አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በመንግሥት አሰራሮች፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በትምህርት እና በሌሎች መስኮች መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በመንግሥት አሰራሮች፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በትምህርት እና ሌሎችም መስኮች መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

አቶ ተመስገን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ዙሪያ የተዘጋጀውን ዐውደ ጥናት ተካፍለናል ብለዋል፡፡

ዐውደ ጥናቱ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች የተገኙበት እና በቢግ ዳታ፣ ጄኔሬቲቭ ኤ.አይ፣ በአመራሮች ውሳኔ አሰጣጥ፣ በፖሊሲ እና ሕዝብን በማገልገል ሂደት ውስጥ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ውጤታማነትን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል ግንዛቤ የተወሰደበት ነበርም ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡


 

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዛሬ ላይ በሁሉም መስኮች አገልግሎት ላይ እየዋለ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡ 

በዚህም በመንግሥት አሰራሮች፣ በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በትምህርት እና ሌሎችም መስኮች መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ ይገኛል ብለዋል፡፡ 

እኛም በዚህ ዘርፍ በርትተን በመስራት እና የሕዝባችንን ችግሮች መፍታት የሚችሉ የተለያዩ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሥርዓቶችን በማበልፀግ መጠቀም ይገባናል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የቴክኖሎጂውን ሙሉ አቅም ተገንዝቦ ወደ ተግባር የሚለውጥ የሰው ኃይል መገንባት ደግሞ ሌላኛው ቁልፍ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡  

ከዚህ አንጻር እንደነዚህ ያሉ ዐውደ ጥናቶች ጉልህ ሚና እንዳለቸው እናምናለን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በወዳጅ ሀገር የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ተቀማጭነቱን ባደረገው ፕሪሳይት በተባለው ተቋም ለሦስት ቀናት የተዘጋጀው ዐውደ ጥናት በዘርፉ ያቀድነውን ወደ መሬት ለማውረድ ከሚሰጠው አቅጣጫ አንጻር ስኬታማ ነበርም ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም