የዘንድሮው የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ውድድር ልዩ አጋጣሚ

በይስሐቅ ቀለመወርቅ

የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ውድድር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1916 በአርጀንቲና አስተናጋጅነት ተጀመረ።

ዘንድሮ ደግሞ 48ተኛው የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ውድድር በአሜሪካን አዘጋጅነት እየተደረገ ይገኛል።

በውድድሩ 16 አሰልጣኞች የተለያየ ሀገራትን ብሔራዊ ቡድን ይዘው የሚያሰለጥኑ ሲሆን፤ ከነዚህ ሰባቱ አርጀንቲናውያን አሰልጣኞች መሆናቸው የዘንድሮውን የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ውድድር ልዩ ያደርገዋል።

በራሳቸው ሀገር ተወላጆች እየሰለጠኑ በኮፓ አሜሪካው እየተሳተፉ የሚገኙ ሀገራትን ስንመለከት ብራዚል በብራዚላዊው አሰልጣኝ ዶሪቫል ሲልቬስትር፤ ሜክሲኮ በሜክሲኳዊው  ጃሚን ሎዛኖ፣ አዘጋጇ ሀገር አሜሪካ ደግሞ በአሜሪካዊው አሰልጣኝ ግሬግ ማቲውና አርጀንቲና ደግሞ በአርጀንቲናዊው ሊዮኔል ስካሎኒ እየሰለጠኑ ይገኛሉ።

ፓናማ በዴንማርካዊው አሰልጣኝ ቶማስ ክርስቲያንሰን፤ ጃማይካ በአዬስላንዳዊው አሰልጣኝ ሂመር ሃልግሪምሰን፤ ካናዳ በአሜሪካዊው ጂሲ አለን፤ኢኳዶር በስፔናዊው ፍሊክስ ሳንቼዝ  ፤ቦሊቪያ በብራዚላዊው አንቶኒዮ ካርሎስ እና ፔሩ በኡራጋዊው አሰልጣኝ በጆርጅ ፎሳቴ እየሰለጠኑ በኮፓ አሜሪካ በመሳተፍ ላይ ናቸው።

በዘንድሮው ኮፓ አሜሪካ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝን ጨምሮ ሰባት አርጀንቲናውያን አሰልጣኞች ሰባት ሀገራትን እያሰለጠኑ ይገኛሉ። 

ለመሆኑ እነዚህ አርጀንቲናውያን አሰልጣኞች እነማናቸው?


 

ሊዮኔል ስካሎኒ፡- ይህ አርጀንቲናዊ አሰልጣኝ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድንን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2018 እያሰለጠነ የሚገኝ ሲሆን በ2021 የኮፓ አሜሪካን፤ በ2022 ደግሞ የዓለም ዋንጫን ከአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ጋር አሸንፏል። 

ዘንድሮም በኮፓ አሜሪካ ውድድር የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድንን ይዞ እየተሳተፈ የሚገኝ ሲሆን አርጀንቲና በምድብ ጨዋታዎቿ ካናዳ፣ ቺሊንና ፔሩን አሸንፋ ወደ ሩብ ፍፃሜ እንድትገባ አስችሏታል።

ማርሴሎ ቤልሳ፡- የ68 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋው አርጀንቲናዊ አሰልጣኝ የኡራጋይ ብሔራዊ ቡድንን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2023 ጀምሮ በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ። 


 

ዘንድሮም በኮፓ አሜሪካ ውድድር የኡራጋይ ብሔራዊ ቡድን የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ ያገዙት ሲሆን ፓናማን፣ ቦሊቪያንና አዘጋጇ ሀገር አሜሪካንን አሸንፎ ሩብ ፍፃሜ እንዲቀላቀል አስችለውታል።

ፈርናንዶ ባቲስታ፡- በ53 ዓመት ዕድሜው ላይ የሚገኘው ይህ አርጀንቲናዊ አሰልጣኝ የቬንዙዌላ ብሔራዊ ቡድንን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2023 ጀምሮ በማሰልጠን ላይ ይገኛል። 


 

ዘንድሮም በኮፓ አሜሪካ ውድድር የቬንዙዌላን ብሔራዊ ቡድንን ይዞ እየተሳተፈ ሲሆን፤ ቬንዙዌላ በምድብ ጨዋታዎቿ ኢኳዶርን፣ ሜክሲኮና ጃማይካን አሸንፋ ሩብ ፍፃሜ እንድትገባ አስችሏታል።

ኔስተር ሎሬንዞ ፡- የ58 ዓመቱ አርጀንቲናዊ የኮሎምቢያ ብሔራዊ ቡድንን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2022 ጀምሮ እያሰለጠነ ይገኛል።


 

ዘንድሮም በኮፓ አሜሪካ ውድድር የኮሎምቢያን ብሔራዊ ቡድንን ይዞ ፓራጓይና ኮስታሪካን በምድብ ጨዋታ በማሸነፍ ኮሎምቢያ ሩብ ፍፃሜ እንድትገባ ያደረገ ሲሆን የመጨረሻ የምድብ ጨዋታውን ከብራዚል ጋር ያደርጋል።

ሪካርዶ ጋርሲያ፡- የ66 ዓመቱ አንጋፋ አርጀንቲናዊ አሰልጣኝ ሪካርዶ ጋርሲያ የቺሊ ብሔራዊ ቡድንን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2024 ጀምሮ እያሰለጠኑ ይገኛሉ። 


 

ዘንድሮም በኮፓ አሜሪካ ውድድር የቺሊ ብሔራዊ ቡድንን ይዘው በሚፈልጉት ርቀት መጓዝ አልቻሉም።

በምድብ ጨዋታቸው ከካናዳና ፔሩ ጋር በተመሳሳይ 0 ለ 0 በሆነ ውጤት አጠናቀውና በአርጀንቲና 1 ለ 0 ተሸንፈው ከውድድሩ ውጪ ሆነዋል።

ዳንኤል ጋርኔሮ፡-  የ55 ዓመቱ አርጀንቲናዊ አሰልጣኝ የፓራጓይ ብሔራዊ ቡድንን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2024 ጀምሮ እያሰለጠነ ይገኛል። ዘንድሮም በኮፓ አሜሪካ ውድድር የፓራጓይ ብሔራዊ ቡድንን ይዞ እተሳተፈ የሚገኝ ሲሆን፤ በሚፈለገው ርቀት መጓዝ አልቻለም።


 

ከኮሎምቢያና ብራዚል ጋር ባደረጋቸው ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ሽንፈትን በማስተናገዱ፤ከኮስታሪካ ጋር የሚያደርገው የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ እየቀረው ከውድድሩ ውጪ ሆኗል።

ጉስታቮ  አልፋሮ፡-  የ61 ዓመቱ አርጀንቲናዊ አሰልጣኝ የኮስታሪካ ብሔራዊ ቡድንን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2023 ጀምሮ በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ።


 

ዘንድሮም በኮፓ አሜሪካ ውድድር የኮስታሪካን ብሔራዊ ቡድንን ይዘው በምድብ ጨዋታቸው በኮሎምቢያ ተሸንፈው ከብራዚል ጋር አቻ ተለያይተዋል።

ወደ ሩብ ፍፃሜው ለማለፍ ከፓራጓይ ጋር የሚደርጉትን የመጨረሻ የምድብ  ጨዋታ ማሸነፍና የኮሎምቢያና የብራዚልን የጨዋታ ውጤት መጠበቅ ግድ ይላቸዋል።

በኮፓ አሜሪካ የዋንጫ ውድድር አርጀንቲና፣ ካናዳ፣ ቬንዙዌላ፣ ኢኳዶር፣ ኡራጋይ፣ ፓናማና ኮሎምቢያ ሩብ ፍፃሜውን የተቀላቀሉ ቡድኖች ናቸው።

ኮሎምቢያ ከብራዚል፤ ኮስታሪካ ከፓራጓይ ከሌሊቱ 10 ሰዓት በሚያደርጉት ጨዋታ ደግሞ ሩብ ፍፃሜ የሚገባው ቀሪ አንድ ቡድን የሚለይ ይሆናል።

በዘንድሮው የኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ውድድር ሰባት አርጀንቲናውያን አሰልጣኞች ሰባት ሀገራትን እያሰለጠኑ እየተፋለሙበት ያለ ልዩ አጋጣሚ ፈጥሯል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም