የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ወጣቶች በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያደርግ ነው - በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2016 (ኢዜአ)፦የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ወጣቶች በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያደርግ መሆኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአምስት ሚሊየን ኮደርስ ኢኒሼቲቭን በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል፡፡

ኢኒሼቲቩ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ኢትዮጵያ መንግስታት የሚተገበር ሲሆን፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ 5 ሚሊዮን ወጣቶች በኦንላይን የኮዲንግ ስልጠና የሚወስዱበት ነው፡፡

ስልጠናውም በዋናነት በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ወሳኝ ከሆኑት መሰረቶች አንዱ የዲጂታል ስነ ምህዳሩን ማስፋት መሆኑን አንስተዋል፡፡

የዲጂታል ስነ ምህዳሩን ከሚያሰፉ ስራዎች መካከል ዋነኛው የክህሎት ግንባታ መሆኑን ገልጸው፤ በዘርፉ እውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ሀይል ማፍራት ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ወጣቶች በዲጂታል ስነ ምህዳር ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችላቸውን ክህሎት የሚያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው መስክ ወደ ፊት እንድትራመድ በር የሚከፍት መሆኑንም እንዲሁ፡፡

ኢኒሼቲቭ መንግስት ወጣቶች ለማብቃት፤ ፈጠራን ለማጎልበት እንዲሁም የዲጂታል አቅም ለመጠቀም ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህም ወጣቶች በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እና አምራች እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ክህሎት የሚያገኙበት መሆኑን ገልጸዋል።

አንድ ሰው የዲጂታል ክህሎት አለው የሚያስብለው ከቴክኖሎጂው ባሻገር ዘመኑን የሚዋጅ አስተሳሰብን ሲላበስ መሆኑን ጠቅሰው፤ በመሆኑም ወጣቶች ከቴክኖሎጂ በተጨማሪ ህሊናዊና ባህሪያዊ የሆኑ የዲጂታል ዘመን ስብዕናን መገንባት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ለኢኒሼቲቩ ስኬታማነት የፌደራል እና የክልል የመንግስት መዋቅሮች፤ የግሉ ዘርፍ የልማት አጋሮች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ እና ወላጆች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 


 

የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አብዱላ ናስር፤ ኢኒሼቲቭ የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ  ያላቸውን አጋርነት ወደ አዲስ ምእራፍ የሚያሸጋግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ሁለቱን አገራት በጋራ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ሌሎች የትብብር መስኮች ለማስተሳሰር በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

በተያያዘ ዜናም የአስፈጻሚ አመራሮች ስልጠና መርሃ ግብር ይፋ ተደርጓል፡፡

ስልጠናው ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በትብብር የሚሰጡት ሲሆን፤ ከ15 የመንግስት ተቋማት የተወጣጡ አመራሮች ስልጠናውን የሚወስዱ ይሆናል፡፡

ስልጠናው ስድስት ወራት የሚወስድ ሲሆን፤ በኦንላይና አካል እንደሚሰጥ ተገልጿል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም