የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማርና ምርምር ሥራቸውን በዲጂታል ሥርዓት የመደገፉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማርና ምርምር ሥራቸውን በዲጂታል ሥርዓት የመደገፉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 20/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማርና ምርምር ሥራቸውን በዲጂታል ሥርዓት የመደገፉ ሥራ ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቆመ።
13ኛው የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች ጉባኤ "ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሽግግር ያለው እድልና ፈተና" በሚል መሪ ኃሳብ ዛሬ ተካሂዷል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጥራት ማረጋገጥ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አበባው ይርጋ በዚሁ ጊዜ፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲጂታል ሽግግር እድሎችና ፈተናዎች ላይ ያተኮረ ጽሁፍ አቅርበዋል።
ዲጂታል ቴክኖሎጂ አሁን የደረሰበትን ደረጃና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዕለት ተዕለት ሥራቸውን ከማቀላጠፍ አኳያ ያለውን ፋይዳ በጹሁፋቸው ዳሰዋል።
በኢትዮጵያ አብዛኞቹ ዩኒቨርስቲዎች በወረቀት የነበረውን አሰራር ወደ ዲጂታል በመቀየር የተሻለ አፈጻጻም እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ የምርምርን፣ የመማር ማስተማርን፣ አስተዳደራዊ ሥራንና የማኅበረሰብ አገልግሎትን ዘመኑን የዋጀ ከማድረግ አንጻር ጅምር ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።
የመሰረተ-ልማት ክፍተት፣ የኢንተርኔት ተደራሽነት ውስንነትና ሌሎች ተያያዥ ችግሮች ዲጂታል ቴክኖሎጂ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በፍጥነት እንዳያድግ ካደረጉት ውስጥ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ብቁና ተወዳዳሪ ለመሆን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች የምክክር መድረክ የወቅቱ ሰብሳቢና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ዲጂታላይዜሽን ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው ፋይዳ ታምኖበት በምክክሩ ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የአስተዳደር ሥራዎችን ዲጂታላይዝ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዩኒቨርስቲው ከዋናው ስድስት ኪሎ ካምፓስ በመጀመር ወደ ሌሎች ለማስፋት በእቅድ ይዞ እየሰራ ነው ብለዋል።
በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ በበኩላቸው ትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የዲጂታል መሰረተ-ልማትን ለማስፋት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ በትምህርት ሚኒስቴር በቀጥታ የሚተዳደሩ 47 ዩኒቨርስቲዎች የዲጂታል መሰረተ-ልማት ቴክኖሎጂ እየተሟላ ይገኛል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በበየነ መረብ የታገዘ ትምህርት በመስጠት የትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋትም ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።