ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በምታደረገው ጥረት ያልተነገረ ታሪክ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በምታደረገው ጥረት ያልተነገረ ታሪክ
ከሚዲያ ሞኒተሪንግና ትንተና ዳይሬክቶሬት
ቀደም ባሉት ዘመናት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን 40 በመቶ እንደነበረ፤ ቀስ በቀስ ይህ የደን ሀብት በተለያየ ምከንያት ተራቁቶ ወደ ሦስት በመቶ ያህል አሽቆልቁሎ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ከደን ሀብት መራቆት ጋር በተያያዘ የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ተፅዕኖ የበረሃማነት መስፋፋት፣ በተደጋጋሚ የድርቅና ሌሎች ተጓዳኝ አደጋዎች መከሰት ያሳሰባት ኢትዮጵያ የደን ሀብት ልማት፣ ጥበቃና እንክብካቤ እንዲሁም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎችን አጠናክራ በመቀጠሏ እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ የደን ሀብቷ ከዓመት ዓመት እድገት እያሳየ ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ከፍ ማለቱንም መረጃዎቹ ይጠቁማሉ።
በሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያን የመምራትና የማስተዳደር ሥልጣንን የተረከቡት ባለራዕይውና የለውጥ አራማጁ መሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2011 ዓ.ም ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለውን እና አያሌ ትሩፋቶችን እያገናጸፈ የሚገኘውን የአረንጓዴ አሻራ ልማት ኢኒሼቲቭ ሀገር አቀፍ መርሃ ግብርን ይፋ አደረጉ። መላው ኢትዮጵያውያን ባለፉት ስድስት ዓመታት መርሃ ግብሩን እውን ለማድረግ በፅናት፣ በቁርጠኝነትና በኅብረት ባከናወኗቸው አያሌ ተግባራት በአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር ከራሳቸው አልፎ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ያስደመመ ውጤት አስመዝግበዋል፤ እያስመዘገቡም ይገኛሉ።
የዚህ ጽሑፍ አብይ ዓላማም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጨነት እውን የሆነውን፣ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለውን እና አያሌ ትሩፋቶቹን እያቋደሰ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ኢኒሼቲቭ ሀገር አቀፍ መርሃ ግብርን ዘርዝሮ ማስረዳት አይደለም። ይልቁንም ተቀማጭነታቸውን በቱርክ አንካራ ያደረጉት የኢትዮጵያ ዲፕሎማት አፈወርቅ ሽመልስ “Untold story of Ethiopia's endeavor in combating climate change” በሚል ርዕስ ያሰናዱትን ጽሑፍ ወደ አማርኛ ቋንቋ በመመለስ ስለኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ልማት ኢኒሼቲቭ ያልተነገረ ታሪክ ላይ የሰጡትን ህያው እማኝነት ለውድ ተደራሲያን በአጭሩ ማቋደስ ነው። የዲፕሎማቱን እማኝነት እነሆ ብለናልና አብራችሁን ዝለቁ።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የምታደርገው ጥረት ተጨባጭ ውጤቶችን እያሳየ ነው። ሆኖም ግን በሚገባው ልክ እንዳልተነገረለት ተቀማጭነታቸውን በቱርክ አንካራ ያደረጉ የኢትዮጵያ ዲፕሎማት አፈወርቅ ሽመልስ ይገልጻሉ።
ዲፕሎማቱ ዴይሊሳባህ ለተባለው የቱርክ ድረገጽ በላኩት ጽሁፍ ከስድስት ዓመት በፊት አረንጓዴ አሻራ ማኖር በሚል የተጀመረው አገር አቀፍ ዘመቻ የተራቆቱ አካባቢዎችን በዛፍ ችግኞች የመሸፈን ብሄራዊ መርሃግብር የደን ሽፋንን በማሳደግ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
እንደ ዲፕሎማቱ ማብራሪያ አየር ንብረት ለውጥ በተደጋጋሚ መከሰቱ ለምድራችንና ለሰው ልጆ የማይታመን ከባድ ፈተና ፈጥሯል። በአሁኑ ጊዜ የአየር ንብረት ለውጥ የሰው ልጅን ህልውና የሚፈታተን የማይቀር አደጋና በዓለም አቀፍ ደረጃ ስጋት ሆኗል።
እ.ኤ.አ. ከ1980ዎቹ ጀምሮ በዓለማችን የከፋ የአየር ሁኔታ መዛባት፣ ተደጋጋሚና ከባድ የሙቀት ማዕበል፣ በረሃማነት፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የአርክቲክ በረዶ መቅለጥ፣ የብዝሀ ህይወት መጥፋት፣ የመሬት መራቆት፣ የደን ሽፋን መመናመን፣ የለም አፈር መከላት፣ የምርታማነት ዕድገት መቀነስ እና ሌሎች በርካታ ፈተናዎች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እየታዩ ነው።
በዚህ ረገድ ያደጉ አገሮች በተለይም በምዕራቡ ንፍቀ ክበብ የሚገኙ ከከባድ ኢንዱስትሪዎቻቸው በሚለቀቀው የሙቀት አማቂ ጋዞች ከባቢ አየርን በመበከል የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። ለዓለም ሙቀት መጨመር እና ለካርቦን ልቀት እዚህ ግባ የሚባል አስተዋጽኦ የሌላት አፍሪካ በጣም የተጎዳችና እየተሰቃየች ትገኛለች።
በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በየጊዜው የሚያጋጥሙ ችግሮች እየተለመዱ ከመምጣታቸው የተነሳ ድንጋጤ መፍጠር እያቆሙ መሆናቸውን ያተቱት ዲፕሎማቱ አፍሪካ ለችግሮቹ እዚህ ግባ የሚባል አበርክቶ ሳይኖራት የጉዳቱ ዋነኛ ሰለባ ከሆነች በርካታ አስርት ዓመታት እንደዋዛ መንጎዳቸውን ይገልጻሉ።
የአፍሪካ ቀንድ ለዓለም ጠቃሚ የጂኦ ስትራቴጂክ አካባቢ ነው። በዚህ የዓለም ክፍል ውስጥ ያሉ ሀገራት ላለፉት አምስት አስርት ዓመታት በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ለከፋ ችግሮች ተጋልጠዋል ይላሉ ዲፕሎማቱ። አገራቱ ካጋጠሟቸው ተግዳሮቶች መካከል በረሃማነት፣ የብዝሀ ህይወት መጥፋት፣ተደጋጋሚ ድርቅ መከሰት፣የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የመሬት መራቆትና የጎጂ ነፍሳት ክስተትና መስፋፋት ዋነኞቹ ናቸው። ይህ ዓለም አቀፍ የአካባቢ ችግር ለከፍተኛ የምግብና የውሃ እጦት እና ለአዳዲስ የወረርሽኝ በሽታዎች መጨመርን አስከትሏል። የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን ለረጅም ጊዜ ድርቅ ተጋላጭ አድርጎታል፤ ለሶስት ተከታታይ የምርት ወቅቶች ያጋጠመው የዝናብ እጥረት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖችን ለዘለቄታው የምግብ እጥረት፣ ለስቃይ እና መፈናቀል አጋልጧል፤ ድርቁ በከብቶች ህልውና ላይም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደረ ሲሆን፤ በሦስት ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶች ሞተዋል ይላሉ ዲፕሎማት አፈወርቅ በጽሑፋቸው።
ዲፕሎማት አፈወርቅ አያይዘውም የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ ቀንድ በምትገኘው ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ ለድርቅ ተጋላጭ እንድትሆን፣ በአካባቢ መራቆት፣ በረሃማነት መጨመር ረገድ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። የአየር ንብረት ለውጥ በአከባቢው በተለይም በኢትዮጵያ ያለውን አደጋ የተረዱት የኢትዮጵያ የለውጥ አራማጅ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ እ.ኤ.አ በ2019 አረንጓዴ ሌጋሲ ኢኒሼቲቭ በመባል የሚታወቀውን ዛፎች የመትከል ሀገራዊ መርሃ ግብር ይፋ ማድረጋቸውን ይገልጻሉ።
ይህ ተነሳሽነት በኢትዮጵያ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ያለመ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በመላ ሀገሪቱ የመትከል ታላቅ ዓላማ ያለው መርሃ ግብር ነው። መንግሥት በመጀመርያው ዓመት ከ4 ቢሊዮን በላይ የተለያዩ ችግኞችን በመትከል በአንድ ጀምበር ከ353 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል የዓለም ክብረ ወሰንን ሰብሮታል ይላሉ።
እንደ ዲፕሎማቱ ማብራሪያ መንግስት ለዚህ ዓለማ መሳካት በየዓመቱ ከ25 ሚሊዮን በላይ የሰው ኃይል በማነሳሳትና በመላ አገሪቱ በማሰባሰብ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ የጋራ የኃላፊነት ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል። መንግስት የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ ከሰኔ እስከ መስከረም ባለው የዝናብ ወቅት ችግኝ ተከላውን ቀጥሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተያዘው የክረምት ወራት 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን የተለያዩ ችግኞችን ለመትከል ግብ አስቀምጠው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር ተጀምሯል። በመላ ሀገሪቱ ባለፉት አምስት ዓመታት ለየአካባቢው ስነምዕዳር ተስማሚ የሆኑ ከ32 ነጥብ 5 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። የአረንጓዴ አሻራ ልማት ኢኒሼቲቭ እውን መሆን በመቻሉ የሀገሪቱ የደን ሽፋን እ.ኤ.አ በ2019 ከነበረበት 17 ነጥብ 2 በመቶ በ2023 ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ አድጓል።
በመላ አገሪቱ በመርሃግብሮቹ ከተተከሉት ችግኞች እንደ ወይራ፣ዋንዛ፣ኮሶና ጽድ የመሳሰሉት ለየአካባቢው ስንምዕዳር ተስማሚ የሆኑ የሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎች ይገኙበታል። ከዚህም በሻገር በምግብ ራስን በመቻል ለምግብ ዋስትና መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው እንደ አቮካዶ፣ማንጎ፣ዘይቱን እና ኮክ የመሳሰሉ ለቆላማና ለከፊል ቆላማ አከባቢዎች ተስማሚ የሆኑ ቋሚ የፍራፍሬ ተክሎች በአረንጓዴ አሻራ ልማት ኢኒሼቲቭ ልዩ ትኩረት የተሰጣቸው መሆናቸውን ዲፕሎማት አፈወርቅ አብራርተዋል።
የአረንጓዴው አሻራ ልማት ኢኒሼቲቭ ዓላማ በኢትዮጵያ መንግስት እና በህዝቦቿ የተቀናጀ ጥረት የኢትዮጵያን ተራሮች፣ ኮረብታዎች፣ ሜዳ ሸንተረሮች እና ከተሞችን አረንጓዴ በማልበስ በኢትዮጵያና በቀጣናው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚያጋጥሙ አስደንጋጭ ተግዳሮቶች ማስወገድ ነው።
ዲፕሎማት አፈወርቅ በጽሑፋቸው እንዳስገነዘቡት የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር የሀገሪቱን የደን ሽፋን በማሳደግ፣ የመሬት መራቆትን በመከላከልና የደን ሀብትን በመጠበቅና በመንከባከብ ስነ-ምህዳሩን በማመጣጠን ለቀጣዩ ትውልድ ምቹና ዘላቂ አረንጓዴ አካባቢን ለማውረስ ይረዳል።
እንዲሁም የዛፍ ችግኞችን በመትከል የተራቆተውን የደን ሀብት መልሶ በማልማት በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኘውን ካርቦን ዳይኦክሳይድ እና ሌሎች አደገኛ የሙቀት አማቂ ጋዞችን በመቀነስ ለኦዞን ሽፋን መሳሳትና ለዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥን አስከፊ ተፅዕኖ ለመቋቋም የላቀ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት አምስት ዓመታት ከ50 ቢሊዮን ዶላር በላይ መዋዕለ ንዋይ አፍስሶና በሀገሪቱ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብን ጨምሮ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ዜጎችን አንቀሳቅሶ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመግታት ብርቱ ጥረት አድርጓል ይላሉ። ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ ቀጣናዊ ውህደት ለመፍጠር 1 ቢሊዮን ችግኞችን ለስድስት ጎረቤቶቿ በማከፋፈል በአረንጓዴ ዲፕሎማሲ የቀጣናዊ ውህደቱ አካል እንዲሆኑ አድርጋለች ሲሉም ይገልጻሉ።
ዲፕሎማቱ አያይዘውም በሌላ በኩል መንግሥት በክረምት ወራት አርሶ አደሩን በማንቀሳቀስ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራውን በመላ ሀገሪቱ አጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህም ባለፉት አምስት ዓመታት በርካታ ሺህ ኪሎ ሜትር የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች ተከናውነዋል።በተለያየ ምክንያት በተራቆቱ ተራራማ፣ ዳገተማና ኮረብታማ አካባቢዎች እንዲሁም ተፋሰሶች መልሰው እንዲያገግሙና እንዲታደሱ የድንጋይና የአፈር እርኮኖችና ጋቢዮኖች ሥራ እንዲሁም ባህላዊ የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ፣ የውሃ መውረጃ ቦዮችና ማስተላለፊያ ቱቦች ግንባታ መካሄዱን በጽሑፋቸው አመላክተዋል።
ፀሐፊው አክለውም የደን ልማቱና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የመሬት መራቆትን፣ በጎርፍ የመጥለቅለቅ አደጋን፣ የለም አፈር መከላትን በመታደግ የከርሰና የገፀ ምድር የውሃ ሀብት እንዲጨምሩ የሚያስችሉና አረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ ውጥኖች የሆኑትን የውሃ ሼድ አያያዝ በኢትዮጵያ ሥነ-ምህዳራዊ ስርዓት መደበኛ በማድረግ በረሃማነትን በዘላቂነት በመከላከል ዓባይን በመሳሰሉት ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የውሃ ፍሰትን ለማስቀጠል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸውም ያስረዳሉ።
በመሆኑም የታችኛው የተፋሰሱ አገራት ግብፅ እና ሱዳን፣ የዓባይን ውሃ በብቸኝነት ካልተቆጣጠርነው በሚል እሳቤ ያልተገባ ስሞታ ከማቀረብ ይልቅ፤ ለራሳቸው ብሄራዊ ጥቅም ሲሉ አረንጓዴ ኢኒሼቲቭን በገንዘብ ጭምር በመደገፍ የውሃ ፍሰትን ዘላቂነት በማረጋገጥ ላይ በትብብር መንፈስ ቢሰሩ ይመራጣል ሲሉ ዲፕሎማት አፈወርቅ ይመክራሉ።
ዲፕሎማት አፈወርቅ በጽሑፋቸው ማጠቃለያ አንኳር ሃሳብ እንዳስገነዘቡት ከዚህም ባሻገር ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የፓርቲዎች ኮንፈረንስ (CoP) እና ሌሎች ማህበረሰቦች ተመሳሳይ መርሃ ግብር በሌሎች የቀጣናው አካባቢዎች እንዲደግሙ ለማነሳሳት ሰብዓዊነትን እንደ አንድ የጋራ ጥቅም እንዲያገለግል በተነሳሽነት መደገፍ አለባቸው። የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሼቲቭ የተራቆቱ አካባቢዎችን በማሻሻል ካስመዘገበው ስኬት ባለፈ ዋነኛ ዓላማው የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝቦችን አንድነት በማጠናከር የአፍሪካ አረንጓዴ ቀበቶ ኢኒሼቲቭን ግብ ለማሳካት ከፍተኛ አበርክቶ ይኖረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህም ባሻገር የካርቦን ልቀትን በ2030 ዜሮ ለማድረግ ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት የኤሌክትሪክ ኃይልን ሙሉ በሙሉ ከውሃ፣ ከነፋስ፣ ከፀሐይና ከእንፏሎት ወዘተ. ለማመንጨት በቁርጠኝነት እየሰራ ነው። ኢትዮጵያ የቀጣናዊ ውህደቱ ዋና አንቀሳቃሽ እንደመሆኗ መጠን የኤሌክትሪክ የመሰረተ ልማት አውታርን ከጅቡቲ፣ ሱዳንና ኬንያ ጋር በማገናኘት ንፁህ ኃይሏን በማጋራት ከታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እየሰራች ነው። እንዲሁም የአዲስ አበባ ቀላል ባቡርን እና የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመርን ከብክለት የፀዳ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ አካል በማድረግ በኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሰራ አድርጓል።