ናፍቆት ድሬዳዋ በዓል በስፖርት ፌስቲቫል እየተከበረ ነው

ድሬዳዋ፤ ሐምሌ 21/2016(ኢዜአ)፦ ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የመጡ የድሬዳዋ ተወላጆች እና ወዳጆች የተሳተፉበት ናፍቆት ድሬዳዋ በዓል በስፖርት ፌስቲቫል እየተከበረ ነው።

በዓሉ በውጭ ካሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ አባላት ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር አባላቱ በሀገር ገፅታ ግንባታና በልማት ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ምቹ አጋጣሚ እየፈጠረ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናግረዋል።

በዓሉ ዛሬ በስፖርት ፌስቲቫል በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ሲሆን በድሬዳዋ ከዚራ የዛፍ ጥላ ጎዳናዎች ላይ በእግር በመጓዝ እና የአስተዳደሩ ቀበሌዎች የተለያዩ የድሬዳዋ መገለጫ የሆኑትን የባህላዊ ምግቦች ትዕይንት በማሳየት ነው።

የከዚራ የዛፍ ጥላ ስር የእግር ጉዞን የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ሲሆኑ የካቢኔ አባላትም ተሳትፈዋል።

በአግር ጉዞው እና በምግብ ትዕይንቱ ላይ ከመላው ዓለም የመጡ የድሬዳዋ ተወላጆች እና ወዳጆች ታድመዋል።


 

ከንቲባ ከድር በእዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በዓሉ ዳያስፖራዎችን ከእናት ሀገራቸው እና ከቀያቸው ጋር ያላቸውን ትስስር በማጠናከር በሀገር ልማት፣ ሰላምና ብልፅግና ማረጋገጥ ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ ያግዛል።

በተለይ በበዓሉ ላይ የተገኙ የሁለተኛው ትውልድ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት የወላጆቻቸውን ሀገር ወግ እና ባህላቸውን ለማወቅና ለመላመድ ጭምር አበርክቶው የጎላ መሆኑን ነው ያስረዱት።

ባለፉት ዓመታት የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት በኢንቨስትመንት እና በማህበራዊ ልማቶች ላይ ያበረከቱትን አስተዋጽኦን ከንቲባ ከድር በአብነት ጠቅሰዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሚካኤል እንዳለ በበኩላቸው በዓሉ ለሦስተኛ ጊዜ እንደሚከበር ገልጸው፣ በዓሉ የሀገርን ገጽታ በመገንባትና የዳያስፖራው ማህበረሰብ በሀገር ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ላይ የድርሻውን እንዲወጣ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።

የዘንድሮው በዓል የተጀመረውን ይህን የለውጥ ጉዞ ለማጠናከር ያስችላል፤ በተለይ ድሬዳዋ ያላትን የቱሪስት መዳረሻዎች ለማስተዋወቅና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ጠቀሜታ አለው ሲሉም አክለዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ቀናት በሚዘልቀው ናፍቆት የድሬዳዋ በዓል ላይ በዳያስፖራው ማህበረሰብ የተገነቡ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ተመርቀው ወደ አገልግሎት ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በፌስቲቫሉ ላይ የብስክሌት ውድድሮች እንዲሁም በሶማሌ ክልል እና በድሬዳዋ አስተዳደር አመራሮች መካከል አዝናኝ የእግር ኳስ ውድድር እንደሚካሄድም ተጠቁሟል።

ለሦስተኛ ጊዜ መከበር በጀመረው ናፍቆት ድሬ በዓል ላይ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እና በሀገር ውስጥ ከተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆችና ወዳጆች እየተሳተፉ ነው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም