በኦሊምፒክ ስፖርት ለመጀመሪያ ጊዜ የተካተተው ብሬክ ዳንስ

በይስሐቅ ቀለመወርቅ

እንደ መነሻ

የኦሊምፒክ ውድድር በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ የስፖርት ዓይነቶችን በማካተት ዘንድሮ ለ33ኛ ጊዜ በፈረንሳይ ከተማ ፓሪስ እየተከናወነ ይገኛል።

ከዛሬ አራት ዓመት በፊት በጃፓን ቶኪዮ በተከናወነው ኦሊምፒክ ስድስት የስፖርት ዓይነቶች ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡

የተካተቱት ስፖርቶች፤ ካራቴ፣ ስኬትቦርዲንግ፣ ቤዝቦልና ሶፍትቦል፣ በገመድና ያለገመድ ግርግዳ መውጣት (Sport climbing) እና በውሃ ላይ መንሸራተት (Surfing) ናቸው።


 

በፈረንሳይ እየተከናወነ በሚገኘው 33ኛው የበጋ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ "ብሬኪንግ" ወይም "ብሬክ ዳንስ" የሚባለው የዳንስ ዓይነት በኢሊምፒክ ጨዋታዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተካቷል።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1970ዎቹ በብሮንክስ ጎዳናዎች ላይ የበቀለው ዳንስ፤ ለኒውዮርክ አፍሪካ አሜሪካዊ ማኅበረሰብ ምስጋና ይግባውና፤ በፓሪስ ኦሊምፒክ አንዱ ስፖርታዊ ውድድር ሆኖ ቀርቧል።

ብሬክ ዳንስ ምንድነው?

ብሬክ ዳንስ በአርባን ፖፕ፣ በሂፖፕና ራፕ በሚባሉ የሙዚቃ ዓይነቶች የሚሰራ የዳንስ እንቅስቃሴ ሲሆን አራት ዓይነት እንቅስቃሴዎች የሚደረጉበት ስልት ነው፡፡ "ቶፕ ሮክ" የሚባለው ደግሞ የመጀመሪያው ስልት ነው።

በቶፕ ሮክ ዳንሰኛው ወይም ዳንሰኛዋ ቆመው በእግር እንቅስቃሴ ይጀምሩና፤ የማማሟቂያ እንቅስቃሴዎችን በማስከተል ወደ ሞቀ እንቅስቃሴ የሚገቡበት ነው።

ሁለተኛው "ዳውን ሮክ" የሚባል ሲሆን፤ እጅና እግርን ወለል ላይ በማሳረፍ፤ ሰውነትን በተለያየ መንገድ እንዲተጣጠፍ በማድረግ፤ ፈጣን እንቅስቃሴ የሚደረግበት ስልት ነው።

ሦስተኛው "ፓወር ሙቭ" የሚባለው የብሬክ ዳንስ ክፍል ሲሆን፤ በፍጥነት አክሮባት በመሥራት  ዳንሰኞች ትርኢት የሚያሳዩበት ነው።

አራተኛውና የመጨረሻው የብሬክ ዳንስ ክፍል ደግሞ፤ "ፍሪዝ" የሚባለውና እየደነሱ በመሀል ቆም በማለት መልሶ ወደ ዳንስ እንቅስቃሴ የሚገባበት ነው።

የብሬክ ዳንስ ውድድር አጀማመርና ወደ ኦሊምሊክ ያደረገው ጉዞ

የመጀመሪያው የብሬክ ዳንስ ውድድር የተከናወነው፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1990 አሜሪካን ውስጥ ነበር።

በተለይ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2004 ጀምሮ፤ "ሬድ ቡል ቢሲ ዋን" የሚባለውና በሁለቱም ፆታዎች የሚከናወነው ዓመታዊ የብሬክ ዳንስ ሻምፒዮና፤ ስመጥር የዘርፉ ውድድር ነው።

ዓለም አቀፉ የዳንስ ስፖርት ፌዴሬሽን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2018 ፤ የብሬክ ዳንስን በአርጀንቲና ቦነስ አይረስ በተደረገው የበጋ የወጣቶች ኦሊምፒክ ላይ አስተዋውቆ ነበር።

አሁን ላይ በተጀመረው 33ኛው የፓሪስ ኦሊምፒክ ውድድር ደግሞ፤ ብሬክ ዳንስ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ተካቶ ውድድር ይደረግበታል።

ውድድሩም ፓሪስ በሚገኘው "ላኮንኮርድ" ከሚባለው የኦሊምፒክና፣ የፓራ ኦሊምፒክ መንደር 5 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ ላይ ይከናወናል። 

በሁለቱም ፆታዎች በሚደረገው የብሬክ ዳንስ ውድድር አንድ ሀገር በወንድም በሴትም በተመሳሳይ 16 ተወዳዳሪዎችን የሚያሰልፍ ሲሆን፤ ተወዳዳሪዎች ዲጄዎች በሚያጫውቷቸው ሙዚቃዎች ታጅበው ውድድሩን ያከናውናሉ።

33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከሐምሌ 19 ጀምሮ በፈረንሳይ ፓሪስ እየተከናወነ ሲሆን እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ ይከናወናል።

በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ 206 ሀገራት እየተሳተፉ ሲሆን፤ 10 ሺህ 714 ስፖርተኞች በ32 የስፖርት ዓይነቶች ውድድራቸውን እያደረጉ ነው። 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም