ዕድሜ ጠገቡ አህጉራዊ የእግር ኳስ ውድድር

በይስሐቅ ቀለመወርቅ

እንደ መነሻ

ጊዜው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር 1859 ነው። ይህ ዓመት የመጀመሪያው የደቡብ አሜሪካ የክሪኬትና የእግር ኳስ ቡድን የሆነው "ሊማ" የተባለው ክለብ ፔሩ ውስጥ የተመሰረተበት ነው። 

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1893 ደግሞ፤ የአርጀንቲና የእግር ኳስ ማኅበር ተመሰረተ። እነዚህ ሁለት ሁነቶች ከኮፓ አሜሪካ ውድድር ጅማሮ መጠንሰስ ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አላቸው። 

ማኅበሩ ከተመሰረተ ከ17 ዓመት በኋላ አርጀንቲና፣ ቺሊና ኡራጋይን በማካተት አህጉራዊ ውድድር ለማዘጋጀት ጥረት አደረገች።

ሆኖም ይህ ወድድር የማዘጋጀት ሀሳብ የደቡብ አሜሪካን እግር ኳስ በሚመራው ኮንሜቦል ዕውቅና ተሰጥቶት አልተመዘገበም።

ነገር ግን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1916 ከአርጀንቲና የነፃነት በዓል ጋር ተያይዞ አርጀንቲና፣ ቺሊ፣ ኡራጋይና ብራዚል የተካተቱበት የእግር ኳስ ውድድር አርጀንቲና አዘጋጀች።

ይህ ውድድርም "ካምፒዎናቶ ሱዳሜሪካኖ ዴ ፉትቦል ( Campeonato Sudamericano de Football )" በሚል፤ አሁን ላይ "ኮፓ አሜሪካ" በሚል መጠሪያ የሚደረገው የመጀመሪያ ውድድር ተካሄደ።

በአርጀንቲና አዘጋጅነት የተጀመረው ይኼ ውድድር፤ 108 ዓመታትን በማስቆጠር፤ ዘንድሮም ለ48ተኛ ጊዜ በሰሜን አሜሪካዋ ሀገር አሜሪካ እየተከናወነ ይገኛል። 

አሜሪካ ዘንድሮ  ውድድሩን እንዴት አዘጋጀች?

የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ውድድር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር እስከ 1975 ድረስ "የደቡብ አሜሪካ የእግር ኳስ ሻምፒዎና" እየተባለ ይጠራ ነበረ ሲሆን፤ ከ1975 በኋላ ደግሞ "ኮፓ አሜሪካ" እየተባለ መጠራት ጀመረ።  

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1993 ደግሞ የደቡብ አሜሪካን ውድድር የሚመራው "ኮንሜቦልና"፤ የሰሜን፣ መከካለኛውና ካሪቢያን ሀገሮች ውድድርን የሚመራው "ኮንካካፍ"  በጋራ ለመሥራት ስምምነት በማድረጋቸው፤ በደቡብ አሜሪካ ካሉ 10 ሀገሮች በተጨማሪ ከኮንካካፍ ሁለት ቡድን በማካተት ውድድሩ መደረግ ጀመረ።

በዚህም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2016 የኮፓ አሜሪካ 100ኛ ዓመት ሲከበር አሜሪካ ውድድሩን የማዘጋጀት ዕድል ያገኘች ሲሆን፤ ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ ውድድሩን በማዘጋጀት ላይ ናት።

ሜክሲኮ ደግሞ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1999 በፓራጓይ ከተደረገው የኮፓ አሜሪካ ውድድር በስተቀር፤ ከ1993 እስከ 2016 ድረስ በተደረጉት የኮፓ አሜሪካ ውድድሮች በተደጋጋሚ ተሳትፋለች። 

የኮፓ አሜሪካ ውድድር በዚህ ብቻ ባለመወሰን ከኮንካካፍ ሀገራት በተጨማሪ፤ ከእስያ የእግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ሀገራትም ቡድኖችን በማካተት ተሳታፊ አድርጓል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1999 በሜክሲኮ አለመሳተፍ ምክንያት ጃፓን በውድድሩ የተሳተፈች የመጀመሪያዋ የእስያ ሀገር ስትሆን፤ በ2019 ኳታርና ጃፓን እንዲሁ በኮፓ አሜሪካ ተሳትፈዋል።

የኮፓ አሜሪካን ውድድርን    በማዘጋጀትና፤ ዋንጫ በማንሳት እነማን የበላይ ናቸው?

የኮፓ አሜሪካ ውድድር ከተጀመረ 11 ሀገራት ውድድሩን ያዘጋጁ ሲሆን፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1975፣ በ1979 እና በ1983 ደግሞ በአንድ አገር ውድድሩ ሳይዘጋጅ አገራት በሜዳቸውና ከሜዳቸው ውጪ የደርሶ መልስ ጨዋታ በማድረግ ውድድሩን አከናውናዋል።

የኮፓ አሜሪካን ውድድርን 9 ጊዜ በማዘጋጀት አርጀንቲና ቀዳሚ ስትሆን፤ ኡራጋይና ቺሊ 7 ጊዜ፤ ብራዚልና ፔሩ ደግሞ 6 ጊዜ በማዘጋጀት ይከተላሉ።

የኮፓ አሜሪካን ዋንጫ በማንሳት ደግሞ አርጀንቲናና ኡራጓይ እኩል 15 ጊዜ ሲያነሱ፤ ብራዚል 9 ጊዜ ዋንጫ አንስታለች።

የ2024 ኮፓ አሜሪካ ውድድር ምን ይመስላል?

የዘንድሮው የኮፓ አሜሪካ ውድድር ባሳለፍነው ሰኔ 14/ 2016 ዓ.ም አርጀንቲናና ካናዳ ባደረጉት የምድብ አንድ ጨዋታ የተጀመረ ሲሆን፤ አርጀንቲና በጁሊያን አልቫሬዝና በላውታሮ ማርቲኔዝ ሁለት ጎሎች ካናዳን 2 ለ 0 አሸንፋለች።

16 ሀገራት በአራት ምድብ ተከፍለው እየተወዳደሩበት በሚገኘው የዘንድሮ ኮፓ አሜሪካ ውድድር፤ ከምድብ አንድ እስከ አራት ያሉት ሀገራት የመጀመሪያ ምድብ ጨዋታዎቻቸውን አድርገዋል።

በዚህም ከምድብ አንድ ፔሩ እና ቺሊ 0 ለ 0 በሆነ ውጤት ጨዋታቸውን የፈፀሙ ሲሆን፤ በምድብ ሁለት ቬንዙዌላ ኢኳዶርን 2 ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፋለች። በዚሁ ምድብ ሜክሲኮ የካሪቢያዋን ሀገር ጃማይካን 1 ለ0 በሆነ ውጤት ረታለች።

አዘጋጇ ሀገር አሜሪካንና ኡራጋይን ባፋጠጠው ምድብ 3 ደግሞ፤አሜሪካ ቦሊቪያን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ስትረታ፤ ኡራጋይ ፓናማን በማክሲሚሊያኖ አራጆ፣ በዳርዊን ኑኔዝና፣ በማትያስ ቪና ጎሎች 3 ለ 1 አሸንፋለች።

በመጨረሻው ምድብ አራት ደግሞ ኮሎምቢያ ፓራጓይን 2 ለ1 ስታሸንፍ፤ ብራዚል ከኮስታሪካ ጋር 0 ለ 0 የአቻ ውጤት በሆነ ውጤት የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋን ፈፅማለች።

የኮፓ አሜሪካ የምድብ ሁለተኛ ጨዋታ ዛሬ ሌሊት ይካሄዳል። በምድብ አንድ ፔሩና ካናዳ ከምሽቱ 7 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ፣ ቺሊና አርጀንቲና ደግሞ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ይጫወታሉ።

የወቅቱ የኮፓ አሜሪካ አሸናፊ አርጀንቲና በዛሬው ጨዋታ ድል ከቀናት በውድድሩ ሩብ ፍጻሜውን የምትቀላቀል የመጀመሪያ አገር ትሆናለች። 

ውድድሩ ነገም ቀጥሎ ሲውል በምድብ ሁለት፤ ኢኳዶር ከጃማይካ ቬንዙዌላ ከሜክሲኮ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የኮፓ አሜሪካ ውድድር በ14 የአሜሪካ ከተሞች በሚገኙ 14 ስታዲየሞች እየተከናወነ ሲሆን፤ ውድድሩ አስከ ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ይቆያል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም