ዲጂታል አቅምና ነገን የሚዋጅ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ በመገንባት ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት የሚሆን ስራ እየተከናወነ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
ዲጂታል አቅምና ነገን የሚዋጅ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ በመገንባት ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት የሚሆን ስራ እየተከናወነ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2016 (ኢዜአ)፦ዲጂታል አቅምና ነገን የሚዋጅ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ በመገንባት ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት የሚሆን ስራ እየተከናወነ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአምስት ሚሊየን ኮደርስ ኢኒሸቲቭን በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል፡፡
ኢኒሸቲቩ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስና የኢትዮጵያ መንግስታት የሚተገበር ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ 5 ሚሊዮን ወጣቶች በኦንላይን የኮዲንግ ስልጠና የሚወስዱበት ነው፡፡
ስልጠናውም በዋናነት በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክኅሎት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ፤የተባበሩት አረብ ኤመሬትስ ፕሬዝዳንት ሸክ መሃመድ ቢን ዛይድ ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመስራት ስምምነት መፈራረማቸውን አስታውሰዋል፡፡
ስልጠናውም የዚሁ ስምምነት አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአሳቢ ወጣት ዜጎቿ ተስፋ አላት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚረጋገጠው ዲጂታል አቅምና ነገን የሚዋጅ አስተሳሰብ ያለው ትውልድ መገንባት ሲቻል ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ኢኒሸቲቭ ይህን ታሳቢ ያደረገ ስራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በኢነሸቲቩ እድሉን የሚያገኙ ወጣቶች በትብብርና በመደመር እሳቤ በዘርፉ ኢትዮጵያን ወደ ታሻለ ምእራፍ ለማሸጋገር መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
በቀጣይም ብቁ ትውልድን በመገንባት ለኢትዮጵያ ብልጽግና መሰረት የሚሆኑ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ጨምሮ ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
በተለይ ከተባበሩት ኤምሬቶች ጋር ትውልድን መገንባት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ጋር በቅርበት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም ትብብርን በማጠናከር የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡