"ከራስ በፊት ለህዝብ እና ለሀገር" - ኢዜአ አማርኛ
"ከራስ በፊት ለህዝብ እና ለሀገር"
"ከራስ በፊት ለህዝብ እና ለሀገር"
"ከራስ በፊት ለህዝብ እና ለሀገር" ከመከላከያ ሠራዊት ቁልፍ እሴቶች መካከል አንዱ ነው። በመሆኑም ይህ እሴት ሠራዊቱ በሚሠማራባቸው አካባቢዎች ሁሉ ተግባር ላይ የሚውል የሠራዊቱ መለያ ባህሪ የሆነ የበጎነቱ ማሳያ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሚሠማራባቸው ቀጠናዎች ሁሉ ከህዝብ ጋር አብሮነትን በመፍጠር በሠላምም ይሁን በልማት ዙሪያ አብሮ መሥራት የዘወትር ተግባሩ ነው።
ይህ ለሠላምና ለልማት በጋራ የመቆም ተግባር ሀገርን ወደ ከፍታ ማማ የሚወስድ ከመሆኑ በሻገር አብሮነትን እና አንድነትን የሚያጎለብት መልካም ሥራ ነው። በዚህ የአንድነት ሂደት ውስጥም መደጋገፍን በሠራዊቱና በህዝቡ ዘንድ በእጅጉ ጎልቶ እናገኘዋለን።
ህብረተሰቡ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ከደጀን እስከ ግንባር ድረስ በመጓዝ ለሠራዊቱ ያደረገው ድጋፍ፣ በበዓላት ጊዜ የእርድ ሠንጋዎችን ማበርከቱ ፣ሠራዊቱን የሚደግፉ ህዝባዊ ሠልፎችን ማካሄዱ እና ሌሎች አብሮነትን የሚያረጋግጡ ሥራዎች ህብረተሰቡ ለሠራዊቱ ያለውን መልካም እይታና ድጋፍ የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡
በተጓዳኝ መከላከያ ሠራዊቱ የሀገርን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ በዘለለ በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረጉ፣ ለተቸገሩ ለተፈናቀሉ ወገኖች ካለው ከትንሿ ቀንሶ መደገፉ፣ መማር እየፈለጉ የአቅም እጥረት ላለባቸው ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ማበርከቱ፣ ለተጠማ ማጠጣቱ፣ ለተቸገረ ማብላቱ ለታረዘ ማልበሱ እና ሌሎች ድጋፎቹ ሁሉ የህዝባዊነቱ ማሳያዎች ናቸው።
መከላከያ ዛሬም በደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የዕለት ደራሽ ምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል ። በመከላከያ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ አማካኝነት ቦታው ድረስ በመገኘት የተደረገው ድጋፍ ሠራዊት በሠው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ፈጥኖ የሚደርስ መሆኑን የሚያሥመሰክር ተግባር ነው።
በአደጋው ለተጎዱ ወገኖች የተደረገው የዕለት ደራሽ የአይነት ድጋፍ ሁለት መቶ ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣ሁለት መቶ ሃያ አምስት ኩንታል ብስኩት ፣ሃምሳ ኩንታል ስኳር፣ ስድስት ኩንታል ሻይ ቅጠል፣ ጥንድ አንሶላ ዘጠኝ መቶ ብርድ ልብስ፣ ሲሆን አጠቃላይ በገንዘብ ሲተመን ስድስት ሚሊየን ሶስት መቶ አምስት ሺህ ብር መሆኑን ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ገልፀዋል።
አደጋው በተከሰተ ማግስት በቀጠናው የሚገኘው የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ አንድ የህክምና ቡድን ከአምቡላንስ ተሽከርካሪ ጋር ወደ ስፍራው ከመላኩ በተጨማሪ ከአምስት ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ምግብ ነክ ድጋፍ ቦታው ድረስ ተገኝቶ ማሥረከቡ የመከላከያ ሠራዊቱን ህዝባዊ ወገንተኝነት የሚያረጋግጡ እውነታዎች ናቸው።
መከላከያ ሠራዊት መተኪያ የሌላትን ህይወቱን ለሀገርና ለህዝብ ከመሥጠቱ ሌላ በማንኛውም ጊዜ የህዝቡን ችግር ተገንዝቦ የቻለውን ሁሉ የሚያደርግ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው።