ከመልከ-ብዙ የኢኮኖሚ ገጽታ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ

በረከት ሲሳይ (ኢዜአ)

አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ገቢራዊ ከመደረጉ ከ2011 ዓ.ም በፊት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተከታታይ እድገት የነበረው ቢሆንም በጥቅሉ ሲገመገም የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ይስተዋልበት ነበር። 

ዕድገቱ በመንግሥት ከፍተኛ ወጪ በተስፋፋ የመሠረተ-ልማት አማካይነት የተመዘገበ በመሆኑ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የፈጠረ፣ አስተማማኝ የሥራ ዕድል በተፈለገው መጠን በቋሚነት መፍጠር የተሳነው፣ ከፍተኛ የብድር ጫና የፈጠረ መሆኑ ተገምግሟል።  

እነዚህን መዋቅራዊ ችግሮች በዘላቂነት በመፍታት በአገሪቱ ቀጣይነትና ጥራት ያለው እንዲሁም ሁሉን አቀፍ የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የኢኮኖሚ እድገት እውን ለማድረግ በማለም በ2011 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ወደ ሥራ ገብቷል። 

ማሻሻያው በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚ የፋይናንስ መረጋጋት ለማረጋገጥ በዋናነት ጥብቅ የፊስካል ፖሊሲ ገቢራዊ አድርጓል። 

የዕዳ ክምችትን ማቃለል 

ከዚህ አንጻር በተለይም የአገሪቱን የብድር ጫና ለማቃለል ከፍተኛ ወለድ ያለው ብድር (commercial loan) በማስቀረት አነስተኛ ወለድ ያለውና የመክፈያ ጊዜው ረዘም ያለውን የብድር አማራጭ (concessional loan) ተግባራዊ ተደርጓል። 

ይህም ብቻ ሳይሆን የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚወስዱትን ከፍተኛ ብድር በመቀነስ አነስተኛ ብድር እንዲወስዱ ማድረግ ተችሏል። በተጨማሪም ፕሮጀክቶች ሲካሄዱ አስፈላጊው ጥናት ተጠንቶ እንዲካሄድና የተቋማት የመፈጸም አቅም እንዲገነባ ለማድረግ ተችሏል። 

ከአበዳሪ አካላት ጋር የዕዳ ቅነሳና ሽግሽግ እንዲደረግ ያላሰለሰ ጥረት ተደርጓል። እነዚህ እርምጃዎች ተግባራዊ በመደረጋቸው አጠቃላይ የብድር ጫናው ላይ አዎንታዊ ለውጥ አምጥቷል።  

የወጪ ገቢ ንግድ ሚዛን   

ሌላው የወጪ ገቢ ንግድ ሚዛኑን ለማስተካከል ምርትና ምርታማነትን ከማበረታታት ጎን ለጎን የዘርፍ ተቋማትን አቅም የማጠናከር ሥራ ተሰርቷል። 

በተለይም የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ምንጭን በማስፋት የብዝኃ-ኢኮኖሚ አተያይ እንዲኖርና ግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን እና አይ ሲ ቲ ዘርፎች ላይ በልዩ ትኩረት የተሰራው ሥራ ውጤት አምጥቷል። 

በዚህ ዘርፍ ላይ የተደረገው ማሻሻያ በተለይም ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የውጭ ንግድ አፈጻጸምን በማሳደግ የንግድ ሚዛኑን ከማሻሻል በተጨማሪ የአገሪቱ ገቢ እንዲያድግና የዕዳ ክፍያ በተገቢው መልኩ እንዲካሄድ ተደርጓል። 

ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከምርትና አገልግሎት ወጪ ንግድ ከ10 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። ከሐዋላ አገልግሎትም 6 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል። በ2016 በጀት ዓመት የ3 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ተመዝግቧል።

ስንዴን ጨምሮ በተኪ ምርቶችም ከፍተኛ ለውጥ እየተመዘገበ ሲሆን፤ ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አሥር ወራት 2 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት ተችሏል። ከ2010 እስከ 2015 ባሉት በጀት ዓመታት በአማካይ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገት 7 ነጥብ 1 በመቶም ደርሷል።

የበጀት ጉድለትን መሙላት 

ሌላው በፊስካል ፖሊሲው ላይ በተወሰደው እርምጃ የመንግሥት ገቢን ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት አኳያ ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ውጤት አምጥቷል። 

ከዚህ አንጻር በተለይም የታክስ ምኅዳሩን በማስፋትና  ዘመናዊ የታክስ አሰባሰብ ሥርዓት ባለፉት ዓመታት ገቢራዊ በመደረጋቸው አዎንታዊ ለውጦች የተመዘገቡ ሲሆን፤ ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ529 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ ተችሏል። 

የዋጋ ንረትን ማርገብ 

የምርት አቅርቦትን በማስፋት በተለይም የሌማት ትሩፋት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ከፍተኛ ሚና እያበረከተ ይገኛል። ምርታማነትን ማሻሻልም ሌላኛው ሥራ ነው፡፡ 

በዘንድሮው ዓመት ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከ100 ሚሊየን ኩንታል በላይ ብልጫ ያለው ምርት መሰብሰብ ተችሏል። በተጨማሪም መንግሥት 10 ቢሊየን ብር ገቢ በመተው መሠረታዊ ሸቀጦችን ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ አድርጓል። 

ጎን ለጎንም የጥሬ ገንዘብ በገበያ ውስጥ ያለው ፍሰት የዋጋ ንረት እንዳያስከትል ለመቆጣጠርና መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረው የገንዘብ መጠን ለመቀነስ ሰፋፊ ሥራዎች ተሰርተዋል። የንግድ ባንኮች ለደንበኞቻቸው የሚለቁትን የብድር መጠን ላይ ገደብ መቀመጡም ተመላክቷል።  

እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ የማስተካከያ ሥራዎች በመሠራታቸው የዋጋ ንረት ከዚህ ቀደም ከነበረው 30 በመቶና ከዚያ በላይ ወደ 19 ነጥብ 9 በመቶ ዝቅ እንዲል ተደርጓል።   

የሥራ ዕድል ፈጠራ 

ባለፉት የሪፎርም ዓመታት የተሰሩ ሥራዎች ውጤት ያመጡ ሲሆን፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ከ3 ነጥብ 8 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። የሥራ ዕድሉ በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በከተማ ልማትና ሌሎች መሠረተ-ልማት ዘርፎች የተፈጠረ ነው። 

በተጓዳኝም ከ300 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ መንገድ ክብራቸውና ጥቅማቸው ተጠብቆ በውጭ አገራት የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል። ከ60 የሚልቁ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በአገር ቤት ሆነው በአውት ሶርሲንግ የተለያዩ የውጭ ድርጅቶች ውስጥ የመሥራት ዕድል አግኝተዋል።  

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ

የመጀመሪያው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርኃ-ግብር ቀሪ ሥራዎች ቢኖሩም፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትን ለማስተካከል በተደረገው ጥረት ውጤቶች ማስገኘቱ ተጠቅሷል። ይህንንም ከግምት በማስገባት ኢትዮጵያ ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ ገብታለች። 

ይህ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በአራት ምሰሶዎች ላይ የተገነባ ሲሆን፤ እነዚህም የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን እና ዘላቂነትን የሚደግፍ ዘመናዊ እና ጤናማ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማዕቀፍ መመሥረት፤ ፈጠራን የሚያበረታታ ምቹ የኢንቨስትመንትና የንግድ ዘርፍ ከባቢ እና ተወዳዳሪነትን ማሳደግ፣ የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት አቅምን ማጠናከር እና ጥራት ያለው አገልግሎትን በብቃት ለማቅረብ የመንግሥትን አቅም ማሳደግ የሚሉ ናቸው።

 የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳው ለጠንካራ፣ በግሉ ዘርፍ ለሚመራ፣ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ መሠረት እንደሚሆን ታምኖበታል። ፕሮግራሙ በሚተገበርበት ወቅት ከፍተኛ እና የተረጋጋ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ነጠላ አኃዝ የዋጋ ግሽበት ይኖራል ተብሎ ግብ ተጥሏል። 

 የውጭ ምንዛሬ መዛባትን በማስተካከል፣ የፋይናንስ ዘርፉን ይበልጥ በማጠናከር፣ የዋጋ ንረትን በመቆጣጠር፣ የታክስ ገቢን በማሳደግ፣ የመንግሥትን ኢንቨስትመንት ውጤታማነት በማሻሻል፣ የባንክ ዘርፍን ተወዳዳሪነትና ጤናማነት በማጎልበት እና የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን በማሻሻል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዘመናዊና ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ሥርዓትን ለመገንባት ትልቅ ሀገራዊ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ይገኛል።

 የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሬ ተመን ሥርዓት እንዲኖር ማድረግ፣ በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት ማዘመን፣ የመንግሥት ፋይናንስ ጫናዎችን የሚቀንስ የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያ፣ የልማት ፋይናንስ ዕድሎች እና የመንግሥት ዕዳ አስተዳደር ማሻሻያ እንዲኖር በማድረግ ጠንካራ፣ አካታች እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ሥርዓት የመገንባት ቁልፍ ዓላማና ግብ ሰንቆ ነው ወደ ተግባር የገባው።  

 የፖሊሲ እርምጃዎቹ ከአጠቃላይ ሀገራዊ የረዥምና የመካከለኛ ዘመን የልማት ዕቅዶች ጋር ተጣጥመው የሚከናወኑ በመሆኑ በመጀመሪያው የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርኃ-ግብር የተስተዋሉ ቀሪ ሥራዎችን በምልዓት በመሥራት የዕዳ ክምችት በማቃለል፣ የወጪ ገቢ ንግድ ሚዛን በመጠበቅ፣ የበጀት ጉድለትን በመሙላት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን በማስፋት፣ የዋጋ ንረትን በማቃለል ትልቅ እመርታ እንደሚኖራቸው ታምኗል።

 በዚህም በሚቀጥሉት አራት ዓመታት በማክሮ ኢኮኖሚ የማሻሻያ እርምጃዎች ምክንያት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአማካይ በ8 በመቶ ያህል እንደሚያድግ፤ የዋጋ ንረት ወደ 10 በመቶ ዝቅ እንደሚል፤ የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ 11 በመቶ እንደሚደርስ፤ የመንግሥት ዕዳ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 35 በመቶ ዝቅ እንደሚል፤ የወጪና የገቢ ንግድ ዋጋ ወደ 20 ቢሊየን ዶላር እንደሚያድግ፤ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት ወደ 8 ቢሊየን ዶላር ከፍ እንደሚል፤ ዓለም አቀፍ የመጠባበቂያ ክምችት ከ10 ቢሊየን ዶላር በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል። 

እነዚህ ትንበያዎች በቀጣይ ዓመታት ሊመጣ የሚችለውን የኢኮኖሚ ሽግግር ደረጃ የሚያመለክቱ ናቸው። በመሆኑም ኢትዮጵያ በተሟላ መንገድ የጀመረችው ይህ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ እና የዜጎችን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲተገበር ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም