በአውሮፓ ዋንጫ ለበርካታ ጊዜ የተሰለፉ ተጫዋቾች

                                     (በሙሴ መለሰ) 

ከተጀመረ 64 ዓመት ያስቆጠረው የአውሮፓ ዋንጫ በርካታ ኮከብ ተጨዋቾችን አስመልክቶናል እያስመለከተንም ይገኛል። 

ፈረንሳይ እ.አ.አ በ1960 ባዘጋጀችው የመጀመሪያ የአውሮፓ ዋንጫ ታሪካዊዋንና የውድድሩን ቀዳሚ ግብ ያስቆጠረው የያኔዋ ዩጎዝላቪያ አጥቂ ሚላን ጋሊች፣ በውድደሩ ታሪክ የመጀመሪያውን ሀትሪክ የሰራው የምዕራብ ጀርመኑ አጥቂ ዲተር ሙለርና በአንድ ውድድር ላይ ሁለት ሀትሪክ የሰራው ፈረንሳዊው ኮከብ ሚሼል ፕላቲኒ ከቀደምት የውድድሩ ድምቀቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

በአውሮፓ ዋንጫ 14 ግቦች በማስቆጠር የውድድሩ የምንጊዜውም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ 16 ዓመት ከ338 ቀናት በመሰለፍ አዲስ ክብረ ወሰን የጨበጠው ስፔናዊ ታዳጊ ላሚን ያማልና በዘንድሮው አህጉራዊ መድረክ በ38 ዓመት ከ289 ቀናት እድሜው ጣልያን ላይ ግብ በማስቆጠር በውድድሩ ታሪክ ኳስን ከመረብ ጋር ያገናኘው በእድሜ ትልቁ ተጫዋች የክሮሺያ ኮከብ ሉካ ሞድሪች ደግሞ ከቅርቦቹ ከዋክብት መካከል ይገኙበታል።

በ23 ሴኮንድ ጣልያን ላይ ግብ በማስቆጠር በውድድሩ ታሪክ ፈጣኗን ግብ ከመረብ ጋር ያገናኘው አልባኒያዊው ኔዲም ባጅራሚ ሌላው አይረሴ ተጫዋች ነው።

በዚህ ጽሁፍ የዘንድሮውን ጨምሮ በአውሮፓ ዋንጫ ለበርካታ ጊዜ የተሰለፉ ተጨዋቾች መረጃን ይዘን ቀርበናል። 

እስከ አሁን በተደረጉት የአውሮፓ ዋንጫ ውድድሮች ለበርካታ ጊዜ የተሰለፈው ፖርቹጋላዊ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ነው። ሮናልዶ የተሰለፈበት ጨዋታ ብዛት 27 ነው።

የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን አምበል ሮናልዶ ፖርቹጋል በቀጣይ በሚኖራት የጥሎ ማለፍ ጨዋታ የያዘውን ክብረ ወሰን ያሻሽላል ተብሎ ይጠበቃል።

የ39 ዓመቱ ተጨዋች በአህጉራዊው መድረክ የተጫወተበት ለአውሮፓ ዋንጫ ለማለፍ የተደረጉ የማጣሪያ ጨዋታዎች ጋር ተደምሮ በ71 ጨዋታዎች ላይ በመሰለፍ የቀዳሚነቱን ስፍራ ይዟል።

የአውሮፓ ዋንጫ የማጣሪያ ውድድሮችን ጨምሮ በአህጉራዊው መድረክ 55 ጎሎችን ከመረብ ላይ ያሳረፈ ብቸኛ ተጫዋችም ነው።

ሮናልዶ የዘንድሮውን ጨምሮ በስድስት የአውሮፓ ዋንጫዎች ላይ በመሳተፍ የመጀመሪያ ተጫዋች ሆኗል።

በተጨማሪም ፖርቹጋል ተርኪዬን 3 ለ 0 ባሸነፈችበት የምድብ 6 ጨዋታ በ39 ዓመት ከ138 ቀናት እድሜው ኳስ በማቀበል በውድድሩ ታሪክ ለጎል የሚሆን ኳስን ያቀበለ በእድሜው ትልቁ ተጫዋች ክብረ ወሰን ባለቤት ሆኗል።

በተጨማሪም በአውሮፓ ዋንጫ ሰባት ግቦችን አመቻችቶ ያቀበለ የመጀመሪያው ተጫዋች መሆንም ችሏል።

ከክርስቲያኖ ሮናልዶ በመቀጠል በአውሮፓ ዋንጫ ብዙ ጊዜ የተሰለፈው ተጫዋች የቡድን አጋሩ ኬፕለር ላቬራን ደ ሊማ ፌሬራ (ፔፔ) ነው።

ፔፔ ፖርቹጋል ከተርኪዬ ባደረገችው የምድብ ጨዋታ ላይ በውድድሩ ላይ ያደረገውን የጨዋታ ብዛት ወደ 21 ከፍ አድርጓል።

ፖርቹጋላዊው የተከላካይ መስመር ተጫዋች ፔፔ አገሩ ከቼክ ሪፐብሊክ ጋር ባደረገችው የምድብ መክፈቻ ጨዋታ በ41 ዓመት ከ113 ቀናት እድሜው በጨዋታው ላይ በመሰለፍ በውድድሩ ላይ የተሳተፈ በእድሜው አንጋፋ ተጫዋች ክብረ ወሰንን ይዟል።

የሀንጋሪ የቀድሞ ግብ ጠባቂ ጋቦር ኪራሊ እ.አ.አ በ2016 ፈረንሳይ ባስተናገደችው 15ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ሀንጋሪ ከቤልጂየም በጥሎ ማለፉ ስትጫወት በ40 ዓመት ከ86 ቀናት እድሜ በመሰለፍ ክብረ ወሰኑን ለስምንት ዓመታት ይዞ ነበር።

በበርካታ ጨዋታዎች የተሰላፊነት ዝርዝር ውስጥ ሶስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አሁንም ፖርቹጋላዊው የ37 ዓመት አንጋፋ ተጫዋች ጆአ ሞቲኒሆ ነው።

ሞቲኒሆ በዘንድሮው የፖርቹጋል የአውሮፓ ዋንጫ ስብስብ ውስጥ ባይካተትም ከዚህ ቀደም በነበረው የውድድሩ ተሳትፎ 19 ጊዜ ተጫውቷል።

የጣልያን የቀድሞ የተከላካይ ክፍል መስመር ተጫዋችና ኮከብ ሊኦናርዶ ቦኑቺ፣ ጀርመናዊው የቀድሞ የአማካይ ተጫዋች ባስቲያን ሽዋይንስታይገርና ጀርመናዊው ማኑኤል ኖየር በተመሳሳይ 18 ጊዜ በመሰለፍ ቀጣዩን ደረጃ ይዘዋል።

ማኑኤል ኖየር በጀርመን አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው 17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የአገሩ የግብ ጠባቂ ዘብ ነው።

ጣልያናዊው ኮከብ ጆርጂዮ ኪዬሌኒ፣ የጣልያን የቀድሞ አንጋፋ ግብ ጠባቂ ጂያንሉዊጂ ቡፎንና ጀርመናዊው የአማካይ ተጫዋች ቶኒ ክሮስ በተመሳሳይ 17 ጊዜ በአውሮፓ ዋንጫው አገራቸውን ወክለው ተሰልፈዋል።

በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ወደ ጥሎ ማለፉ የገባችው የውድድሩ አዘጋጅ አገር ጀርመን ስብስብ አባል የሆነው ክሮስ ቀጣይ በሚያደርገው ጨዋታ ደረጃውን የማሻሻል እድል አለው።

ጣልያናዊያኖቹ ኮከቦች ሊኦናርዶ ቦኑቺና ጆርጂዮ ኪዬሌኒ እ.አ.አ በ2020 በ11 አገራት አዘጋጅነት በተካሄደው 16ኛው የአውሮፓ ዋንጫ ባለቤት የሆነችው ጣልያን ስብስብ ውስጥ የነበሩ ተጨዋቾች ናቸው።

ኔዘርላንዳዊው የቀድሞ ግብ ጠባቂ ኤድዊን ቫን ደር ሳር፣ ፖርቹጋላዊው ግብ ጠባቂ ሩዊ ፓትሪሲዮ፣ ስፔናዊው ኮከብ አንድሪያስ ኢኒዬሽታ፣ፈረንሳዊው የቀድሞ ተጫዋች ሊሊያን ቱራም፣ ስፔናውያኑ ጆርዲ አልባና ሴስክ ፋብሪጋዝ፣ ጀርመናዊው አንጋፋ ተጨዋች ቶማስ ሙለርና ክሮሺያዊው ኮከብ ሉካ ሞድሪች በተመሳሳይ በአውሮፓ ዋንጫ 16 ጊዜ የተሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው።

ፖርቹጋላዊው ፓትሪሲዮ፣ ጀርመናዊው ቶማስ ሙለርና ከውድድሩ የተሰናበተችው ክሮሺያ ተጫዋች ሉካ ሞድሪች በ17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ የተሳተፉ ተጫዋቾች ናቸው።

ስፔናውያኑ ጆርዲ አልባና አንድሬስ ኢኒዬሽታ በአሁኑ ሰዓት በቅደም ተከተል ለጃፓኑ ክለብ ቪሴል ኮቤና ለአሜሪካዊው ኢንተር ሚያሚ ክለቦች እየተጫወቱ ይገኛሉ።

17ኛው የአውሮፓ ዋንጫ እስከ ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን በውድድሩ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ተጫዋቾች የተሰለፉበትን የጨዋታ ብዛት ሊያሳድጉ ይችላሉ። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም