል በዘንድሮው የአውሮፓ ዋንጫ አፍሪካዊ የዘር ግንድ ያላቸው 58 ተጨዋቾች የተለያዩ የአውሮፓ ሀገራትን ወክለው በውድድሩ ተሳትፈዋል።

ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም፣ ስዊዘርላንድ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ፖርቹጋል፣ ጣልያን፣ ስፔን፣ ዴንማርክና ኦስትሪያ ትውልደ አፍሪካውያን ተጨዋቾችን ይዘው በ17ተኛው የጀርመን የአውሮፓ ዋንጫ የተሳተፉ ሀገራት ናቸው ።

ከነዚህም ውስጥ 14 ትውልደ አፍሪካውያን ተጨዋቾችን በመያዝ ቀዳሚ የሆነችው ሀገር ፈረንሳይ ናት።

ፈረንሳይ፡-

በዘንድሮውም የአውሮፓ ዋንጫ ፈረንሳይ ያካተተቻቸውን ትውልደ አፍሪካውያን ተጨዋቾች ምልከታ ከብሔራዊ ቡድኑ ኮከብ ኪሊያን ኢምባፔ እንጀምራለን።

ኢምባፔ የዘር ግንዱ ከአፍሪካ የሚመዘዝ ሲሆን ከካሜሮናዊ አባትና ከአልጄሪያዊት እናት ነው የተወለደው።

ለፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድንና ለሪያል ማድሪድ አብሮት የሚጫወተው ፌርላንድ ሜንዲ ደግሞ የዘር ግንዱ ከሴኔጋልና ጊኒ ቢሳው ይመዘዛል።

ለጀርመኑ ባየርሙኒክ የሚጫወተው ዳዮት ኡፓሜካኖም እንዲሁ ትውልዱ ከጊኒ ቢሳው የዘር ሐረግ የሚመዘዝ ነው ።

ለፈረንሳዩ ሌንስ በግብ ጠባቂነት እየተጫወተ የሚገኘው ብራይስ ሳምባ፤ የሪያል ማድሪዱ ኤድዋርዶ ካማቪንጋና የፒኤስጂው ኮሎ ሙዋኒ ደግሞ ትውልዳቸው ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ይመዘዛል።

የሳውዲ አረብያው አል ኢትሃድ ተጫዋች ኢንጎሎ ኮንቴ፤የሊቨርፑሉ  ኢብራማ ኮናቴና ለሞናኮ በአማካይ ሥፍራ እየተጫወተ የሚገኘው የሱፍ ፎፋና ደግሞ ትውልዳቸው ከማሊ ነው።

የፒኤስጂው ኡስማን ዴምበሌም በአባቱ የማሊ ተወላጅ ሲሆን እናቱ ደግሞ ሞሪታኒያዊት ነች።

ኦሬሊን ቹዌሚኒ ከካሜሮን፣ ጁል ኩንዴ ከቤኒን፣ ዊሊያም ሳሊባ ከካሜሮንና ብራድሌ ባርኮላ ከቶጎ ሌሎቹ ለፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የሚጫወቱ ተጫዋቾች ናቸው።

ቤልጂየም፡-

ከፈረንሳይ በመቀጠል በአውሮፓ ዋንጫው 9 ትውልደ አፍሪካውያን ተጨዋቾችን በመያዝ ቤልጂየም በሁለተኛነት ትከተላለች።

ከቼልሲ በውሰት ለሮማ የሚጫወተው ሮሜሎ ሉካኩ፤የሲቪያው ዶዲ ሉካባኪዮ፤ከኖቲንግሃም ፎረስት በውሰት ለሊዮን የሚጫወተው ኦሬል ማንጋላ፤ ለአስቶንቪላ የሚጫወተው ዩሪ ቲሌማንስና ከዎልፍስበርግ በውሰት ለኤሲ ሚላን የሚጫወተው አስተር ፍራንክስ ትውልዳቸው ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ይመዘዛል።

ለጀርመኑ አርቢ ላይፕዚግ የሚጫወተው ሎይስ ኦፔንዳ እንዲሁ የዲሞክራቲክ ኮንጎና የሞሮኮ የዘር ግንድ አለው።

ለኔዘርላንዱ ክለብ ፒኤስቪ አይንዶቨን የሚጫወተው ዡዋን ባካዮኮ ደግሞ በእናቱ ሩዋንዳዊ በአባቱ ኮትዲቯራዊ ነው።

ለእንግሊዙ ክለብ ኤቨርተን የሚጫወተው አማዱ ኦናና ከካሜሮናዊ አባትና ከሴኔጋላዊ እናት ነው የተወለደው።

የማንችስተር ሲቲው ዠርሚ ዶኩ ደግሞ ትውልደ ጋናዊ ተጨዋች ነው።

ስዊዘርላንድ ፡-

ስምንት ትውልደ አፍሪካውያን ተጨዋቾችን በመያዝ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የምትቀመጠው ስዊዘርላንድ ናት።

የማንችስተር ሲቲው ኢማኑኤል አካንጂና፤ የኤሲ ሚላኑ ኖአ ኦካፎር ትውልደ ናይጄሪያውያን ተጨዋቾች ናቸው።

ለፈረንሳዩ ክለብ ሎሪዮ የሚጫወተው ዩቩን ናኖማና፤ የሞናኮው ብሬል ኢምቦሎ ደግሞ ትውልዳቸው ከካሜሮን ነው።

ከሞኖኮ ለቼልሲ በውሰት እየተጫወተ የሚገኘው ዴኒስ ዛካርያ ደግሞ፤ ከዲሞክራቲክ ኮንጎ አባትና ከደቡብ ሱዳናዊ እናት ነው የተወለደው።

የበርንሌዩ አጥቂ መሐመድ አምዱኒ፤ የዘር ግንድ ስንመለከት ከተርኪዬ አባትና ከቱኒዚያዊ እናት ይመዘዛል።

የቦሎኛው ዳን ንዶዬ ደግሞ  ከስዊዘርላንድ እናትና ከሴኔጋላዊ አባት ነው የተወለደው።

ለቡልጋሪያው ሉዶጎሬትስ ራዝጋርድ የሚጫወተው ኩዋድዎ አንቲ ዱአህ ሲሆን፤ ትውልደ ጋናዊ ተጨዋች ነው።

እንግሊዝ፡-

ከስዊዘርላንድ በመቀጠል 6 ትውልደ አፍሪካውያን ተጨዋቾችን በመያዝ አራተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው እንግሊዝ ናት።

ለአርሰናል የሚጫወተው የቀኝ ክንፍ ተጨዋች ቡካዮ ሳካና፤ የክርስቲያል ፓላሱ ኢቤርቺ ኢዜ፤ ትውልደ ናይጀሪያውያን ተጨዋቾች ናቸው። 

የሊቨርፑል ተጫዋች  ጆ ጎሜዝ ደግሞ ከጋምቢያዊ አባትና ከእንግሊዛዊ እናት ነው የተወለደው። 

ቀሪዎቹን ተጨዋቾች ስንመለከት የማንችስተር ዩናይትዱ ኮቢ ሜይኑ ከጋና ፣ የክርስቲያል ፓላሱ የመሀል ማርክ ጌይ ከኮትዲቯር፣ የአስቶንቪላው ኢዝሪ ኮንሳ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ትውልዳቸው ይመዘዛል።

ጀርመን፡-

ከእንግሊዝ በመቀጠል 5 ትውልደ አፍሪካውያን ተጨዋቾችን በመያዝ በአምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ደግሞ ጀርመን ናት።

ለሪያልማድሪድ  የሚጫወተውና በ17ተኛው የአውሮፓ ዋንጫ የራሳቸው ቡድን ላይ ጎል ካስቆጠሩ ተጨዋቾች ቀዳሚ የሆነው አንቶኒዮ ሩዲገር አባቱ የዘር ሐረጉ ከአፍሪካ የሚመዘዝ ጀርመናዊ (Afro German) ሲሆን እናቱ የሴራሊዮን ተወላጅ ነች።

ቀሪዎቹን ተጨዋቾች ስንመለከት የባየር ሙኒኩ ወጣት ኮከብ ጀማል ሙሲያላ ከናይጄሪያ፤የባየር ሌቨርኩዘኑ  ጆናታን ታህ ከኮትዲቯር፤ ለአርቢ ላይፕዚግ የሚጫወተው ቤንጃሚን ሄንሪክስ ከጋና፣ እንዲሁም የባየር ሙኒኩ ሊሮይ ሳኔ ደግሞ ከሴኔጋል የዘር ግንዱ ይመዘዛል።

ኔዘርላንድና ፖርቹጋል ፡-

ከጀርመን በመቀጠል በተመሳሳይ 4 ትውልደ አፍሪካውያን ተጨዋቾችን በመያዝ በስድስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ደግሞ ኔዘርላንድና ፖርቹጋል ናቸው።

የአትሌቲኮ ማድሪዱ ሜምፊስ ዲፓይ፣ የባየር ሌቨርኩዘኑ ጀርሚ ፍሪምፖንግና ለአያክስ በአጥቂ ሥፍራ የሚጫወተው ብሪያን ብሮቤይ ትውልደ ጋናውያን ተጨዋቾች ናቸው።

ለሊቨርፑል የሚጫወተው ኮዲ ጋክፖ ደግሞ በአባቱ ቶጎዋዊ በእናቱ ጋናዊ ነው።

ለፖርቹጋል የሚጫወቱ ትውልደ አፍሪካውያን ተጨዋቾችን ስንመለከት ደግሞ ለፈረንሳዩ የፒኤስጂው ኑኖ ሜንዴዝ በትውልዱ አንጎላዊ ነው።

በተመሳሳይ ለፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን አብሮት የሚጫወተው ራፋኤል ሊያው ከአንጎላዊ አባትና የሳኦቶሜ ፕሪንሲፔ ተወላጅ ከሆነችው እናቱ ነው የተወለደው።

ቀሪዎቹን ለፖርቹጋል እየተጫወቱ የሚገኙ ተጨዋቾችን ስንመለከት ለዎልቭስ በቀኝ ተመላላሽና በቀኝ ክንፍ መስመር ላይ የሚጫወተው ኔልሰን ሴሜዶ ከኬፕ ቬርዴ፤ እንዲሁም ዳንኤሎ ፔሬራ ከኢኳቶሪያል ጊኒ  የዘር ግንዳቸው ይመዘዛል። 

ጣልያን፣ ስፔን፣ ዴንማርክና ኦስትሪያ፡- 

ከኔዘርላንድ በመቀጠል በተመሳሳይ ሁለት ትውልደ አፍሪካውያን ተጨዋቾችን በየቡድናቸው በማካተት ደግሞ ጣሊያን፣ ስፔን፣ ዴንማርክና ኦስትሪያ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ጣልያን ለሄላስ ቬሮና የሚጫወተው ትውልደ ናይጄሪያዊ ማይክል ፎሎራንሾና ትውልደ ግብፃዊውን የሮማ ተጫዋች ስቴፋን አል ሻራዊ በአውሮፓ ዋንጫው በቡድኗ ውስጥ አካታለች። 

ስፔን ደግሞ ከሞሮኳዊ አባትና ከኢኳቶሪያል ጊኒ እናት የተወለደውን የባርሴሎና የክንፍ መስመር ተጨዋች ላሚን ያማልንና ትውልደ ጋናዊውን የአትሌቲኮ ቢልባኦ ተጨዋች ኒኮ ዊሊያምስን በአውሮፓ ዋንጫ ቡድኗ ውስጥ በማካተት እየተወዳደረች ትገኛለች። 

ዴንማርክ በበኩሏ ከታንዛኒያዊ አባትና ከዴንማርካዊ እናት የተወለደውን የአርቢ ላይፕዚግ ተጨዋች የሱፍ ፖልሰንና ትውልደ ጋምቢያዊውን የቤኔፊካ የቀኝ ተመላላሽ አሌክሳንደር ባህን በቡድኗ አካታለች።

የመጨረሻዋ ትውልደ አፍሪካዊ ተጨዋቾችን በቡድኗ ያካተተችው ሀገር ኦስትሪያ ስትሆን፤ ትውልደ ጋናዊውን የሌንስ ተጫዋች ኬቨን ዳንሶ፤ ከኬንያዊ አባትና ከኦስትሪያዊ እናት የተወለደውን የሜንዝ ተከላካይ ፍሊፕ ሙዌኔን በቡድኗ ይዛለች። 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም