ብሔራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲን ማስተግበሪያ ስትራቴጂና ማስፈጸሚያ ፕሮግራሞች ተዘጋጅተዋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ ብሔራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲን መተግበር የሚያስችሉ ስትራቴጂና ማስፈጸሚያ ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸውን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

የተለያዩ የዓለም ሀገራት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ከመዝናኛና የመገልገያ ዘዴዎች እስከ ብሔራዊ ደህንነትና መረጃ አገልግሎት ላሉ ቁልፍ ጉዳዮች ጭምር ጥቅም ላይ እያዋሉት ነው፡፡

ኢትዮጵያም ቴክኖሎጂውን ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ አገልግሎት ለማዋል፣ ፀጥታና ደህንነት ለማስጠበቅና በዘርፉ ተወዳዳሪ አቅም ለመፍጠር በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

በተለይም ከለውጡ በኋላ ዘርፉን የሚመራ ተቋም በመመስረት የኢትዮጵያን ትልሞች ለማሳካት እየተሰራ ነው።

ከዚህም ባለፈ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው 37ኛ መደበኛ ስብሰባ ብሔራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር ኢ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ፖሊሲውን ለማዘጋጀት ከሁለት ዓመት በላይ ጊዜ ወስዷል፡፡

ፖሊሲው መንግስት በዘርፉ ሊደርስበት የፈለገውን ግብ ማሳካት እንዲችል የተለያዩ ባለሙያዎችን በማሳተፍና የሀገራትን ልምድ በመቀመር ስለመዘጋጀቱም ነው ያብራሩት።

በርካታ ሀገራት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲ እንደሌላቸው የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ የኢትዮጵያ መንግስት ፖሊሲው ወደ ስራ እንዲገባ መወሰኑ ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ፖሊሲው ማንኛውም በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ወደ ሀገሩ በመምጣት በዘርፉ በመሰማራት ራሱንና ሀገሩን በቴክኖሎጂ ማሳደግ የሚችልበትን እድል እንደሚፈጥርም አንስተዋል።

ብሔራዊ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ፖሊሲን በፍጥነት ሥራ ላይ ለማዋል የሚያግዙ ስትራቴጂና የማስፈጸሚያ ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም