ኢትዮጵያና ቻይና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያና ቻይና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለፁ
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 18/2016 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ቻይና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ልማት ያላቸውን ትብብር ይበልጥ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገለፁ።
የኢትዮጵያና ቻይና ሦስተኛው የሳይንስና ቴክኖሎጂ የጋራ ኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
ያለፉት ዓመታት የሳይንስና ቴክኖሎጂ የትብብር ማዕቀፎችን በመገምገም በቀጣይ አምስት ዓመታት በአዳዲስ ዘርፎች ላይ አብሮ ለመስራትም የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በንግግራቸው፥ ኢትዮጵያ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እውን የማድረግ ጉዞን መጀመሯን ገልጸው፥ ለውጤታማነቱም ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል ብለዋል።
ለሳይንስ፣ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ በተሰጠው ትኩረት በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የዜጎችን ህይወት ለማሻሻልና የሀገርን እድገት ለማፋጠን ቴክኖሎጂ ወሳኝ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ለስኬቱም ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ያላቸው ኢትዮጵያና ቻይና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍም በትብብር እየሰሩ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የሀገራቱ ትብብር ለኢትዮጵያ የዲጅታል ሽግግር መሳካት የላቀ ሚና እንዳለው በማንሳት፥ በቀጣይም የቴክኖሎጂ ፈጠራን በሚያሳድጉ የትምህርትና ስልጠናና ሌሎች ትብብሮች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ዛሬ የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነትም ባለሙያዎች በሳይንስና ቴክኖሎጂ የእውቀት ሽግግርና የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ እንዲሁም በዘርፉ የጋራ የጥናትና ምርምሮችን ለማድረግ ያስችላል ነው ያሉት።
የቻይና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሊን ዢን በበኩላቸው የዛሬው መድረክ የሀገራቱን የፈጠራ ስራ ትብብር ለማጠናከር የሚያግዝ እንደሆነ ተናግረዋል።
ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ያላትን ትብብር ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።