የተዛባ የእንቅልፍ ሰዓት ለስኳር በሽታ እንደሚያጋልጥ ተመላከተ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11/2016(ኢዜአ)፡- መደበኛ ያልሆነ ወይም የተዛባ የእንቅልፍ ሰዓት በስኳር በሽታ የመያዝ እድልን እንደሚጨምር ተመላክቷል።

የዩናይትድ ኪንግደም ባዮባንክ ያካሄደው ተከታታይ ጥናት መደበኛ ያልሆነ የመኝታ ሰዓት አጠቃቀም ለታይፕ 2 ስኳር በሽታ አጋላጭ ምክንያቶች ሰፊ ድርሻ እንደሚኖረው አስገንዝቧል።

የተለያየ የመኝታ ሰዓት የሚጠቀሙና መደበኛ የእንቅልፍ ቆይታ የሌላቸው ሰዎች ለስኳር በሽታ ተጋላጭ እንደሚሆኑ ነው ጥናቱ ያመለከተው።

ጥናቱ የተካሄደው በአማካይ 62 አመት የሞላቸው 84 ሺህ ስኳር ታማሚ ባልሆኑ ግለሰቦች ላይ ሲሆን ለ7 ተከታታይ ቀናት የእንቅልፍ ሰዓታቸው ላይ ቁጥጥር ሲደረግ ነበር።

በጥናቱ ውጤት መሰረት "መደበኛ ያልሆነ" የእንቅልፍ ሰዓት ተብሎ የተለየው በየቀኑ በአማካይ ከ1ሰዓት በላይ የሚለዋወጥ የእንቅልፍ ቆይታ መሆኑን ዩፒአይ ዘግቧል።

በዚህም ከ60 ደቂቃ በላይ በየቀኑ የእንቅልፍ ሰዓታቸው የሚዛባ 34 በመቶው የጥናቱ ተሳታፊዎች ለስኳር ተጋላጭ መሆናቸውን ጥናቱ እንዳመለከተ ተገልጿል።

በተጨማሪም የጥናቱ ተሳታፊዎች ባለፉት ሰባት ዓመታት ባጋጠማቸው የስኳር በሽታ ተጋላጭነት ላይ የዳሰሳ ጥናት መደረጉም ተመልክቷል።

የጥናት ቡድኑ ለስኳር በሽታ ተጨማሪ አጋላጭ የሆኑ ምክንያቶችን ከለየ በኋላ የተዛባ ወይም መደበኛ ያልሆነ የእንቅልፍ ሰዓት ለታይፕ 2 ሰኳር በሽታ አጋላጭ ምክንያት መሆኑን አረጋግጧል።

የጥናት ቡድኑ መሪ የሆኑት ሲና ኪያነርሲ ወጥነት ያለው የእንቅልፍ ሰዓት በታይፕ 2 ስኳር በሽታ የመያዝን እድል ለመቀነስ ጉልህ ድርሻ እንዳለው በጥናቱ መረጋገጡን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም