ቻይና በቴክኖሎጂና በወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፍ የኢትዮጵያ ወጣቶችን ለማብቃት አስፈላጊውን እገዛ እንደምታደርግ ገለጸች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ ቻይና በቴክኖሎጂና በወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፍ የኢትዮጵያ ወጣቶችን ለማብቃት አስፈላጊውን እገዛ እንደምታደርግ ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ፉአድ ገና ከብሪክስ የወጣቶች ጉባኤ ጎን ለጎን ከቻይና የወጣቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ጎንግ ጂንሎንግ ጋር ተወያይተዋል፡፡

መሪዎቹ በቻይና አፍሪካ የትብብር ማዕቀፍ ስር በትምህርት ፤ በስራ ፈጠራ፤ በወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡


 

በቻይና በየዓመቱ በሚካሄደው የአለም ወጣቶች ዴቨሎፕመንት ፎረም ላይ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በስፋት የሚሳተፉበትን እድል ለማመቻቸት በሚያስችሉ ነጥቦች ላይም ተወያይተዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት የወጣት ለወጣት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋር እንደሚሰሩ ያረጋገጡት መሪዎቹ በኢትዮጵያ የቻይንኛ ቋንቋ ማስተማሪያ ማዕከላትን ለማስፋፋትም ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ በቻይና የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ማዕቀፍ ስር ተጠቃሚ የምትሆንበትን አማራጭ ለማስፋትም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ምክትል ፕሬዝዳንት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ-ቻይና ወጣቶች ጉባኤን በ2025 እንደምታስተናግድ የወጣቶች ምክር ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም