ከወዳደቁ ቁሳቁስ አነስተኛ የእርሻ ትራክተር ሰርቶ ለአገልግሎት ያበቃው የሽሬ እንዳስላሴው ወጣት

ሸሬ እንዳስላሴ፤ ሐምሌ 24/2016(ኢዜአ)፦ በችግር ፈቺ የፈጠራ ስራ የተሰማራው ወጣት የወዳደቁ ቁሳቁስን በመጠቀም አነስተኛ የእርሻ ትራክተር ሰርቶ ለአገልግሎት ማብቃቱ ተገለፀ። 

ወጣቱ ከዚህ ቀደም አንድ ሄሊኮፕተር ሰርቶ ለሶስት ደቂቃ በአየር ላይ እንድትንሳፈፍ በማድረግ በአገር አቀፍ የፈጠራ ስራ ውድድር ተሸላሚ መሆንም ችሏል። 

ሥራ ፈጣሪው ወጣት ዕበ ለገሰ ይባላል። የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ነዋሪ ነዉ።

የሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ባዘጋጀው የፈጠራና  የሥራ እድል ፈጠራ ውድድር ተሳታፊ ለመሆን ከወዳደቁ ቁሳቁስ የሰራትን አነስተኛ የእርሻ ትራክተር ይዞ በመቅረብ በውድድሩ ከተሳተፉት ስምንት ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ቀዳሚ በመሆን የገንዘብ ተሸላሚ ሆኗል። 

የእርሻ ትራክተሯ ከሞተርዋ ውጭ ሌላ አካልዋ ከወዳደቁ ብረታ ብረቶችና የፕላስቲክ ውጤቶች የተሰራች መሆኑን የተናገረው ወጣቱ በአራት ሰዓት አንድ ሄክታር ማሳ የማረስ አቅም እንዳላትም አስረድቷል። 

ባለ ትዳርና የሁለት ልጆች አባት የሆነው የ36 ዓመቱ ስራ ፈጣሪ ወጣት የእርሻ ትራክተሯን 56 ሺህ ብር ወጪ በማድረግ ለአገልግሎት ማብቃቱን ተናግሯል። 

የትራክተር ስራውን በፕሮጀክት መልክ በማስቀጠልና የፈጠራ ስራውን በማስፋት በቋሚነት ትራክተር እየገጣጠመ ለገበያ ለማቅረብ የባለ ድርሻ አካላት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ገልጿል። 

ዘመናዊ የግብርና አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ መሰል የፈጠራ ስራዎች ጠቀሜታቸው የጎላ ከመሆኑም ባሻገር ለሌሎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ ስለሚያደርግም የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ድጋፍ ሊያደርጉ እንደሚገባም ወጣቱ በአፅንኦት ጠይቋል። 

በአሁኑ ወቅት ትራክተሯ በሰው ጉልበት እየተገፋች የምታርስና በቤንዚን የምትሰራ ብትሆንም በየጊዜው እየተሻሻለች እንደምትሰራም ወጣቱ ተናግሯል። 

በአራት ጥማድ በሬዎች አንድ ቀን ሙሉ የሚፈጀውን ስራ ትራክተሯ በአራት ሰዓት ስታጠናቅቅ ግርምትን እንዳጫረባቸው በአካል ተገኝተው የተመለከቱ አርሶ አደሮች ገልፀዋል። 

በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የሽሬ ካምፓስ ዲን ዶክተር ዳዊት ማሞ በበኩላቸው የወጣቱ የፈጠራ ስራ የሆነችዉ ይህቺ አነስተኛ የእርሻ ትራክተር አስገራሚና በእጅጉ የሚበረታታ መሆኑን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። 

የፈጠራ ስራው እንዲሰፋም የባለ ድርሻ አካላት ሚና ጉልሀ መሆኑን ገልፀው ለወጣቱ ድጋፍ ሊያደርጉለት እንደሚገባም አመልክተዋል።

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ሽሬ ካምፓስም አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል። 

ወጣት ዕበ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ባዘጋጀው የሳይንስና ቴክኖሎጁ የፈጠራ ውድድር ላይ ከተለያዩ ቁሳቁስ የሰራትን ሄሊኮፕተር ይዞ በመቅረብ የውድድሩ አሸናፊ ከመሆኑም በላይ የአንድ መቶ ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኖ እንደነበርም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም