በትውልድ ቅብብሎሽ ሀገርን ማጽናት - ኢዜአ አማርኛ
በትውልድ ቅብብሎሽ ሀገርን ማጽናት
ከሀብታሙ ገዜ (ድሬዳዋ ኢዜአ )
ዕለቱ ደማቅና ውብ ነው፤ ድምቀቱ የአካባቢውን በረሃማነት ያስረሳል። ቢሆንም የፀሐዩ ግለት ይለያል_። ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም የሁርሶ ቅጥር ጊቢው ውስጥ ነበርኩ።
በስፍራው የተገኘሁት በመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ የኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለስምንተኛ ዙር በመሠረታዊ ወታደርነት ሙያ ያሰለጠናቸውን ወታደሮች በማስመረቁ ይህኑን ሁነት ለመዘገብ ነው።
ፀሐይ ከነ ቅደመ አያቶቿ ካለችበት ተጎልጉላ የወጣች ይመስል፤ አካባቢውን በተለየ መንገድ አጉናዋለች።
የለበስኩትን ሸሚዝ አሸቀንጥሬ ወለሉ ላይ ብጥልም በላብ ከመጠመቅ አላዳነኝም ።
በዚህ ሐሩር ውስጥ ከነ ሙሉ ወታደራዊ የደንብ ልብሳቸው በወታደራዊ ሰላምታ በሜዳው ደምቆ የሚታየው ወጣት አገር ጠባቂ መሠረታዊ ወታደሮች ለተመለከተ ሐረሩ ሳይሆን ቀዝቀዝ ያለ ውሽንፍር የተቀላቀለበት ዝናብ እያካፋ ይመስላል
።
ድንገት የአካባቢውን ድባብ የለወጠ፤ በደም ስር ውስጥ የሚገባ መዝሙር ተለቀቀ፤ የአገር መከላከያ ሠራዊት መዝሙር መናኘት ያዘ።
ታላላቅ የሠራዊታችን ጀነራሎች ፤ ሲቪል የለበሱ የምስራቅ ኢትዮጵያ አመራሮች ከተቀመጡበት ተነስተው ሙዝሙሩን አስተጋቡ።
ቀና ብዬ የተመራቂ ወታደሮችን ገፅታ ቃኘው፤ በአብዛኞቹ ገፅታ ላይ ቁርጠኝነት ፤ ከከፊሎቹ የአይን ብሌኖች ውስጥ የእንባ ዘለላ እየተንቆረቆረ ነው፤ የማያቋርጥ ጅርት---
እስኪበቃኝ አነባሁ፤ አልወጣልህ አለኝ፤ መዝሙሩ እንዳለቀ ወደ ተመራቂ ወታደሮች ስፍራ አመራሁ።
ቆራጥነት ፣ ጀግንነት፣ ትህትና ከድርጊትና ከአንደበታቸው ይፈሳል፤ ካሜራዬን ደቅኜ ከጥቂቶቹ ጋር አወጋሁ፤
ለአገር ሉአላዊነት ፤ ለአገር ነፃነት፤ ለህዝባችን ዘላቂ ሰላም እና ዕድገት ህይወታችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናል አሉኝ።
የአገር መከላከያ ሠራዊትን መቀላቀል የኛ የወጣቶች ኃላፊነት ነው፤ አባቶች በከፈሉት መስዕዋእት ለኛ ያስረከቡንን አገር ጠብቀን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ የሚቻለው ሠራዊቱን በመቀላቀል ነው" ቀጠሉ፤ እንደ ጅረት በሚፈሰው የወጣት አንደበታቸው ።
አገር የተሸመነችው በቅብብሎሽ ነው፤ አገር የሚፀናው ለአገር መስዕዋትነት ለመከፈል በቆረጠ ወጣት ትውልድ ነው፤ የሆነ ጥልቅ ስሜት ወረረኝ፤ ወጣትነት ሁሉንም መሆን የሚቻልበት ዕድሜ ነው፤ ወጣት ሁሉንም ከመውጣትና ከመሻገር የመጣ አመላካች ስያሜ መሆኑን በትክክል ተረዳሁ።
ከመሠረታዊ ወታደሮች መካከል አንዱዓለም ባዘዘው ድንገት ከመድረኩ አካባቢ መሠረታዊ ወታደር ሳሙኤል ከዲር ጫጬ የሚል ስም ተጠራ።
አንድ ቁመተ መለሎ ቀጭን ወጣት ሜዳው ላይ ከተጠቀጠቁት እኩዮቹ መሐል ተመዞና በወታደራዊ እርምጃ ተውቦ ወደ መድረኩ ተጓዘ። ሜዳው በታላቅ ጩኸት ደመቀ....
የደመቀው እልልታና ጩኸት መነሻው መሠረታዊ ወታደር ሳሙኤል ከዲር በሰላም ማስከበር የሁርሶ የአጭር ኮርስ ዕጩ መኮንኖች ትምህርት ቤት አዛዥ የኮሎኔል ከድር ጫጬ ልጅ በመሆኑ ነው።
ይሄም ብቻ አይደለም ኮሎኔል ከድር ወደ መደረኩ በወታደራዊ ሰላምታ እየተመመ ለሚገኘው ልጃቸው ልዩ ስጦታ በአደባባይ ለመስጠት በመዘጋጀታቸው ጭምር የተፈጠረ ነው።
አባት ያዘጋጁትን ሽልማት ለዕለቱ የክብር እንግዳ ለሌተናል ጀነራል ሐጫሉ ሸለመ አስረከቡ፤
መሠረታዊ ወታደሩ በመከላከያ ህብረት የሰው ሃብት አመራር ዋና መምሪያ ኃላፊ ለሌተናል ሀጫሉ ሸለመና ለአባቱ ወታደራዊ ሰላምታ በማቅረብ እና ጎንበስ ብሎ በመሳም የተዘጋጀውን ሽልማት ተቀበለ፤
የሁሉም ታዳሚ አይኖች ወደ ትዕይንቱ ተጎለጎሉ፤ ወታደሩ ሽልማቱን ከታሸገው ከረጢት ውስጥ ፈልቅቆ ለመላው ታዳሚ አሳየ፤ በፍሬም የተለበደ የእናት ኢትዮጰያ የተዋበ ካርታ!!!!
ጩኸቱ ይበልጥ ቀጥሎ ልዩ መንፈስ ሜዳውን አደበበው።
ሌተናል ሐጫሉ ሸለመ ገፅታቸውን ኩራት ፣ መመካትና ትልቅ ተስፋ አልብሷቸው አለፈ...
የአገር ሉአላዊነትና ክብር ፀንቶ የሚቆየው በዚህ መንገድ እና ቅብብሎሽ ነው፤ የአገር ዋልታ የሆነው ወጣቱ ትውልድ በዚህ ታላቅ ሙያ ውስጥ በስፋት በመግባት ለአገር አለኝታ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል ፤ አገርም ህዝብም የሚፀናው በዚህ ፈለግና ቅብብሎሽ ነው ....
በፍጥነት አይኖቼ አሻግረው አፈጠጡ፤ ባዘኑ ፤ ደልዳላው ወታደራዊ አቋማቸው ታየኝ፤ ተፈተለኩ ወደ አጠገባቸው።
ኮሎኔል ከድር ጫጬ የሁርሶ አጭር 'ኮርስ' ዕጩ መኮንኖች ትምህርት ቤት አዛዥ ናቸው፤ በፈገግታ ተቀበሉኝ።
እኔ አባቶቼ የሰጡኝን አገር ከነ ሙሉ ክብሯ ለልጄ አስረክቤያለሁ፤ ለ33 ዓመታት አገሬን በዚህ ሙያ በፍቅር አገልግያለሁ ፤ አሁን ወደ ጡረታ ዋዜማ እየተጓዝኩ ነው ።
ትህትናቸው ፤ በዝግታ የሚናገሩት ቃላት ሰው ሰርስረው ይገባሉ፤ ያስደምማሉ። ግዙፍና ጠንካራ አቋማቸው 20 አመት እንኳ ያገለገሉ አይመስሉም።
የአገር መከላከያ የአገር ኩራት ነው፤ እዚህ ተቋም ተቀላቅሎ አገሩን እንዲያገለግል ተስማምተን ነው ልጄ ሳሙኤል ወደ ሠራዊቱ የገባው።
አገሬ ሉአላዊነቷ ሲከበር ህዝቤ ይከበራል፤ እኔም እከበራለሁ፤ ኢትዮጵያን ጠብቃት -ኢትዮጵያን በታማኝነት አገልግላት ብዬ ነው አደራዬን በአደባባይ ያስረከብኩት፤ ከኢትዮጵያ በላይ የምሰጠው ሌላ ውድ ስጦት የለኝም ይላሉ።
ሰላሳ ሶስት ዓመታት ሙሉ በታማኝነት ለኢትዮጵያ ያለኝን ፍቅርና ኩራት በተግባር አሳይቻለሁ፤ ይህንን የማስቀጠል ኃላፊነት የልጄና የዘመኑ ወጣቶች ኃላፊነት ይሆናል፤ ለአፍታ ድምፃቸውን አቆሙና ቃና ብለው ወደ አዲሶቹ ወጣት ወታደሮች ተመለከቱ፤ መለስ አሉና ለኢትዮጵያውያን ወላጆች መልዕክት ሰደዱ።
የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲረዳኝ የምፈልገው -ውትድርና ማለት እጅግ የላቀ ሙያ መሆኑን ነው፤ አገርን በታማኝነት መጠበቅ ማለት ነው።
ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ እዚህ ግዙፍ ተቋም ሲልኩ ኩራት ሊሰማቸው ይገባል፤ ወደ ሞት መላክ የሚመስላቸው ካሉ ስህተት ነው፤ ቀን ከደረሰ ሞት የትም ቢሆን የማይቀር ዕዳ ነው።
ለህዝብና ለአገር የሚከፈል መስዕዋትነት ፀፀት የሌለው ኩራት ነው.....
እውነት ነው፤
በሃሳብ የኋሊት ተንደረደርኩ፤ በተጋመደ ኢትዮጵያዊ ወኔና ጀግንነት አገርን ለማፅናት የተዋደቁቱ አያቶች-አባቶች -እናቶች ድቅን አሉብኝ።
በክብር በኩራት ያለፀፀት አገርን ለማፅናት የከፈሉት ዋጋ ፈካብኝ።
" እኔን -አንተን-እሱን-እሷን- እነሱን- እነዚያን- በጥቅሉ እ-ኛ-ን እንድንሆን ፤ ኢትዮጵያውያን እንድንሆን ዋጋ ከፍለዋል።
" ...ሰው ተከፍሎበታል፤ ከደምና ከአጥንት " እንድትል ከያኒዋ!!!
ከሃሳቤ መለስ ብዬ የኮሎኔል ከድርን ልጅ ፍለጋ ሜዳውን አሰስኩ።
በትህትና ተቀብሎ ሃሳቡን አከፋለኝ፤ በአደራ በአደባባይ ስለ ተቀበላት አገር አጫወተኝ።
የልጅነት ዕድሜውን በወታደራዊ ካንፕ ማደጉ፤ በሠራዊቱ ፍቅርና ክብካቤ መገመዱ ፤ ለመከላከያ ሠራዊት ፣ ለአየር ኃይል፣ በአዲስ ለተደራጀው ባህር ኃይል ...የተለየ ፍቅር አለው።
ለኢትዮጵያ የሚከፈልን ዋጋ ከአባቱና ከአባቱ ባልደረቦች በታሪክና በተግባር ውስጡ ሰርጿል።
" ዛሬ ኢትዮጵያን ከአባቴ ተረክቤያለሁ፤ አባቴ ኢትዮጵያን ጠብቃት ፤በታማኝነት አገልግላት ብሎ ሸልሞኛል፤ እኔ አደራውን በቁርጠኝነት እውጣለሁ፤ ቀና ብለን ደረታችንን ሞልተን እንድንጓዝ አባቶቻችን አገርን ጠብቀውና አፅንተው አስረክበውናል፤ የኔም ትውልድ እናት አገራችንን አፅንቶ ለቀጣዩ ትውልድ ያስረክባል---"
እውነቱን ነው፤ አገር የትውልድ ቅብብሎሽ ውጤት ናት፤ በሚሰጥና በሚቀበል ፅናት ነው ፀንታ ያለችው።
ያየሁትን ዘግኜ በጥቂቱ ለማሳየት የተጓዝኩበትን ይሄን ፈለግ የምቋጨው ከዕለቱ ተመራቂ መሠረታዊ ወታደሮች መካከል ወጣት አንዱዓለም ባዘዘው በሰደደው መልዕክት ነው፦
የኢትዮጵያ ህዝብ ለአገር ሠራዊት ያለውን ጥልቅ ፍቅርና ክብር አውቃለሁ፤ ለዚህ ህዝብ መስዋዕትነት መክፈል ያኮራል፤ ሠራዊታችን የተጣለበትን አገራዊ ታላቅ ኃላፊነት በታላቅ ድል የሚደመደመው ህዝባችን ያለውን የርስበርስ ፍቅርና አንድነት ጠብቆ ሲያፀና ነው።
የህዝብ ፍቅርና አንድነት፤ መከባበርና ተነጋግሮ መግባባት ለኛ ለሠራዊት አባላት ተልዕኮ መሳካት ስንቅ ይሆናል
አበቃሁ/