በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟላ ምርመራ ተደርጓል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ለሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን  አትሌቶች ዓለም አቀፍ መስፈርትን ያሟላ ምርመራና የክትትል ስራ መከናወኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን አስታወቀ።

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የፀረ-አበረታች ቅመሞች አማካሪ ቡድን ውስጥ አፍሪካን በብቸኝነት መወከሏንም ገልጿል። 

33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ በፓሪስ የሚጀመር ሲሆን የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በውድድሩ አበረታች ቅመሞች ምርመራና ቁጥጥር የተለየ ትኩረት ሰጥቷል። 

በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የአበረታች ቅመሞች ምርመራ እንዲያደርግ ፈቃድ የተሰጠው ተቀማጭነቱን በስዊዘርላንድ ሉዛን ያደረገው ' ኢንተርናሽናል ቴስቲንግ ኤጀንሲ' የተሰኘው ገለልተኛ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን ይደርሳል የዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ(ዋዳ) ባስቀመጠው አሰራር መሰረት በውድድሩ ለሚሳተፉ ኢትዮጵያውያን  አትሌቶች የአበረታች ቅመሞች ምርመራ መደረጉን ገልጸዋል።

ባለስልጣኑ ስፖርተኞቹ ከአበረታች ቅመሞች የጸዱና ነፃ ሆነው እንዲወዳደሩ የቅድመ መከላከልና የቁጥጥር ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከአበረታች ቅመሞች የፀዳ ስፖርት እንዲፈጠር በትኩረት እየሰራች መሆኗን  ጠቅሰው፤ በኦሊምፒክ ጨዋታዎችም ላይ ያለው መልካም ተሞክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊ ጥረት መደረጉን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።    

ምርመራዎቹ ለስፖርተኞች የተከለከሉ ብሎ የለያቸው ቅመሞችን መሰረት በማድረግ መከናወኑና ሁሉም አትሌቶች ነጻ መሆናቸውን አመልክተዋል። 

ከክትትልና ቁጥጥር ስራው በተጨማሪ ለአትሌቶች የአበረታች ቅመሞችን አስመልክቶ የግንዛቤ መፍጠር ስራ ማከናወኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ስፖርተኞች፣ አሰልጣኞችና የቡድን መሪዎች በጉዞና በውድድር ወቅት አበረታች ቅመሞችን አስመልክቶ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።    

በተያያዘም በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ(ዋዳ) ባቋቋመው አማካሪ ቡድን ውስጥ አፍሪካን የወከለች ብቸኛ ሀገር መሆኗን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ አፍሪካን በወከል የአበረታች ቅመሞች ክትትልና ቁጥጥር ስራ ላይ እንደምትሳተፍና ለዋዳ የተለያዩ ምክረ ሀሳቦችን እንደምታቀርብ ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በፓሪስ በሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአበረታች ቅመሞች ላይ ከሚያደርገው ቁጥጥርና ክትትል በተጨማሪ ስፖርተኞችን የማስተማር ስራ ያከናውናል።

የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የዓለም አቀፉ የፓራኦሊምፒክ ኮሚቴ ከእ.አ.አ 1960ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ የአበረታች ቅመሞች ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርጉ መረጃዎች ያመለክታሉ። 

ዛሬ በፓሪስ በሚጀመረው በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በእያንዳንዱ ውድድር በሚደረግበት ስፍራ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ቁጥጥር ቦታ ተዘጋጅቷል።

በዚህም 360 የሚሆኑ ግለሰቦች የአበረታች ቅመሞች ናሙና በመውሰድ ምርምራ ያደርጋሉ፣ የአትሌቶችን በውድድር የመሳተፍ ተገቢነትም ያረጋግጣሉ ተብሏል።

ኢትዮጵያ በዘንድሮው የፓሪስ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች በአትሌቲክስና ውሃ ዋና የስፖርት ዓይነቶች በ38 ስፖርተኞች ትወከላለች።  

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም