ሰው ለማዳን የተከፈለ ዋጋ! - ኢዜአ አማርኛ
ሰው ለማዳን የተከፈለ ዋጋ!
ጠዋት ሁለት ሰዓት ላይ ነው "ድረሱልን!" የሚለውን ድምጽ የሰሙት ወይዘሮ ውድነሽ ዶአ። የድረሱልን ጥሪውን እንደሰሙ 'ለሰው ደራሽ ሰው ነው' በማለት ከባለቤታቸው ጋር ከቤታቸው ወደ ስፍራው ያቀናሉ።
በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ የተደናገጡት የአካባቢው ነዋሪዎች የተጎዱትን ለማትረፍ ርብርብ እያደረጉ ነው። ወይዘሮ ውድነሽ እና ባለቤታቸው ከእነዚህ ሰዎች መካከል ተገኝተዋል።
"ኬንቾ ቀበሌ የሚገኙ ቤተሰቦች በመሬት መንሸራተት ተውጠዋል" ተብሎ ሲነገራቸው ከቤታቸው ወጥቶ ለመሄድ ለአፍታም እንዳልቆዩ ነው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወይዘሮ ውድነሽ ያወጉት።
ሰብዓዊነት በልጦባቸው ሰው ለማዳን ነው ከትዳር አጋራቸው ጋር ተያይዘው ከቤታቸው የወጡት።
በስፍራው ሲደርሱ በርካታ ሰዎች በመሬት መንሸራተቱ የተጎዱ ወገኖችን ለመታደግ ይጥራሉ፤ በእጃቸው በያዙት መሳሪያ ቆፍረው በማውጣት ህይወታቸውን ለመታደግ እየጣሩ እንደነበረም ያስታውሳሉ።
"እኛም እነርሱን ተቀላቅለን ፍለጋውን ጀመርን" ሲሉም በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ይገልጻሉ።
"በወቅቱ የተጎዱትን ነፍስ ማዳን እንጂ የመሬት መንሸራተቱ ዳግም የሚከሰት አልመሰለንም ነበር። በዚያ ሰዓት ሁላችንም አፈሩን ባገኘነው ነገር መቆፈራችንን ቀጠልን። 'ዳግም ሌላ ናዳ ሊመጣ ይችላል ውጡ የሚል መልዕክት ቢደርሰንም የታየን የሌሎችን ነፍስ ማትረፍ ስለሆነ ፍለጋውን ቀጠልን” ይላሉ።
"ወገኔ ጎረቤቴ" ያሉት ሰው አፈር ተጭኖት ትቶት መሄድ አንጀታቸው አልቻለም፤ ለራሳቸው ህይወት ሳይሳሱ በናዳው የተጎዱትን ለማዳን ጥረታቸውን ቀጠሉ።
ብዙም ሳይቆይ ግን ድንገት ሌላ የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከሰተ። እርሳቸው እንደሚያስታውሱት ሁሉም ከአደጋው ለማምለጥ ነፍስ አውጪኝ ብሎ እግሩ ወደመራው መሸሽ ጀመረ።
“እኔም እንዲሁ መሮጥ ጀመርኩ፤ ግን ብዙም ሳይቆይ እኔም ከፊቴ ሲሮጡ የነበሩትም ናዳው በላያችን አርፎብን ወደቅን። ፊቴን የሸፈነውን ጭቃ እየጠረኩ "አድኑኝ! አድኑኝ!" የሚል ድምጽ ደጋግሜ ማሰማት ጀመርኩ” ይላሉ ዛሬ ላይ ሆነው ሲያስታውሱት።
የሰው ህይወት ለማዳን ከቤታቸው በአንድ ላይ የወጡት ባልና ሚስቶች አደጋው ለያቸው። እርሳቸው ወደ ሆስፒታል ሲሄዱ ባለቤታቸው ግን ዳግም ወደማይመለሱበት ዓለም ሄዱ። ለሰው ልጅ ፍቅር፤ ለሰብዓዊነት ሲባል የተከፈለ ዋጋ ሆኖ ታሪክ ይከትበዋል።
“በሰዎች ድጋፍ ከተረፍኩ በኋላ ባለቤቴ አጠገቤ አልነበረም። በወቅቱ በጭንቅላቴና በእጄ ላይ ጉዳት ደርሶብኝ ስለነበር ወደ ሕክምና አመጡኝ።" የሚሉት ወይዘሮ ውድነሽ፤ ባለቤታቸው ግን ሰው ለማዳን ሲሉ ህይወታቸው አልፎ መቀበራቸውን ሆስፒታል ውስጥ ሆነው መስማታቸውን በሀዘን ድባብ ውስጥ ሆነው ነው የሚናገሩት።
በአካባቢው የደረሰው ጉዳት ሁሉንም አሳዝኗል። በመንግስት የታወጀው የሦስት ቀናት ብሔራዊ የሀዘን ቀን ትናንት መጠናቀቁን ተከትሎም በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡትን ያሰበ የሻማ ማብራት መርሃ ግብር ተካሂዷል። ቤተሰቦቻቸውን እና ዘመድ ወዳጆቻቸውን በአደጋው ያጡትንና የተጎዱትን ከማጽናናት ባለፈ በዘላቂነት ለማቋቋም መንግስት፣ ህዝብና የተለያዩ አካላት በጋራ እየሰሩ ናቸው።