የ33ኛው ኦሊምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ስርዓት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2016(ኢዜአ)፦በፓሪስ የሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች የመክፈቻ ስነ ስርዓት በመከናወን ላይ ይገኛል።

በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ቶማስ ባክ፣ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የተለያዩ የሀገራት መሪዎችና ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የዘንድሮው ኦሊምፒክ መክፈቻ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከስታዲየም ውጪ በወንዝ ላይ እየተደረገ ነው።

በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ 10 ሺህ 500 ስፖርተኞች በሰሜናዊ ፈረንሳይ በሚገኘው ሴይን ወንዝ ላይ በመርከብ የ3 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር በማቋረጥ የመክፈቻ ስነ ስርዓቱ የሚካሄድ ይሆናል።

የመክፈቻ ስነ ስርዓቱን 300 ሺህ ተመልካች በስፍራው በመገኘት እንደሚከታተለው ይጠበቃል።

በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከ203 ሀገራት የተወጣጡ 10 ሺህ 500 አትሌቶች በ32 የስፖርት አይነቶች እንደሚወዳደሩ የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መረጃ ያመለክታል።

ከሀገራቱ በተጨማሪ በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጥላ ስር ገለልተኛ አትሌቶችና የኦሊምፒክ የስደተኞች ቡድን ይሳተፋሉ።

ኢትዮጵያም በአትሌቲክስና በውሃ ዋና የስፖርት ዓይነቶች በ38 ስፖርተኞች የምትካፈል ሲሆን አትሌቶቹ ከሚያዚያ 2016 ዓ.ም አንስቶ ከፍተኛ ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም